Monday, 01 March 2021 19:49

የዓለማቀፍ ግንኙነት ሁለት ገፅታዎች - በአድዋው አስደናቂ ድል!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)


         የኢትዮጵያ የአድዋ ድል፣ ድርብ ድል ነው። እውቀትንና ቴክኖሎጂን ከመላው ዓለም እየገበዩ፣ ህልውናን የማደላደልና የማሳደግ ፍላጎት፣ ከዚያም የተግባር ትጋትና ስኬት፣ የአድዋ ድል አንድ ደማቅ ገጽታ ነው። በርካታ የኢትዮጵያ መሪዎችና ብዙ ተዋጊዎች፣ ከጥንቱ የጎራዴና የጋሻ ትጥቅ ጋር ብቻ ተጣብቀው አልጠበቁም፡፡ በደንዛዜ የኋሊት አልቀሩም። የዘመኑ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን፣ ከጠምንጃ እስከ መድፍ ድረስ፣ በትጥቅና በችሎታ ከዓለም ጋር ለመገስገስ፣ ብልህ ብልሆቹ ተግተዋል። የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤት፣ቀስ በቀስ እየገነነ፣ፍጥነቱም እየጨመረ ዓለማቀፍ መልካም የለውጥ ማዕበል እንደተፈጠረ እንደነበር ገብቷቸዋል፡፡ ወደ ኋላ መቅረት፣ ለኢትዮጵያ ትልቅ የህልውና አደጋ እንደሆነ ተገንዝበዋል፡፡ በሳይንስና በቴክኖሎጂ፣ በኢንዱስትሪና በቢዝነስ ውህደት አማካኝነት የተቀሰቀሰው ዓለማቀፍ የለውጥ ማዕበል እንዳያመልጣቸው እነ አፄ ማኒልክ ተጣጥረዋል። 80 ሺ የአድዋ ዘማቾች፣ ከጦርና ከጎራዴ ተሻግረው ጠመንጃ ታጣቂ የሆኑትም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ በጠመንጃ የትጥቅ ብዛት፣ የኢትዮጵያውያን ዝግጅት በጣም
አስደናቂ እንደሆነ፣ ታሪክ አዋቂዎች በተደጋጋሚ ፅፈዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን፣ በጦር መሳሪያ ብዛት ብቻ ሳይሆን፣ በአይነትና በጥራትም፣… በደንብ
ታጥቀው መዘጋጀታቸው ጠቅሟቸዋል። ብልህነታቸውንና አርቆ አሳቢነታቸውን ያሳያል። ለነፃነት ምን ያህል ክብር እንደነበራቸውም፣ ፅናታቸውም፣… ከዝግጅታቸው ያስታውቃል። ወደ አድዋ የዘመቱ የኢትዮጵያ አርበኞች፣ በብዛት የታጠቁት የጠመንጃ አይነትና ጥራት፣ ከጣሊያን ጦር ትጥቅ አይተናነስም። እንዴት ቢባል፣ “በአፈሙዝ በኩል ጥይት የሚጎርሱ” የድሮ ጠመንጃዎች፣ በአዳዲስ ጠመንጃዎች ተቀይረዋል። አንድ በሉ። በተሻሻለ ቴክኖሎጂ፣ ከጎን በኩል ጥይት የሚቀበሉ ጠመንጃዎች፣ በተለያዩ ኩባንያዎች ተፈብርከው ከዓለም ገበያ ሲቀርቡም፣ ኢትዮጵያውያን የሩቅ ተመልካች ሆነው አልቀሩም፡፡ ባለማቀባበያ ጠመንጃዎችም የዘመኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ናቸው። ጥይት ከተተኮሰ በኋላ፣ ማቀባበያው በራሱ ጊዜ ቀልሃ የሚተፋ የጦር መሳሪያ ቴክኖሎጂ፣ ቶሎ ቶሎ ለመተኮስ የተፈጠረ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ በዚያን ወቅት፣ በመላው ዓለም ገና አዲስ ነበር። ከ20 ዓመት ያለፈ ብዙ እድሜ አልነበረውም። ኢትዮጵያውያን፣ ከአለም ጋር እኩል አዲሱን ቴክኖሎጂ እየታጠቁ ነበር ማለት ይቻላል። የመታጠቅ ጉዳይ ብቻ አይደለም። ጥይት የሚሰሩና የሚፈበርኩ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች፣ ከቴክኖሎጂው ጋር እኩል ለመራመድ መጣጣር የጀመሩበት ዘመንም ነው። ይህም ብቻ አይደለም፡፡ የአድዋ ድል፣
ጠመንጃ ከጥይት ዝናር ጋር የመታጠቅ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ ለቴክኖሎጂው የሚመጥን “ጎበዝ ተኳሽ” የመሆን፣ የችሎታና የሙያ ጉዳይም ነው፡፡
• “ጥይት አያባክኑም” - እሳት ተኳሾች። በእርግጥ ሁሉም ዘማች ሁሉም ታጣቂ፣ እሳት ሊሆን አይችልም፡፡ ነገር ግን ታሪክ ዘጋቢዎች በማስረጃ እንደፃፉት፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን አርበኞች፣ ከጠመንጃቸው ቴክኖሎጂ ጎን ለጎን፣ በችሎታም የሚቀመሱ አልሆኑም። ስለ ኢትዮጵያ ጦር ፣ በአድዋ ዘመቻ
ከተመዘገቡት ድንቅ ታሪኮች መካከል አንዱ፣ የተኩስ ችሎታውን ይመሰክራል። “ጥይት አያባክኑም” በሚል አገላለፅ፣ብዙ የኢትዮጵያ ተዋጊዎች አድናቆትን አትርፈዋል። በእርግጥ የኢትዮጵያ ጦር፣ ከላይ እስከ ታች፣ በክፍል እና በዘርፍ፣ በተወሰነ ደረጃ ቢሰናዳም፣ ገና ጥንቅቅ ባለ መዋቅር የተደራጀ አልነበረም።
ነገር ግን፣ ጠመንጃውን እንደጓደኛው ከጎኑ የማይነጥል እያንዳንዱ ታጣቂ፣ ተኩስና ውጊያን ጠንቅቆ ያውቃል። በእውር በድንበር አይተኩስም፡፡ አብዛኞቹ ባለጠመንጃ ዘማቾች፣ በጥንቃቄና በፍጥነት ወደ ጠላት ምሽግ የመጠጋት ፣ ኢላማን መርጠው የመተኮስ ሙያና ወኔ፣ ነበራቸው፡፡ ታዲያ፣ “ጥይት አያባክኑም” ሲባል፣ “ተኩሰው አይስቱም” ማለት ብቻ አይደለም። ጥይትና ቀልሃ፣ በዚያን ጊዜ፣ በጣም ውድ ነው። ከውድነቱ የተነሳ፣ ቀልሃ ለብዙ ዓመታት፣ መገበያያ ገንዘብ ሆኖ ነበር፡፡ ምናለፋችሁ! ኢትዮጵያውያን የአድዋ ዘማቾች፣ በገንዘብ ነው የተዋጉት ማለት ይቻላል። በዘፈቀደ መተኮስ ኪሳራ ነው፡፡ ተኩሶ መሳት፣ ገንዘብን በዋዛ ከመወርወር ከማቃጠል አይተናነስም፡፡ ግን የሙያም ጉዳይ ነው፡፡ “ጥይት ማባከን”፣ የገንዘብ ኪሳራ ብቻሳይሆን፣
የሙያ ቀሽምነትም ይሆናል። በጀግንነትና በችሎታ የሚኮሩ ብዙ ኢትዮጵያውያን አርበኞች ደግሞ፣ ኢላማቸውን ለይተው የመተኮስ ልምዳቸውንና
ችሎታቸውን አሳይተዋል፡፡ በአጠቃላይ፣ የአድዋ ባለድል ዘማቾች፣ የሙያ ብቃትንም ልበ ሙሉ ወኔንም የተላበሱ ጀግና ተዋጊዎች መሆናቸው ተመስክሮላቸዋል፡፡ እነዚህ የጠመንጃ ታጣቂዎች ናቸው፡፡ በመድፍ ትጥቅና በሌሎች ከባድ መሳሪያዎች ላይም፣ የኢትዮጵያ መሪዎች፣ የኋሊት አልቀሩም። የአቅማቸውን ያህል፣ከዓለማቀፍ ቴክኖሎጂ ጋር እኩል ለመራመድ ጥረዋል። ቀላል ፈተና አይደለም፡፡ አንዳንዶቹ ከባድ መሳሪያዎች፣ በሃረር በኩል፣ በምርኮ የተገኙ የድሮ መድፎች ናቸው። ነገር ግን፣ የጣሊያን ጦር ከታጠቃቸው ከባድ መሳሪያዎች የሚበልጡ ከባድ መሳሪያዎች፣ በኢትዮጵያውያን እጅ ገብተዋል፡፡
አፄ ሚኒሊክ ያስቀመጧቸው 6 አውቶማቲክ ተኳሽ ከባድ መሳሪያዎች፣ ገና አዲስ የዘመኑ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች መሆናቸውን ታሪክ ፀሀፊዎች ጠቅሰዋል፡፡ የጣሊያን ጦር መድፎችን ለመመከት ብቻ ሳይሆን ላንቃቸውን ለመዝጋትና ለማዳፈን፣ ችለዋል የምኒሊክ ጥቂት ዘመናዊ መድፎች፡፡ ከርቀት በመተኮስ
ብልጫ ነበራቸው፡፡ ኢላማቸውን በትክክል በመምታትም፤ የኢትዮጵያውያንን ከባድ መሳሪያ ትጥቅና የተኳሾች ችሎታ፣ ለአድዋ ድል፣ የድርሻቸውን አበርክተዋል። በግልጽ የሚታይ ውጤት አስመዝግበዋልና፡፡ በአጠቃላይ፣ የኢትዮጵያ መሪዎችና አርበኞች፣ የዘመኑን ቴክኖሎጂ በብዛትና በጥራት ቅ ለመታጠቅ ቀድመው መዘጋጀታቸው ጠቀመ፡፡ ይሄ አይገርምም፡፡ ከአፄ ቴዎድሮስ ጀምሮ፣ በአፄ ምኒልክና ከዚያም በኋላ፣ በርካታ የኢትዮጵያ መሪዎች፣ እውቀትንና ቴክኖሎጂን፣ ሳይንስንና ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት ተጣጥረዋል። ባይሳካላቸውም እንኳ ተመኝተዋል፡፡ ደግሞም፤ ለስልጣኔ ቅንጣት ደንታ ያለው
ሰው፣ ለራሱና ለአእምሮው ቅንጣት ክብር ያለው ሰው፣ እውቀትንና ቴክኖሎጂን ይሻል፡፡ ከየትም ቢመጣ፣ በጉጉት ይቀበላል፡፡ ዓለማቀፍ እውቀትና ቴክኒሎጂን፣ ከራሱ ጋር ያዋህዳል፡፡ በዚያው ልክ፣ የአገራችን ጥበበኛ መሪዎችና አዋቂዎች፣ አለማቀፍ መልካም የለውጥ mማዕበልን ብቻ ሳይሆን፣ የጥፋት ማዕበልንም በአስተዋይነት ይመረምራሉ፤ ይገነዘባሉ፣ አስቀድመው ይጠነቀቃሉ፤ ይዘጋጃሉ ለህልውናና ለነፃነት ክብር ያላቸው፡፡ ለዚህም ነው፣ አፄ ቴዎድሮስ፣ አፄ ዮሐንስ፣ አፄ ምኒሊክ የትፋት ማዕበልን በሩቁ ለማስቀረት ተግተዋል። ገፍቶ ሲመጣም ይሰብሩታል፡፡ ዓለማቀፍ የቅኝ ግዛት ወረራና ጥቃት ሲመጣባቸው ይከላከላሉ፣ ይገታሉ፤ ያባርራሉ - ከየትም የዓለም አካባቢዎች ቢመጣባቸው። • የዓለማቀፍ ግንኙነት ሁለት ገፅታዎች - ለክፉም ለደጉም፡፡
የአድዋ ድል ሁለቱንም ገፅታዎች ያሟላል፡፡ አንደኛ ነገር፣ የአድዋ ዘማቾች ዘመናዊ ጠመንጃ እንደታጠቁት ሁሉ፣ በእውቀትና በኢኮኖሚ፣ ዓለማቀፍ መልካም ለውጦች፣ በጭራሽ ሊያመልጡን አይገባም፡፡ ከመልካም ዓለማቀፍ በረከት ርቀን የኋሊት መቅረት የለብንም፡፡ ከአለማቀፍ መጥፎ የለውጥ ማዕበሎች ደግሞ በሩቁ የማምለጥ እርቅ አስተዋይነት፣ እውቀትና ጥበብ ሊኖረን ይገባል፡፡ ለይቶለት ከመጣ ደግሞ፣ መመከትና ማሸነፍ አለብን። ከሆነልን ግን፣ የጥፋት ማዕበልን በሩቁ የማስቀረትና የማምለጥ አቅምና ብልሃት ሊኖረን ይገባል፡፡ የአድዋ ዘመቻ በሁለቱም ገፅታ፣ ድንቅ ስኬት ነው። ዓለማቀፍ የቴክኖሎጂ ግስጋሴና መልካም የለውጥ ማዕበል አላመለጠውም። የያኔው ኢትዮጵያውያን ቴክኖሎጂውን ታጥቀውታል። ዓለምን ከዳር ዳር ያዳረሰ
የያኔው አጥፊ ዓለማቀፍ ማዕበልን፣ ማለትም የቅኝ ግዛት ወረራን ደግሞ መክተው አሸንፈዋል። አገራችንም ከዓለማቀፍ መጥፎ የለውጥ ማዕበል አምልጣለች።

Read 8305 times