Print this page
Saturday, 06 March 2021 13:02

ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የተደረገበት ሆስፒታል አገልግሎት መስጠት ጀመረ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

  በውጪ አገር የሚሠጡ ሕክምናዎችን በአገር ውስጥ ለመስጠት ያስችላል የተባለውና ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የተደረገበት ሲልክ ሮድ አጠቃላይ ሆስፒታል ስራ ጀመረ።
በቻይና ባለሀብት የተሠራው ሆስፒታሉ፤ በህብለሠረሰር ህክምና፣ በጭንቅላት ቀዶ ጥገናና በሽንት ቱቦ ህክምና በአለም አቀፍ ደረጃ ጥራቱን የጠበቀ ህክምና ይሰጣል ተብሏል።
ሆስፒታሉ ከአንድ አመት በፊት ግንባታው ተጠናቆና በዘመናዊ የህክምና መሣሪያዎች ተደራጅቶ ስራ ለመጀመር ዝግጅት በማድረግ ላይ እያለ የኮቪድ 19 በሽታ በመከሠቱ ምክንያት ሆስፒታሉ ሙሉ በሙሉ ለኮቪድ ህሙማን አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል። በ11 ወራት ጊዜም ከ600 በላይ ለሚሆኑ የኮቪድ ህሙማን ህክምና ሰጥቷል።
የሆስፒታሉ ባለቤትና ዋና ስራ አስኪያጅ ሚስተር ፍራንክ እንደተናገሩት፤ ሆስፒታሉ አለም በደረሰበት ዘመናዊ የህክምና መሣሪያዎችና በብቁ ባለሙያዎች በመታገዝ በአገር ውስጥ የማይሰጡ ህክምናዎችን በመስጠት ታማሚዎች ወደ ውጪ አገር በመሄድ እንዲታከሙ የሚገደዱበትን ሁኔታ ያስቀራል። ይህም የውጭ ምንዛሬን ከማስቀረቱም በላይ ወደ ሌሎች አገራት በመሄድ የሚደርሰውን እንግልት ይቀንሣል ብለዋል።
ከጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጋር በመተባበር የህክምና ባለሙያዎች የተሻለ ዕውቀትና ሙያዊ ክህሎት የሚያገኙበት የስልጠናና የምርምር ማዕከል ለማድረግ እየተሠራም እንደሆነ ተገልጿል።
በሆስፒታሉ የተለያዩ ከባድና ውስብስብ ህክምናዎች የሚሠጡ ሲሆን የህብለሠረሰር ህክምናና የጭንቅላት ቀዶ ህክምና በሙያው የረጅም ጊዜ ልምድ        ባላቸው ባለሙያዎች  እየተሠጠ እንደሆነና  ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት ህሙማን ወደሆስፒታሉ በመምጣት ህክምናውን  እያገኙ እንደሆነ ተገልጿል። ሆስፒታሉ የአየር አምቡላንስ አገልግሎት ለመስጠት እየሠራ ነው ተብሏል ።
ሆስፒታሉ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን በመስጠት ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሆነና የኮረና ወረርሽኝን ተከትሎ ለ11 ወራት ሙሉ በሙሉ ለኮቪድ ታማሚዎች አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱም ተገልጿል ። ከጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጋር በመተባበር የሆስፒታሉ የህክምና ቦርድ ወደ ውጭ አገር ሄደው እንዲታከሙ የጻፈላቸውና የመታከሚያ ገንዘብ የሌላቸው 6 ሰዎች እያንዳንዳቸው ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቁና ከ12 ሰዓታት በላይ የወሰዱ ውስብስብ የጭንቅላት ቀዶ ህክምናን በነጻ መስጠቱም ተነግሯል ። በቀጣይነትም ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለሚላኩና ከፍለው መታከም ለማይችሉ ህሙማን የሚሆን 20 ኢኮኖሚ ክፍሎች መዘጋጀታቸውም ተገልጿል።
ሆስፒታሉ እስካሁን በአገራችን የሌሉ ዘመናዊ የMRI እና የCITYSCAN መሣሪያዎችን ጨምሮ ሌሎች የዘመኑ ቴክኖሎጂ  የደረሠባቸውን መሣሪያዎች ከብቁ ባለሙያዎች ጋር አሟልቶ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል


Read 600 times