Monday, 22 February 2021 08:38

የግለሰብና የቡድን መብቶች ቁርኝትና የፓርቲዎች ያልጠራ ዕይታ

Written by  ጌታሁን ሔራሞ
Rate this item
(1 Vote)

  በሀገራችን የፖለቲካ ውይይት መድረኮች እንደነገሩ አድበስብሰን ለማለፍ ጥረት የምናደርገው የግልና የቡድን/የወል መብቶች ቁርኝት ርዕሰ ጉዳይ፣ በሌላው የዓለም ክፍል የፖለቲካ ሳይንቲስቶችንና ፈላስፎችን ለሁለት ከፍሎ የሚያነታርክ አጀንዳ ነው። ቀደም ሲል ከተስተዋሉ የሀገራችን የምርጫ ውድድር ክርክሮች ካለን ተሞክሮ አኳያ፣ የሀገራችን ፖለቲከኞች በዚህኛው ርዕሰ ጉዳይ ሲበዛ “reductionist” ነበሩ ብንል ማጋነን አይሆንም፣ ማለትም ውስብስቡን ፅንሰ ሐሳብ አቅልለው የማየት አባዜ አለባቸው።
ለማንኛውም በግለሰብና በቡድን/በወል መብቶች መካከል ያለውን ግንኙነት በተመለከተ በአሁኑ ወቅት በዋናነት ሁለት ዓይነት ዕሳቤዎች አሉ።
1. አንዳንድ የፖለቲካ ሳይንቲስቶችና ፈላስፎች፣ የግለሰብ መብቶችን መነሻ የሚያደርገው መደበኛው የሊብራል ዲሞክራሲ ሞዴል (John Rawls, Immanuel Kant,Jean Jacques Rousseau) የቡድን/የወል መብቶችን የማቀፍ አቅም አለው የሚል አቋም አላቸው። እነዚህ ሳይንቲስቶች የቡድን/የወል መብቶች ጥያቄ በግለሰብ መብቶች መከበር ዕውን ይሆናሉ የሚል እምነት አላቸው። ይህን አቋም ከሚያራምዱ ሳይንቲስቶች ውስጥ ጀርመናዊው ዩርገን ሐበርመስ እና ካናዳዊው ዊል ኪሚሊካ ተጠቃሾች ናቸው።  
2. በሁለተኛው ጎራ ያሉ የፖለቲካ ሳይንቲስቶች፣ የቡድን/የወል መብቶችን ከግለሰብ መብቶች ነጥለው የሚፈትሹ ናቸው። በዚህኛው ምድብ ያሉ አጥኚዎች፣ የቡድን/የወል መብቶች በግለሰብ መብቶች ውስጥ ሳይጠቀለሉ በራሳቸው ለብቻቸው መጠናት አለባቸው ይላሉ። ይህን አቋም የሚያራምዱ የዘርፉ ሳይንቲስቶች “Communitarians” ተብለው ይጠራሉ። ካናዳዊዉ ፈላስፋ ቻርልስ ታይለር፣ አሜሪካዊው ፈላስፋ ሚካኤል ዋልዜርና የሕግ ፕሮፈሰሩ ዱዋይት ኒውማን የዚህ ዕሳቤ አራማጆች ናቸው።
ትናንት ይፋ በተደረገው በብልፅግና አዲሱ ማኒፌስቶ ወትሮ ሚዛኑን በዋናነት ወደ ቡድን መብት ያጋዳለው ኢሕአዴጋዊው ዕሳቤ በተሻሻለና በልምድ ላይ በተመሠረተ ዕሳቤ ተተክቶ ይሆናል የሚል እምነቱ ባይኖረኝም፣ የማኒፌስቶው አሁናዊ ይዘት ምን እንደሚመስል ለማወቅ ፍላጎቱ አለኝ። በአንፃሩም በተለይም ኢዜማ በግለሰብና የዜግነት መብቶች አተገባበር ሂደት፣ ቡድናዊ መብቶች “by default” ይከበራሉ የሚል አቋም እንዳለው የፓርቲው መሪዎች በተለያዩ ሚዲያዎች ከሚሰጡት ማብራሪያዎች መረዳት ይቻላል። አሁንም ደግሜ የማሰምረው በእኔ አተያይ፣ በርዕሰ ጉዳዩ ብልፅግናም ሆነ ኢዜማ “reductionist” የሆነ ፅንፍ ይዘው የሚከንፉ ይመስላሉ። በተለይም በግለሰብና በቡድን/በወል መብቶች መካከል ግጭቶች በሚፈጠሩበት ወቅት የመፍትሔ አፈላለግ ሂደቱ ምን እንደሚመስል በግልፅ መቀመጥ አለበት። ለምሣሌ ከመላ ሀገሪቱ አንፃር አናሳ የሆኑ የካናዳ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ኪውቤካዊያን፣ በኪውቤክ የራስ ገዝ አስተዳደር ውስጥ አብላጫዎቹ በመሆናቸው፣ በክልላቸው የሚለጠፉ ማስታወቂያዎች በሙሉ በፈረንሳይኛ ቋንቋ ብቻ እንዲፃፉና ነዋሪዎችም ልጆቻቸውን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት ወደሚሰጥባቸው የትምህርት ተቋማት እንዳይልኩ ማዕቀብ እስከመጣል ሁሉ ደርሰው ነበር። ይህ ውሳኔ ከግለሰብ መብት አኳያ የካናዳዊያንን ፖለቲከኞች ናላ ያዞረ ርዕሰ ጉዳይ ነበር።
እኛም ሀገር በኢሕአዴጋዊዉ የቡድን መብት ሰበብ፣ በየክልሉ የሚጣሱትን ግለሰባዊ መብቶችንና በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የሚፈፀሙ መገለሎችን ቆጥሮ መጨረስ የሚቻል አይደለም። በነገራችን ላይ ኪውቤክ ከካናዳ ጋር ያላት ዕድሜ-ጠገብ ውዝግብ ሙሉ በሙሉ ባይሆንም፣ በተወሰነ መልኩ ከእኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው፣ በሌላ አንፃር የግለሰብንና የቡድንን መብት ቁርኝትን ለማመላከት፣ የኢዜማ አመራሮች የሚጠቅሷት አሜሪካ፣ ከእኛ ሀገር ፖለቲካዊ አውድ ጋር ያላት ምስስሎሽ እምብዛም ነው። በአብዛኛው በፍልሰት የተገነባውን ብዝሃ-ባሕልን፣ እንደ ኢትዮጵያ በሕብረ ብሔራዊነት ከተዋቀረው ጋር በእኩል ሚዛን ላይ አስቀምጦ ማነፃፀር ተገቢ መስሎ አይታየኝም።
 በእንደዚህ ዓይነት የተለያየ አውድ ውስጥ የሚነሱ ቡድን-ተኮር ጥያቄዎች ተመሳሳይነትም በእጅጉ አጠያያቂ ነው። እንዲያውም ካናዳዊው የብዝሃ-ባሕል አጥኚ ዊል ኪምሊካ፣ የአሜሪካው ሕገ መንግሥት “Ethnicty-blind” ነው በማለት ይተቸዋል። ሌላው ይቅርና በውስጡ ላቀፋቸው ለአሜሪካ-ሕንዳዊያንና “Puerto Ricans” ዕውቅናን የነፈገ ነው ይለናል (Multicultural Citizenship, 1996) ስለዚህም ሕገ መንግሥታዊ ንፅፅሮች በሚደረጉበት ወቅት አውዳዊነት ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅብናል።
የዚህ ፅሁፍ ዋናው መልዕክት፤ የግለሰብንና የቡድን/የወል መብትን ከማስከበር አኳያ፣ ለሀገራችን ፖለቲካዊ እንቆቅልሾች መፍትሔ በማፈላለጉ ሂደት፣ ከገዳፊነት ዕይታ (Reductionist view) እንድንቆጠብ ማሳሰብ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ የማህበራዊና የፖለቲካ ሳይንስ ዘርፎችን ሳይንቲስቶች፣ በሁለት ጎራ ከፍሎ የሚያፋልማቸውን ፅንሰ ሐሳብ፣ እንደነገሩ በአንድና ሁለት ዐረፍተ ነገር ሸውዶ ለማለፍ የሚደረገው ጥረት፣ ውሎ ሲያድር መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር መጣረሱ የማይቀር ነው። በእኔ እምነት፤ በግለሰብና በቡድን/የወል መብቶች ዙሪያ ጥልቀትነት ያላቸው፣ የሀገራችንን ፖለቲካዊ አውድ ማዕከል ያደረጉ፣ ሰፋ ያሉ ውይይቶች፣ በቀጣዩ የምርጫ ዋዜማ መደረግ አለባቸው። እኔም በርዕሰ ጉዳዩ ዙሪያ፣ በምርጫ ፉክክር ወቅት የተፎካካሪ ፓርቲዎች አቋም ይፋ ሲሆን፤ በየዘርፉ ሳይንስ ላይ በመመስረት፣ በፌስ ቡክ ገፄ ላይ እንደ አንድ ዜጋ የበኩሌን ለማለት እንደምሞክር ከወዲሁ ለወዳጆቼ አሳውቃለሁ።

Read 2383 times