Sunday, 21 February 2021 17:21

የአደገኛ ኬሚካሎች ክምችትና አጠቃቀም አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተነገረ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

https://youtu.be/duji2pSKHQE?t=33

- ኢትዮጵያ ፀረ-ተባይ ኬሚካሎችን ያለፍተሻ የምታስገባ ብቸኛ የምስራቅ አፍሪካ አገር ናት
       - ዩኒቨርሲቲዎች አደገኛ ኬሚካሎችን በላዳ ታክሲዎች እያስጫኑ ያስጥላሉ ተብሏል
       - ከ50 ዓመታት በፊት ጥቅም ላይ እንዳይውል የታገደ ከ1300 ቶን በላይ አደገኛ ኬሚካል በአዳማ ተከማችቶ ይገኛል፡፡
            
             ካንሰርን ጨምሮ የተለያዩ ከባድ የጤና ችግሮችን ሊያስከትሉ የሚችሉ አደገኛ ኬሚካሎች ክምችት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገለፀ። ኬሚካሎቹ እንደ ስኳርና ጨው በየሱቁ እየተሸጡ ነው ተብሏል።
የእነዚህን አደገኛ ኬሚካሎች አጠቃቀምና የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ኬሚካሎች በአግባቡ ስለሚወገዱበት ሁኔታ የሚመክር  አገራዊ ውይይት ሰሞኑን ተካሂዶ ነበር። ለሁለት ቀናት የተካሄደውን ይህንኑ ውይይት ያዘጋጀው የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ሲሆን በውይይቱም ኬሚካሎቹ በአገር አቀፍ ደረጃ እያስከተሉ የሚገኙትን ጉዳት የተመለከተ ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቧል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኬሚስትሪ ትምህርት ክፍል ባልደረባ የሆኑት ዶ/ር መስፍን ረዲበዚሁ ወቅት ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ እንዳመለከቱት፤ የጉበት ካንሰርን ጨምሮ የተለያዩ የካንሰር ህመሞችን ሊያስከትሉ ይችላሉ የተባሉ ኬሚካሎች  እነደ ሽንኩርት፣ ቲማቲምና ቃሪያ ባሉ የዕለት የምግብ ፍጆታዎች  ውስጥ ተገኝተዋል። ፀረ-ተባይ ኬሚካሎቹ አፈርና ውሃችንን በክለው ወደምንመገባቸው ምግቦች ውስጥ ገብተዋል ያሉት ዶ/ር መስፍን፤ ይህም በአሁኑ ወቅት በአገራችን በስፋት እየታየ ላለው የካንሰር ህመም መነሻ ምክንያት ሊሆን ይችላል ብለዋል።
 ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተለያዩ የአካል ጉዳት ያለባቸውን ህፃናት መውለድና በተለያዩ የካንሰር ህመሞች መያዝ እየተበራከተ ሄዷል ያሉት ዶክተሩ ይህም የነዚህ ኬሚካሎች ውጤት ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ፀረ-ተባይ ኬሚካሎችን ያለ ፍተሻ የምታስገባ ብቸኛ የምስራቅ አፍሪካ አገር መሆኗን የጠቆሙት ዶ/ር መስፍን፤ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ምን ያህል ኬሚካል እንዳለ እንኳን እንደማይታወቅና ኬሚካሎች በየሱቁ እንደ ስኳርና ጨው እንደ ልብ እየተቸበቸቡ እንደሆነ ተናግረዋል።
ለግብርና ዘርፍ የሚገቡ ኬሚካሎች አያያዝና አጠቃቀም ላይ ትኩረቱን አድርጎ በተዘጋጀው በዚሁ አገራዊ የውይይት መድረክ ላይ እንደተገለጸው፤ ለጤና እጅግ አደገኛ የሆኑ ኬሚካሎች በየሱቁ እንደ ልብ የሚገኙ በመሆናቸው አርሶ አደሩ እየገዛ እየተጠቀመባቸው ነው ብለዋል። ኬሚካሎቹ ለከብቶች መኖ እንደ ማጣፈጫና እንደ ከብቶች ማድለቢያ ሁሉ እያገለገሉ መሆናቸውንም ተናግረዋል። ፀረ-ተባይ መድሃኒቶች፣ በሙያው ዕውቀት ባላቸው ሰዎች በአግባቡ መሸጥና ጥቅም ላይ መዋል የሚገባቸው ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ኬሚካሎቹ በዘፈቀደና እጅግ አሳሳቢ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ እየዋሉ እንደሆነ ተናግረዋል። ምንም አይነት ፍተሻና ቁጥጥር ሳይደረግባቸው ወደ አገር ውስጥ የሚገቡት ኬሚካሎች ምንነታቸው የማይታወቅ፣ የሚያስከትሉት ጉዳት ምን ያህል እንደሆነ እንኳን ለማወቅ የማይቻል መሆኑንም ዶክተሩ አመልከተዋል።
አርሶ አደሩ ኬሚካሎችን እየገዛና እየቀላቀለ ጥቅም ላይ እያዋላቸው መሆኑም ተመልክቷል። ኬሚካሎቹ ከግብርናው ዘርፍ በተጨማሪ ለትምህርትና ለምርምር እንዲሁም ለኢንዱስትሪዎች ግብአትነት ጥቅም ላይ የሚውሉ ሲሆን የአገልግሎት ጊዜያቸው በሚጠናቀቅበት ወቅት የሚወገዱበት ሁኔታም እጅግ አሳሳቢ መሆኑን በጥናት እንደተደረሰበት ተገልጿል።
ዩኒቨርሲቲዎችና ት/ቤቶች ለቤተ-ሙከራቸው በትምህርት ሚኒስቴር በኩል የሚቀርብላቸውን ኬሚካል የሚያስወግዱበት ሁኔታም አስደንጋጭ እንደሆነ ተገልጿል።
ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ባልደረባ ዶ/ር ኢዮቤል ሙሉጌታ ያቀረቡት ጥናታዊ ፅሁፍ እንደሚያመለክተው፤ በርካታ ት/ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች ለቤተ-ሙከራቸው የተሰጣቸው ኬሚካሎች የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ሲያልፍ ቤተ-ሙከራዎቹን ከነኬሚካሎቹ መዝጋት አለያም ኬሚካሎቹን ፈሳሾቹን በውሃ እየቀላቀሉ በቦዮች ማስወገድ ደረቅ ቆሻሻዎችን ደግሞ በየቦታው እንደ አልባሌ ቆሻሻ መጣል ምርጫቸው አድርገዋል ብለዋል።
አንዳንድ ት/ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች ኬሚካሎቹን ወስደው የሚጥሉላቸው የላዳ ታክሲ ደንበኞች እንዳላቸውና ኬሚካሎቹን በየመንገዱና በየስፍራው እየጣሉላቸው እንደሆነም ተገልጿል።
የእነዚህ ለጤና እጅግ አደገኛ የሆኑ ኬሚካሎች፣ በአልባሌ ሁኔታ በየመንገዱ ላይ መጣል በአሁኑ ወቅት በአገራችን በስፋት እየታየ ለመጣው የካንሰርና ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መበራከት ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም ባለሙያዎቹ ተናግረዋል።
ለጤና እጅግ አደገኛ በመሆኑ ከ50 ዓመታት በፊት በዓለም በጥቅም ላይ እንዳይውል የታገደውና ዲዲቲ እየተባለ የሚጠራው ኬሚካል፣ በአገራችን በብዛት እንደሚገኝና ይኸው ኬሚካል በአዳማ በአንድ መጋዘን  ውስጥ ከ1300 ቶን በላይ ተከማችቶ እንደሚገኝ በውይይት መድረኩ ተገልጿል።
የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃጂ ኢብሳ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ አገራዊ ምክክሩ ለዚህ አሳሳቢ ችግር መፍትሄ ለመሻትና የኬሚካል አወጋገድ ስርዓት ተግባራዊ ለማድረግ የሚስችል አሰራር እንዲፈልግ ለማድረግ ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በአገር አቀፍ ደረጃ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውን ኬሚካሎች ለማስወገድ የሚያስችል አሰራር አለመኖሩም በዚሁ ወቅት ተገልጿል።


Read 1557 times Last modified on Thursday, 25 February 2021 20:08