Print this page
Saturday, 06 March 2021 14:09

በ2.2 ቢ. ዶላር ወጪ ኢንዱስትሪያል ኮምፕሌክስ ሊገነባ ነው

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(2 votes)

  ግንባታው በ18 ወራት ይጠናቀቃል ተብሏል  “የሰላም ዋስትና እንሰጣለን፤ መጥታችሁ አልሙ”
                       
                በ2.2 ቢሊዮን ዶላር ይገነባል የተባለው “ለሚ ናሽናል ሲሚንቶ አክስዮን ማህበር ኢንዱስትሪያል ኮምፕሌክስ” ባለፈው ረቡዕ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠለት።
ከአድዋው ጦርነት 3 ዓመት በኋላ በትንሽ ቤተሰባዊ ንግድ በተጀመረውና አሁን በሶስተኛ ትውልድ በሚመራው ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግና መቀመጫውን ሆንግ ኮንግ ባደረገው የቻይናው ዌስት ኢንተርናሽናል ሆልዲንግ ኩባንያ አካል በሆነው ዌስት ቻይና ሲሚንቶ ሊሚትድ ኩባንያ ሽርክና በሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ ለሚ ከተማ አጠገብ የሚገነባው  ግዙፍ ኢንዱስትሪያል ኮምፕሌክስ፤ በውስጡ በቀን 10 ሺህ ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም ያላቸው ሁለት ግዙፍ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች፣ በቀን 600 ቶን መስተዋት የማምረት አቅም ያለው የመስተዋት ፋብሪካ፣ በዓመት 30 ካሬ ሜትር ጂብሰም ቦርድ የሚያመርት ፋብሪካ፣ ሴራሚክስና ሌሎችንም ፋብሪካዎች የሚያካትትና ራሱን ችሎ ኢንዱስትሪ ዞን መሆን የሚችል ኢንዱስትሪያል ኮምፕሌክስ ነው ተብሏል።
ወደ 300 ሄክታር በሚጠጋ መሬት ላይ የሚገነባው ይሄው ኮምፕሌክስ፤ ለክልሉ የመጀመሪያው ሲሚንቶ ፋብሪካ ሲሆን ግንባታው ሲጠናቀቅ ለአገር ኢኮኖሚ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማምጣት፣ ከ10 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠርና የአካባቢውን ዕድገት በማፋጠን ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ተነግሯል። የኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ባለቤትና ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ብዙአየሁ እንዳለ (ዶ/ር)፣ በመሰረት ድንጋይ ማስቀመጥ ስነ-ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ “በአያቶቼ በትንሽ እንቅስቃሴ የተጀመረው ኢስት አፍሪካ  ሆልዲንግ አያቶቼ ባላቸው የስራ ፍቅር፣ ጥንካሬና ታማኝነት ዛሬ ላለበት ደርሶ በማየቴና ከዚያም አልፎ ከውጭ አገር እንዲህ አይነት ግዙፍ ኢንቨስትመንት ማምጣት በመቻላችን በእጅጉ ደስ ብሎኛል” ብለዋል። ይህ ኢንቨስትመንት እውን የሚሆንበትን ብስራት የመሰረት ድንጋይ እስከመጣል የነበረውን ሂደት በማሳካት በኩል ከፌደራል፣ ከክልል፣ ከዞንና ከወረዳ አመራሮች ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
የዌስት ኢንተርናሽናል ሆልዲንግ ኩባንያ የቦርድ ሊቀመንበር ሚስተር ዣንግ በበኩላቸው፤  በደቡብ አፍሪካ፣ በአንጎላ፣ ለኮትዲቯር በናምቢያና በሌሎችም የአፍሪካ አገራት ኩባንያዎቻቸው እንደሚገኙና ዋና ማዕከላቸው ደቡብ አፍሪካ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ይህንን ግዙፍ ኢንቨስትመንት ለመመስረትና መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ የዶ/ር ብዙአየሁ እንዳለ ለአገሩ ያለው ቀናኢነት፣ ያካበተው የስራ ልምድ፣ በጥናት ያረጋገጥነው የጥሬ ዕቃ ክምችት፣ የኢትዮጵያ መንግስት ቅልጥፍናና ትብብር፣ ከፍተኛ የግንባታ እቃ ፍላጎትና የኢትዮጵያ ተፈጥሮ ማራኪነት ዋና ዋናዎቹ ጉዳዮች ናቸው ብለዋል። የቦርድ ሊቀመንበሩ አክለውም ኢንዱስትሪያል ኮምፕሌክሱን ሀይል ቆጣቢ፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደራጀ፣ ለአካባቢ ደህንነት የተስማማና ምቹ አድርገን ገንበተን ለስራ እናበቃዋለን ሲሉ ቃል ገብተዋል።
በዚሁ ኢንዱስትሪ ኮምፕሌክስ ውስጥ የሚሰሩ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ለማፍራት ለሚ ናሽናል ስሚንቶ ኢንዱስትሪያል ኮምፕሌክስ ፣3 ሺህ ያህል ወጣቶችን በቴክኒክና ሙያ አሰልጥኖ ለመውሰድ እቅድ ከመያዙም በተጨማሪ ለወጣቶች የስራ ዕድል ከመፍጠር አኳያም ከኢፌዲሪ የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ጋር የመግባቢያ ሰነድ በዚሁ ዕለት ተፈራርመዋል።
የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ ስነ-ስርአቱ ላይ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ የአማራ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር  ፋንታ ማንደፍሮ (ዶ/ር) ፣እንዲሁም  የኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ አማካሪ ቦርድ ሊቀ መንበርና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ በርካታ የመንግስት ሃላፊዎች፣ ባለሃብቶችና ታዋቂ ሰዎች ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አገኘሁ ተሻገር ባደረጉት ንግግርም፣ “ይህንን ሁሉ እያየን ያለነው በለውጡ ነው፤ ከለውጡ በፊት ቢሆን ይህ ግዙፍ ፋብሪካ እዚህ አይገነባም ነበር” አማራ ክልል እስከ ዛሬ ሆን ተብሎ እንዳይለማ ሲደረግ ነበር። ብለዋል። አክለውም፤ “ክልሉ ብሎም የሸዋ ህዝብ ለለውጡ የራሱን አስተዋጽኦ በማድረጉ ከዚህም በላይ ይገባዋል። አማራ ክልል በተፈጥሮ ማዕድናት በግንባታ  ጥሬ ዕቃ ክምችት እንዲሁም በርካታ የተፈጥሮ ሀብት ቢኖረውም፤ ባሀብቶች አልተጠቀማችሁበትም” በማለት ለባለሃብቶች ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን የክልላችን ወጣት ፋብሪካ አያቃጥልም ይጠብቃል እንጂ፣ እስከዛሬም በክልላችን እንዲህ አይነት ችግር አልተከሰተም ወደፊትም አይከሰትም የሰላም ዋስትና እንሰጣን መጥታችሁ አልሙ” ሲሉ ባሃብቶችን ጋብዘዋል። አሁን ለሚገነባውም ኢንዱስትሪያል ኮምፕሌክስ አጠቃላይ ስራ እንደ ኩባንያዎቹ ስታፍ በመሆን አብረናችሁ ለመስራት በክብርት ፕሬዚዳንታችን ፊት ቃል እገባሁ  ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ “ ክልላችን ለኢንቨስትመንት ምቹና ተመራጭ ቢሆንም በሀይል አቅርቦት እጥረት ኢንቨስተሮችን ማስተናገድ አልቻልንምና ከሌላው በላይም ባይሆን የሚገባንን የሀይል አቅርቦት ልናገኝ ይገባል ሲሉ ለክብርት ፕሬዚዳንት በአጽንኦት ጥያቄ አቅርበዋል።”
ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው፤ 2፡30 ሰዓት በወሰደው የኪመና ጉዞዬ የተለያዩ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችን ስመለከት ያላየሁት መለያየትና መከፋፈልን ነው ያሉ ሲሆን በልጅነታቸው ስለሸዋ ህዝብ እየተነገራቸው ያደጉትን በአካል ተገኝተው በማየታቸውና ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል አመስግነዋል። ይህን ግዙፍ ኢንቨስትመንት ወደ ሀገር ቤት ለማምጣት ላደረጉት ትግልና በዚህ አገር ኢኮኖሚ ላይ ላበረከቱት የረጅም ጊዜ አስተዋፅኦ ዶ/ር ብዙአየሁ እንዳለን “የአገር ባለውለታ” ሲሉ በማሞካሸት ምስጋናና አክብሮት ቸረዋቸዋል።
“ለሚ ናሽናል ሲሚንቶ አክስዮን ማህበር ኢንዱስትሪያል ኮምፕሌክሱን ለመገንባት ከሚውለው 2.2 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ 11 ቢሊዮን ብር በኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ኩባንያ የሚሸፈን ሲሆን ቀሪው በቻናው ዌስት ኢንተርናሽናል ሆንዲንግና ከሌሎች የፋይናንስ ተቋማት በሚገኝ ገንዘብ ይሸፈናል ተብሏል።
ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ከአድዋ ጦርነት ከ3 ዓመት በኋላ በትንሽ የቤተሰብ ቢዝነስ እንቅስቃሴ ጀምሮ የራሱን የሻይ ቅጠል እርሻ በማበልፀግ እንደነ ጉድ ሞርኒንግና አንበሳ ሻይን ለገበያ ከማቅረብ ጀምሮ፣ ዛሬ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ድርሻ ባላቸው አምራች ኢንዱስትሪ፣ የማዕድን ፣ የሪል እስቴት ፣ ግብርናና አግሮ ኢንዱስትሪ፣ የድሬደዋው የረጅም አመቱ ናሽናል ሲሚንቶ”ና የግንባታ እቃዎች ንግድ፣ የሎጂስቲክና የትራንስፖርት ዘርፎች ላይ ተሰማርቶ ከልጅ ልጅ ሲቀባበል የመጣ ትልቅ አገር በቀል ኩባንያ ሲሆን ላለፉት 40 ዓመታት ደግሞ በብዙአየሁ አንዳለ (ዶ/ር) በጥንካሬ እየተመራ እዚህ መድረሱንና አራተኛው ትውልድ ይህንን ግዙፍ ኩባንያ ለመምራት በዝግጅት ላይ መሆኑም ተገልጿል።
የቻይናው ዌስት ኢንተርናሽናል ሆልዲንግ ኩባንያው እንደዚሁ የረጅም አመታት ታሪክ ያለው ሲሆን በቻይናና በዓለም ተወዳዳሪ ሆኑ የቴክኖሎጂ፣ የሲሚንቶ፣ ግብአቶች አምራች፣ የአማካሪ ድርጅትና በርካታ ኩባንያዎችን በስሩ አቅፎ በመላው ዓለም ሚንቀሳቀስ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን የቦርድ ሊቀመንበሩ ሚስተር ዣንግም ከ40 ዓመት በላይ የስራ ልምድ እንዳላቸው ተገልጿል።  ኩባንያው በቅርቡ  ደቡብ አፍሪካ የሚገኘውን የአፍሪካ ማዕከሉን ወደ ኢትዮጵያ አዙሮ አዲስ አበባ ላይ ዋና ማዕከሉን ለመክፈት ማሰቡንም ሚስተር ዣንግ ተናግረዋል።


Read 2089 times