Saturday, 06 March 2021 14:06

ጠ/ሚኒስትሩ ዙሩን ያከረሩት የምርጫ ቅስቀሳ!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(1 Vote)

  • ተቃዋሚዎች ከምርጫው እንዳይወጡ ተማጽነዋል
         • የማኒፌስቶ ድርሰት የሚጽፉ ፓርቲዎች አሉ ተብሏል
         • ለ"ተረኝነት" አቀንቃኞች ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል
             
              በኮሮና ሳቢያ መራዘሙን ተከትሎ፣ ፓርቲዎችን ያወዛገበው 6ኛው አገራዊ ምርጫ፤ እነሆ በግንቦት ወር መጨረሻ ላይ ሊካሄድ ቀን ተቆርጦለታል - በወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ  በሚመራው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ። (ለወ/ት ብርቱካን ጥናቱን ይስጥሽ!)
 የዛሬ ሦስት ሳምንት ግድም መሰለኝ የምርጫ ቅስቀሳው በይፋ የተጀመረው። በነገራችን ላይ #በምርጫ ብቻ; የሚለው የቦርዱ መሪ ቃል ወይም መፈክር ተመችቶኛል፡፡ (አዎ፤ ሥልጣን በምርጫ ብቻ!)
ገዢው ፓርቲ ብልጽግና፤ የምርጫ ቅስቀሳውን በሸራተን አዲስ፣ ማኒፌስቶውን በማስተዋወቅ ነበር ሞቅ ደመቅ ባለ ሥነ ስርዓት የጀመረው፡፡ በሂልተንም የሙዚቃ ኮንሰርት በነጻ አቅርቧል፤ ለአባላቱና ደጋፊዎቹ፡፡ (#ቱጃር ፓርቲ ምን አለበት; ብለው ያሽሟጠጡት አልጠፉም!) ግን እኮ ፓርቲውም ብልጽግና ነው፡፡ ብልጽግናን እያቀነቀነ ቱጃር ባይሆን ነበር የሚገርመው፡፡
የገዢው ፓርቲ ሁነኛ ተፎካካሪ እንደሚሆን የሚጠበቀው ኢዜማ በበኩሉ፤ ነጻ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ ቅስቀሳውን ሲያካሂድ ሰንብቷል። ከተቃዋሚ ፓርቲዎች በፋይናንስ አቅም የሚመራው ኢዜማ ሳይሆን አይቀርም። ለምርጫው ከ140 ሚሊዮን ብር በላይ መመደቡን የሰማሁ መሰለኝ፡፡ የሌሎቹ ግን ብዙም አይታወቅም፡፡ አብዛኞቹ የምርጫ ቦርድን ድጋፍ እንደሚጠብቁ አልጠራጠርም፡፡ አያደርገውና ቦርዱ "የፋይናንስ እጥረት አጋጥሞኛል" ቢል፣ ምን ይውጣቸዋል? ቀላል ነው፤ ሰበብ አድርገው ራሳቸውን ከምርጫው ያገላሉ፡፡ አንዳንዶቹ ግን ለምርጫው የሚሰጠውን የፋይናንስ ድጋፍ አስልተው ነው የሚቋቋሙት። በየአምስት ዓመቱ ብቻ ድምጻቸውን የምንሰማቸው ፓርቲዎች እኮ አሉ፡፡ (ስም መጥራት የምርጫ ሥነምግባሩ አይፈቅድም ብዬ ነው!)
ወደ ጀመርኩት አጀንዳ ልመለስ፡፡ እናላችሁ---ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ በምርጫ ቅስቀሳው ብዙ ቁም-ነገሮችን፣ ብዙ ወቀሳዎችን፣ ብዙ ሽንቆጣዎችን፣ ብዙ መልዕክቶችን፣ ብዙ ምክሮችንና ብዙ የስኬት ታሪኮችን ለሚመለከታቸው ሁሉ አድርሰዋል፤ ስም ሳይጠቅሱ (ይመለከተኛል ያለ የራሱን እየመረጠ ይወስዳል!)፡፡
በነገራችን ላይ የምርጫ ቅስቀሳ መጀመሩን የማብሰሪያ ፕሮግራም ነው በተባለበት ዕለት፣ ጠ/ሚኒስትሩ የተጧጧፈ ቅስቀሳ ነበር ያደረጉት - በሸራተኑ መርሃ ግብር! (ስህተት ነው አልወጣኝም!) ግን በአንድ ጊዜ  ዙሩን አከረሩት ብዬ ነው፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ምን እንደተሰማቸው ግን አላውቅም፡፡ ወደ ቁም ነገሩ ስንመጣ፣ የጠ/ሚኒስትሩ የምርጫ ቅስቀሳ፣ ማራኪና ቀልብ ሳቢ ነበር። ልብ በሉ! ስለ ይዘትና ሃሳብ ወይም የፖለቲካ ፕሮግራምና ፖሊሲ አይደለም የማወራው (እሱን ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ!) ይልቁንም ስለ ምርጫ ቅስቀሳ ስልትና አቀራረብ ነው (አንደበተ ርዕቱነትንም ይጠይቃል!)፡፡
በልምድ እንደምናውቀው፤ የጦቢያ ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የራሳቸውን ፕሮግራምና ፖሊሲ ከማስተዋወቅ ይልቅ የገዢውን ፓርቲ ሃጢያትና በደል መደስኮር ነው የሚቀናቸው። (ሥልጣን የያዘውን ፓርቲ አፈር ድሜ ማስበላት!) እንዲያ የሚያደርጉት ምናልባት አጓጊ ፖሊሲና ፕሮግራም ስለሌላቸው ሊሆን ይችላል፡፡ አሊያም ደግሞ ፕሮግራምና ፖሊሲያቸው ከገዢው ፓርቲ ጋር ተመሳሳይ እየሆነባቸውም ሊሆን ይችላል፡፡ ለዚህ ሁነኛ መላ ሆኖ ያገኙት ገዢውን ፓርቲ ማሳጣት፣ ማሳቀቅ፣ ማስወገዝ፣ ማስረገም ብቻ ነው፡፡ ይታያችሁ---ባለፉት ምርጫዎች ለውድድር የቀረቡ በብሔር የተደራጁ ፓርቲዎች፣ ከኢህአዴግ በምንድነው የሚለዩት?  (ባይብሱ ነው!)
ጠ/ሚኒስትሩ በሸራተኑ የምርጫ ቅስቀሳቸው፣ የብልፅግና ማኒፌስቶን በእጃቸው ይዘው ለታዳሚው እያሳዩ፤ “ይሄ ሰነድ ድርሰት አይደለም፤ ብዙ የሚፎካከሩን ፓርቲዎች ድርሰት እያዘጋጁ ነው፤ድርሰት ፖሊሲ አይሆንም” ሲሉ ተፎካካሪዎቻቸውን  ሸንቆጥ አደረጉ (እንደኔ ስም ሳይጠቅሱ!)፡፡
“ከአንድ ወር በኋላ የትምህርት ፖሊሲ አለኝ፤ የጤና ፖሊሲ አዘጋጅቻለሁ የሚል ሃይል ካለ፣ ድርሰት እንጂ ፖሊሲ መሆን አይችልም” ሲሉም ጨከን ብለው ወርፈዋል - ጠ/ሚኒስትሩ። (የምርጫ ፉክክር ሆናባቸው ነው!) እንግዲህ ትችቱ ውሸት ነው፤  መልካም ስምና ዝናችን በብልጽግና ጠፍቶብናል የሚሉ ተቃዋሚዎች (ምናልባት ካሉ ማለቴ ነው!)፤ የቃላት ጥይት ዝም ብሎ ከማባከን ይልቅ ፖሊሲዎቻቸውን  ወይም ማኒፌስቷቸውን ለህዝብ አቅርበው ትችቱ ሃሰተኛ መሆኑን ያረጋግጡ፡፡ (የማታ ማታ እኮ ዳኞቹ እኛ ነን፤ መራጮቹ!)
በዚህ አጋጣሚ በምርጫው የሚወዳደሩ ፓርቲዎችን የማሳስባቸው ወይም የማስታውሳቸው አንድ ብርቱ ጉዳይ አለ። ይኸውም፤ በምርጫው ሂደት ህግና ደንብ ጥሰው “ማኖ” እንዳይነኩና፣ ባለቀ ሰዓት ከውድድሩ የመሰረዝ ክፉ አጋጣሚ እንዳይደርስባቸው፡፡ ልብ በሉ! ምርጫ ቦርድ የድሮው አይደለም። በገዥው ፓርቲው ወይም በመንግስት የሚዘወር ዓይነት አይደለም፡፡ በራሱ ህግና ስርዓት የሚመራ ነው። የህግ ጥሰት ከተፈፀመ ማንንም አይምርም!! (ብልጽግናም ተቃዋሚዎችም ለቦርድ ለውጥ የላቸውም!)
በነገራችን ላይ  ከ100 በላይ የነበሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከግማሽ በላይ ቀንሰው ለምርጫው ወደ 50 ግድም የቀረቡት  እኮ በምርጫ ቦርድ የተቀመጠውን ህጋዊ መስፈርት ሳያሟሉ ቀርተው ነው፡፡ ምናልባት ባለማወቅ ይሆናል አሊያም በቸልተኝነት፡፡ ውጤቱ ግን በምርጫ ቦርድ መሰረዝ ሆነ፡፡ ወለም ዘለም አያውቅም፤ቦርዱ! በቅርቡም ቦርዱ ለብልፅግና ፓርቲ ሃላፊዎች የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ሳትሰሙ አትቀሩም፡፡ "በህግና ሥርዓት ተመሩ” ብሏቸዋል፡፡ ያለዚያ ግን ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስድ አሳስቧል፤ እጩዎችን እስከ መሰረዝ የሚደርስ!! እንደ ምርጫ ቦርድ በመንግስት ባጀት እየተንቀሳቀሰ፣ በራሱ መንገድ በገለልተኝነት የሚሰራው  ሌላው ተቋም፣ በቀድሞው የሂዩማን ራይትስዎች የአፍሪካ ዳይሬክተር  በዶ/ር ዳንኤል የሚመራው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ይመስለኛል። በኦሮሚያ ከተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ጋር በተያያዘ ያወጣቸውን ሪፖርቶች መመልከት ይቻላል፡፡ (ያውም ገና አቅሙን ሳያደረጅ!)  
ወደ ጠ/ሚኒስትሩ የምርጫ ቅስቀሳ ልመልሳችሁ። “ብልፅግና ጆሮ አለው፤ ዓይኑ የንስር ዓይን ነው፤ አፉ ቁጥብ ነው” አሉ ዶ/ር ዐቢይ፡፡ ("ድንቄም አፉ ቁጥብ" ብሎ የሚፎትት አይጠፋም!) ከዚያም የሼክስፒርን አባባል ተውሰው ማብራራት ያዙ፡፡ በኪሳችን ውስጥ ያሉ ሳንቲሞችና የ200 ብር ኖት ነበር ለንጽጽር ያቀረቡት። “በኪሳችን ውስጥ ያለ ሳንቲም ክብደቱና ድምፁ አያስቀምጥም፤ ይንጫጫል፤ ይጮሃል፤ በኪሳች ያለው የ200 ብር ኖት ግን በዝምታ በግርማ ሞገስ ይቀመጣል፤ አይንጫጫም። ልዩነቱ ገበያ ሲወጣ ነው፤ የሚንጫጫው ሳንቲም አንዲት ዳቦ አይገዛም። ባለ ግርማ ሞገሱ ኖት ግን ባይናገርም… ባይረብሽም… ባይንጫጫም… ሲወጣ በገበያ ላይ ትርጉም ያለው ነገር ያደርጋል።” በማለት የብልፅግና ፓርቲ በ200 ብር ኖት እንደሚመሰል ተናገሩ። (የሚንጫጩት እነማን ይሆኑ?) አሁንም ስም አልጠሩም፡፡ (ባለቤቱ ያውቀዋል በሚል!)
እኛ አፋችን ቁጥብ ሆኖ የምንናገረውን የምንተገብር ስብስቦች ነን አሉ - በአንደበተ ርዕቱነታቸው የማይታሙት ጠ/ሚኒስትሩ፡፡ “የተናገረውን የሚያደርግ፤ የጀመረውን የሚጨርስ ፓርቲ ነው” ሲሉም አሞካሽተውታል - ከተመሰረተ 3 ዓመት ያልሞላውን ብልፅግና ፓርቲያቸውን። ግን ማስረጃዎችን እየጠቀሱ ነው። የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት፣ ዩኒቲ ፓርክ፣ ሸገር ፓርክ፣ እንጦጦ ፓርክና ሌሎችንም የክልል የልማት ስኬቶች ዘርዝረዋል፡፡  
“ኢህአዴግን አፍርሰን ህብረ-ብሄራዊ ፓርቲ እንፈጥራለን ስንል ያመነን ፖለቲከኛ፣ ምሁር አንድም አልነበረም፤ ግን ማድረግ ችለናል” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ፓርቲው ከመፈጠሩም የበለጠ የሚያስደስተኝ ግን የኢትዮጵያን ህዝብ ከአይዲዮሎጂ እስራት ነፃ ያወጣ ፓርቲ መሆኑ ነው ብለዋል። ለዘመናት የማናውቀውን ሊብራሊዝም፣ ሶሻል ዲሞክራሲ፣ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ወዘተ -- ከማቀንቀን ወጥተን (ሰብረን) የራሳችንን ርዕዮተ ዓለም መፍጠር ችለናል ብለዋል- የመደመርን ፅንሰ ሃሳብ ወይም ፍልስፍና ማለታቸው ነው፡፡
 እኔ ደግሞ ብልጽግና ፓርቲን  ከልቤ የማመሰግነውና ባለውለታዬ ነው ብዬ ዕድሜ ዘመኔን የማወራለት በዕድሜ የገፉት የጦቢያ ፖለቲከኞች ከተለከፉበትና ለኢትዮጵያችን አደጋ ከጋረጠው "የብሔር ፖለቲካ!" እስር ነጻ ሲያወጣን ነው (ከዘረኝነት ስንፈወስ ማለቴ ነው!)፡፡ ያኔ ድንገት የብልጽግና ፓርቲ አባል ልሆን ስለምችል አደራ እንዳትታዘቡኝ። (ኢትዮጵያ ዳነች ማለት እኮ ነው!)፡፡ ያኔ ጉዳያችን ሁሉ ከዘርና ጎሳ ይላቀቅና የሀሳብ ልዕልና ላይ ይሆናል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ በምርጫ ቅስቀሳቸው ተቃዋሚዎች በምርጫ ፉክክሩ ድንገት ይስቡታል ተብሎ የሚጠበቀውን የ“ተረኝነት” ካርድ ቀድመው አንስተውታል። ማስጠንቀቂያም፣ ማሳሰቢያም  የሚመስል ሃሳብም ሰንዝረዋል፡፡  
“መላው የብልጽግና አባላት…መላው የብልጽግና ደጋፊዎች መገንዘብ ያለባቸው፣ ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና መውጣት የምትችለው፣ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በእኩልነት፣ በወንድማማችነት በፍቅር፣ ተከባብረው…ተፈቃቅደውና ተዋድደው መትጋት ሲችሉ ብቻ በመሆኑ ተረኝነት ብሎ የሚያስብም፣ተረኝነት ብሎ የሚያውጅም ካለ፣ የኢትዮጵያን ብልጽግና በአጭር የሚያስቀር ስለሆነ እኛ… ብልጽግናዎች…መላው የኢትዮጵያ ህዝብን በአንድ ልብና መንፈስ ተሳስረን፣ ሁሉንም የምንጠቅምና ሁሉንም የምናገለግል ….ሁሉንም የምንወድና ለሁሉም የምንቆም መሆን ይጠበቅብናል፡፡” ብለዋል፡፡ ("ተረኞች" ነን ባዮች ሰምተውት  ይሆን?!)
ቀጣዩን አገራዊ ምርጫ በተመለከተ የዛሬ 3 ዓመት ግድም ገና ወደ ሥልጣን ሲመጡ የተናገሩትን ደግመውታል፡፡ (ተቃዋሚዎች ካሸነፉ አቅፈን ሥልጣን እናስረክባቸዋለን በማለት!!) በነገራችን ላይ ተቃዋሚዎች ይሄን የጠ/ሚኒስትሩን ቃል በተደጋጋሚ ሲሰሙ ምን እንደሚሰማቸው ባውቅ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ (ከዚህ ቀደም ኢህአዴግ ተሳስቶ እንኳን "ከተሸነፍን" የሚል ቃል ከአንደበቱ ወጥቶ አያውቅም!) በነገራችን ላይ አሁን ለምርጫው የሚወዳደሩ አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በምርጫው ጠንካራ ተፎካካሪያቸው ማን እንደሆነ ስጠይቃቸው፤ ማንም እንደሌለ ነው አፋቸውን ሞልተው የሚናገሩት፡፡ (ከልባቸው እንደማይሆን እገምታለሁ!) በሌላ አነጋገር በምርጫው ከማሸነፍ ውጭ ሌላ አያስቡም ማለት ነው። (እንደ ቀድሞው ኢህአዴግ!) ይሄ ደግሞ እንደ 97ቱ ምርጫ ዓይነት ያልተጠበቀ ሽንፈት ሲገጥም መደነባበርን ያስከትላል። የሚይዙት የሚጨብጡት ያሳጣል፡፡ ቀጥለዋል፤ ጠ/ሚኒስትሩ፡፡  
“በሚቀጥለው አገራዊ ምርጫ የብልጽግና እሳቤና ማኒፌስቶ በግልጽ የተቀመጠ ቢሆንም፣ ዋናው ፍላጎታችን ግን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን አሸናፊ የሚያደርግ ምርጫ ማድረግ ነው፡፡” ብለዋል፡፡ (ጆሮ ገብ አገላለጽ ነው አይደል!?) ግን  ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን አሸናፊ የሚያደርግ ምርጫ ምን ዓይነት ነው? ዶ/ር ዐቢይ ሲያብራሩ፤ “ሰላማዊ ዲሞክራሲያዊ፣ ሁሉም በነፃነት የሚሳተፍበት… በሃሳብ ልዕልና የሚመረጥበት ወይም የሚወድቅበት ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ (ከዘር ፖለቲካ ሳንወጣ የሃሳብ ልዕልና ከየት ይመጣል!?)  
በዘንድሮ አገራዊ ምርጫ ላለመሳተፍ በቋፍ ላይ ለሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም አደናጋሪ የሚመስል መልዕክትም አስተላልፈዋል፡፡ ፓርቲዎቹ እንደ ምንም ብለው በምርጫው እንዲሳተፉ ተማጽነዋል፡፡ "ብናሸንፍም ዋጋ የለውም" በሚል ተስፋ ቆርጣችሁ ራሳችሁን ከምርጫው እንዳታገሉ፤ እንደ ቀድሞዎቹ ምርጫዎች ማጭበርበር አይኖርም ያሉት ዶ/ር ዐቢይ፤ በምርጫው ተወዳድራችሁ ለህዝቡ አማራጭ ሃሳቦችን አስፉለት ብለዋል፡፡ በዚህም ሳይበቁ  ፓርቲዎቹ በምርጫው እንዲሳተፉ ማናቸውም ድጋፍ ይደረግላቸዋል ብለዋል፡፡
በእርግጥ ለዚህ ንግግራቸው አንዳንድ ተቃዋሚዎች ምን እንደሚሏቸው መገመት አያስቸግርም፡፡ "አመራሮቻችንንና አባላቶቻችንን አስሮና ቢሮዎቻችንን ከርችሞ በምርጫ እንድንሳተፍ በአደባባይ መማጸን የክፍለ ዘመኑ ምርጥ ስላቅ ነው፤" እንደሚሉ አልጠራጠርም፤ እሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው፡፡
የዛሬውን ከምርጫ ቅስቀሳ ጋር የተገናኘ ፖለቲካዊ ወጌን የምቋጨው፣ ለዘንድሮ አገራዊ ምርጫ ለድምጽ ሰጪው ባዘጋጀሁት በዓይነቱ የመጀመሪያው ማኒፌስቶ ነው - የመራጮች ማኒፌስቱ በሉት!!
"ለምርጫው ድምጽ እንጂ ደም አንሰጥም!" ይላል፤ የመራጮች ማኒፌስቶው፡፡

Read 2917 times