Monday, 22 February 2021 08:39

አድማስ ትውስታ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

                   ሪቻርድ ፓንክረስት በጣሊያን ወረራ ጉዳይ


                      (“ቆርጦ መሰንበት” ለተባለው የጄፍ ፒርስ መፅሐፍ የፃፉት መቅድም)

        "የግራዚያኒን ሐውልት እንርሳው ካልን፣ ቀጥሎ የሚመጣው ለሒትለር ወይም ሙሶሎኒ የሚሰራ ሐውልት ነው። ከዚያ የሚቀጥለው ነገር ደግሞ ህዝቡ የዚህን ወንጀለኛ ተግባር እጀ- ሥራ እንዲኮርጅ መጠበቅ ነው።--"
              ትርጉም፡- ነቢይ መኮንን


         በውጭ መጻህፍት ዘንድ በሰፊው አቢሲኒያ በመባል የምትጠቀሰውንና ከአፍሪካ ብቸኛዋን፤ መቀመጫውን ጄኔቭ ያደረገው የሊግ ኦፍ ኔሽንስ አባል አገር- ኢትዮጵያን፤ ሙሶሊኒ ሳትነካው ወረራ አካሄደባት። ፋሽስት ኢጣሊያ የዓለም አቀፉን ስምምነት ጥሳ የመርዝ ጭስ ተጠቀመች። የተባበሩት መንግሥታት ሊግ፤ የግፈኛዋን አገር የገቢ ዕቃዎች፣ ማለትም ያለዚያ መኖር እየቻለች፣ የምታጋብሰው ሸቀጥ ላይ ማእቀብ አለመጣሉ ሳያንስ፣ ስዊስ ካናልን ለወራሪዎች ለመዝጋት ፍቃደኛ  አለመሆኑ ታየ። ንጉስ ኃይለ ሥላሴ፤ ለጄኔቭ እጅግ ሩቅ ከሆነችው አዲስ አበባ ተነስተው በባቡር፣ በጀልባና በአውሮፕላን ተጉዘው፤ በአንደበተ- ርቱዕ ንግግር፣ በዓለም ህሊና እንዲሁም “ለታሪክ ፍርድ ትውስታ…” የሚሆን አቤቱታቸውን አቀረቡ።
እነዚህ ሁሉ እንግዲህ ቀደም ባለው ዘመን የማይረሱ፤ ክዋኔዎች ናቸው። ያ ዘመን በአንድ ራስ -ሁለት ምላስ ሽፍጥ፣ የኃይል እና ግፍ ወረራ የተካሄደበት ዘመን ነው። የዚያ ዘመን ሰዎች የረሱት የሚመስልና የኋለኞቹ ትውልዶች ደግሞ በጭራሽ የማያውቁት ዘመን ነው። የእናቴን የሲልቪያ ፓንክረስትን ቅድመ- ጦርነት ኢትዮጵያ ወዳጅ የሆነውን “ኒው ታይምስ ኤንድ ኢትዮጵያ ኒውስ” የተባለውን ሳምንታዊ ጋዜጣ ያነብቡ የነበሩ አያሌ አንባቢያን፤ ያን ዘመን በብዛት ያስታውሱታል።
ያም ሆኖ የዚያን ዘመኑ ታሪክ ዛሬም በኢትዮጵያ ህያው እንደሆነ ሁሉ በኢጣሊያ ውስጥ ህያው ነው። በሁለቱም አገሮች ውስጥ በድንጋጤ፣ የሐዘን፣ እና የትውስታ ድምጾች እንደገና ሲያስተጋቡ ይሰማሉ።
ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በ2012 እ.ኤ.አ፤ እጅግ አስደንጋጭና እጅግ ልዩ የሆነ ክስተት እንዳለ አወቁ። ይኸውም በጣሊያን አገር ለግፈኛው የፋሽስት ጦር አዛዥ ለሮዶልፎ ግራዚያኒ፤ የትውልድ ቦታው በሆነችው በአፊሌ ከተማ፤ ሐውልት የመሰራቱ ዜና ነው። ግራዚያኒ፤ በ1935-6 ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ከነበሩት ሁለት የፋሽስት ጦር አዛዦች አንዱ ነው። ሌላኛው አዛዥ የእሱ ተቀናቃኝና ይስሙላ የበላይ ፒየትሮ ባዶሊዮ ነበር። እኒህ ሁለት ሰዎች በኢትዮጵያ ላይ የጋዝ ጭስ እንዲዘንብ ያዘዙ ናቸው። ግራዚያኒን ለየት የሚያደርገው ኢትዮጵያውን የጦር እስረኞችን ያለ ርህራሄ እንዲጨፈጨፉ በማድረጉ ተጠያቂ መሆኑ ነው። ከዚህ የከፋው የግፍ ድርጊቱ ደግሞ በኢትዮጵያና በሊቢያ “ተወላጆች” ላይ “እገሌ ከገሌ የማይል” የሽብር ተግባር መመሪያ፤ ስራ ላይ እንዲውል ማድረጉ ነው። (በዚያ ጊዜ ሊቢያም በጣሊያን ቅኝ አገዛዝ ሥር ወድቃ ነበር)
መቼም ብዙዎቻችን እንደነዚህ ያሉ ክስተቶችን ትልቅ ፋይዳ ያላቸው፣ እንዲያውም እጅግ አሰቃቂ ከመሆናቸው የተነሳ፤ እንኳንስ ሊሸሸጉ ይቅርና ሊተውና ሊረሱ እንደማይገባ እናምናለን። የሰው ልጅ፤ እነዚህ ወንጀሎች ትልቅነታቸውን ከማወቁ ባልተናነሰ ትልቅ ትምህርት ይወስድባቸዋል።
የጄፍ ፒርስ የ1935-1941 ኢታሎ -አቢሲኒያ (የጣሊያንና የኢትዮጵያ) ጦርነት ጽሁፍ፣ ፍፁም የሆነ ፋይዳ ፍንትው የሚለው እዚህ ላይ ነው። ዓለም አቀፍ ሞራልና ፍትህ፣ ከፖለቲከኞችና ከወታደሮች ተግባራት ጋር ሲፋጠጥ የሚኖረው መልክ ቁልጭ አድርጎ የሚያብራራልን በመሆኑ ነው!
 ዛሬ የሙሶሎኒን ቀኝ እጅ ግራዚያኒን ከበሬታ መስጠት፤ ዱቼን ራሱን ማክበር ማለት ነው። ግራዚያኒ ለሙሶሎኒ የ1983 ዝና-ቢስ፣ ዘረኛ ህግጋት ድጋፍ የሰጠ ሰው ሲሆን፣ ወደ አውሮፓው ጦርነት ማብቂያ ግድም በኢጣሊያ አምባገነኑ መሪ ከስልጣኑ ሲፈነገል፤ ግራዚያኒ የዱቼ ዋነኛ የፋሽስት አዛዥ በመሆኑ የሳሎ ሪፑብሊክ በመባል በሚጠራው ስርዓት ዘንድ ተሾመ። የግራዚያኒን ሐውልት እንርሳው ካልን፣ ቀጥሎ የሚመጣው ለሒትለር ወይም ሙሶሎኒ የሚሰራ ሐውልት ነው። ከዚያ የሚቀጥለው ነገር ደግሞ ህዝቡ የዚህን ወንጀለኛ ተግባር እጀ- ሥራ እንዲኮርጅ መጠበቅ ነው።
እነዚህን በመሰሉ ፍርሀቶችና ስጋቶች ተውጠው ነው በለንደን፣ በዋሽንግተን፣ በኒውዮርክ በሌሎችም ቦታዎች የሚገኙት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት፤ ከሌሎች የፋሽስት ኢጣሊያና የቅኝ ግዛት ህግ ተገዢ የነበሩ ሰዎች ጋር በመሆን፤ በሰላማዊ ሰልፍ የሰላም ድምጻቸውን ያሰሙት። ባለቤቴ ሪታ እና እኔ ለንደን ውስጥ ባለው የጣሊያን ኤምባሲ ፊት ለፊት በተደረገው ሰልፍ ውስጥ ነበር መሳተፍ የመረጥነው። እዚህ ቦታ ከዚህ ቀደም የጣሊያን መንግስት፣ ሙሶሎኒ በ1937 ወደ ሮም ወስዶት የነበረውን የአክሱምን ሐውልት መመለሱን ሲያዘገየው፣ ሁለት ጊዜ ሰልፍ አድርገን ነበር። ሁለት ጊዜም እንዲመለስ የተገደደበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር።
ግራዚያኒ በኢትዮጵያ ለፈፀማቸው አያሌ የጦርነት ወንጀሎች በፍፁም ተከሶ ለፍርድ ቀርቦ አያውቅም። በሊቢያም እንደዚያው። እርግጥ ከጦርነቱ በኋላ ከጀርመን ጋር በማበር፣ በኢጣሊያ ህዝብ ላይ  ፈጽሟል ለተባለው ወንጀል ተከሶ ጣሊያን ውስጥ አስራ ዘጠኝ ዓመት ተፈርዶበት ነበር። ዳሩ ምን ያረጋል? በአፋጣኝ እንዲፈታ ተደርጓል።
የባዶሊዮ የድህረ-ጦርነት ክስ ጉዳይም፣ እንደ ግራዚያኒ ኮሚክና አስገራሚ ነበር። ከሙሶሊኒ ከሥልጣን መውደቅ በኋላ ባዶሊዮ ለኅብረቱ እጁን ሰጠ። በድኅረ-ጦርነት ኢጣሊያን፣ የቀኝ ክንፍ መንግሥት በማቋቋም ሰበብ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲያደርጉት ግፊት አደረገ። ባንድ ፊት ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን፣ በሌላ ፊት የጦር ወንጀለኛ ተብሎ ለፍርድ መቅረብ የማይታሰብ ነውና፤ የፍርድ ሂደቱ “በፍትሀዊ መንገድ” ተተወ። ሮማ ውስጥ የነበረው የብሪታኒያ አምባሳደር፤ በአዲሱ መንግስት ባዶሊዮ እንዳይታሰር ጥበቃ እንዲደረግለት ታዘዘ። ውጤቱም ያኔ አያሌ ጀርመናውያንና ጃፓናውያን የጦር ወንጀለኞች እየተባሉ በፍርድ ሲገደሉ፤ በኢትዮጵያ ለተፈፀሙ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የጦር ወንጀሎች፣ አንድም ጣሊያን ተከሶ ለፍርድ አልቀረበም። ለ1936-38ቱ ነብሰ-ገዳይ ለግራዚያኒ፤ የተሰጠው ክብር እንግዲህ በርካታ ክንዋኔዎች መደምደሚያ ሲሆን፤ ይህ የጄፍ ፒርስ መፅሐፍ፣ በዚያ ወቅት መጀመሪያ የተፈጸሙ ድርጊቶች በላቀ ዕውቀትና ልዩ ጥናት አስደግፎ በትኩረት የተነተነበት ነው። እግረ-መንገዱንም (inter alia)፤ የብሪታኒያንና የፈረንሳይን፤ ሁለቱን የአውሮፓውያን ዲሞክራሲዎች፤ በማነጻጸር ቁልጭ ያለ ሂስ የሰጠበት ነው።
ይኸውም፤ ሙሶሎኒን ከዋና አጋሩና የነብስ ወዳጁ ከሂትለር ማለያየት በሚል ሰበብ፤ ለኢትዮጵያ ድጋፍ መንሳትን መምረጣቸው፣ መሰረተ-ቢስ ተስፋ ወይም ዕምነት ላይ መንጠልጠላቸውን በማስረዳት፣ ከንቱነታቸውን ማሳየት ነው።
(አዲስ አድማስ፣  የካቲት 25 ቀን 2009 ዓ.ም)


Read 1416 times