Sunday, 28 February 2021 00:00

በኦሮሚያ ክልል የሠብአዊ መብት አያያዝ አሳሳቢ ሆኗል - ኢሰመጉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

    “ህገ-ወጥ እስርና ግድያ እየተፈጸመ ነው”
                            
           በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በርካቶች ያለ አግባብ ታስረው እንደሚገኙ ያመለከተው ኢሰመጉ፤ በክልሉ የሰዎች ደህንነትና የሰብአዊ መብት አጠባበቅ አሳሳቢ ሆኗል ብሏል። ጉዳዩን ገለልተኛ የሰብአዊ መብት ተቋማት እንዲያጣሩት ሊደረግ ይገባል ብሏል -ኢሰመጉ። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ)፤ “የሰዎች ደህንነትና ሰብአዊ መብቶች የማስከበር ግዴታውን ይወጣ ለሚለው ውትወታ መንግስት ጆሮ ይስጥ” በሚል ርዕስ ባወጣው አስቸኳይ መግለጫው፤ “በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የመብት ጥሰቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባበሱ መምጣታቸው አሳሳቢ ሆኗል” ብሏል።
በተለይ በምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ፣ ምስራቅ ወለጋና ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ በመንግስት ታጣቂዎችና በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች መካከል የሚደረግ የተኩስ ልውውጥ የበርካታ ንፁሃንን ህይወት እየቀጠፈ ነው ብሏል -ኢሠመጉ። የኦሮሚያ ልዩ ሃይል በአካባቢው በሰዎች ላይ ድብደባ ፣ ህገ-ወጥ እስርና ግድያ እንዲሁም “ልጆቻችሁ ኦነግ ሸኔን ተቀላቅለዋል፤ ካሉበት አምጡ” በሚል ደካማ እናቶችና አባቶች ላይ እስርና እንግልት እንደሚፈጽም ኢሰመጉ መረጃዎች ማሰባሰቡን አመልክቷል። በተጨማሪም በምስራቅ ወለጋ ዞን ዲጋ ወረዳ፣ በጉዳቱ ኦርጆ ፖሊስ ጣቢያ እንዲሁም
በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን አባይ ጮመን ወረዳ፣ በፊንጫ ፖሊስ ጣቢያና ፊንጫ ሸለቆ ፖሊስ ጣቢያ ያሉ ተጠርጣሪዎች ፍ/ቤት የመቅረብ መብታቸው ተነፍጎ፣ በጠባብ ክፍል ውስጥ ታስረው ከረጅም ጊዜ በኋላ የተፈቱ በርካቶች መሆናቸውን ነው ሪፖርቱ የጠቆመው። አሁንም በህገ ወጥ መንገድ
ታስረው የሚገኙ ስለመኖራቸው መረጃዎች እንዳለው ነው ኢሰመጉ ያመለከተው። በአጠቃላይ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች የሰዎች መደብደብ ፣ ግድያና
ህገ-ወጥ እስር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን በመግለጫው የጠቆመው ኢሰመጉ፤ መንግስት በአፋጣኝ የእርምት እርምጃዎች እንዲወስድ አሳስቧል። ወደ እነዚህ ቦታዎችም ገለልተኛ አካላት ገብተው ጉዳዩን እንዲያጣሩ እንዲፈጸም ጠይቋል። ኢሠመጉ በዚሁ መግለጫው አያይዞ ባወጣው ሪፖርቱ፤ በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን የአስተዳደር ጥያቄ አንስተዋል የተባሉ በ22 ቀበሌዎች የሚኖሩ ሰዎች ለህገ-ወጥ አስር መዳረጋቸውን አስታውቋል።


Read 7780 times