Monday, 01 March 2021 19:36

"በዓለም ረዥሙ የትንፋሽ መሳሪያ"

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  የዳውሮ ዞን ባህል ኪነት ቡድን ድምፃዊና ተወዛዋዥ ነው፤ ታምራት ተክሌ። የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ባለፈው ሳምንት ለስራ ወደ ዳውሮ ዞን ባቀናችበት ወቅት አግኝታ ስለ ሙያው፣ ስለ ዲንካ ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያ አሰራርና አጨዋወት እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች አነጋግራዋለች፡፡

        በዳውሮ የባህል ኪነት ቡድን ውስጥ ያለህ ሚና ምን ይመስላል? እኔ በባህል ኪነት ቡድኑ ውስጥ በዋናነት ድምፃዊ ሆኜ የማገለግል ቢሆንም
ተወዛዋዥም ነኝ። ስለ ዳውሮ ባህላዊ ሙዚቃ መሳሪያዎች እስኪ አብራራልኝ? የዳውሮ ዞን ዋነኛ ባህላዊ ሙዚቃ “ዲንካ” ይባላል። አንድ በጣም ረጅምና ሶስት አነስ አነስ ያሉ ዲንካዎች ከከበሮ ጋር ተጣምረው በሚያወጡት ጥኡመ ዜማ ነው ባህላዊ ውዝዋዜውም የ ሚከወነው። እ ንግዲህ ዲንካ በዓለም ትልቁና ረጅሙ የትንፋሽ መሳሪያ ሲሆን ሰባት ሪትሞች አሉት። እስኪ ሰባቱን ሪትሞች ዘርዝርልኝ? አንደኛው “የዳ”፣ ሁለተኛው “ታርቻ”፣ ሶስተኛው “ዜቃ”፣ አራተኛው “ሎማቶ”፣ አምስተኛው “ሀታ” እና ሌሎችም ሆነው ሰባት ሪትሞች ላይ ነው የምጫወተው። እንደሰማሁት ሰባቱም ሪትሞች የየራሳቸው የውዝዋዜ አይነት አላቸው። ትክክል ነው? በሚገባ! ሁሉም ሪትሞች የየራሳቸው የውዝዋዜ አይነት አላቸው። በጣም ከባዶች ናቸው፤ ግን እኛ ሁሉምን ሪትሞች በውዝዋዜ ነው የምንገልፃቸው። አራቱንም ሪትሞች ያለ ዘመናዊ መሳሪያና ዳንስ ቅልቅል በአንድ መድረክ ላይ በዲንካ ብቻ እንጨፍራለን።
ስለ ዲንካ የትንፋሽ መሳሪያ እናውራ። አንዱ በጣም ረጅሙ በሶስት አነስ አነስ ያሉ ዲንካዎች ታጅቦ ነው የሚሰራው… አራቱም ስም አላቸው? አራቱም የተለያየ ስም አላቸው። “ሄሴያ”፣ “ኦይቴ”፣ “ሙራ” እና “አዎ” ይባላሉ። አዎ የሚባለው በጣም ረጅሙና 1 ሜ. ከ50 ሳ.ሜ በላይ ቁመት አለው። ከሁሉም ረጅሙ ሲሆን የቀሪዎቹን ሶስቱን ዲንካዎች ድምጽ ሰብሰብ አድርጎ የሚያቀናጀው ይሄው “አዎ” የተባለው ረጅሙ መሳሪያ ነው። ሁለተኛው “ኦይቴ” ይባላል። “ሙራና” እና “ሄልያ” የሚባሉትም “ አዎ” የ ሚባለውን በ ቁመት ትልቁን ዲንካ ተከትለው ነው የሚጫወቱት። ሶስቱ ትንንሾቹ ሪትም ላይ አንዱ ቢያበላሽ፣ ትልቁ “አዎ” መልሶ ወደ ሪትም ያስገባቸዋል። ከሁለቱም ትንሿ “መራ” ትባላለች። “መራ” ማለት በዳውሮኛ “ጥጃ” ማለት ነው። ከዲንካዎቹ እና ከከበሮው ውጪ ሶስት በሸንበቆ የታሰሩ የሙዚቃ መሳሪዎች አያለሁ። ስለነዚህ መሳሪያዎች አስረዳኝ እስኪ? እነዚህ ቀሪዎቹ “ህጥጢያ” ይባላሉ። ከከበሮው ጋር አራተኛ ሆነው ያጅባሉ። ከቀርከሃና ከተለያዩ እንጨቶች ነው የተሰሩት። “አዎ” የሚባለው ትልቁ ዲንካ ቀርቀሃ፣ ቀንድ ቆዳና መሰል ነገሮች አሉት። ቆዳው አስፈላጊነቱ ምንድነው? ቀንዱስ? ዲንካ ከቀርቀሃ፣ ከአጋዘን ቀንድ፣ ከአጋዘን ቀንዱ ቀጥሎ በሬ ቀንድ አለው። ቁልምሙ ላይ የተንጠለጠለው ቆዳ እንደ
ከረባት ተንጠልጥሎ ይታያል። የሚሰራው ከፍየል ቆዳ ሆኖ በጌጥነት ያገለግላል። ከዚያም ባሻገር ይህን የሙዚቃ መሳሪያ የጥንት የዳውሮ አባቶች ሲሰሩ ዝሆን እንዲመስል አድርገው ነው። በዳውሮ እንደምታውቂው፣ ከበፊት ጀምሮ፣ በጨበራ ጩርጩራ ብሄራዊ ፓርክ ዝሆን አለ። አሁንም ፓርኩን ለየት ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ፣ የአፍሪካ ዝሆኖች መገኛ መሆኑ ነው። የጥንት አባቶች ዝሆንን እንደ አካባቢያቸው መለያ ስለሚወስዱት፣ ዲንካን የዝሆን ምስል እንዲኖረው አድርገው ነው የሰሩት። እናም አንገቱ ላይ የተንጠለጠለው የፍየል ቆዳ ጌጥ ነው። ትልቁ ነገር ይህንን “ዲንካ” ጎንበስ ብለሽ ብታይው ዝሆን ነው
የሚመስለው። ሌላውና የሚገርምሽ ነገር፣ ከዲንካ የሚወጣው ድምጽ ራሱ የዝሆንን ድምፅ ይመስላል። ርርርርር የሚለው ድምጽ ለምሳሌ ጨበራ ጩርጩራ አንድ ቀን ብታድሪ የዝሆን ድምጽ ነው፤ ትሰሚዋለሽ። እኔም ፓርኩ አካባቢ ተወልጄ ስላደግሁ በደንብ አውቀዋለሁ። በልጅነቴ በዚህ ጫካ ውስጥ ከብት ስጠብቅ የዝሆንን ድምጽ እሰማ ነበር። ልክ እንደ ዲንካ ነው ድምጹ። ዝሆኖቹ ትክክለኛ የዲንካ ሙዚቃ መሳሪያ ድምጽ ነው በአፍንጫቸው የሚነፉት።
አያት ቅድመ አያቶቻችን ምን ያህል ሊቅ እንደሆኑ መገመት ትችያለሽ። አንደኛ የዝሆንን ድምፅ በሙዚቃነት ሲጠቀሙ፣ ለዚህ ሙዚቃ የሰሩትን የሙዚቃ መሳሪያ በዝሆን ቅርፅ ሰሩ፡፡ የአካባቢያቸውን ተፈጥሮ ለመጠቀምና ለማስተዋወቅ የሄዱበት ርቀት ያውም በዚያን ጊዜ የሚገርም ነው፡፡ ይሄ በምሁራን ቢጠና ለአለም ሊታይና ሊዳሰስ የሚችል ቅርስ ይሆናል፡- ዝሆን በዳውሮኛ “ዳንጌርሳ” ይባላል። የዲንካ ሙዚቃ ከዝሆን የተፈጥሮ ድምጽ የተቀዳ፣ ምንም
ያልተቀላቀለበት ድንቅ የዳውሮ መገለጫ ነው፡፡ “ዲንካ” በዓለም በርዝመቱ ወደር ያልተገኘለት የትንፋሽ የሙዚቃ መሳሪያ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በዓለም ረጅሙ የትንፋሽ መሳሪያ መሆኑን ማነው ያረጋገጠው? እንግዲህ ይህ መሳሪያ ብዙ ተዋውቋል ብዬ አላምንም። አሁን ላለበት እውቅና እንኳን ያደረሰው አዲስ አበባ የሚገኘው “ፈንዲቃ” የባህል ቤት ባለቤት አቶ መላኩ በላይ በግሉ የሚያደርገው ጥረት ነው። በተለይ በጥምቀት በዓል ሰሞን በጎዳና ላይ ትርኢት እንድናሳይ እያደረገ መሳሪያው ቀልብ መሳብ ጀምሯል፡፡ ይህን ያዩ የውጭ ዜጎች ይመስሉኛል በዓለም ትልቁ የትንፋሽ መሳሪያ ነው ያሉት፡፡ ብዙ ጉልበትና ትንፋሽ የሚጠይቅ ድንቅ መሳሪያ ነው፡፡ መላኩ እኛን ጃፓን ቶኪዮ ወስዶ ለማሰራትና ዲንካ ይበልጥ በዓለም እንዲተዋወቅ ጥረት በማድረግ ላይ ሳለ ነው፣ ኮሮና ገብቶ ከመንገዳችን የገታን፡፡ መላኩ በግሉ ዲንካን ለማስተዋወቅ የሚደክመውን ያህል በዞንና በመንግስት ደረጃ እስከ ዛሬ ጥረት አልተደረገም፡፡
እንዲህ አይነት ሁነቶች ሲኖሩ ነው እየተጠራን እየመጣን የምንሰራው እንጂ ሌላ ጊዜ በቃ ቁጭ ነው፡፡ ዛሬ እዚህ ያገኛችሁን በዚህ በሶዶ ዩኒቨርስቲ ዳውሮ ታርጫ ካምፓስ የተማሪዎች ምረቃ ላይ ሙዚቃ እንድናቀርብ ስለተጠራን ነው። ምን ዓይነት ድጋፍ ነው የምትፈልጉት? በርካታ ድጋፎችና ትኩረቶች
ያስፈልጉታል። ትኩረት አግኝቶ ቢሰራበትና “ዲንካ” ይበልጥ ቢተዋወቅ ጥቅሙ ለዳውሮ ብቻ አይደለም፤ ለሀገርም ይጠቅማል፡፡ ብዙ ጎብኚዎች በመሳብ ለሀገር ኢኮኖሚም የማይናቅ ጥቅም ይኖረዋል፡፡ አንድ መላኩ ብቻውን ቢደክም ምንም ዋጋ የለውም፡፡ መሳሪያው ራሱን ችሎ በዩኔስኮ መመዝገብ
የሚያስችለው ታሪክና አሰራር አለው። እስካሁንም የዘገየው ሰው በማጣት ይመስለኛል። በየወረዳው እየሄድን ተተኪ የማፍራት፣ የማሰልጠን ሥራ የምንሰራበት ሁኔታ ቢመቻች፣ ዲንካ እንዲተዋወቅ የተለያዩ መድረኮች መፍጠር ቢቻል ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ዲንካ ከተሰራና ጥቅም ላይ መዋል ከመጀመረ ምን ያህል ዘመን ሆኖታል? እንደምንሰማው ዲንካ ጥቅም ላይ ከዋለ ከ100 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል። በእኔም በአባቴም ዕድሜ የሚለካ አይደለም፤ ከ100 ዓመት በእጅጉ እንደሚበልጥም እገምታለሁ። እስኪ ስለ ራስህና የሙዚቃ ሥራዎችህ ንገረኝ? እኔ የዞኑን የባህል ኪነት ቡድን ከተቀላቀልኩ 13ኛ ዓመቴን ይዤአለሁ፡፡ የባህል ሙዚቃ ድምፃዊ ነኝ። ብዙ ዘፈኖችን ሰርቻለሁ፡፡ ከዘፈኖቼ መካከል በዳውሮ ዘመን መለወጫ በዓል (ቶኪቢአል) ላይ የሚያጠነጥን ዘፈን አለኝ። ይህን የዘመን መለወጫ ዘፈን ምንም አይነት ዘመናዊ የሙዚቃ መሳሪያ ሳይቀላቀል በዲንካ ነው የሰራሁት፡፡ የፈንዲቃው መላኩ ጃፓን
ቶኪዮ ሊወስደኝ የነበረው በዚህ ዘፈን ነው። የዘፈኑ ይዘት የዘመን መለወጫ በየዓመቱ ሲመጣ የሚፈጥረውን ደስታ፣ ለበዓሉ ያለው ዝግጅት፣ ቱባ ባህሉን በአጠቃላይ የዳውሮ የዘመን መለወጫን የሚያደንቅና የሚያሞግስ ዘፈን ነው፡፡ ከድምጽ ባሻገር ውዝዋዜ ላይ ተሳታፊ ነህ? አዎ የዲንካን ሰባቱንም ሪትሞች
እጨፍራለሁ፤ በጦርም እጨፍራለሁ፡፡ ዲንካንስ በትንፋሽ አትጫወትም? እሱን ገና ነኝ፤ ግን በትኩረት እየተለማመድኩ ነው። በቀጣይ ምን ለመስራት አስበሃል? የከፋ ቋንቋ 50 በመቶ፣ ኦሮሚኛ መቶ በመቶ እችላለሁ። ዳውሮኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋዬ ነው። በነዚህ ቋንቋዎች ሙዚቃ የመስራት እቅድ አለኝ፡፡ በከምባታ ጢምባሮኛ፣ በዳውሮኛና በአማርኛ ቋንቋዎች ተቀላቅሎ የተሰራ አንድ ዘፈን ሰሞኑን አውጥቼአለሁ፡፡ “ዋንቴ ዳውሮ ዋንቴዳ” (ለዳውሮ ህዝብ ንጋቱ ነገ) ይሰኛል። በቀጣይም በምችለው ቋንቋ ሁሉ ሙዚቃ ለመስራት ጥረት አደርጋለሁ፡፡


Read 928 times