Tuesday, 09 March 2021 00:00

በዓለም መስማት የተሳናቸው ሰዎች ቁጥር ከ1.5 ቢሊዮን ማለፉ ተነገረ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  የአለም የጤና ድርጅት በመላው አለም የሚገኙ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ቁጥር ከ1.5 ቢሊዮን ማለፉንና አስፈላጊው የጥንቃቄና የህክምና እርምጃ ካልተወሰደ በመጪዎቹ 30 አመታት በአለማችን 2.5 ቢሊዮን ሰዎች የተለያዩ የመስማት ችግሮች ተጠቂ ሊሆኑ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል፡፡
የተለያዩ የመስማት ችግሮች ያሉባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መገለል እንደሚደርስባቸውና አብዛኛውን ህይወታቸውን ተነጥለው እንደሚገፉ የገለጸው ድርጅቱ፤ የመስማት ችግር አለማችንን በየአመቱ ለ1 ትሪሊዮን ዶላር ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እየዳረጋት እንደሚገኝም ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ለመስማት ችግር ከሚያጋልጡ ምክንያቶች መካከል የጆሮ ኢንፌክሽንና የጆሮ ደግፍ በሽታ እንደሚገኙበትና አብዛኞቹ አጋላጭ ሰበቦች ልንከላከላቸው የምንችላቸው መሆናቸውን የጠቆመው መግለጫው፣ ከእነዚህም መካከል ከፍተኛ ድምጽ ያለው ሙዚቃ በጆሮ ማዳመጫ መስማት አንዱ መሆኑን አመልክቷል፡፡
የመስማት ችግሮችን ሊያቃልሉ የሚችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችና የመስማት ብቃትን ለማሻሻል የሚረዱ ህክምናዎች ቢኖሩም ለአብዛኛው ሰው ተደራሽ አለመሆናቸውን የጠቆመው ድርጅቱ፤ በአለማችን መሰል ድጋፎች ከሚያስፈልጋቸው ሰዎች መካከል 17 በመቶ ያህሉ ብቻ ተጠቃሚ መሆናቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡


Read 2534 times