Monday, 22 February 2021 09:03

የፍቅር ቀጠሮ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ታገል ሰይፉ


ጠበቅኩሽ እኔማ-እዚያው ሥፍራ ቆሜ
በአክሱም ቁመና- በላሊበላ ዕድሜ
እግሮቼን ተክዬ-ቀኔን አስረዝሜ
በሔድሽበት መንገድ- ልቤ እንደነጎደ
ስንት ነገር መጣ-ስንት ነገር ሄደ
ስንት ጊዜስ ነጋ- ስንቴ ጎህ ቀደደ
ስንቴ ዝናብ ጣለ-ስንት ጊዜ አባራ
ትመጫለሽ ብዬ -በቆምኩበት ሥፍራ
ስንቴ አድማሱን ማተርኩ-ስንትና ስንት ዓመት
አንገቴን አስግጌ-በራስ ዳሽን ቁመት
በአክሱም ቁመና- በላሊበላ ዕድሜ
በቀጠርሽኝ ሥፍራ-ስጠብቅሽ ቆሜ
ስንት ሳቅ አለፈ-ስንትና ስንት ዕንባ
ስንቴስ ክረምት ሆነ-ስንቴ ፀደይ ጠባ
ስንቱ ተገናኘ-ስንቱ ሰው ተጋባ
ሽል ስንቴ ልጅ ሆነ-ስንትስ ጊዜ አረጀ
ስንት ኮት ጨረሰ- ስንት እንጀራ ፈጀ
ስንት ዓይነት ሞት አየሁ- ስንት ዓይነት ፍፃሜ
በአክሱም ቁመና-በላሊበላ ዕድሜ
በቆምኩበት ሥፍራ-ስጠብቅሽ ቆሜ?
ስንት ውበት አለፈ-ስንት ውበት ነጎደ
ስንት ትውልድ መጣ -ስንት ትውልድ ሄደ
ስንት ዕውነት ከፍ አለ-ስንት ዕውነት ወረደ
ስንት ዓለም ተሻረ- ስንት ዓለም ነገሠ
ስንት ሀገር ተሰራ-ስንት አገር ፈረሠ
ስንት ሺህ ዓመት ሸኘሁ-ስንት ሺህ ተቀበልኩ
እዚያች ሥፍራ ቆሜ-አንችን እየጠበቅኩ
እግሬን አስረዝሜ-ቆየሁ ቆየሁና
በላሊበላ ዕድሜ- በአክሱም ቁመና
ሳትመጪ ወደኔ-ሳላገኝሽ ገና
ብዙ ነገር መጥቶ -ብዙ ነገር ያልፋል
የራስ ዳሽን ራስ-አንገቱን ይደፋል
አክሱምም ተንዶ- እንደጨው ይረግፋል
ላሊበላም ወርዶ-ቁልቁል ይነጠፋል
ሰማይና ምድርም ያልፋሉ ታያለሽ
እኔ ግን እዛው ነኝ-አንች እስክትመለሽ…

Read 3297 times