Monday, 01 March 2021 19:45

ኢትዮጵያ ከአቋሟ ንቅንቅ ማለት የለባትም

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

 ከአፍሪካ ኅብረት በተጨማሪ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የአውሮፓ ኅብረትና የአሜሪካ መንግሥት በሶስቱ ሀገሮች መካከል በሚደረገው የሕዳሴ ግድብ ውኃ አሞላልና አስተዳደር ላይ በአደራዳሪነት እንዲገቡ ሱዳን ከሰሞኑ ጥያቄ አቅርባለች። ይህን ጥያቄ የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ
ሽኩሪ እንደሚደግፉት ገልጸዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን፣ የአውሮፓ ኅብረትንና አሜሪካን በአደራዳሪነት ማስገባት ማለት ችግሩን የበለጠ ማወሳሰብ ነው የሚሆነው፡፡ አሜሪካ በታዛቢነት ገብታ ያሳየችው ምግባር ጥሩ ትምህርት እንደሚሆን አያጠራጥርም። “ማን የሠራውን ግድብ ማን ያስተዳድረዋል” የሚል መልስ ከዚህ ቀደም የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ዲና ሙፍቲ፤ “ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ኅብረት ውጭ ሌላ
አደራዳሪ አትቀበልም” ሲሉ ቁርጥ ያለ መልስ ሰጥተዋል። ተገቢም ነው፡፡ ሌላው እጅግ ደስ ያሰኘኝ ጉዳይ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ፣ ዶ/ር ኢንጂነር
ስለሽ በቀለ፤ ሁለተኛው የግድቡ ውኃ ሙሌት የማንንም ወገን ፈቃድ ሳይጠብቅ በመጪው ሐምሌ የሚከናወን መሆኑን ማረጋገጣቸው ነው። ሱዳንና ግብፅ እንደ ሌሊት ቅዠት እያባተታቸው ያለው፣ እነሱ በራሳቸው የሠሩት በላይኛው የተፋሰሱ አገራት ላይ ሥልጣን ሰጥቶናል ብለው የሚያምኑት እ.ኤ.አ የ1929
እና 1959 የሁለቱ አገሮች የውኃ ክፍፍል ስምምነት ነው። ኢትዮጵያ ይህን ስምምነት እንደማትቀበለውና በስምምነቱ እንደማትገባ ሺ ጊዜ ተናግራለች፤ እነሱ መስማት ባይፈልጉም፡፡ ኢትዮጵያ በፊንጫ ግድብ የጀመረችውን የዐባይ ተፋሰስን የማልማትና ለጥቅሟ የማዋል ሥራ በተከዜ ቀጥላለች። አሁን ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ ደርሳለች። ነገ ደግሞ ባሮና አኮቦ፣ ሌሎችም በተራቸው ይቀጥላሉ፡፡ የሱዳን የመስኖና የውኃ ሚኒስትር ያሲር አባስ፤ ኢትዮጵያ በራሷ ውሳኔ አንድም አስገዳጅ ስምምነት ሳትገባ የሕዳሴውን ግድብ ውኃ የምትሞላ ከሆነ፣ ለአገራቸው ከፍተኛ ሥጋት እንደሚጋርጥባት ሰሞኑን ለሮይተርስ
ተናግረዋል፡፡ በሌላ ጊዜ ደግሞ የግድቡ መሞላት በመካከለኛው ሱዳን የሚኖሩ ሱዳናዊያን እጅግ እንደሚቸገሩ ተናግረዋል። የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ፤ ሃያ ሚሊዮን ሱዳናውያን ችግር ላይ እንደሚወድቁ አስታውቀዋል። በዚህም አሉት በዚያ ዋናው ፍላጎታቸውና ጥረታቸው፣ ኢትዮጵያን አንድ አስገዳጅ ውል ውስጥ ማስገባት ነው። ሰምተው እንዳልሰሙ መሆን ካልፈለጉ በስተቀር “ኢትዮጵያ በውኃ ሃብቷ የመጠቀም መብቷን አሳልፎ የሚሰጥና የሚገድብ ምንም አይነት ስምምነት አትፈርምም” ሲሉ ዶ/ር ኢንጂነሩ በቀለ ቀደም ሲል በግልጽ ቋንቋ ተናግረዋል፡፡ የደንቆሮ ለቅሶ መልሶ መልሶ ሆነ እንበል? ሱዳንና ግብፅ “ኢትዮጵያ አስገዳጅ ውል መፈረም አለባት” ሲሉ እራሳቸውን የሚያዩት እነሱ አዛዥ፣ ኢትዮጵያን ታዛዥ አድርገው ነው። ውኃው ከየት ወደ የት እንደሚፈስ እንኳ በሃሳባቸው ውስጥ አይመጣም። ትዕቢታቸው እስኪተነፍስ ድረስ ኢትዮጵያ ጊዜ ወስዳ ልትጠብቃቸው ያስፈልጋል። እቴጌ ጣይቱ ብጡል፣ ጣሊያን የመቀሌ ምሽጉን ለቆ እንዲወጣ ያደረጉት፣ የጣሊያን ጦር የሚጠቀምበትን የምንጭ ውኃ በእጃቸው
በማስገባታቸው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርም ሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከታሪኩ የሚማሩት እንደሚኖር ተስፋ አደርጋለሁ። ኢትዮጵያ ግብፅና ሱዳን በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ የሚያደርጉትን ድርድር ወደ ፊት እንዳይራመድ አንቀው የያዙት ጉዳዮች፡- የግድቡ አስተዳደር፣ ድርቅና ከፍተኛ ድርቅ በሆነ ጊዜ የታችኛው አገሮች የሚያገኙት የውኃ መጠን ምን ያህል መሆን አለበት የሚል መሆኑን በብዙ የመገናኛ ብዙኃን ተደጋግሞ ተዘግቧል። ስለ ግድቡ አስተዳደር በግልፅ ቋንቋ መልስ የተሰጠ በመሆኑ ወደ እርሱ አልገባም። ምን ያህል የሚለውን የመጠን ጉዳይ ግን ኢትዮጵያ
አስቀድሞ መቀበል የለባትም። ለዚሁ መልሷ #እኔ እግዜር አይደለሁም; የሚል መሆን አለበት። ድርቅም ሆነ ተከታታይ ድርቅ የሚከሰተው በኢትዮጵያ መሬት ላይ ነው። የጎደለ ግድቧን መሙላት የሚቸግራት ኢትዮጵያ ናት። የአየር ትንበያውን አምና ብትጠቀምም ሆነ ብትጎዳ የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያ ናት። ግብጽና ሱዳን በኢትዮጵያ ከታየው ሁኔታ ተነስተው ራሳቸውን ለማዘጋጀት በቂ ጊዜ አላቸው። ስለዚህም ድርቅም ሆነ ተከታታይ ድርቅ ፈፅሞ የኢትዮጵያ
ሸክም መሆን አይኖርበትም። ሁሉም ራሱን መታደግ ይገባዋል፡፡ ኢትዮጵያ አምርራ መቃወም መታገልና ለሌላው ዓለም ማሳወቅ ያለባት አንድ ነገር አለ። ይኸውም “የግብፅ ኅ ልውና ዘጠና በመቶ የተንጠለጠለው በዓባይ ውኃ ነው” የሚለው ነው። ግ ብፅ ለ ብዙ መ ቶ ዓ መት የ ሚበቃ የከርሰ ምድር ውኃ አላት። እስከ ሁለት ሺህ ኪሎ ሜትር በሚዘረጋ መሬት ከቀይ ባሕር ጋር ትዋሰናለች። በዚህ ሁሉ ርዝመት የባሕር ውኃ ታገኛለች። ሁለቱንም ለማልማት አለመፈለጓ እንጂ የውኃ ችግር ያለባት አገር አይደለችም። ስለዚህም ኢትዮጵያ ግብፅ ያላትን የውኃ ሃብት እንድታለማ በመገፋፋት ዓለም አቀፍ ተፅእኖ
እንዲያርፍባት ማድረግ ይኖርባታል። ሱዳን ድንበር አልፋ የኢትዮጵያን መሬት የያዘችው፣ በጦር በማስፈራራት ኢትዮጵያን አንድ አይነት አስገዳጅ ውል ውስጥ ለማስገባት በማሰብ እንጂ ነገሩ ያዛልቀኛል ብላ እንዳልሆነ ይታመናል። በአንድ ወቅት ሱዳኖች፤ “ኢትዮጵያ የውኃ ሃብቷን ብታለማና ሌሎች ግድቦችን ብትሰራ ሱዳን አትቃወምም” ለማለት የተገደዱት ከአንድ አመት በላይ ለሆነ ጊዜ ኢትዮጵያ ምንም አይነት አሳሪ ውል ላለመፈረም በያዘችው አቋሟ
በመጽናቷ ነው። አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ ከአቋሟ ንቅንቅ ማለት የለባትም፡፡


Read 959 times