Saturday, 06 March 2021 12:57

የኮሮና ፅኑ ህሙማንን በጤና ተቋማት መረዳት የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሷል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

    • በየቀኑ በአማካይ 12 ሰዎች በበሽታው ሕይወታቸውን እያጡ ነው
          • በ10 ቀናት ውስጥ 8 ሺ ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል
          • በርካታ ፅኑ ህሙማን የመተንፈሻ መሳሪያዎች ወረፋ እየተጠባበቁ ነው
          • የግል ሆስፒታሎች በህሙማን ተጨናንቀዋል ተባለ
                     
            የኮቪድ ህሙማን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ መጠን  እየጨመረ መምጣቱን ያስታወቀው የጤና ሚኒስቴር ፤ በአሁኑ ወቅት ህሙማኑን ተቀብሎ በጤና ተቋማት ውስጥ ህክምና እንዲያገኙ ማድረግ የማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን ጠቁሟል። በ10 ቀናት ብቻ ከ8ሺ በላይ ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸውና 123 ህይወታቸውን ማጣታቸውን የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
በተለይም ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ መጠን እያጨመረ መምጣቱን  የጠቆሙት ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ፤ የህክምና ማዕከላት አዳዲስ ህሙማንን መቀበል የሚያስችል ቦታም ሆነ አቅም እንደሌላቸው ተናግረዋል። የጽኑ ህሙማን  ክፍሎችም በአዲስ አበባ ከተማም ሆነ በሁሉም የክልል ከተሞች መሙላታቸውንና በአገሪቷ ውስጥ ያሉት ሁሉም የመተንፈሻ መሳሪያዎች በህሙማን ተናግረዋል።
 በርካታ ፅኑ ህሙማንም በሞትና በህይወት መካከል ሆነው የመተንፈሻ መሳሪያዎች ወረፋ እየተጠባበቁ እንደሆነም ዶ/ር ሊያ ገልፀዋል። በበሽታው በየቀኑ በአማካይ 12 ሰዎች ህይወታቸውን እያጡ እንደሆነ የጠቆሙት ሚኒስትሯ፤ ይህ ቁጥር ተመርምረው በሽታው የተገኘባቸው ሰዎች ብቻ እንደሆኑም አመልክተዋል።
የበሽታው ስርጭት መስፋፋት ከዚህ ቀደም የበሽታ ምጣኔው ከ9-10 በመቶ የነበረውን አሁን በአማካይ ወደ 13 በመቶ እንዳሳደገውም የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ለፅኑ ህሙማን ቁጥር ማሻቀብ ዋንኛ ምክንያቱ በርካታ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ህመሙ እስኪባባስ ድረስ በቤታቸው መቆየታቸው እንደሆነም ተናግሯል። በኮቪድ የተያዙ ሰዎች ራሳቸውን አግልለው በቤታቸው መቆየታቸው የሚበረታታ ጉዳይ ቢሆንም በሽታው መቆየቱ ግን ለከፋ ችግር ያጋልጣል ብለዋል ሚኒስትሯ።
በአሁኑ ወቅት በአገራችን በኮቪድ -19 ቫይረስ የሚያዙ፣ ወደ ፅኑ ህክምና ክፍል የሚገቡና በበሽታው ሳቢያ ህይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየጨመረ በመሆኑ ህብረተሰቡ ራሱን ከበሽታው መከላከል የሚችልባቸውን መንገዶች ሁሉ መተግበር ይኖርበታል ሲሉም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ባወጣው መረጃ መሠረት፤ ካለፉት 3 ሳምንታት ወዲህ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን ለዚህም በአሁኑ ወቅት በማህበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ መዘናጋት መፈጠሩ ነው ተብሏል። ከዚህም በተጨማሪ፣ ሰርግ፣ ሃዘንና መሰል ሰዎች የሚሰባሰቡባቸው ፕሮግራሞች በስፋት እየተከናወኑ መሆናቸውም  ለቫይረሱ ስርጭቱ መስፋፋት በምክንያትነት ተጠቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅት በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙና የኮቪድ ህክምናን ሲሰጡ የቆዩ የግል የጤና ተቋማት መሉ በሙሉ በመሙላታቸው ሳቢያ ህሙማንን መቀበል እያቆሙ በመሆኑ ችግሩን ይበልጥ እያባባሰው መምጣቱን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለከተው።
ይህንን ችግር ለመቅረፍም ሁሉም የመንግስት የጤና ተቋማት ከሚሰጡት መደበኛ ህክምና ጎን ለጎን ፣ ለኮቪድ ህሙማን ህክምና ለመስጠት እንዲችሉ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ዶ/ር ሊያ ገልፀዋል።


Read 622 times