Print this page
Saturday, 13 March 2021 12:40

የዳውሮ መጪ ዘመን - ተስፋዎችና ተግዳሮቶች

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

   በዞኑ ሁለተኛው ግዙፍ የሃይል ማመንጫ ይገነባል


           በገበታ ለሃገር ፕሮጀክት ውስጥ የተካተተው የኮይሻ የተቀናጀ ፕሮጀክት፣ ለዳውሮ አዲስ ዕድልና ትልቅ ተስፋን ሰንቆላታል፡፡ በዚህ ፕሮጀክት ሰበብ የሚፈጠረው መነቃቃትም፣ ዳውሮ ለዘመናት ቸል ያለቻቸውን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም መስህቦቿን አስተዋውቃና ሸጣ ትልቅ የገቢ ምንጭ የማድረግ ሰፊ ዕድል እንደሚፈጠርላት
ብዙዎች ያምናሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ የዞኑን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተክሌ በዛብህን፣ በዳውሮ መጪ ዘመን ተስፋዎችና ተግዳሮቶች ዙሪያ አነጋግራቸዋለች፡፡  እነሆ፡-


             እስኪ የዳውሮን ዞን በአጭሩ ያስተዋውቁን?
ዞኑ በአጠቃላይ ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ምቹ የሆነ አካባቢ ነው። የመልክአ ምድራዊ አቀማመጡም ሆነ የአየር ጠባዩ በእጅጉ ምቹና ማራኪ ነው፡፡ ከቆላ እስከ ደጋ የተሰባጠረ የአየር ጠባይ ነው ያለው፡፡ ከፍ ያለውን ድርሻ የሚወስደው ቆላማው የአየር ጠባይ ሲሆን ደጋና ወይና ደጋው ተቀራራቢ መጠን ያለው ነው፡፡ በብዙ መልኩ ውብና ማራኪ ተፈጥሮ ያለው አካባቢ ነው፡፡
የዞኑ ዋና ከተማ ታርጫ መሰረተ ልማቶች በቅጡ ያልተሟሉላት ከተማ ናት። ለዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው?
እውነት ለመናገር ከተማዋ የተቆረቆረችው በ1993 ዓ.ም ነው። እድሜዋ ትንሽ ቢመስልም ቀላል የሚባልም አይደለም። ሆኖም የእድሜዋን ያህል አላደገችም። ለዚህ ትልቅ ማነቆ ደግሞ ከተማዋን የሚያቋርጥ ሀገራዊ የመንገድ ትስስር አለመኖሩ ነው። የሀይል አቅርቦት እጥረት፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግርና ሌሎችም ተግዳሮቶች ኢንቨስተሮች መጥተው መዋዕለ ንዋያቸውን እንዳያፈሱ እንቅፋት ሆነዋል። ዋነኛው ማነቆ  ግን የመንገድ ትስስር አለመኖሩ ነው። አይደለም ከክልል ወረዳ፣ ከዞን በአግባቡ የሚያገናኝ መንገድም የለም፡፡ እነዚህ ችግሮች ታርጫ በተፈለገው መጠን እንዳታድግ እንቅፋት ሆኖባታል።
እርስዎ ወደ ኃላፊነት ከመጡ ወዲህ ችግሮቹን ለመቅረፍ ምን የተከናወኑ ሥራዎች አሉ?
እኔ ወደ ሀላፊነት ከመጣሁ አንድ ዓመት ከስድት ወር ገደማ ሆኖኛል። በዚህ ጊዜ ውስጥ በፌደራልና በክልል ደረጃ የተጀመሩ ልማቶች በሰላም መደፍረስ ምክንያት ይቋረጡ ነበር፡፡ በዚያው ልክ የበጀት ሁኔታም ተፅዕኖ ያደርግባቸዋል፡፡ ቀደም ብለው የታቀዱና የተጀመሩ፣ ነገር ግን በወቅቱ የሀገሪቱ ሁኔታ የተቋረጡ ስራዎች መልሰው እንዲጀመሩ ከማድረግ ረገድ ትርጉም ያለው ስራ ሰርተናል፡፡ እንደሚታወቀው፤ የመንግስት ዋነኛ ሚና፣ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ ሲሆን ከዚያ በተጓዳኝ ልማትን ማምጣትና ዜጎችን ማርካት ነው። ከዚህ አንፃር የዞናችን መንግስት ህዝቡ ከስጋት ነፃ ሆኖ እንዲኖር በማድረግ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ ህዝቡም ለሰላም ያለው ቀናኢነት፣ ሁኔታዎች በተረጋጋ መልኩ እንዲሁ አድርጎልናል፡፡ የኛ ሚና የማስተማር ነበር ማለት ይቻላል፡፡
ልማትን በተመለከተ በዞኑ አቅም ሊሰሩ የሚችሉ  ስራዎችን አቅደን እየሰራን እንገኛለን። በመደበኛነት የሚሰሩ ማህበረሰባዊ ሥራዎች ማለትም የትምህርት የጤናና መሰል ስራዎች ሳይደናቀፉ እንዲቀጥሉ አጥብቀን እየሰራን ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን፣ በተለይ ደቡብ ክልል አዳዲስ መዋቅሮች እየወጣ ስለሆነ፣ ከዚህ አንጻር፣ እንደ ዞን በርካታ አከራካሪ ጉዳዮች ገጥመውን ነበር።
ከክልልነት ጋር በተያያዘ ማለት ነው?
ትክክል ነው። የክልል እንሁን ጥያቄ ለምክር ቤቶቻችን አቅርበናል፡፡ ዳውሮም ጥያቄውን በራሱ ምክር ቤት ወስኖ አቅርቧል፡፡ የፌደራሉ መንግስት "ሀብት ለመመደብ ሰብሰብ ብላችሁ አንድ ብትሆኑ ይሻላል"  የሚለውን ምክረ ሀሳብ ማቅረቡን ተከትሎ፣ እኛም መተዳደር ካለብን እዚሁ በደቡብ ምዕራብ አካባቢ ካሉ (ወደ ስድስት መዋቅሮች ማለት ነው) ህዝቦች ጋር ተደራጅተን፣ በልማትም በኢኮኖሚ ተጠቃሚነትም ሆነ በአካባቢ ጥበቃ ተመሳሳይ ስነ-ልቦና በህዝቡ ዘንድ የተገነባ ስለሆነ ይህንን ማበልፀግና ማቆየት ይቻላል፣ ህዝቡንም ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል የሚል እምነት በህዝቡ ዘንድ ሰርጿል፡፡ እኛም የህዝቡን ሀሳብ መደገፍና ማስኬድ ስለነበረብን፣ ይህንን ስናደርግ ቆይተናል፡፡ ይህን ስናደርግ ከተለያዩ ግለሰቦችና ቡድኖች የተለያዩ ጫናዎች ደርሰውብናል፡፡ ህዝብ እንደ ህዝብ መሰረታዊ የሆነ መቃቃርና ጥላቻ ኖሮት አያውቅም፣ ይህንን መቃቃርና ጥላቻ የምንፈጥረው እኛ በመሪነት ደረጃ ያለን ነን፡፡ ሁልጊዜ ህዝብ ቅር እናሰኛለን። ስንሰራም የሚታየው ይሄ መቃቃር የሚረግብበትን ሳይሆን የሚባባስበትን ነው። ለውጡ ከመጣም በኋላ “ህዝቡ ከለውጡ በፊት ያሉ ይሻለን ነበር” እንዲልና እንዲማረር ለማድረግ የሚተጉ ሀይሎች ነበሩ፡፡ “ህዝቡ የፈለገው ትክክል አይደለም” እስከ ማለት የደረሱና የራሳቸውን ፍላጎት ለመጫን የእጅ ጥምዘዛ ሙከራዎች ያደረጉ አልጠፉም፡፡ ይህንን ለማስተካከልና ለማረም ስናደርግ የነበረው ትግልና እንቅስቀሴ ብዙ ጊዜያችንን ወስዶብናል። ምስጋና ለፈጣሪ ይሁንና መንግስትም የህዝብን ፍላጎት ተረድቶ፣ ይኸው አሁን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አደረጃጀት እውን ሊሆን ጫፍ ላይ ደርሷል። የተለያዩ የሕግና የአደረጃጀት ጉዳዮችን የሚያስኬዱ ኮሚቴዎች ተሰባጥረው ተመርጠው ስራው ቀጥሏል። በአጠቃላይ በዓመቱ ትልቁን ጊዜ የወሰደው ይሄ የአደረጃጀት ጉዳይ ነው።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አደረጃጀት መሰረት የዚህ ክልል መቀመጫ ማን ይሆናል ተብሎ ነው የሚጠበቀው?
በዚህ አደረጃጀት ውስጥ ዳውሮ ዞን፣ ኮንታ ልዩ ወረዳ ፣ ከፋ ዞን፣ ሽካ ዞን፣ ቤንቺ ሸካና ምዕራብ ኦሞ ናቸው የሚካተቱት። ስለዚህ በዚህ መወቅር ውስጥ ወደ 13 የሚደርሱ ብሔር ብሔረሰቦች አሉበት። እነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች አንድ ላይ ለመደራጀት ፈቅደው ነው እየተንቀሳቀስን ያለነው። ዋና መቀመጫን (ማዕከልን) በሚመለከት በአዲስ ቅኝት ከሌሎች አገራት ተሞክሮዎችን በመውሰድ አንድ ማዕከልን ማሳደግ የሚለውን አስተሳሰብና አሰራርም መቀየር አለብን። ሴንትራላይዜሽኑን ቀይረን  በየቦታው መዋቅሮችን በሚያስተሳስር መልኩ ከአንድና ከሁለት በላይ ማዕከላትን ማደራጀት አለብን የሚል ስምምነት ላይ ተደርሷል። ይሄ ብዙ ጥቅም አለው። አንድ ከተማ በጣም ሲያድግና ሌላው ከተማ ባለበት ቀጭጮ ሲቀር፣ የህዝቡም ፍሰት ወደ አደገው ከተማ ይበዛል። የተለያዩ ከተሞች ሲያድጉና ሲለሙ ደግሞ የህዝብ ፍሰቱ ሚዛናዊ ይሆንና ሁሉም ነገር አንድ ከተማ ላይ እንዳይጨናነቅ ያደርጋል። ስለዚህ  ማዕከላት ተያይዘው ቁጥራቸውም ከፍ ብሎ እኩል ማደግና መበልፀግ አለባቸው የሚል እምነት አለን፡፡
500 ዓመት በላይ እድሜ ያለው የንጉስ ሁላላ የድንጋይ ካብ (ሀላላ ኬላ)፣ የአፍሪካ ዝሆኖችን ጨምሮ በርካታ እንስሳትና ዕፅዋት ያሉበት ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ፣ ጊቤ-3 ሰው ሰራሽ ሀይቅ፣ በዓለም ረጅሙ የትንፋሽ የሙዚቃ  መሳሪያ (ዲንካ)፣ እንዲሁም ሌሎች የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሀብቶች መገኛ ነው፤ ዳውሮ። እነዚህን ሃብቶች በማስተዋወቅና በመሸጥ ከዞኑ  አልፎ ለአገርም ሀብት ማምጣት ሲቻል ብዙ አልተሰራበትም። ለወደፊት በዚህ ምን አቅዳችኋል?  
ቀደም ብዬ በመግቢያዬ እንደገለጽኩልሽ፤ የዚህ ዞን ዋነኛ ችግር ዞኑን አቋርጦ የሚያልፍ ሀገራዊ መንገድ አለመኖር ነው። በዚህ ምክንያት ከላይ የዘረዘርሻቸውና ሌሎችም እየተጎበኙ አይደለም። ይሁን እንጂ የዓለምንም ሆነ የአገራችንን አይን የሚስቡ በተፈጥሮ የተጎናፀፍናቸው፣ አሁን አሁን ሰው ሰራሽ ሆነው እየመጡ ያሉ ሀብቶች አሉ። ከነዚህም ውስጥ ህዝቡ ተንሰፍስፎ በስስት የሚጠብቀውና አጥንትና ደሜ ነው የሚለው ሀላላ ኬላ፤ ተመራማሪዎች፣ “የመካከለኛው ዘመን የዳውሮ ህዝብ የመከላከያ ግንቦች” በሚል የሚጠሩት ይገኙበታል።  በ1532 ዓ.ም ግንባታው ተጀምሮ በኋላም ግንባታውን ባስጨረሱት ንጉስ ሀላላ የሚጠራው “ሀላላ ኬላ” የሚባሉት ግንቦች በአጠቃላይ 1225 ኪ.ሜ ርዝመት ዙሪያውን ነው የተገነባው። ሰባት በሮችም አሉት። በሰዓቱ በጠባቂ ሹሞች ነበር የሚጠበቀው። ለዲፕሎማሲ ስራ ትዕዛዝ ሲተላለፍ መግባትና መውጣት ይቻላል። ከዚያ ውጪ በጦርነት ጊዜ ጥበቃም ይደረጋል። የግንቡን አንዱን ክፍል ከታርጫ ከተማ 40 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ማየት ይቻላል። ዳውሮን ዙሪያውን ለማጠር ታስቦ ነው የተገነባው። ጎጀብና ኦሞ ወንዞችን ተከትሎ የተገነባ ሲሆን ድንጋይ በሌለበት የደጋው አካባቢ ጉድጓድ ይቆፈር ነበር። ፈረስ እንዳይዘለው ታስቦ ነው የተሰራው። ይሄ ማለት ጠላት በእግር ሲያቅተው  በፈረስ ዘሎ እንዳይገባ በሚል የግንቡ ከፍታ እስከ ሶስት ሜትር ርዝመት እንዲኖረው በጣም በሚገርም ሁኔታ ነው የተሰራው፡፡ አሸዋና ሲሚንቶ ሳይኖር፣ በድንጋይ ላይ ድንጋይ ደራርበው ሰርተው እስካአሁን ሳይናድና ሳይፈርስ ለትውልድ መተላለፋቸው እጅግ የሚደነቅ ምህንድስና ነው፡፡ ከብት አርቢዎች ይሄዱበታል፤ ሰደድ እሳት በየጊዜው ይነሳል፡፡ ይሄን ሁሉ ተቋቁሞ ነው ያለው፡፡ በቅርቡም የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ከጉብኝት በኋላ ለተመራማሪዎችና ለሚያስተምሯቸው ተማሪዎች አሳይተው፣ ከዚህ ዲዛይን በመነሳት ወደ ዘመናዊ ግንባታ  ለማሳደግ ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ በኮይሻ የተቀናጀ ፕሮጀክት ከሚለሙት አካባቢዎች አንዱ ይሔው ቦታ ነው።  በሚለማበት ጊዜ ታሪካዊ ይዘቱን ሳይለቅ ሌሎች ግንባታዎችን ለመስራት እንዲያስችላቸው ጥናት ሰርተዋል።
ኮይሻ ኮንታ ልዩ ወረዳ ውስጥ ያለች አንድ ቀበሌ ናት። በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ውስጥ ተካትቶ በኮይሻ የሚሰራው በአገሪቱ ሁለተኛው ግዙፉ የሀይል ማመንጫ ይመስለኛል፡፡ ይሄ ለዳውሮ የሚኖረው ፋይዳ እንዴት ይገለጻል?
 ከግቤ ሦስት ቀጥሎ የሚሰራው የሀይል ማመንጫ ኮይሻ ላይ ነው፡፡ ሲጠነናቀቅ ከህዳሴው ግድብ ቀጥሎ ሁለተኛው ግዙፍ የሀይል ማመንጫ ነው የሚሆነው። ኮይሻ ከጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ጋር የተያያዘ አካባቢ ነው። ስለዚህ የኮይሻን አካባቢ ልዩ ውበት ያጎናጽፈዋል፡፡ ግድቡ ውሃ መያዝ ሲጀምር፣ ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ጎን ነው የሚሆነው። ብሔራዊ ፓርኩ ደግሞ የዳውሮና የኮንታ ልዩ ወረዳ የጋራ ሀብት ነው፤ ስለሆነም በኮይሻ ፕሮጀክት አማካይነት ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክን በማልማትና በውስጡ ያሉትን ሀብቶች በማሳደግ፣ የህዝቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማስፋፋት ይቻላል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የኮይሻ ሀይል ማመንጫ የሚይዘውን ሰው ሰራሽ ሀይቅ እንዲሁም በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘው የጊቤ ሶስት ሰው ሰራሽ ሀይቅ፣ (ጊቤ ሦስት ሀይቅ ደግሞ ከንጉስ ሀላላ የድንጋይ ግንብ ጋር በተያያዘ በመሆኑ)) ለዳውሮ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ያመጣል፡፡ ይሄ ለዳውሮ ህዝብ እጅግ ከፍተኛ እድል ነው። ኮይሻ ግድቡ ሲሰራ ሀይቁ ወደ ኋላ 150 ኪ.ሜ ቦታ ላይ ይገኛል። በነዚህ ሃይቆች የአሳ ምርት፣ የመዝናኛ ሥፍራ ልማት፣ የሀላላ ኬላ ታሪካዊ ጉብኝት -- ዕድሉ ሰፊ በመሆኑ ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ ይሔ ለዳውሮ ብቻ ሳይሆን ለሀገርም ትልቅ እድል ነው። እነዚህ አካባቢዎች ሲለሙ እስካሁን ዳውሮ ያሉባትን ጥያቄዎች እየመለሰ ይሄዳል። በነገራችን ላይ ዳውሮ ከፍተኛ የቀርከሀ ምርትና የእንሰት ምርት የሚበቅልባትም ሥፍራ ናት፡፡
ወደ ባህሉ ስንመጣ፣ ባህላዊ የአመጋገብ ስርአቱና የምግብ አዘገጃጀቱ ቀልብን የሚገዛ ነው፡፡ ይሄም በራሱ እንደ መስብህ የሚቆጠር ነው፡፡ ቅድም ያነሳሽው በዓለም ረጅሙ የትንፋሽ የሙዚቃ መሳሪያ- “ዲንካ”-  የእኛው ሀብት ነው፡፡ ለሀገርም ለውጭም በመዝናኛነትና በጥበባዊ ውበቱ ቀልብ ሳቢ ነው፡፡ በአጠቃላይ ዳውሮ አሁን ባለው እንቅስቃሴ፣ እጅግ ተስፋ ሰጪ ዞን ነው፤ብዙ ዕድሎች አሉት፡፡



Read 1349 times