Monday, 08 March 2021 00:00

ኢንተርፖል ከኮሮና ክትባት ጋር የተያያዙ ወንጀሎች በእጅጉ መስፋፋታቸውን ገለጸ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  - በደቡብ አፍሪካና በቻይና ከ5 ሺህ በላይ ሃሰተኛ ክትባቶች ተይዘዋል
    - በኮሮና ሳቢያ በአለማችን 888 ሚ.ህጻናት ከትምህርታቸው ተስተጓጉለዋል

          ከሰሞኑ በደቡብ አፍሪካና በቻይና በህገወጦች የተመረቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሃሰተኛ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች መያዛቸውን ያስታወቀው አለማቀፉ የፖሊስ ጥምረት ኢንተርፖል፤ የወንጀል ቡድኖች መሰል ክትባቶችን በስፋት በማሰራጨት ላይ እንደሚገኙና ከክትባቶች ጋር የተያያዙ የወንጀል ድርጊቶች በእጅጉ መስፋፋታቸውን አስጠንቅቋል፡፡
በቻይና ከ3 ሺህ በላይ ሃሰተኛ ክትባቶችና በህገወጥ ክትባቶች ሽያጭ ላይ ለመስራት የተደራጀ ቡድን አባላት የሆኑ 80 ሰዎች በቁጥጥር ስር ሲውሉ፣ በደቡብ አፍሪካም 2 ሺህ 400 ሃሰተኛ ክትባቶችና ደረጃቸውን ያልጠበቁ 3 ሚሊዮን ማስኮች እንዲሁም አራት ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን ኢንተርፖል ባለፈው ረቡዕ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የአሜሪካ ፖሊስ ባለፉት ሳምንታት ከ10 ሚሊዮን በላይ ደረጃቸውን ያልጠበቁ ማስኮችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ያስታወሰው ዘ ጋርዲያን፤ ኢንተርፖል ለአለማችን መንግስታት የተደራጁ ወንጀለኞች ከኮሮና ጋር የተያያዙ ወንጀሎችን ሊፈጽሙ እንደሚችሉ ከወራት በፊት ማስታወቁን አስታውሷል፡፡
በአፍሪካ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ከትናንት በስቲያ ወደ 4 ሚሊዮን መጠጋቱንና የሟቾች ቁጥር ደግሞ ከ105 ሺህ ማለፉን የአፍሪካ የበሽታ መከላከልና ቁጥጥር ማዕከል ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የተለያዩ የአፍሪካ አገራት በአንድ አመት ውስጥ ለ190 የአለማችን አገራት ከ2 ቢሊዮን በላይ ክትባቶችን ለማሰራጨት ካቀደው አለማቀፉ የክትባት ጥምረት ኮቫክስ የተላኩላቸውን የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች በመቀበል ላይ ሲሆኑ፣ ክትባቶቹን ከተቀበሉት አገራት መካከልም ጋና፣ ኬኒያ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ናይጀሪያ፣ አንጎላና ጋምቢያ ይገኙበታል፡፡
የአለም ባንክ በበኩሉ፤ ለ30 የአፍሪካ አገራት የኮሮና ቫይረስ መግዣ የገንዘብ እርዳታ ለመስጠት መወሰኑ የተነገረ ሲሆን፣ የእርዳታው ተጠቃሚዎች ከሚሆኑት አገራት መካከል ኢትዮጵያ፣ ኒጀር፣ ሞዛምቢክ፣ ቱኒዝያ፣ ሩዋንዳና ሴኔጋል እንደሚገኙበት ዥንዋ ዘግቧል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ በመላው አለም ከ168 ሚሊዮን በላይ ህጻናት የሚማሩባቸው ትምህርት ቤቶች አመቱን ሙሉ መዘጋታቸውንና 214 ሚሊዮን ያህል ተማሪዎችም በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ በትምህርት ገበታቸው ላይ መገኘት ከነበረባቸው ጊዜ 75 በመቶ ያህሉን በትምህርት ገበታቸው አለመገኘታቸውን የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ከመጋቢት 2020 እስከ የካቲት 2021 በነበረው ጊዜ በአለማችን በሚገኙ 14 አገራት አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው መክረማቸውን ያስታወሰው የድርጅቱ መረጃ፣ በመላው አለም የሚገኙ ከ888 ሚሊዮን በላይ ህጻናት በኮቪድ ሳቢያ የትምህርት መስተጓጎል እንደገጠማቸውም አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ የኮሮና ዜና፣ ብራዚል ባለፈው ማክሰኞና ረቡዕ ከፍተኛውን ዕለታዊ የቫይረሱ ሟቾች ቁጥር ማስመዝገቧን የዘገበው ሮይተርስ፤ በአገሪቱ ማክሰኞ ዕለት 1 ሺህ 641፣ ረቡዕ ደግሞ 1 ሺህ 910 ሰዎች ለሞት መዳረጋቸውንና አጠቃላይ የቫይረሱ ሟቾች ቁጥር 259 ሺህ 271 መድረሱን አመልክቷል፡፡


Read 2670 times