Tuesday, 02 March 2021 00:00

የመቀሌዋ የግቢያችን ቃል አቀባይ

Written by  ብሩህ ዓለምነህ
Rate this item
(5 votes)

 ክፍል 4፡ የዶ/ር ደብረፅዮን መጥፋትና የታጋይ ገብረ ገ/ፃድቅ መምጣት
                     

          የጦርነት ወጋችንን እንደቀጠልን ነው፡፡ ህዳር 7 ቀን 2013 ምሳ በልተን ሻይ እየጠጣን ሳለ፣ ሁለት ተዋጊ ሚጎች በቅርብ ርቀት ሲበሩና የሆነ ራቅ ያለ ቦታን ሲደበድቡ ሰማን፡፡ ወዲያውኑ የሰፈራችን ሰዎች ከየቤታቸው እየወጡ መንገድ ላይ እየተሰባሰቡ ማውራት ጀመሩ፡፡ ስለ ሚጎቹ ሰው የመሰለውን ያወራል፣ አንዳንዱ #ሚጎቹ የደበደቡት የአውቶብስ መናኸሪያና የገበያ ማዕከል ነው; ይላል፤ ሌላው ደግሞ ‹‹መኖሪያ ቤቶችን ነው የደበደቡት›› ይላል።
ተዋጊ ሚግ በመቀሌ ሰማይ ላይ በበረረ ቁጥር አንድ የማይቀረው ወሬ ግን ‹‹ተመትታ ወድቃለች›› የሚለው የጀብደኝነት ወሬ ነው፡፡ እ ናም እ ነዚህም ሚ ጎች ይ ሄ ሃ ሜት ደርሷቸዋል፡፡ የትኛው እውነት እንደሆነ ባናውቅም፣ የመንግስትም ሆነ የትግራይ ቴሌቪዥኖች በየቀኑ ‹‹የድል ሰበር ዜና›› አላቸው። መንግስት በየቀኑ አዳዲስ ከተሞችን መቆጣጠሩን ሲነግረን፣ የትግራይ ቴሌቪዥንም በየቀኑ ‹‹የዐቢይን›› ክፍለ ጦሮች መደምሰሱን ይነግረናል፡፡
ህዳር 8 ቀን 2013 መከላከያ ሰራዊትና የአማራ ልዩ ኃይል በሁለት አቅጣጫ (በደቡብና በምዕራብ) ህወሓት ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ በመቀጠል በደቡብ ጨርጨርንና መሆኒን፣ በምዕራብ በኩል የመጣው ጦር ደግሞ ሽሬን በመቆጣጠር ወደ አክሱም እየገሰገሰ መሆኑን አስታወቀ። ህዳር 8 ቀን 2013 መከላከያ ኃይል የትግራይ ልዩ ኃይልና ሚሊሺያ በሰላም እጁን እንዲሰጥ የተሰጠው የ72 ሰዓታት ወይም የ3 ቀናት የጊዜ ገደብ ማለቁን አስታወቀ።
መንግስት ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ህወሓት ላይ ከጦርነቱ በተጨማሪ የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን መጣል ጀመረ፡፡ በዚህም፣ ህዳር 8 ቀን 2013 የህወሓት ንብረት የሆኑ
34 የኢፈርት ድርጅቶች (ለምሳሌ፣ መስፍን ኢንደስትሪያል፣ ድምፂ ወያነ ቴሌቪዥ፣ ሜጋ አሳታሚ፣ ሱር ኮንስትራክሽን፣ ጉና የንግድ ሥራዎች ድርጅት…) የባንክ ሂሳባቸው እንዳይንቀሳቀስ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ወሰነ። በነጋታው ደግሞ 76 የሚሆኑ የህወሓት የጦር ጀነራሎች፣ የጦር መኮንኖችና የበታች ሹማምንት ላይ በሀገር ክህደት ወንጀል እንዲያዙ አቃቤ ህግ የመያዣ ትዕዛዝ አወጣባቸው። ህዳር 10 ቀን 2013 ስለ ጦርነቱ በየቀኑ መግለጫ ሲሰጡ የነበሩት ዶ/ር ደብረፅዮን በሌላ ገብረ ገብረፃድቅ በሚባል ታጋይ ተተኩ፡፡ ከዚሁ ቀን ጀምሮ የትግራይ ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች የኢፌዲሪን መከላከያ ኃይል ‹‹የዐቢይ መከላከያ ኃይል›› በማለት መጥራት ሲጀምሩ፣ የትግራይ ልዩ ኃይልን ደግሞ ‹‹የትግራይ ሰራዊት›› በማለት መጥራት ጀመሩ፡፡ ገብረ ገብረ ፃድቅ ደግሞ
‹‹የትግራይ ሰራዊት ቃል አቀባይ›› ሆኖ በየቀኑ መግለጫ መስጠት ጀመረ፡፡ ህዳር 10 ቀን 2013 ታጋይ ገብረ ገብረ ፃድቅን በመጥቀስ የትግራይ ቴሌቪዥን
በሰበር ዜናው በአላማጣ ግንባር ሁለት የ‹‹ዐቢይ›› ክፍለ ጦሮችን መደምሰሱን አስታወቀ። ታጋይ ገብረ ይሄንን ያለው መከላከያ ኃይል አላማጣን አልፎ መሆኒን ከተቆጣጠረ በኋላ ነው። የዚያኑ ዕለት ከቀኑ 07:00 አካባቢ ህወሓት ሁለት ሮኬቶችን ወደ ባህርዳር ኤርፖርት ማስወንጨፉንና ውሃማ አካል
ላይ መውደቃቸውን የኢፌዲሪ አየር ኃይል አስታወቀ። ሮኬቶቹም የተወነጨፉት በምዕራብ ትግራይ ከአማራ ክልል ጋር በሚዋሰንበት አካባቢ መሬት ውስጥ
በተቆፈረ ጉድጓድ ውስጥ መሆኑን ገለፀ። ህዳር 11 ቀን 2013 መከላከያ ሰራዊት ሽሬን አልፎ አክሱምን መቆጣጠሩንና በ3 አቅጣጫ (በአዲግራት፣ በአድዋና በአላማጣ መስመሮች) ወደ መቀሌ እየገሰገሰ መሆኑን መንግስት ገለፀ፡፡ አክሱምንና አድዋን ከተቆጣጠሩ የመከላከያ አዛዦች አንዱ በተደረገለት ቃለ መጠይቅ እንዲህ አለ፡ - ‹‹ይሄ አሁን ያለንበት የኮንክሪት ምሽግ ከወራት በፊት እነ ዶ/ር ደብረፅዮን እዚህ ድረስ በመምጣት ያስመረቁት ምሽግ ነው፤ የህወሓት ልዩ ኃይል ግን ከ20 እና ከ30 ደቂቃ በላይ አልተዋጋበትም፤ የአድዋና የአክሱም ተራሮችን የመሰለ ስትራቴጂካዊ ቦታዎች ላይ እንኳ ሳይቀር ልዩ ኃይላቸው
የረባ ውጊያ ሳያደርግ ነው የተበታተነው፡፡›› ጄነራሉ ይሄንን ሲል በአእምሮዬ የመጣው፣ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት የህወሓት አክቲቪስቶች በፌስቡክ ሲፅፉት
የነበረው ድንፋታ ነው፡፡ በተለይ ጳጉሜ 5 ቀን 2012 የመንግስት ሪፐብሊካን ጋርድ ወታደራዊ ትርኢት ሲያሳይ የተለጠፈው ፎቶ ሥር አንድ የህወሓት አክቲቪስት የሰጠው አስተያየት አሁን ድረስ ትዝ ይለኛል፤ ‹‹ወታደራዊ ትርኢቱን አየነው፤ ጋርዶቹ የያዙት መሳሪያም እጅግ ዘመናዊ ነው፤ ግን መቼ ነው የምንማርካችሁ!!?›› ነበር ያለው አክቲቪስቱ፡፡ ሌላኛው ታዋቂ የህወሓት አክቲቪስት ደግሞ ቃል በቃል እንዲህ ነበር ያለው፡- ‹‹አሁን ባለን የዓላማ አንድነት፣ አሳማኝ ‹‹cause››፣ ቆራጥነትና ወታደራዊ ቁመና ኢትዮጵያን ለማንበርከክ ጥቂት ቀናት (ገፋ ካለም ሳምንታት) ቢወስድብን ነው፤ ይሄ ጉራ
ሳይሆን መሬት ላይ ያለ ሐቅ ነው፡፡›› መከላከያ ‹‹አክሱምን ተቆጣጥሬያለሁ›› ሲል፣ ‹‹የትግራይ ሰራዊት ቃል አቀባይ›› ገብረ ገብረ ፃድቅ ግን አሁንም ጦርነቱ ገና ሁመራ ላይ እንደሆነና የመከላከያ ኃይልንም ሁመራ ላይ እንደደመሰሰው ገለፀ። ከአምስት ቀን በፊት እንዲሁ መንግስት በራያ ግንባር ዋጃን፣
ጥሙጋንና አላማጣን በመቆጣጠር ጨርጨርንና መሆኒን ለመያዝ ተቃርቤያለሁ ሲል፣ የትግራይ ቴሌቪዥን ግን ‹‹በአላማጣ ግንባር ሁለት ‹‹የዐቢይ›› መከላከያ ክፍለ ጦሮችን ደመሰስኩ›› ሲል ነበር፡፡ ለማንኛውም አብዛኛው የመቀሌ ህዝብ ከመንግስት ቴሌቪዥን ይልቅ የትግራይ ቴሌቪዥንን ያምናል፡፡ ኢቲቪና የአማራ ቴሌቪዥን መከላከያ በተቆጣጠራቸው ከተሞች ሽሬና አክሱም ላይ ያደረጉትን ቃለ መጠይቅ እያዩ እንኳን አብዛኛው የመቀሌ ህዝብ ግን
አሁንም ሽሬና አክሱም በመከላከያ መያዛቸውን አያምንም ነበር። ህወሓትን ብቻ እንዲሰሙ፣ ህወሓትን ብቻ እንዲያምኑ ተደርገው ተሰርተዋል!!
ህዳር 12 ቀን 2013 በትግራይ ቴሌቪዥን የቀረቡት የትግራይ ሰራዊት ቃል አቀባይ ገብረ ገብረ ፃድቅ፤ ልዩ ኃይላቸው ሁመራ ላይ የ‹ዐቢይ››ን መከላከያ ኃይል እንደደመሰሰ ተናገረ። ቃል አቀባዩ ይሄንን የሚለው መከላከያ ሰራዊት ሁመራን፣ ሽሬን፣ አክሱምንና አዲግራትን ተቆጣጥሮ እያለ ነው፡፡ ምንም እንኳ አብዛኛው የመቀሌ ህዝብ የትግራይ ቴሌቪዥንን የሚያምን ቢሆንም፣ መንግስት በዚሁ ዕለት (ህዳር 12/2013) ያሰራጨው ዜና ግን ፍርሃት ለቆበታል።
ዜናውም ‹‹መከላከያ ኃይል አዲግራትን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠረ›› የሚል ነው፡፡ አዲግራት ከመቀሌ በመኪና የሁለት ሰዓት መንገድ ናት፡፡
የመቀሌ ነዋሪዎች የመከላከያ ኃይል ወደ መቀሌ መገስገሱ ያስፈራቸው ‹‹መከላከያ ከመጣ ትግሬ የተባለን ሰው በሙሉ ይገድላል›› የሚለውን የህወሓት ፕሮፓጋንዳ ስላመኑ ነው፡፡ መቀሌ ላይ እንደዚህ ዓይነት የፍርሃት ድባብ በሰፈነበት ወቅት ነበር ሜሮን ሽንኩርት ለመግዛት ደጃችን ላይ ጉሊት ዘርግታ
ወደምትቀመጠው ሰናይት የሄደችው፡፡ ሰናይት የ13 ዓመት ልጅ ስትሆን አምና በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ትምህርት ቤቶች ሁሉ ከተዘጉ በኋላ ቀኑን ሙሉ የእናቷን ጉሊት ስትጠብቅ ትውላለች። ሰናይት ሁልጊዜ ሥራዋን በፈገግታና በቅልጥፍና የምትሰራ ቢሆንም ዛሬ ግን ፍርሃት ነግሶባታል፡፡ ‹‹ምነው ሰኒ?›› አለቻት ሜሮን ሐዘኗን ለመጋራት። ሰናይትም ባዘነ ልብ፤ «መከላከያ መቀሌ ሲገባ ሁላችንንም ያርደናል አይደል?›› አለቻት፡፡ ሜሮን ደነገጠች፤ ‹‹ማንነው እንደዚህ ያለሽ?›› ሰናይት፤ ‹‹ዛፉ!!›› (ዛፉ የሰናይት እናት ናት) ሜሮንም ቀበል አድርጋ፤ ‹‹ሰኒ፤ መከላከያ እንደዚህ አያደርግም፤ አይዞሽ እሺ›› በማለት
አረጋግታት ወደ ቤቷ ሄደች፡፡ ሜሮን ወደ ግቢ ስትገባ፣ ቃል አቀባያችን የዕለቱን ማብራሪያዋን መስጠት ጀምራለች። ቃል አቀባያችን ብዙ ጊዜ እንደታዘብኳት
አብዛኛው ወሬዋ አማራን ማዕከል ያደረገ ቢሆንም፣ የዛሬው ንግግሯ ግን ይበልጥ አማራዊ ሆኗል፤ ‹‹የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት የተናገረውን ሰማችሁ?! #ልዩ ኃይላችን ትግራይን ከተቆጣጠረ በኋላ ፊታችንን ወደ አሰብና ምፅዋ እናዞራለን; ብሏል፡፡ ለዚህም ዓላማው 50 ሺ የአማራ ሰራዊት በዛላንበሳ አስፍሯል፡፡ አማራ ግን አንድ የተሸወደው ነገር ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ?! መከላከያን በፍፁም ማገዝ አልነበረበትም፤ ምክንያቱም ብልፅግና ትግራይን ካጠፋ በኋላ አማራንም ያጠፋና ኦሮሞን ብቻ የማስቀረት ድብቅ ዓላማ አለው። …;
(ሳምንት ክፍል-5 ይቀጥላል)Read 8115 times