Sunday, 21 February 2021 17:07

ኦነግ እና ኦፌኮ እስካሁን አንድም እጩ ተወዳዳሪ አላስመዘገቡም

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

   በኦነግ በኩል በምርጫው ላለመሳተፍ ሁለት ምክንያቶች ቀርበዋል

          በምርጫው ለመሳተፍ ውሳኔ ላይ ያልደረሱት ኦፌኮ እና ኦነግ እስካሁን እጩ ተወዳዳሪዎችን እንዳላስመዘገቡ ለማወቅ የተቻለ ሲሆን ኦፌኮ በበኩሉ ጥያቄዎቼ ካተመለሱ በምርጫው አልሳተፍም ብሏል።
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) እጩዎችን ላስመዘገበው የአመራር አባላቱ በመታሰራቸው እንዲሁም ጽ/ቤቶቻቸው በመዘጋታቸው መሆኑን ሲገልፅ፣ በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ከኦፌኮ ጋር ተመሳሳይ ምክንያት ያቀርባል፤ የድርጅቱ አመራሮች በበኩላቸው ምክንያቱ የውስጠ ፓርቲ ችግር ነው ብለዋል።
ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ መሰረት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከየካቲት 8 እስከ መጪው ሰኞ የካቲት 21 እጩዎችን እንዲያስመዘግቡ የሚጠበቅ ሲሆን በአፋር፣ አማራ፣ ሲዳማ ፣ ደቡብና ሱማሌ ክልል ደግሞ ከየካቲት 15 እስከ 26 ቀን 2013 ዓ.ም ይሆናል ተብሏል።
መሰረታቸው የኦሮሚያ ክልል የሆነው ኦነግ እና ኦፌኮ እጩዎቻቸውን ከየካቲት 8 እስከ 21 ማስመዝገብ የሚገባቸው ቢሆንም፣ ሁለቱም የፖለቲካ ድርጅቶች የእጩ ምልመላ እንኳ ማድረግ እንዳልቻሉና እስካሁን አንድም እጩ አለማስመዝገባቸውን ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል።
ኦፌኮ እስካሁን በምርጫው ይሳተፉ አይሳተፉ ማረጋገጥ አለመቻሉን  የገለጹት የፓርቲው ም/ሊቀመንበር  አቶ ሙላቱ ገመቹ፤ በአሁኑ ወቅት ፓርቲው መሰረቱ በሆነው ኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ሁሉም ጽ/ቤቶቹ ዝግ መሆናቸውን ፣ አብዛሃኞቹ ለእጩነት የተመረጡ አባላትም ታስረው እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
“በአሁኑ ወቅት ምን ማድረግ እንዳለብን እንኳ ውሉ ጠፍቶብናል” ያሉት አቶ ሙላቱ፤ “መንግስት ሁሉንም በር ዘግቶ ወደ ምርጫው ግቡ ማለቱ አስገራሚ ሆኖብናል” ብለዋል።
የጽ/ቤቶችን መዘጋትና የአባላትን መታሰር ጉዳይ ለምርጫ ቦርድና ለሚመለከታቸው አካላት ፓርቲው ማሳወቁንና ቦርዱም ችግሩን በውይይት ለመፍታት ጥረት ማድረጉን ነገር ግን በመንግስት ወገን ምንም ምላሽ አለመገኘቱን ጠቁመው ይህም ሁኔታውን አስቸጋሪ አድርጎታል ብለዋል አቶ ሙላቱ።
ከዚህ አንፃር ኦፌኮ በምርጫው የመሳተፉ ጉዳይ በእጅጉ አጠራጣሪ መሆኑን ነው አቶ ሙላቱ የተናገሩት።
በተመሳሳይ መሰረቱን የኦሮሚያ ክልልን ያደረገውና ለመጀመሪያ ጊዜ በምርጫ ይሳተፋል ተብሎ የሚጠበቀው ኦነግ በሊቀመንበሩ ዳውድ ኢብሳ በኩል በሰጠው መግለጫ፤ የአባላት መታሰርና የጽ/ቤቶች መዘጋት ፓርቲው ከምርጫው ተገፍቶ እንዲወጣ እያደረገው መሆኑን አስታውቋል።
ሊቀ መንበሩ ይሄን ይበሉ እንጂ በእነ አቶ አራርሶ ቢቂላ የሚመራው ቡድን አባል የሆኑት የፓርቲው ቃል አቀባይ አቶ ቀጄላ መርዳሳ ምክንያቱ ሌላ ነው ይላሉ።
በዋናነት የፓርቲው የውስጥ  አመራር ችግር ለምርጫው እጩዎች እንዳያቀርብ እንቅፋት እንደሆነው የሚናገሩት አቶ ቀጄላ፤  በአባላት መታሰር ነው የሚለውን እንደማይቀበሉት ይገልፃሉ።
በቀጣይ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ተጨማሪ የእጩ ማስመዝገቢያ ጊዜ የሚሰጠን ከሆነ፣ ጠቅላላ ጉባኤ አድርገን የፓርቲውን ችግር በመፍታት ለምርጫው እንደርሳለን ያሉት አቶ ቀጄላ፤ ፓርቲው ግን እስካሁን በሊቀ መንበሩ አቶ ዳውድ ኢብሳ እምቢተኝነት ጠቅላላ ጉባኤም ለመጥራት መቸገሩን ነው የተናገሩት አቶ ቀጄላ።
እነ አቶ ቀጄላ እንደ መፍትሄ ያስቀመጡትም የፓርቲውን ጠቅላላ ጉባኤ በራሳቸው በማድረግ ወደ ምርጫው ለመግባት በፍጥነት ዝግጅት ማድረግን ነው።


Read 13863 times