Saturday, 06 March 2021 13:43

የተፈጥሮ መልክ ጭምብል ሲሆን!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

    እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ይኸው እንግዲህ ኑሮም ግራ እንዳገባን፣ ‘ቦተሊካውም’ ግራ እንዳጋባን፣ የሰዉ ባህሪይ ግራ እንዳጋባን፣ የፖለቲካ ስብስቦች እውነተኛ ዓላማና ግብ ግራ እንዳጋባን፣ በሀገራችን ዙሪያ እየተካሄዱ ያሉ መሰባሰብ የሚመሳስሉ ነገሮች ግራ እንዳጋቡን፣ የ‘ፈረንጆች’ ነገር ግራ እንዳጋባን ...የ2013 ግማሿን ላፍ አደረግናት፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ! አንድዬ!
አንድዬ፡— ማነህ አንተ?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ! ያው ሁልጊዜ የማስቸግርህ ምስኪኑ ሀበሻ ነኝ፡፡ አንደኛውን ጠፋሁብህና አረፍኩት እንዴ፣ አንድዬ?
አንድዬ፡— ድምጽህ ጠፋብኛ፡፡ በሬ ላይ ቆመህ ነው ድምጽህ ከወንዝ ወዲያ ማዶ የሚመጣ የሚመስለው? ለመሆኑ እንዴት ከረምክ ምስኪኑ ሀበሻ?
ምስኪን ሀበሻ፡— ምንም አልል አንድዬ። ምንም አልል...
አንድዬ፡— ሁኔታህን እንደማየው ኑሮህ ምንም አይል የሚባልለት አይመስልም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል ይባል የለ...
አንድዬ፡— እንደው ቤተሰቦችህስ፣ ዘመዶችህስ ሁሉ ደህና ናቸው?
ምስኪን ሀበሻ፡— ደ...ደህና ናቸው፡፡
አንድዬ፡— አንተ ምንም አይል አልከኝ እንጂ ጭር ብለሀል እኮ፡፡ ለመሆኑ ራስህን በመስተዋት አይተህ ታውቃለህ?
ምስኪን ሀበሻ፡— ምኔን አየዋለሁ፣ አንድዬ! ምን የሚታይ ነገር ቀረኝ ብለህ ነው! አንድዬ፣ ኑሮ ከባድ ነው፡፡ የዕኛ ትከሻ ሆኖ ነው እንጂ ማንም የሚችለው አይደለም፡፡ ታከተን አንድዬ...አንዱን ልንጨብጠው ነው ስንል ሌላው እያመለጠን ትክት ነው ያለን፡፡
አንድዬ፡— ይሄን ያህል እንኳን ስብርብር ማለት አያስፈልግም፡፡ ጭር ብለሀል ስልህ ጭራሽ ልትጠፋ ተቃርበሀል አላልኩም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— እንደዛ ያላልከኝ አሳዝኜህ ነዋ፣ አንድዬ፡፡
አንድዬ፡— እናንተ እኮ ኑሮ መቼ ቀላል ነው ብላችሁ ታውቃላችሁ? የአንተስ እሺ፣ እንደው ሌላውስ ሰው ደህና ነው?
ምስኪን ሀበሻ፡— ደ..ደህና...አንድዬ፣ ዛሬ ተለወጥክብኝ እኮ!
አንድዬ፡— ተለወጥኩብህ! እንዴት ነው የተለወጥኩብህ? ብቻ እኔንም ለካስ ስትፋቅ ሌላ ነበርክ እንዳትለኝ!
ምስኪን ሀበሻ፡— ኸረ አንድዬ፣ እየው በአንተ ፊት እምላለሁ...
አንድዬ፡— ግዴለም፣ ምስኪኑ ሀበሻ፣ ግዴለም፡፡ መሀላው ይቅር፡፡ ስማ፣ መሀላን እኮ መጫወቻ ካደረጋችሁት ውላችሁ አደራችሁ፡፡ በእኔ ስም መጽሐፉን ግጥም አድርጋችሁ እየመታችሁ ትምሉ፤ ትገዘቱና ዘወር ብላችሁ ሌላውን መላ ማሳጣትና መገዝገዝ  ዋና ሥራችሁ ከሆነ ውሎ አደረ፡፡ እሺ...ግን ለምንድነው የተለወጥኩ የመሰለህ?
ምስኪን ሀበሻ፡— ምን መሰለህ አንድዬ፣ እንደው ደጋግመህ ጤንነቴንና የዘመዶቼን ጤንነት ስትጠይቀኝ ትንሽ ግራ ገብቶኝ ነው።
አንድዬ፡— ከዚህ በፊት ደህንነታችሁን ጠይቄህ አላውቅምና ነው!
ምስኪን ሀበሻ፡— እንደሱ ሳይሆን፣ የዛሬው ጠንከር ብሎብኝ ነው፡፡ ካጠፋሁ እታረማለሁ፣ አንድዬ፡፡
አንድዬ፡— (ይስቃል) አየህ አሁን ገና ጨዋታ አመጣህልኝ፡፡ ምን ነበር አሁን መጨረሻ ላይ ያልከኝ፣  እስቲ ድገምልኝ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ካጠፋሁ እታረማለሁ ነው ያልኩት፣ አንድዬ፡፡
አንድዬ፡— አየህ አይደል፣ አየህልኝ አይደል ምስኪኑ ሀበሻ! ለመሆኑ እናንተ መቼ ነው ጥፋት ካጠፋችሁ በኋላ ታርማችሁ የምታውቁት? በል ንገረኛ፣ መቼ አንድ ጊዜ የሠራችሁትን ጥፋት አምናችሁ ታርማችሁ ታውቁና ነው?
ምስኪን ሀበሻ፡— እሱማ አንድዬ...
አንድዬ፡— እውነቴን እኮ ነው፡፡ ዛሬ ከደረሳችሁበት እኔንም እያሳዘነ ያለ መላ ቅጡ የጠፋ ነገር ውስጥ የደረሳችሁበት ትልቁ ምክንያታችሁ ይኸው አይደለም እንዴ! ከመታረምና ከመስተካከል ይልቅ በስህተት ላይ ስህተት ማድረግን ጀግንነት እያደረጋችሁት አይደለም እንዴ! በጥፋት ላይ ያንኑ  ጥፋት መድገምን አዋቂነት ስላደረጋችሁት አይደለም እንዴ! የእናንተን ትልቁን ጥፋት አምናችሁ ማረም እያቃታችሁ በሌሎች ጥቃቅን ጥፋቶች ላይ ስለምትረባረቡ አይደለም እንዴ! ንገረኛ ምስኪኑ ሀበሻ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አስቆጣሁህ እንዴ አንድዬ?
አንድዬ፡— እየው እንግዲህ፣ እዛ የለመዳችሁትን ነገር ጥምዘዛ፣ እዛ የለመዳችሁትን ወደቀ ተብሎ የተነገራችሁን ተሰበረ ብላችሁ መተርጎም ድ...ተወው ብቻ፡፡ አላስቆጣኸኝም፡፡ አሁን ጥያቄዬን መልስልኝ፡፡ እናንተ መቼ ነው ከስህተታችሁ ታርማችሁ የምታውቁት?
ምስኪን ሀበሻ፡— እሱማ አንድዬ፣ እሱማ...ብቻ ምን እላለሁ፡፡ እውነትህን ነው አንድዬ፣ ስህተት አንገት የሚያስደፋባት ሳይሆን ደረት የሚያስነፋባት ሀገር ሆናለች፡፡
አንድዬ፡— ጎሽ አንተ ከእኔ የተሻለ አልከው፡፡ ብቻ ወደ ነገራችን እንመለስና ምን መሰለህ ምስኪኑ ሀበሻ ቀደም ሲል ነገራችሁ ሁሉ ግራና ግራ እየሆነ ግራ ትገቡኝ ነበር፡፡ በእርግጥ አሁን ግራ አትገቡኝም ማለት አይደለም፡፡ እንደውም በተጨማሪ ታሳዝኑኝ ጀምራችኋል...እንደውም አንዳንዴ እንባ እንባ እንዲለኝ ልታደርጉኝ ምንም አይቀራችሁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ይህን ያህል!
አንድዬ፡— አዎ፣ ይህን ያህል፡፡ እንደው ፍራሽ አንጥፌ አልቀመጥላችሁ ሆኖ ነው እንጂ...
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ አንድዬ፣  ተው እንደሱ አትበል! እንደሱ ስትል ሞራላችን ሁሉ እንክትክት ይላል፡፡
አንድዬ፡— አሁን አላችሁ እንዴ?
ምስኪን ሀበሻ፡— ምኑ፣ አንድዬ?   
አንድዬ፡— የሌለ ነገር እንዴት እንክትክት ይላል ብዬ ነዋ! እውነቱን ንገረኛ...እንክትክት ለማለት የሚበቃ ሞራል አሁን አላችሁ እንዴ! እኔ እኮ እንደውም ገንዘቡንም ወርቁንም ምኑንም ወንዝና ውቅያኖስ እያሻገራችሁ ወደየዓለም ክፍሉ እንደምታሸሹት ሞራሉንም አንደኛውን ወደ ውጪ ልካችሁት ይሆናል ብዬ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ነገሩስ እውነትህን ነው፡፡ ሞራሉን አሻግረነው ሳይሆን እዚሁ ዓይናችን እያየ ነው ተሸርሽሮ፣ ተሸርሽሮ ባዶ ሆኖ ነው፡፡ ለነገሩ የእኛን ሞራል ማን ይፈልገዋልና ነው ወደ ውጪ የምንልከው፡፡
አንድዬ፡— የእናንተ የአሁኖቹን ሞራል ነዋ ሌላው ያልፈለገው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አልገባኝም አንድዬ...
አንድዬ፡— ማለቴ መጀመሪያ አሸዋ ላይ እንደተሠራ ቤት መሰረት የሌለው ሞራል ይዛችሁ ነው እንጂ አሁን የደረሳችሁበት ደረጃ አትደርሱም ነበር፡፡ ያው ያለፈ ትውልድን የመቀጥቀጥ፣ የራሳችሁን ሳሎን ሳታጸዱ፣ የትናንቶቹ ጓዳ ውስጥ ያለውንም፣ የሌለውንም ቆሻሸ የመፈለግ አባዜ ይዟችሁ እንጂ የሞራል ጥንካሬያቸው ለሌላው የሚተርፍ ትወልዶች ነበሯችሁ፡፡ ብቻ እንዳልኩህ አሁን፣ አሁን ታሳዝኑኛላችሁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ አንተም እኮ ዝም ብለኸናል፡፡ ይሄ ሁሉ ጉዳችንን እያየህ ዝም ብለኸናል፡፡
አንድዬ፡— ታዲያ ምን ላደርግላችሁ ትፈልጉ ነበር?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ታውቀን የለ፣ መንገድ ስንስት ወደ ዋናው መንገድ መልሰና፡፡
አንድዬ፡— ታውቀን የለም ወይ አይደለም ያልከው?
ምስኪን ሀበሻ፡— አዎ፣ አንድዬ...ራሳችንን ከምናውቀው በላይ እኮ ታውቀናለህ፡፡
አንድዬ፡— በጭራሽ አላውቃችሁም። አውቃችሁ ይመስለኝ ነበር፡፡ ለምን መሰለህ...አብዛኞቻችሁ
 ከላይ ያለው የተፈጥሮ መልካችሁ ጭምብል እየሆነብኝ እኔንም ግራ አጋብታችሁኛል፡፡ በእናንተ ቋንቋ ልጠቀምና ካልተፋቃችሁ እውነተኛ መልካችሁን ማወቅ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ብቻ...ደህና ሁን ለዛሬ ይበቃሀል፡፡ ሰላም ግባ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አሜን አንድዬ፣ አሜን።
ደህና ሰንብቱልኝማ!_________________________________

Read 812 times