Monday, 08 March 2021 00:00

የመቀሌዋ የግቢያችን የጦርነት ቃል አቀባይ

Written by  ብሩህ ዓለምነህ
Rate this item
(9 votes)

       ክፍል 5፡ አስፈሪው ጊዜ መምጣት ጀመረ
                       
                 ጦርነቱ በመከላከያ ኃይልና በህወሓት መካከል ሆኖ ሳለ፣ ብዙ ጊዜ የቃል አቀባያችን ንግግሮች ለምን አማራን ማዕከል እንደሚያደርጉ ግራ ይገባኛል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ባህሪ ያላቸው የህወሓት ካድሬዎችና የህወሓት አክቲቪስቶች ናቸው፡፡ ቃል አቀባያችን ግን የህወሓትን ስልጠና የወሰደች አይመስለኝም፡፡ ታዲያ ይሄ ልክፍት ከየት ያዛት? ምናልባት ከፖሊሱ ባሏ ሊሆን ይችላል፡፡
የህወሓትም ቢሆን ግን ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ አቶ መለስ ዜናዊን ጨምሮ የህወሓት ባለ ሥልጣናት በአደባባይ በሚያደርጉት ንግግር ስለ አማራ ሲያወሩ አይሰሙም፡፡ ታዲያ ካድሬዎቻቸውና አክቲቪስቶቻቸው፣ የፀጥታና የደህንነት አባሎቻቸው በዚህን መጠን ያህል አማራን ማዕከል ያደረገ ንግግር እንዴት ሊቆራኛቸው ቻለ?
ለዚህ ጥያቄ መልሱ አንድ ነው፡፡ ምንም እንኳ የህወሓት ባለ ሥልጣናት፣ የአደባባይ ሰነዶቻቸውና ንግግሮቻቸው ላይ አማራን ማዕከል ያደረጉ ሐሳቦችን ከማንሳት ቢቆጠቡም፣ በውስጥ መድረኮቻቸው ለካድሬዎቻቸውና ለአክቲቪስቶቻቸው በሚሰጧቸው ሥልጠናዎችም ሆነ ስብሰባዎች ላይ ግን አማራን በጠላትነት በሚፈርጁ የፖለቲካ ሐሳቦች፣ ታሪኮችና ትረካዎች ይግቷቸዋል፡፡ ህወሓት ለአማራ ያለው ጥላቻ ስር የሰደደ ከመሆኑ የተነሳ፣ አማራ የነካውን ነገር ሁሉ (ኢትዮጵያን፣ ኦርቶዶክስን፣ የሀገሪቱን የ3000 ዓመት ታሪክ፣ ባንዲራን፣ አማርኛ ቋንቋን፣ አንድነትን፣ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን…ሁሉ) እንዲጠላ አድርጎታል፡፡
ህወሓት የትግራይ ብሄርተኝነትን የገነባው ‹‹ህዝባችንን ተረባርበን ከድህነት ማውጣት አለብን›› ከሚል መንፈሳዊ ቁጭት ሳይሆን፤ የትግራይ ህዝብ በታሪክ ውስጥ ላጋጠመው ድህነትና ማህበራዊ ችግሮች የአማራን ህዝብ ተጠያቂ በማድረግና በጠላትነት በመፈረጅ ነው፡፡ ህወሓት በተመሰረተ በዓመቱ በ1968 የፃፉት የትግል ማኒፌስቶ ላይ ‹‹በትግራይ ክልል ለተስፋፋው የሴተኛ አዳሪነት ማህበራዊ ችግር የአማራን ህዝብ ተጠያቂ›› አድርጎ ፅፏል፡፡ ይሄንንም የፃፉት ተወልደው ካደጉበት ቀዬ በስተቀር ሌላውን የኢትዮጵያ አካባቢዎችንና ህዝቦችን የማያውቁና የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ በረሃ የገቡት የ19 እና የ20 ዓመት ጎረምሶች ናቸው፡፡
እነዚህ ጎረምሶች በአፍላ ስሜታቸው ላይ የፃፉትን የህዝብ ፍረጃ ክለሳ እንኳ ሳያደርጉበት አርጅተውበታል፡፡ ይሄም ፍረጃ ህወሓትን ከአማራ ህዝብ ጋር ደም ያቃቡ የባህል፣ የታሪክና የግዛት ግጭቶች ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል፡፡ ድህረ-ህወሓት የትግራይ ፖለቲካ ከእንደዚህ ዓይነት የብሄርተኝነት መንገድና አስተሳሰብ መውጣት አለበት፡፡
ህዳር 13 ቀን 2013 የህወሓት ልዩ ኃይል ከአክሱም ሲሸሽ የአክሱም ኤርፖርት የአውሮፕላን መንደርደሪያውን በርካታ ቦታዎች ላይ በዶዘር መቆፈሩን ኢቲቪ በቪዲዮ አስደግፎ አሳየ።
ህዳር 13 ቀን 2013 ረፋድ ላይ ‹‹የኢፌዲሪ መከላከያ ኃይል ከአዲግራት ወደ መቀሌ በሚወስደው መንገድ ላይ የምትገኘውን ዕዳጋ ሓሙስ ከተማን መቆጣጠሩንና መቀሌ ለመድረስም የምትቀረው ከተማ ውቅሮ ብቻ መሆኗን›› ኢቲቪ በሰበር ዜናው ተናገረ።
ይሄንን ዜና የሰማው የመቀሌ ህዝብም ተደናገጠ፤ "መከላከያ ኃይል መቀሌ ከገባ ይጨርሰናል" በማለትም  ትልቅ ፍርሃትና ጭንቀት ውስጥ ገባ። በዚህም የተነሳ ዜናው በተሰማ በተወሰኑ ሰዓታት ውስጥ መንገዶች በአንድ ጊዜ ጭር አሉ። ትራንስፖርት ማግኘት ከባድ ሆነ፤ ታክሲዎችና ባጃጆች አልፎ አልፎ ቢታዩም፣ የአገልግሎት ታሪፋቸውን ታክሲዎች በ100%፣ ባጃጆች ደግሞ በ300% ሰቀሉት። የከተማዋ የፀጥታ አካላት (ፖሊሶች) ደብዛቸው ጠፍቷል፤ ምክንያቱ ደግሞ አብዛኛዎቹ ወደ ጦርነቱ  የዘመቱ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ደግሞ  ዩኒፎርማቸውን አውልቀው በፍርሃት ተደብቀዋል። በየቀኑ ከመቀሌ ሲተኮሱ የነበሩ መድፎችም መሰማት አቁመዋል። የመጨረሻው የመድፍ ተኩስ የተሰማው መከላከያ ዕዳጋ ሓሙስን በያዘበት ዕለት እሁድ ህዳር 13 ቀን 2013 ማታ ነበር። ከዚያን ቀን በኋላ እስከ ህዳር 18 ቀን 2013 ድረስ የመድፍ ድምፅ መቀሌ ላይ ተሰምቶ አያውቅም።
የዕዳጋ ሓሙስ በመከላከያ ኃይል መያዝን ተከትሎ፣ ጠ/ሚ ዐቢይ ‹‹ህግን የማስከበርና የህልውና ዘመቻው›› ሁለተኛው ምዕራፍ በድል መጠናቀቁን ገለፁ፤ ‹‹ወደ 3ኛው ምዕራፍ (ማለትም ወደ መቀሌ በ3 አቅጣጫ የመግባት ምዕራፍ) ከመሸጋገራችን በፊት ለህወሓት ልዩ ኃይልና ሚሊሺያ እንዲሁም ባለ ሥልጣናት ለሁለተኛ  ጊዜ በሰላም እጃቸውን እንዲሰጡ የ72 ሰዓታት (የ3 ቀን) ጊዜ ሰጥተናቸዋል›› አሉ።
እኔ ግን በልቤ ‹‹…የ72 ሰዓታት ጊዜ ሰጥተናቸዋል›› የሚለው ነገር አናደደኝ። ‹‹ስንት ጊዜ ነው የ72 ሰዓታት የእፎይታ ጊዜ የሚሰጣቸው?! ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፈርቶ ከሆነ በግልፅ ይንገረን፤ በዚህ የተንዛዛ የእፎይታ ጊዜ ውስጥ ህወሓት ተሰባስቦና ዳግም አቅም ፈጥሮ መከላከያን የሚያጠቃ ከሆነ ዋነኛ ተጠያቂው ራሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንደሆነ ይወቅ!!›› በማለት በልቤ ዛትኩ፡፡
የዕዳጋ ሓሙሱን ዜና ተከትሎ፣ ሁለት አስፈሪ ዜናዎች ከመንግስት ባለ ሥልጣናት መጡ፡፡ የመጀመሪያው ከመከላከያ ባለ ሥልጣን ነው፣ ‹‹ወደ መቀሌ ስንገባ ህወሓት ህዝቡ መሐል ተወሽቆ ከባድ መሳሪያ የሚተኩስ ከሆነ፣ እኛም አፀፋ ለመስጠት እንገደዳለን፡፡ እንደዚህ የሚሆን ከሆነ ህዝቡ ከተማውን ለቆ ቢወጣ ይሻለዋል›› የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማስጠንቀቂያ ነው፡፡ ‹‹የመቀሌ ህዝብ ህወሓት ከሚንቀሳቀስባቸው ታርጌት ቦታዎች ራሱን ማራቅ አለበት›› የሚለው ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማስጠንቀቂያ፤ መቀሌ ላይ የአየር ድብደባ እንደሚኖር ፍንጭ የሰጡበት ስለሆነ እጅግ ፈራሁ፡፡ መቀሌን ሦስት ዓመት ብቻ ነው የኖርኩባት፤ ያንን ያህል መውጫ መግቢያዋን አላውቀውም። እናም ወዴት እንደምሄድ ጨነቀኝ፡፡ እስቲ ለማንኛውም የመቀሌ ልጆች ከሆኑት የሥራ ባልደረቦቼ ጋር ልመካከር በሚል በነጋታው ታክሲ ይዤ ወደ እነሱ ሄድኩ፡፡
እነሱ ጋ እንደ ደረስኩ ተሰባስበው ሻይ ሲጠጡ አገኘኋቸው፡፡ እኔም ተቀላቅያቸው ሻይ ካዘዝኩ በኋላ ‹‹እናንተ ሰዎች ስለ ጦርነቱ እውነተኛ መረጃ አላችሁ ወይ? አሁን ጦርነቱ ምን ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው? ኢቲቪና ትግራይ ቴሌቪዥን የሚያወሩት ነገር እኮ እርስበርሱ የሚጣረስ ነው፤ ማንን እንደማምን ግራ ገባኝ›› አልኳቸው፡፡ ‹‹እኛም ግራ ገብቶናል፤ መንግስት ዕዳጋ ሓሙስ ደርሻለሁ ይላል፤ ትግራይ ቴሌቪዥን ደግሞ አላማጣና ሁመራ ላይ ድል ተቀዳጅቻለሁ›› ይላል፤ ትክክለኛው መረጃ የትኛው እንደሆነ እኔም ግራ ገብቶኛል›› አለኝ አንደኛው ጓደኛዬ፡፡
እኔም፤ ‹‹እሺ ዶ/ር ደብረ ፅዮንስ ከቴሌቪዥን የጠፉት ለምንድን ነው? ከጠፉ ሳምንት ሊሆነው እኮ ነው›› አልኩት፡፡
እሱም፤ ‹‹እውነትህን ነው! ሌላኛው ግራ የሚያጋባው ነገር የእሱ መጥፋት ነው›› አለኝ፡፡
እኔም፤ ‹‹የዶ/ር ደብረ ፅዮን መጥፋት መከላከያ እያሸነፈ ይሆን እንዴ?›› አልኩት፡፡
እሱም፤ ‹‹አይ ለታክቲክ ሊሆን ይችላል የጠፋው›› አለኝ፡፡
‹‹ከሁሉም በላይ ግን አስፈሪው ጊዜ ከነገ ጀምሮ ያለው ነው›› አለኝ መልሶ፡፡
እኔም ‹‹እንዴት?›› አልኩት፤ አዲስ መረጃ የሚነግረኝ መስሎኝ፤
እሱም፤ ‹‹የዐቢይን መግለጫ አልሰማኸውም እንዴ?››
‹‹ምን የሚለውን?›› አልኩት፤
«ህወሓት ቤ/ክርስቲያን አካባቢ ኢላማ እያስቀመጠና የጦር መሳሪያ እያከማቸ ነው›› የሚለውን፤
‹‹ይሄንንማ ሰምቸዋለሁ›› አልኩት፡፡
‹‹ዐቢይ ይሄንን ያለው ቤተ ክርስትያናትን በአየር ለመደብደብ አስቦ ነው» ሲለኝ ደነገጥኩ!! ‹‹ህወሓት አብያተ ክርስትያናት ውስጥ ኢላማ እያስቀመጠና የጦር መሳሪያ እያከማቸ መሆኑን ደርሰንበታል›› የሚለውን የመንግስት መረጃ፣ ጓደኛዬ እንዴት አድርጎ እንደተረጎመው በጣም ገረመኝ፡፡ በጓደኛዬና በበርካታ የህወሓት ደጋፊዎች አመለካከት፣ ‹‹ህወሓት ቤ/ክ ውስጥ ኢላማማ ሆነ የጦር መሳሪያ እንዳያስቀምጥ ህሊናው ይከለክለዋል፤ እንደዚህ ዓይነት የወረደ ሥራ ህወሓት ሊሰራ አይችልም››፡፡
ከዚህ በፊት ቃል አቀባያችን በማይካድራ ከተማ ህወሓት አማራዎች ላይ ያደረሰውን ጭፍጨፋ በተመለከተ፣ ‹‹ህወሓት እንደዚህ ዓይነት አረመኔያዊ ድርጊት አይፈፅምም›› ብላ ስትከራከር ሰምቻታለሁ፡፡ እናም አሁን እስከ ዛሬ ድረስ እንቆቅልሽ የሆነብኝ ነገር ተገለፀልኝ፤ ይሄውም የትግራይ ህዝብ ህወሓትን እንደማያውቀው እርግጠኛ ሆንኩ። ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ የህወሓትን ባህሪና ግብር የሚያውቀውን ያህል የትግራይ ህዝብ ህወሓትን አያውቀውም፡፡ ይሄም በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው፤ ይሄ ሁኔታ ተነጋግሮ ለመግባባት አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ የትግራይ ህዝብ ህወሓትን የሚያምነው ‹‹ከእኛው አብራክ የወጣ ድርጅት ስለሆነ ጠንቅቀን እናውቀዋለን›› ብሎ ስለሚያስብ ነው፤ የሚያሳዝነው ነገር ግን የህወሓትን ተንኮልና አረመኔነት የእኛን ያህል አለማወቃቸው ነው፡፡
(ይቀጥላል…)


Read 8890 times