Sunday, 21 February 2021 16:54

ኢዜማ በቢሾፍቱ በተገደሉት አመራሩ ጉዳይ የከተማዋ የመንግስት ሃላፊዎች ላይ ምርመራ እንዲደረግ ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

ለሟች የሀውልት ማቆሚያ ቦታ ይሰጠኝ ብሏል የክልሉ የብልጽግና ሃላፊዎች ግድያውን እንዲያወግዙ ተጠይቋል

           መንግስት በጥይት ተደብድበው ለተገደሉት የኢዜማ አመራር አባሉ አቶ ግርማ ሞገስ ፍትህ እንዲሰጠው እንደሚሻ ያስታወቀው ኢዜማ፤ ቀደም ሲል በሟች ላይ ማስፈራሪያና ዛቻ ሲሰነዝሩ የነበሩ የመንግስት ሃላፊዎች የምርመራው አካል እንዲሆኑ ጠይቋል፡፡
በአባሉ ላይ እሁድ የካቲት 7 ቀን 2013 ዓ.ም የተፈፀመው ግድያ “ፖለቲካዊ ነው” የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሱን የገለፀው ፓርቲው፤ በፖሊስ በኩል የግድያውን አቅጣጫ ለማሳት የሚደረገው ሙከራ ተቀባይነት የለውም ብሏል፡፡
በቢሾፍቱ ከተማ የኢዜማን እንቅስቃሴ የሚገድቡ ተግባራት በከተማ አስተዳደሩ በተደጋጋሚ ሲፈፀሙ መቆየታቸውን ስብሰባዎች ለማካሄድና ጽ/ቤት ለመክፈት ተቸግሮ እንደቆየ የጠቆመው የፓርቲው መግለጫ፤ ችግሮችን ከማጉላት ይልቅ በውይይት ለመፍታት ጥረት ማድረጉን ቢመርጥም ጉዳዩ በአመራር አባሉ ግድያ መቋጨቱን አስገንዝቧል፡፡
ሟች አቶ ግርማ ሞገስ ላይ በመንግስትና በፓርቲ መዋቅር ውስጥ ባሉ ግለሰቦች ተደጋጋሚ ዛቻ ይደርሳቸው እንደነበር የገለጸው  ኢዜማ፤ በዚህና ሌሎች ለፓርቲው እንቅስቃሴ እንቅፋት በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ከከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ጋር ለረቡዕ የካቲት 10 ቀን 2013 ቀጠሮ ተይዞ ባለበት ሁኔታ የቢሾፍቱ ከተማ የኢዜማ አስተባባሪው አቶ ግርማ ባለፈው መገደላቸው፣ ይህም “ግድያው ፖለቲካዊ ነው” ወደሚል ድምዳሜ እንደወሰደው ኢዜማ አስታውቋል፡፡
“የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ ሃላፊ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፤ ሟች አቶ ግርማ ሞገስ የኢዜማ አባል እንደሆኑ እንደማያውቁ በመካድ፣ የግድያውን አቅጣጫ ለማስቀየር የሄዱበት ርቀት እንዳስገረመውና እንዳሳዘነው ፓርቲው ጠቁሞ፤ ከዚሁ በፊት በከተማው የፓርቲው እንቅስቃሴና  አባሎች ላይ ሲደርስ ከነበረው ወከባና እንግልት ጋር ተዳምሮ ግዲያው የተቀነባበረ ነው ብሎ እንዲያምን እንዳስቻለው ገልጿል ፓርቲው ብሏል ኢዜማ በመግለጫው፡፡
መንግስት ለሟች አባሉ ተገቢውን ፍትህ እንዲሰጠው የጠየቀው ኢዜማ፤ ወንጀለኞችን አድኖ በአስቸኳይ ለህግ እንዲያቀርብ፣ቀደም ሲል አቶ ግርማን ጨምሮ በአባሎቹ ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ የሰነዘሩ የፓርቲና የመንግስት የስራ ሀላፊዎችም ላይ ምርመራ እንዲደረግለት ያሳሰበው ኢዜማ፤ የክልሉና የብልጽግና ፓርቲ ሃላፊዎች ግድያውን በይፋ እንዲያወግዙም ጠይቋል፡፡
በተጨማሪም የአቶ ግርማ ሞገስ ግድያ “ፍፁም ፖለቲካዊ ነው ያለው” ኢዜማ፤ ለአመራር አባሉ ማስታወሻ የሚሆን ሃውልት በከተማው ለማቆም ይቻል ዘንድ ቦታ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡
አቶ ግርማ ሞገስ፤ ባለትዳርና የሁለት ህፃናት ልጆች አባት እንደነበሩም የኢዜማ መግለጫ ያመለክታል፡፡Read 12281 times