Saturday, 06 March 2021 13:21

ሙአዛ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በአዲስ አበባ በወረዳ 13 ለፓርላማ በግል ይወዳደራሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

  “ሐ የምርጫ መወዳደሪያ ምልክታቸው ነው”

            ሙአዛ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በአዲስ አበባ ከተማ የወረዳ 13 ምርጫ ክልል የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የግል እጩ ሆነው እንደሚወዳደሩ ለአዲስ አድማስ ገለፁ።
ቀደም ሲል በተለያዩ መገናኛ ብዙኃንና ማህበራዊ ሚዲያዎች ሙአዛ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ በአዲስ አበባ ወረዳ 12/13 ይወዳደራሉ ተብሎ ሲገለፅ የቆየው ትክክል እንዳልሆነና የሚወዳደሩት በወረዳ 13 መሆኑን ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል።
ይህም ከሲ ኤምሲ ሚካኤል ጀምሮ ሃያት አዲሱን ክፍለ ከተማ ድረስ የሚያካልል የምርጫ ወረዳ መሆኑን ጠቁመዋል።
በምርጫው በግልዎ ለምን ለመወዳደር አቀዱ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም ሁለት ምክንያቶች ወደ ምርጫው እንደጋበዟቸው ያስረዳሉ። “ቀጣይ አምስት አመት በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ የሽግግር ወቅት ነው ብዬ አስባለሁ የሚሉት መአዛ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ በየአጋጣሚው ስንናገረው የነበረው የህገ-መንግስት ማሻሻያን ጨምሮ አዳዲስ ሂደት ይኖራሉና አንደኛው ወደ ምርጫው እንድገባ ያነሳሳኝ በዚህ ሂደት ውስጥ መሳተፍ ስለምፈልግ ነው ብለዋል።
“በሁለተኛ ደረጃ ኢትዮጵያዊ እሴቶችን በተመለከተ በየመድረኩ ሲቀነቅኑ የነበሩትንና ፓርቲዎች የማያነሷቸው ሃሳቦች በፓርላማው ሊደመጥ ይገባል። ከዚህ አንፃር ተሳትፎ ማድረግ  እፈልጋለሁ” ብለዋል።
“ሐ” የምርጫ ምልክታቸው አድርገው የሚወዳደሩት ሙአዛ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል፤ ምልክቱን የመረጡትም “ሐ” ፊደል በግዕዝ ሐመር (መርከብ) ማለት በመሆኑ መሻገርን የሚያመለክት ነው ብለዋል።
መሻገርን፣ ማዳንን የሚያመለክት በመሆኑ ሃሳቤ ይገልጽልኛል፤ በሌላ በኩል ደግሞ “ሐ” ቅርጿ እንደ መርኸ (የእህል ማበራያ) የምታገለግል በመሆኗና ገበሬው ገለባውን ከምርት ከሚለይባቸው መሳሪዎች አንዱ በመሆኑ መርጨዋለሁ ብለዋል።
የምርጫ ቅስቀሳና ሂደቱን የሚመራ ኮሚቴም እያቋቋሙ መሆኑንና በቅርቡ ዝርዝር መረጃዎችን በተለይም ይዘውት ስለተነሱት ሃሳቦች ለህዝብ ይፋ እንደሚደርጉ ተወዳዳሪው ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል።




Read 12587 times