Saturday, 13 March 2021 12:07

“አሁን የት ይገኛል ቢፈልጉ ዞሮ መስማት ከማይፈልግ የባሰ ደንቆሮ” - ከበደ ሚካኤል

Written by 
Rate this item
(7 votes)

      ከእለታት አንድ ቀን ጠዋት አንድ አዝማሪ ለሚስቱ እንዲህ ይላታል፡-
“ማታ በህልሜ መልአከ ሞት መጥቶ እዳ ከሜዳ አለብህ ሲለኝ አደረ።”
ሚስቲቱም “ይሄማ ባላጠፋኸው ጥፋት ቅጣት ይጠብቅሃል ማለቱ ነው። ስለዚህ አርፈህ እቤትህ ተቀምጠህ ይሄን ቀን ብታሳልፈው ይሻላል” አለችው።
ባልም፡- “ባላጠፋሁት ጥፋት ማን አባቱ ነው የሚቀጣኝ፤ እንዲያውም አሁኑኑ ነው የምወጣላቸው” ብሎ ተነስቶ ወደ ጫካ ሄዶ ክራሩን ይዞ ማንጎራጎር ጀመረ። የተቀመጠው አንድ ትልቅ ዋርካ ስር ነው። ከጥቂት ጊዜ በኋላ አካባቢው በሁካታ ተዋጠ። በርካታ ሰዎች በአዝማሪው ዙሪያ ተሰበሰቡ። እነዚህ ሰዎች ለካ በሬ የጠፋባቸው ኖረዋል።
በሬውን የነዱት ወንበዴዎች ወደ ጫካ አምጥተውት አርደው በጥጋብ ሲፈነድቁ ቆይተው ወደ ሰፈራቸው ሄደዋል። የተረፋቸውን ደግሞ እዚያው እዋርካው ስር ጥለውታል። ግጥምጥሞሹ ያስገርማል፤ አካባቢው ላይ ውር ውር ከሚሉት ማህል አንደኛው፡- “ይሄ ጥጋበኛ አዝማሪ በሬያችንን አርዶ በልቶ ጠግቦ ሲያበቃ፣ ይሄው የፈንጠዝያውን እዚህ ክራሩን እየከረከረ ዘፈኑን ያቀልጠዋል። እንግዲህ ሌባ ተይዞ ዱላ አይጠየቅም” አለ።  
ሁሉም አንዳንድ ቡጢ እያሳረፉ አዝማሪውን ከሰውነት ውጪ አደረጉት።
ወደ ቤቱ ሲመለስም፤ ባለቤቱ “ውድ ባሌ ሆይ፤ እንዲህ እዳ ከሜዳ ያጋጥምሃል ብሎ በግልጽ አማርኛ ነግሬህ ነበር። አንተ ግን አላዳመጥከውም። እንግዲህ ችግሩ ያንተው የራስህ ነው ማለት ነው። ለወደፊቱ ቀልብህን አዳምጠው። የሰው ነገርንም እህ ብለህ ስማ” አለችው።
*   *   *
ስራዬ ብሎ የማዳመጥን አጀንዳ ማድመጥ ብልህነት ነው። የማዳመጥ፤ ክህሎት ቀዳሚ ጥበብ ነው።  ተናጋሪነት  ህፀፅ  አያጣውም። ማዳመጥ ግን ምሉዕ በኩላሄ ነው።  ወደ መመራመር ካልመራ መላ የለውም” እንደሉት ነው፤ አለቃ ስርግው፡፡ ማየት የተሳነው መሆን ተፈጥሯዊ ነው። መስማት የተሳነው መሆንም ተፈትሯዊ ነው። ማሽተት የተሳነው መሆንም አካላዊ ክስተት ነው። ማሰብ የተሳነው መሆን ግን ክፉ መርገምት ነው። መላም መድሃኒትም የለውም። ምናልባትም ዘመናችን እንደ ፈጠራቸው ፈውስ አልባ በሽታዎች ተርታ የሚቆጠር ነው። ከሀሳብ ማጣት የከፋ መርገም የለም። ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን  እንዳለው፤  “ከመርገምት ሁሉ የከፋ መርገምት ቋንቋ ለቋንቋ መጠፋፋት” ይለናል።  ሀሳብ ለሃሳብ አንጠፋፋ፣ ልብ ለልብ አንራራቅ፣ መንፈስ ለመንፈስ እንተቃቀፍ፣ ልዩነታችንን አውቀን ነቅተን  Vive La Diference (ልዩነት ለዘለዓለም ይኑር!) እንባባል። ወደን እንማማር፣ አውቀን እንዋደድ፣ የማንንም ጣልቃ ገብነት አንፍቀድ፣ ኢትዮጵያዊነትን ማንም አልሰጠንም፤ እኛው እራሳችን እንጂ!
 ዛሬም ከሮበርት ብራውን ጋር በገ/ክርስቶስ ትርጓሜ “ከውጪ ያለውን ሄዶ ከመፈለግ ከውስጥ የበራውን እንዲወጣ ማድረግ” የምንለውን ያህል ከፀጋዬ ገ/መድህን ጋር፤
“ያለፈ ጥረታችንን ሳስታምመው ትዝ ሲለኝ
ከሞከርነው ነገር ይልቅ ያልሞከርነው ነው የሚቆጨኝ
ማለታችን አይቀሬ፡፡ ነው ዞሮ ዞሮ የምንደመድመው፤ “የምንለውን አንጣ” የምንለውን ስናገኝ የሚያናጥበን አይምጣ”፡፡  ለዚህ ነው  ደራሲ ከበደ ሚካኤል በታሪክና ምሳሌያቸው፤
“ምንኛ ታድሏል የሰነፍ አዕምሮ
እንኳን መማር ቀርቶ ፊደል ሳያጠና
ሁሉንም ያወቀ ይመስለዋልና  
   “አሁን ይት ይገኛል ቢፈልጉ ዞረው
 መስማት ከማይፈልግ የባሰ ደንቆሮ” ያሉት ለዚህ ነው።

Read 13555 times