Sunday, 21 February 2021 17:11

ESOG 2021---29ኛ አመታዊ ጉባኤ

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

  የኢትዮጵያ የፅንስና የማህፀን ሐኪሞች ማበህር ከተቋቋመ እነሆ የ29ኛውን አመት አመታዊ ጉባኤ እ.ኤ.አ ከ Feb 14-17 በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከየካቲት 7-10 አካሄዶአል፡፡
ጉባኤው የተካሄደው በአዲስ አበባ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር (ESOG) የተቋቋመው የዛሬ 29 አመት እ.ኤ.አ በ1992 ዓ/ም ነው፡፡ ሲቋቋም በዋነኛነት ምክንያት ተደርጎ የተወሰደው ጤናማ የሆነ እናትነትን እውን ማድረግ ሲሆን ለዚህም የእናቶችን እና ጨቅላ ህጻናትን በወሊድ ጊዜ የሚያጋጥሙ ሞት እና ጉዳትን ማስወገድ እንዲቻል እንዲሁም በአገሪቱ ውስጥ ያለውን አነስተኛ የስነተዋልዶ ጤና እንክብካቤ ለማሳደግ ብሎም ለማዳረስ እንዲቻል የጽንስና ማህጸን  ህክምና ባለሙያዎች ተነሳሽነትና ትኩረት እንዲኖረው ለማድ ረግ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር (ESOG)  በኢትዮጵያ ያሉ የጽንስና ማህጸን  ሕክምና ባለሙያዎች በኢትዮጵያ ያለውን የስነተዋልዶ ጤና አገልግሎት ጥራት እንዲኖረውና ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆን ማስቻል ሲሆን ይህንንም  ማህበሩ አላማው አድርጎ እየተ ጓዘባቸው ካሉ ዋነኛ ነጥ ቦች ውስጥ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ባለፉት 28 አመታት የስነተዋልዶ ጤና አገ ልግሎ ትን ለህብረተሰቡ እንዲደርስ በማድረጉ ረገድ የማህበሩን አባላት በማሳተፍ እንዲሁም ከፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር እጅ ለእጅ በሚባል ደረጃ ተያይዞ በመተጋገዝ በተጨ ማሪም ሌሎች በጉዳዩ ዙሪያ የሚሰሩና የሚመለ ከታቸው አካላት ጋር በመተጋገዝ ሲሰራ ቆይቶአል፡፡ በዚ ህም የትብብር ስራ የሚጠቀሱ ዋነኛ የስነ ተዋልዶ ጤና ዝርዝሮች በመጠኑ የሚከተሉት ናቸው፡፡
ጤናማ እናትነትን እውን ማድረግ፤
ኤችአይቪ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ ማድረግ(PMTCT)፤
በወሊድ ጊዜ የሚከሰት የደም መፍሰስን መከላከል፤ (Post-Partum Hemorrhage)
የወሲብ ጥቃት የደረሰባቸው የአካልና የስነልቡና ጉዳት እንዳይደርስባቸው ድጋፍ ማድረግ፤
የተሟላ እና አፋጣኝ የሆነ የማህጸንና ጨቅላ ህጻናትን ሕክምና አገልግሎት ጥራት ማሻሻል ፤
አገር አቀፍ የህክምና አገልግሎት አቋምና መመሪያዎችን ማስተዋወቅ ….ባለፉት አመታት ከተሰሩት አበይት ስራዎች መካከል ናቸው፡፡
የ(ESOG) የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር 29ኛው አመታዊ ጉባኤ አከባበር እንደከአሁን ቀደሙ የማህበሩ አባላት፤ ተባባሪ የኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች ፤እንዲሁም ከአገር ውስጥና ከውጭ ሀገር ሳይንሳዊ የምርምር ወረቀቶችን የሚያቀርቡ ባለሙ ያዎች ሁሉ በግንባር ከኮንፍረንሱ አዳራሽ በመሆን ያቀረቡበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ የህክምና ባለሙያዎች በተለያዩ ጊዜያት አዳዲስ ሳይንሳዊ ምርምሮችንና አፈጻጸሞችን እንዲያውቁ እና የህክምና እውቀታቸውን እንዲያ ዳብሩ የሚያስችለው Continual medical education (CME) በተለያዩ የውጭ ሀገርና የአገር ውስጥ ባለሙያዎች አማካኝነት የተሰጠ ሲሆን ይህ የተካሄደውም በኢንተርኔት አማ ካኝነት ነው፡፡ ከአገር ውስጥ ስልጠናውን ለመውሰድ ፈቃደኛ የሆኑ ባለሙያዎች ትንሽ ቁጥር ያላቸው እየሆኑ በተለያዩ ክፍሎች ውስጥ እየተመደቡ እንዲሁም በየትኛውም ቦታ ያሉ ባለሙያዎች በስራቸው ላይ ባሉበት ሆነው በኢንተርኔት በመታገዝ ስልጠናውን እንዲወስዱ በመደረጉ ሂደቱ በስኬት ተጠናቆአል፡፡ ስልጠናው በዚህ መንገድ እንዲሆን ያስገደደው ዋናው ምክንያት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሊከሰት የሚችለውን አደጋ ለመከላከል ነው፡፡
Feb/14-15 ለሐኪሞች የሚሰጠው ስልጠና ከተጠናቀቀ በሁዋላ Feb/16-17 ኮንፍረንሱ እንዲ ካሄድ ተደርጎአል፡፡ በኮንፍረንሱ ላይ የተገኙት ተሰብሳቢዎችም የኢትዮጵያ የማህጸንና ጽንስ ሐኪሞች ማህበር አባላት ብቻ ሲሆኑ በመጀመሪያው ቀን ስብሰባ ላይ ብቻ በበቂ ሁኔታ በተዘጋጀ ቦታ በአንድ ላይ የተደረገ ሲሆን ኮንፍረንሱ በሁለተኛው ቀን በኢንተርኔት አማካኝነት በተለያዩ ክፍሎች ሳይንሳዊ ወረቀቶች የቀረቡበት አሰራርን የተከተለ ነበር፡፡ ስለሁኔታው አስተያየት እንዲሰጡ የተጠየቁ ባለሙያዎች ካለምንም ስጋት ስልጠናውንም ሆነ ኮንፍረንሱን በማጠናቀቃቸው ደስተኞች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስን በሚመለከት የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ትኩረት ያደረገ በመሆኑ በተለያየ ወቅት ከእናቶች እንዲሁም ከሚወለዱ ልጆች አንጻር በተጨማሪም ከእርግ ዝና ጋር በተያያዘ የተለያዩ ለግንዛቤ የሚረዱ ጽሁፎችን በዚህ አምድ ማስነበቡ ይታወሳል፡፡ ለትውስታ ያህል ዋና ዋና ከምንላቸው ነጥቦች የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
አንዲት እርጉዝ ሴት እንዴት አድርጋ እራስዋን ከCOVID-19 መከላከል ትችላለች?
በእርግዝና ላይ ያለች ሴት የCOVID-19 ቫይረስ ለመከላከል የታወቀ እና ማንኛውም ሰው የሚጠቀምባቸውን  የመከላከያ ዘዴዎች መጠቀምዋ በቂ ነው፡፡ ይህ ከተደረገ የኮሮና ቫይረስን መከላከል ይቻላል፡፡ እጅን በተደጋጋሚ በሳሙና መታጠብ። እጅን በአልኮሆል ወይንም ከአልኮሆል ጋር ተደባልቆ ለእጅ ማጽጃነት በተዘጋጀ ሳኒታይዘር በደንብ ማጽዳት፤በራስና በሌሎች ሰዎች መካከል በሚፈጠረው ግንኙነት ምንጊዜም እርቀትን መጠበቅ እና ሰዎች ከሚበዙበት ቦታ እራስን ማራቅ፡፡ ቢቻል ቢቻል ከቤት ሆኖ ስራን መስራት እና ወደውጭ የሚወጡበትን ጊዜ መቀነስ፤ አይንን አፍንጫንና አፍን ከመነካካት መቆጠብ፤አፍንጫንና አፍን በፊት መሸፈኛ ጭንብል (Face Mask) መሸፈን ተገቢ ነው።
በእርግዝናና ልጅ በመውለድ ጊዜ ምቹ የሆነ የጤና አገልግሎት ምን አይነት ነው?
ክብርና ጥሩ ቀረቤታ ባለው መንገድ የጤና አገልግሎትን ማግኘት፤
በመውለድ ጊዜ የሚተማመኑበት ፤የሚፈልጉትን የሚያሟሉበት እድል መኖር፤
ከአዋላጅ የህክምና ባለሙያዎች ጋር ግልጽ የሆነ ግንኙነት፤  
ተገቢ የሆነ ህመምን የሚያስታግስ ዘዴ መኖር፤
ምጥን እንደአመጣጡ ማስተናገድ እና በምን መንገድ ሊወለድ እንደሚችል ማሳወቅ፤
የመሳሰሉት ተግባራት በማዋለድ ስራ ላይ ከተሰማሩት ባለሙያዎች ይጠበቃል፡፡
እናትየው የኮሮና ቫይረስ ካለባት የተወለደውን ልጅ መንካት እና ማጥባት ትችላለችን?
የተወለደው ልጅ ያላቋረጥ ጡት መጥባት ከተደረገለት እና ከእናቱ ጋር የቅርብ ግንኙነት ካለው ሊደርስበት ከሚችለው ህመም እንዲያመልጥ ይረዳዋል፡፡ ስለዚህ
ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ጡት ማጥባት፤
የልጁን ሰውነት ወደ እናትየው ሰውነት በማስጠጋት መያዝ፤
እናት ከልጁ ጋር ክፍልን መጋራት እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡
ነገር ግን ልጁን ከመንካት በፊትም ሆነ ከነኩ በሁዋላ አፍና አፍንጫን መሸፈን ፤እጅን በደንብ አድርጎ መታጠብ እንደሚገባ መረሳት የለበትም። ልጁ የሚተኛበትን ክፍል መሬቱን ሁሉ ቫይረስ እንዳይኖርበት ካለማሰለስ ማጽዳት ይገባል፡፡
በአጠቃላይም እስከአሁን ድረስ ባለው እውታ በእርግዝና ላይ ያሉ ሴቶች ከሌሎች በተለየ መን ገድ በቫይረሱ ይጠቃሉ ባይባልም ነገር ግን እርግዝና በራሱ በሰውነት ላይ በሚያስከትለው ጫና ሴቲቱ አቅምንና ምቾትን የሚያሳጠ በመሆኑ በዚህ ላይ COVID-19 ሲጨመር ጉዳቱ ከፍ እንዳይል ሲባል እጅግ በጣም ጥንቃቄ ማድረጋቸውን እንዳይዘነጉት ይመከራል፡፡
ከCOVID-19 ጋር በተያያዘ ከላይ በተገለጸው መልክ ለእናቶችና ጨቅላዎቻቸው እንዲሁም ለመላው ቤተሰብ የሚጠቅሙ መረጃዎችን በተለያዩ ጊዜያት እየተከታተለ አምዱ ለአንባቢዎች እስከአሁን ሲያደርስ እንደቆየው ሁሉ መፍትሔው እስኪገኝ ድረስ ወደፊትም ማስተማር የሚችሉ ቁምነገሮችን ለንባብ ማለቱን ይቀጥላል፡፡
በኢሶግ 29ኛው አመታዊ ጉባኤ ላይ የተነሱ ተያያዥ ሳይንሳዊ እውነታዎችን ወደፊት ለአንባበ ቢዎች እንላለን፡፡



Read 13580 times