Sunday, 28 February 2021 00:00

የባሌው ሃሬና ደን መመናመን የአለም ሳይንቲስቶችን አሳስቧል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

  በአፍሪካ ሁለተኛው በኢትዮጵያ ቀዳሚው የተፈጥሮ የደን ሃብት የሆነው የባሌው ሃሬና ደን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መጠነ ሰፊ ወድመት እያጋጠመው መሆኑን የናሳ የሳተላይት መረጃ ሪፖርት አመልክቷል፡፡ የአሜሪካ የስነ ህዋ ምርምር ተቋም ናሳ በድረ ገፁ ባወጣው ዘገባ፤ በኦሮሚያ ክልል
ባሌ ዞን የሚገኘው የሃሬና የደን ሽፋን በሃገሪቱ በመጀመሪያ ደረጃ የሚቀመጥ ፤ መሆኑን ጠቁሞ በሳተላይት በተሰበሰበ መረጃ መሰረት፤ ይህ ሃብት በምንጣሮ፣በግብርና መስፋፋትና ከሰል ምርት ተፈጥሮአዊ ይዘቱ እየተመናመነ መሆኑን አሳሳቢ ነው ብሏል፡፡ በአፍሪካ የትሮፒካል ደን ከሚባሉት የደን
ሃብቶች በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠው የሃሬና ደን ይዞታ አሳስቦናል ያሉት የሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስቶች፤ የደን ሃብቱ መመናመን በአካባቢው ከፍተኛ የተፈጥሮ መዛባትን ሊያስከትል ይችላል ብለዋል፡፡ ሃሬና ደን በምድር ላይ ካሉ የደን ሃብቶች ብቸኛ የጫካ የተፈጥሮ ቡና የሚለቀምበት መሆኑን ያተተው ዘገባው፤ ሰፊ የንብ ማነብና የማር ምርት የሚታፈስበትም ነው ብሏል፡፡ የደን ሀብቱ በውስጡ ለባህላዊና ዘመናዊ ህክምና የሚውሉ መድሃኒትነት ያላቸው እጽዋት እንዲሁም በርካታ የዱር እንስሳት ዝርያዎች መጠለያ መሆኑም በዘገባው የተመለከተ ሲሆን መንግስት ለደን ሃብቱ የተጠናከረ ጥበቃ እንዲያደርግ ተጠይቋል፡፡

Read 1039 times