Saturday, 06 March 2021 12:59

የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት በ6 ወር አፈፃፀም ከ90 በመቶ በላይ ማሳካቱን አስታወቀ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  በ6 ወር ውስጥ 233 ሚ. ብር ገቢ ሲያደርግ 88 ሚ ብር ያልተጣራ ትርፍ አግኝቷል
                                      
               ላለፉት 127 ዓመታት ዓለም አቀፍ የፖስታ አገልግሎት በመስጠት ታሪክ ያለው የኢትዮጵያ ፖስታ  አገልግሎት የ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹን 6 ወራት በስኬት ማጠናቀቁን አስታወቀ። የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ሃና አርአያ ስላሴ ትላንት ረፋድ በፅ/ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት ተቋሙ በ6 ወራት ሊሰራ ካቀደው 91.2 በመቶ ያሳካ መሆኑን ገልጸው ሊያስገባ ካቀደው 258 ሚ. ብር ውስጥ 233 ሚሊዮን ማስገባቱንና ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ10 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ገልጸዋል።
በ2012 ዓ.ም የበጀት ዓመት በ34 ሚ.ብር ኪሳራ የበጀት ዓመቱን ማጠናቀቁን የገለጹት ወ/ሮ ሃና በያዝነው የበጀት ዓመት በተሰራ የሪፎርም ስራ ተቋሙን ከገባበት ኪሳራና አዘቀት ለማውጣት በርካታ ስራዎች በመሰራታቸው ከኪሳራ ወጥቶ 88 ሚ.ብር ያልተጣራ ትርፍ በስድስት ወራት ማስመዝገቡ አበረታች ነው ብለዋል።
ይህንን ስኬት ያስመዘገበውም የኮቪድ -19 ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ በፖስታ አገልግሎት ሰጪዎች ላይ ያደረሰው አሉታዊ ተፅዕኖ ተቋቁሙም መሆኑንም ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ተናግረዋል።
ይሄው ረጅም ዓመት አገልግሎት ያለው ድርጅት በዋናነት አገልግሎት ከሚሰጥባቸው በደብዳቤ፣ በጥቅልና ኤክስፕረስ ሜይል ሰርቪስ (EMS) በተጨማሪ አዳዲስ አሰራሮችን መጨመሩንና ከነዚህም መካከል በቅርቡ የጀመረው የአሜሪካ ቪዛ አመልካቾችን ፓስፖርት የማድረስ ስራ ተጠቃሽ ሲሆን ይህንን አገልግሎት ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በባህር ዳርና በሀዋሳ ከተሞች መስጠት መጀመሩም ተገልጿል።
በሪፎርም ስራው ላይ በሙስና የተዘፈቀውን አሰራር በማስወገድ፣ አጥፊዎችን ለህግ በማቅረብ ፣ አሰራሩን በማዘመንና አቶሜትድ በማድረግ፣ ውዝፍ ገቢዎችን በመሰብሰብ፣ ወጪን በመቀነስ፣ የሰራተኛውን አቅም በስልጠና በመገንባት በኩል ባደረገው ጠንካራ እንቅስቃሴዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ተቋሙን ኪሳራ ማውጣትና ወደ ትርፋማነት እንዲሸጋገር ማድረግ መቻሉን ነገር ግን ከዚህም በላይ ብዙ ጠንካራ ስራዎች እንደሚጠበቅ አብራርተዋል።
በቀጣይ ሊሰሩ የታቀዱ አራት ዋና ዋና ጉዳዮች የተጠቀሱ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ተቋሙ የነበሩትበትን የፋይናንስ አቅም ማስተካከል፣ አጠቃላይ የአሰራር ሂደቶችን ማሻሻል፣ ተወዳዳሪ አገልግሎትና ገፅታ ግንባታ ላይ መስራት፣ ተቋማዊና የሰራተኛውን ብቃት ማሳደግን ጨምሮ የአግልግሎት ደህንነትና ፍጥነትን ማሳደግና የፋይናንስ ቁጥጥሩን ማጥበቅ የሚሉት ይኙበታል፡፤
እንደ ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ገለፃ ከላይ የተዘረዘሩት ጉዳዮች የተጀመሩ ሲሆን በዚህም ለውጥ መምጣቱንና በ6 ወር የተመዘገበው ውጤት ይህንኑ ስኬት እንደሚሳይ ገልጸዋል።  እንደ ሃፊዋ ገለፃ ምንም እንኳን ተቋሙ ለትርፍ የተቋቋመ ቢሆንም አገልግሎት ሲሰጥ የኖረው ማህበረሰቡን በማይጎዳ መልኩ እንደነበረና አሁንም ማህበረሰቡን በማይጎዳ መልኩ የአገልግሎት ክፍያ ማሻሻያ መደረጉን አስታውቀው  ከአግልግሎት ፍጥነትና ደህንነት አንፃር ብዙ መስራት እንደሚጠበቅባቸውና ያሉት ሃላፊዋ ባለፉት 6 ወራት ከመልዕክት ደህንነት ጉዳት ጋር በተያያዘ 200 ሺህ ብር የካሳ ክፍያ መክፈላቸውን ገልጸዋል በቀጣይ መልእክት በማስተላለፍ ሂደት ከተቋሙ ጋር ከሚሰሩት የኢትዮጵያ አየር መንገድና መልእክት አዳይ አገሮች ጋር ያለንን አሰራር በማዘመን የአገልግሎት ቅልጥፍናችን ደህንነቱን እናሻሽላለን ብለዋል።
በቀጣይ በፋናንስም ሆነ በደህንነት በኩል ያለብንን ችግር ለመቅረፍ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን፣ CCTV ካሜራዎችን፣ የሚላኩ እቃዎች ከተቋሙ ከወጡበት ጀምሮ እስከ ተቀባዩ ያለውን ሂደት መቆጣጠር የሚያስችከል ዘመናዊ አሰራር ላይ ትኩረት አድርገዋል ያሉት ሃላፊዋ የፖስታ ባህልን ለመመለስ የህፃናት የደብዳቤ ውድድርን ከመጀመር ጀምሮ ከብዕር ጓደኞች ማህበራት ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸወንና ላለፉት አራት አመታት የተቀዛቀዘውን የቴምብር ማሳተም ስራ ተቋሙ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

Read 751 times