Monday, 22 February 2021 06:56

መንግስት በትግራይ የሚጠብቀው ፈታኝ የፖለቲካ ሥራ

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(2 votes)

የሕወሓት የፕሮፓጋንዳ ክንፍ ገና አልተነቀለም
                           
           ላለፉት ሁለት አሰርት ዓመታት፣ ሁለንተናዊ ኪሳራ ሲያደርስ የነበረው አውዳሚው ድርጅት ሕወሓት፣ አሁን ታሪክ ሆኗል፡፡ ሕወሓት በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ገሃድ የወጣ ክህደትን ጥቅምት ሃያ አራት ከፈጸመ በኋላ፤ በውጭ  ሀገር የሚገኙ ድርጎ ተቀባዮቹ፣ እስትንፋስ ሊቀጥሉለት በብርቱ ባዝነዋል፡፡ በታላላቅ መገናኛ ብዙኃን  የከፈቱት ፕሮፓጋንዳ ግን አሁንም አልበረደም፡፡
ለድርጅቱ  ስስ ልብ ያለው ሀርማን ኮን፣ ገና በጦርነቱ መባቻ ላይ “ህወሓት የውጊያ ልምድ ስላለው፤ ማእከላዊው መንግሥት ምእራፉ ወደማይታወቅ ትርምስ ሀገሪቱን ይከታታል::” ሲል አስጠንቅቆ ነበር፡፡ በውጪው አለም ያሉት  የድርጅቱ ደጋፊዎች፣ “ጦርነት ባህላዊ ጨዋታችን ነው፤ እኛን ማሸነፍ ተራራ በገመድ እንደ መጎተት የማይሞከር ነው” በሚል ከልክ ባለፈ ለራስ የተሰጠ ምስል ታውረው ነበር፡፡ ሌሎች አለም አቀፍ ሚዲያዎች፣ የሕወሓት ተከፋይ ነጭ ሎቢስቶችን  ዋቢ በማድረግ፤ "ኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ተዘፍቃለች፤ ግጭቱም ቀጠናዊ ነው፤ መንግሥት ከሕወሓት ጋር ለድርድር መቀመጥ ይኖርበታል፤; የሚል መጠነ ሰፊ ዘመቻ በየአቅጣጫው ከፈቱ፡፡
በሶስት ሳምንታት ውስጥ ሕወሓት በሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ በአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ  ከባድ መስዋእትነት ተፍረክርኮ ድብቃ ሲመታ፣ ሌላ የፕሮፓጋንዳ ማሽን ተከፈተ፡፡
ድህረ ሕወሓት ፕሮፓጋንዳ
ያ ሁሉ ሽለላና ቀረርቶ፤ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አፈር ሲለብስ፤ ሕወሓታዊያን የደረሰባቸውን የመንፈስ ስብራት ለማከም ሌላ መላ ዘየዱ፡፡ በጦርነቱ የኤርትራ ወታደሮች ተሳትፈዋል የሚለው ዘመቻ፤ በሕወሓት ሽንፈት ማግሥት በሰፊው ተቀነቀነ፡፡ “የኤርትራ ወታደሮች ለጆሮ የሚዘግንን ግፍ  ፈጽመዋል፤ በርካታ ሴቶች ተደፍረዋል፤ ፋብሪካዎች ተቃጥለዋል፤ ንብረቶች ተዘርፈዋል” የሚል የተጠና ፕሮፓጋንዳ፣ የታላላቅ ሚዲያዎች አርእስተ ዜና እየሆኑ መውጣት ጀመሩ፡፡ ለጊዜውም ቢሆን የሁሉም አትኩሮት ከሕወሓት ሽንፈት  ይልቅ በኤርትራ ወታደሮች ድርጊት ላይ ሆነ፡፡ በዚህም የተነሳ ሕወሓታዊያን፣ ሽንፈታቸውን አዲስ በመመዘዙት  አጀንዳ ለጊዜው አዳፈኑት፡፡
የዚህ መጠነ ሰፊ ዘመቻ  ዋና አላማው፣ የሕወሓት ምስልን መከላከል ነው፡፡  “ጎረቤት ሀገር እጁን ባያስገባ ኖሮ አንሸነፍም ነበር” በማለት የተሰበረ ስነልቦናቸውን እንደ መጠገኛ ተጠቅመውበታል፡፡ እዚህ አንድ ትርጉም የሚሰጥ አባባልን ላንሳ፤ አንጋፋው የኢሳት ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና “እለታዊ” በተባለው ተወዳጅ ፕሮግራም ላይ “ሕወሓቶችን ጠብመንጃ ብቻ ሳይሆን ሱሪ ያስታጠቃቸው ሻዕቢያ ስለነበር ከተሸነፍን አይቀር በሻዕቢያ ብንሸነፍ ክብር ነው፤ በሚል ነው ዘመቻውን የከፈቱት” ብሏል። ሕወሓታዊያን በትግል ዘመን ሻዕቢያ ያሳደረባቸው የባርነት ስሜት፣ ከመቃብር ወርደውም የለቀቃቸው አይመስልም፡፡   
የምእራቡ ዓለም የሕወሓት ፕሮፓጋንዳ ዘዋሪዎች እነ ማርቲን ፕላውት፣ አሌክስ ዳዋልና ሪኔ ሊፍሮህ  ናቸው፡፡ እነዚህ ግለሰቦች፣ የማእከላዊውን መንግሥት የሚኮንኑ ትንታኔዎችን በተለያዩ የዜና አውታሮች ላይ ሰጥተዋል፡፡ ነገሩን ወለፈንዲ የሚያደርገው፤ ግለሰቦቹ ለመረጃ ተአማኒነትና ለጋዜጠኛነት ሙያ ስነምግባር ጥብቅና እንቆማለን በሚሉ ገናና የሚዲያ ተቋማት ውስጥ መስራታቸው ነው፡፡
የስነመለኮት ባለሙያው አቶ ደስታ ሀሊሶ፣ “ሪልጅንንፕላግድ” በተባለው ድረገጽ ላይ ከዚሁ ጋር የተያያዘን ሐሳብ አስፍረዋል፤ “ማርቲን ፕላውት የተባለው የሕወሓት ደጋፊ፣ በርካታ  የውሸት ታሪኮችን በመፈብረክ፣ በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች በማሰራጨት ይታወቃል፡፡ ጋዜጠኛው በተለይ የሕወሓት ቱባ ባለስልጣናት፣ በሀገር መከላከያ ሰራዊት ሲያዙ፤ በትዊውተር ገጹ፣ ለ24 ሰዓት የሐዘን ስሜቱን ይገልጻል። ፕላውት ለሕወሓት ያለው ልብ ስስ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ አስደንጋጭ የሚያደርገው፣ ይህ ሚዛናዊ ያልሆነ ባለሙያ፣ “ለእውነት ጥብቅና እቆማለሁ” በሚለው ዓለም አቀፍ ተቋም፣  ቢቢሲ ውስጥ  መስራቱ ነው” ብለዋል፡፡
እነዚህ ጸጉረ ልውጥ ሎሌዎች በሚነዙት ፕሮፓጋንዳ የተነሳ፣ አለም የጥቅምት 24ቱን  ገሃድ የወጣ ክህደት ዘንግቶ በተቀደደለት ቦይ መፍሰስ ጀመረ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የሕወሓታዊያን ፕሮፓጋንዳ ረሃብ ሆኗል፡፡ ሕወሓት በ1977 ድርቅ፣ በትግራይ ስም በመነገድ፣ ዳግም እንዳንሰራራ ከታሪክ መረዳት እንችላለን፡፡ እንደውም፤ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ቢቢሲ በአንድ ወቅት የሰራውን ዘገባ ዋቢ ማድረግ ይቻላል፡፡ በርግጥ በስሙ የሚነገደው ደጉና ሀገር ወዳዱ የትግራይ ሕዝብ፣ በመሀል ጭዳ መሆኑ የሚያሳዝን ነው፡፡
ሕወሓታዊያን ረሃብን እንደ ዋነኛ የፕሮፓጋንዳ ስልት እየተጠቀሙበት ያለው፣ ለትግራይ ሕዝብ ከልባቸው አዝነው እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ ለሴራ ፖለቲካ እንደሆነ ከማንም የተሰወረ ሐቅ አይደለም፡፡ የታዋቂውን ኢኮኖሚስት  መጽሔት “ረሃብን እንደ መሳሪያ” የተሰኘ ትንታኔ ላነበበ፣ የሕወሓት እጅ ምን ያህል ረጅም እንደሆነ ማወቅ አይሳነውም፡፡
የድህረ ሕወሓት ፈተናዎች
ተረፈ ትህነግን መጠራረግ የመንግሥት ቀዳሚ ፈተና ሊሆን ይችላል፡፡ ተቆርጠው የቀሩ የድርጅቱ አንጋቾች በየበረሃው ይኖራሉ፡፡ አሁን አሁን የተረፉት የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች በቀበሮ ጉድጓድ ሆነው፤ አለን ማለት ጀምረዋል፡፡ እነዚህን ለመጠራረግ መደበኛ ውጊያ አያስፈልግም፡፡ በልዩ ሁኔታ በሰለጠነ የጸረ ሽምቅ ኃይል አማካኝነት መደምሰስ ይቻላል፡፡ ከዚህ በላይ፣ ላለፉት አርባ አመታት፣ በሕወሓት ፕሮፓጋንዳ የተሰራ ቁጥሩ ቀላል የማይባል፣ ያልታጠቀ ሰላማዊ ማኅብረሰብ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ይኽንን የቆየ ትርክት ለማፍረስ መንግሥት ፈታኝ የፖለቲካ ሥራ ይጠብቀዋል፡፡
ሌላው  ተገዳዳሪ ሁነት፣ መንግሥት የጥይት እርሳስ አስወንጭፎ ማስወገድ የማይችለው ባላጋራ ነው፡፡ የሕወሓት የሙት መንፈስ፣ በሕገ መንግሥቱና በፌዴራል ሥርዓቱ አማካኝነት ተገልጦ፣ ሀገር ማመሱን እንደሚቀጥል እሙን ነው፡፡ ይህንን  ውርስ በወታደራዊ ዘመቻ እልባት መስጠት የማይታሰብ ነው፡፡ ከችግሩ ለመላቀቅ፣ ሀገራዊ መግባባት ሊያመጣ የሚችል፣ ሀሉን አቀፍ የውይይት መድረክ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡Read 2499 times