Tuesday, 23 February 2021 00:00

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ - “ከሌለው ይቀነስበታል። ላለው ይጨመርለታል፡፡”

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

1  የየደከመ፣ የደኸየ፣ የተናጋ አገር፣… የባህር በር ያጣል። በውጭ ትንኮሳና በወረራ እየተጎሳቆለ ይፍረከረካል። ትንሹም ትልቁም ይጫወትበታል። ሂሳብ ማወራረጃ፣ ኪሳራ ማድበስበሻ፣ ጭንቀት ማብረጃ ያደርጉታል።
2. በተቃራኒው፣ ባለታሪክና ባለተስፋ ጠንካራ አገር፣… የባሕር በር ባለቤት ይሆናል። የወዳጅ ድጋፍና የተባባሪ ኢንቨስትመንት ይጎርፍለታል። በሚተናኮሉና በሚዳፈሩ ፀበኞች ምትክ፣ ታማኝ አጋሮች፣ አክባሪ ጎረቤቶችና ገበያተኞች ይበዙለታል።  ኢትዮጵያ ከየትኛው ነች? የሚቀነስባት ወይስ የሚጨመርላት? በአንድ በኩል፣ ኢትዮጵያ ትልቅ ባለታሪክ አገር ናት።
           
             ከሩቅም ከቅርብም፣ ብዙዎች በመልካም ትዝታ የሚያስቧትና በጎ የሚመኙላት፣ ትልቅ ባለታሪክ አገር ናት። እንደገናም፣ ኢትዮጵያ ወደፊት እንደምትራመድ፣ ወደ ከፍታ እንደምትጓዝ በማመን፣ ለአካባቢዋም እንደምትተርፍ በመመኘት፣ በርካቶች በተስፋ ይጠብቋታል - የተስፋ ምድር እንደሆነች ያስባሉ ማለት ይቻላል። ታዲያ፣ ባለ ታሪክና ባለ ተስፋ ትልቅ አገር መሆኗ፣ ባዶ ትዝታና ምኞት አይደለም።
የአፍሪካ ህብረት መዲናነቷ፣ በተጨባጭ፣ የረዥም ዘመናት መልካም ታሪኳን ይመሰክራል። የነፃነት አርአያነቷን በአድናቆት ያውጃል። በሌላ በኩል፤ ቁጥብ የጨዋነት ባህሏ፣ ለወደፊት የስልጣኔ ጉዞ የሚረዳ ጥሩ መነሻና ተስፋ ነው። የኢትዮጵያን የጨዋነት ልማድ በማየትም፣ የእርጋታና የሰላም ማዕከል እንድትሆን በርካታ የዓለም መንግስታት ተስፋ ይጥሉባታል። ተመልከቱ። በተጨባጭ፣ ኢትዮጵያ፣ የሰላም አስከባሪ ሃይል ዋና ምንጭ ሆናለች። ደግሞም እስከአሁን አላሳፈረቻቸውም። ባለፉት 30 ዓመታት፣ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሃይል፣ በበርካታ አገራት ተሰማርቷል። አስከ ዛሬም፣ በመልካም ብቃትና በጨዋነት እንጂ፣ ስሙ በክፉ አልተነሳም።
ምን ለማለት ነው? የረዥም ዘመናት የህልውናና የነፃነት፣ የስልጣኔ ቅርስና የጨዋነት ታሪኮቿ፣ በራሳቸው፣ ለኢትዮጵያ ታላቅነት፣ ከፍተኛ ፋይዳ አላቸው። የዚያኑ ያህልም፣ ተጨማሪ በረከትን ያስገኛሉ - ለምሳሌ የአህጉር መዲናነትንና የሰላም አስከባሪነትን። መልካም ታሪክ ላለው አገር፣ ሌላም በረከት ይጨመርለታል። ይህም ብቻ አይደለም።
ኢትዮጵያ፣ በዛም አነሰ፣ አለማቀፍ የኢኮኖሚ ድጋፍና የዲፕሎማሲ ትብብር፣ አልተነፈገችም። ምንም እንኳ፣ ተመፅዋችነት አስቀያሚ ቢሆንም፣ ከአመት አመት የማይቋረጥ የእህል፣ የመድሃኒትና የግንባታ እርዳታቸውን የሚሰጡ ወዳጅ አገራት አላጣችም። ለዚያውም የእርዳታቸውን ያህል፣ “እርዳታ ሰጠን” ብለው ብዙ አያወሩም። አንዳንዶቹማ ትንፋሽ አይሉም።
በእርግጥ፣ በእርዳታ ብቻ፣ ከጊዜያዊ ችግሮችና ከደራሽ አደጋዎች መዳን እንጂ፣ በቅጡ መሻሻልና ማደግ አይቻልም። ቢሆንም፣ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ደራሽ እርዳታና የገንዘብ ድጋፍ በየዓመቱ ማግኘት፣ ቀልድ ‹እድል› አይደለም። በብልሃት ለዘለቄታው ከችግር መላቀቅና ወደ ከፍታ መራመድ ደግሞ፣ የኢትዮጵያውያን ድርሻና ምርጫ ነው። “ሃሳብን በእርዳታ ላይ ጥሎ” መፍዘዝ መደንዘዝም፣ የኛው ምርጫ ከመሆን አያልፍም።
መታዘብ ትችላላችሁ። ሌላው ቀርቶ፣ “የኮረና ቫይረስ ክትባት፣ ለራሳችን ለመግዛት ምን ያህል ገንዘብ እናወጣለን? ወጪውን እንችለዋለን?” የሚል ቅንጣት ጥያቄ የማናነሳው፣ ለአፍታ የማንነጋገረው ለምን እንደሆነ አስቡት። በሆነ መንገድ፣ በሃብታሞቹ መንግስታት ወጪ፣ ነገ ከነገወዲያ፣ የክትባት እርዳታ እንደሚመጣ በመተማመን አይደለም? ነው እንጂ። አዎ፣ እርዳታ ላይ መተማመን አያዋጣም። ነገር ግን፣ ኢትዮጵያ ባለወዳጅ አገር መሆኗ መልካም ነው።
ከዚህ ጎን ለጎን፣ “ኢትዮጵያ፣ ታድጋለች፤ ትሻሻላለች” የሚል ተስፋ መኖሩ፣ ለአገራችን ይጠቅማታል። የተስፋ ምድር በመሆኗ፣ ወዳጅና ደጋፊ ጥሎ አይጥላትም። የማደግ ተስፋዋ፣ በዓለም ዙሪያ፣ ተሰሚነትንና አክብሮትን ያስገኝላታል። በእድገት የመጓዝ ውጥኗና ተስፋዋ ተቋርጦ እስካልጨለመ ድረስ፣ ወዳጅ አልባ አትሆንም። በተለይ ዋና ዋናዎቹ አገራት፣ በሆነ ባልሆነ ሰበብ ለፀብ አይነሱባትም።
ለምን ቢባል፣ ‹ላለው ይጨመርለታል› ነው ነገሩ። በትልቅነት ወደ ከፍታ መገስገስ ከምትችል አገር ጋር ለመጣላት የሚቸኩል ሳይሆን ወዳጅነትን የሚመኝ ይበረክታል።
ኢትዮጵያ፣ ባለታሪክ ብቻ ሳትሆን ባለተስፋ ትልቅ አገር መሆኗ፣ ፀብና ጥቃትን ሳይሆን፣ እርዳታንና ክብርን፣ ወዳጅነትንና ትብብርን ይዞላት ይመጣል።
በሌላ በኩልስ?
“ከሌለው ይቀነስበታል” ተብሏል። ምን ይጠየቃል? የደከመ፣ የደኸየ፣ የተናጋ አገር፣… ለባሰ መከራ እንደሚጋለጥ፣ ከአገራችን የድሮ ታሪክና የዛሬ ሁኔታ መገንዘብ እንችላለን።
ኢትዮጵያን የመሰለች ትልቅ ባለታሪክ አገር፣ በሕዳሴ ግድብ ሳቢያ፣ ለዶናልድ ትራምፕ ተፅዕኖ መጋለጥ ነበረባት? ”እርዳታ ታግዶብሻል” የሚል የሂሳብ ማወራረጃ ወጥመድ ሲወረውሩባት ታዝበናል።
ኢትዮጵያን የመሰለች ትልቅ ባለታሪክ አገር፣ በትናንሽ የጎረቤት ነውጠኞጭና በጥቃቅን አላዋቂዎች ሳቢያ፣ ሰላም ማጣት ነበረባት? በሶማሊያ፣ በኤርትራ፣ አሁንም ደግሞ በሱዳን በኩል፣ ኢትዮጵያን ለመውረር ይቅርና ለመተንኮስ የሚደፍር ባለስልጣን መኖር ነበረበት?
ኢትዮጵያን የመሰለች ትልቅ ባለ ታሪክ አገር፣ የ110 ሚሊዮን ሰዎች አገር፣ መግቢያና መውጫ የባህር በር ማጣት ነበረባት?
”ከሌለው ይቀነስበታል” የሚል ነው ነገሩ።
አስተውሉ። ኢትዮጵያ፣ የደከመችው፣ የደኸየችውና የተጎሳቆለችው፣ ‹ወደብ አልባ› ከሆነች በኋላ አይደለም።
ይልቅስ፣ ስለተዳከመችና ስለደኸየች ነው፣ የባሕር በር ያጣችው። ዛሬ፣ መውጪያና መግቢያዋ ሁሉ፣ የተውሶ ብቻ ሆኗል። ይሄ፣ ቀላል ውድቀት አይደለም። ይህን ውድቀት የሚሽር ሁነኛ መፍትሄ መፍጠር የግድ ያስፈልጋል። በእርግጥ፣ የዚህ ውድቀት መፍትሄ፣ ፀብና ጦርነት በመቀስቀስ ሊሆን አይችልም። አይዘልቅምም። የትም አያደርስም። ምንም ብታገኝ እንኳ፣ ኢትዮጵያ፣ በቀውስ አዙሪት የምትናጋ ድሃ፣ በግጭትና በአመፅ የምትታመስ ደካማ ድሃ አገር ከሆነች፣… ያገኘችውን ስታጣ ታሪክ አሳይቶናል። በተጎዳች ቁጥር፣ በብዙ ነገር ይቀነስባታል።
ደካማና ድሃ አገር፣ ከዓለም ጋር የሚያገናኝ መውጪያና መግቢያ የባሕር በር ከማጣትም ባሻገር፣ ከቤት ወደ ስራ በሰላም ወጥቶ የመመለስ እርጋታም ጭምር ታጣለች። በጊዜ መንገዷን ካላስተካከለች፣ ሕልውናዋም ይጠፋል። “ከሌለው ይቀነስበታል” ነውና ነገሩ። በተቃራኒው፣…
አገራችን፣ ትንሽ ሰላምና እርጋታ ካገኘች ግን፣ ትንሽ ደልደል ያለ ህግና ስርዓት ካሰፈነች ግን፣ በኑሮ የመሻሻልና በኢኮኖሚ የማደግ ትንሽ እየተራመደች ለእመርታ ከደረሰች፣… በእንዲህ አይነት መንገድ በተጓዘች ቁጥር፣… ሌላም ሌላም ይጨመርላታል።
ደግሞም የግድ ነው። በደህና ከተጓዘች፣ በአምስት በሰባት ዓመት ውስጥ ብቻ፣ ወደ ውጭ የሚሄድና ወደ አገር የሚመጣ የጭነት ብዛት በእጥፍ እንደሚጨምር አስቡት። የኢትዮጵያ መውጪያና መግቢያ መስመር፣ ምንኛ እንደሚጣበብ መገመት ትችላላችሁ። ይሄ በ5 ወይም በ7 ዓመት ውስጥ ነው። ከአስርና ከአስራ አምስት ዓመት በኋላስ?
ያኔም በጂቡቲ ወደብ ብቻ? ያኔም በሌላ የተውሶ ወደብ ብቻ? ከመቶ ሚሊዮን በላይ ህዝብ የያዘና ኢትዮጵያን የሚያክል ትልቅ አገር፣ ያለ አስተማማኝ ወደብ፣ ለጊዜው ካልሆነ በቀር፣ በእድገትና በሰላም ብዙ መቀጠል አይችልም።
በአጭሩ፣ የባህር በር ባለቤትነት፣ ለኢትዮጵያ፣ የኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን፣ የሰላምና የህልውና ጉዳይ እየሆነባት ይመጣል። ከ10 ዓመት በኋላ፣ የወደብ ጥያቄ አንገብጋቢና አጣዳፊ ጉዳይ ይሆንባታል። እስከዚያው፣ እጅን አጣድፎ አይንን ጨፍኖ መጠበቅ አይበጅም።
ይልቅስ፣ ከወዲሁ ማሰብና በወዳጅነት መንፈስ አስተማማኝ መፍትሄ ለማዘጋጀት መትጋት ያስፈልጋል። አዎ፣ ቀላል አይደለም። ከባድ ፈተና ነው። ነገር ግን፣ ከባድ ስለሆነ ልንሸሸው አንችልም።
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት፣ የሰላምና የእድገት አይቀሬ ጉዳይ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ፣ አገር፣ በሰላም እየተደላደለችና እያደገች የምትጓዝ ከሆነ፣ ጥንካሬዋና እድገቷ፣ ፈተናዋን ቀለል ያደርግላታል። አቅም ይሰጣታል። ዓለማቀፍ የወዳጅነት መንፈስን ያመጣላታል።
ካልሆነስ? ከሰላምና ከእድገት ከራቀችስ? ችግር ይበዛበታል።
በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ እንዳየነው፤ ከግብፅ መንግስት አንዳች ውለታ የሚፈልግ መንግስት፣ የኢትዮጵያን ጉዳይ፣ የሂሳብ ማሟያ ሊያደርገው ይሞክራል። በቅርቡ የሱዳን ባለስልጣናት፣ ድክመታቸውን ለመሸፋፈን፣ የህዝብን ተቃውሞና ቁጣ ለማብረድ፣ የህዝብን ስሜታዊ ድጋፍ ለማግኘት፣ ምን አደረጉ? የድንበር ትንኮሳ፣ የቁጣ ማብረጃ እንዲሆንላቸው ምን እንዳደረጉ አይተናል። የትንሽ የትልቅ መጫወቻ እንሆናለን። “ከሌለን ይቀነስብናል”።
በእርግጥ፣ በዛሬው ፅሁፍ፣ የውጭ ግንኙነት ቅኝትን አጉልተው ከሚገልፁ አባባሎች መካከል አንዱን ብቻ ነው ያየነው - “ላለው ይጨመርለታል። ከሌለው ይቀነስበታል” የሚለውን አገላለፅ።
በሚቀጥለው ሳምንት ሌላኛውን ገፅታ እንመለከታለን። ‹‹ዓለማቀፍ የበረከት ግስጋሴ እንዳያመልጥህ የመትጋት፣ ከዓለማቀፍ የጥፋት ማዕከል የማምለጥ ፅናት› ምን እንደሚመስል፣ የአድዋን ድል፣ እንዲሁም የዘመናችንን ፈተናዎች በማነፃፀር ለማየት እንሞክር።Read 4004 times