Saturday, 20 February 2021 00:00

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አንድነቷ የተጠበቀች ኢትዮጵያን ማየት እንደሚመኙ ተናገሩ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

“ህወኃት በዚህ መልኩ ጦርነት መጀመሩ ፍፁም ዕብደት ነው” - ኢሣያስ አፈወርቂ (የኤርትራ ፕሬዝዳንት


           አሁንም በኢትዮጵያ ካለው ብሔር ተኮር ግጭት ዋነኛው ምንጭ ህወኃት ነው ያሉት የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፤ በደርግ መውደቅ ማግስት ክልሎች በብሔር መደራጀታቸውንና አንቀጽ 39 የመገንጠል መብት መደንገጉን በተመለከተ ለአገሪቱ እንደማይጠቅም ለመለስ ዜናዊ ነግሬው ነበር ብለዋል በህገ መንግስቱ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ከመለስ ተጠይቀው እንደነበር በማውሳት፡፡ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ሰሞኑን ከአገራቸው ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት በዚህ ቃለ ምልልስ፤ በተለይ የኤርትራና የኢትዮጵያን የቀድሞ ግንኙነት ፣ ከለውጡ በኋላ ስለተፈጠረው አዲስ ወዳጅነት ስለ ህውሃት ጦር መስበቅ፣ ስለ ምስራቅ አፍሪካ አካባቢና የተደቀኑበት አደጋዎች ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ባለፉት ጥቂት ወራት በትግራይ የተከሰተው ሁኔታ ያልተጠበቀና ህውሃት በፍጹም እብደትና ጀብደኝነት የጀመረው ጦርነት መሆኑን ያስገነዘቡት ፕሬዝዳቱ፤ ኤርትራ የጦርነቱ አካል እንድትሆን ከህውሃት በኩል ሮኬቶችን በማስወንጨፍ ሙከራ መደረጉን አውስተዋል። ወታደሮቻቸው በጦርነቱ ስለመሳተፍ አለመሳተፉ ግን ፕሬዝዳቱ ያሉት ነገር የለም።
ለጦርነቱ መነሻ የሆነው ህውሃቶች በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መፈጸማቸው መሆኑን ያወሱት ፕሬዝዳንቱ ከቀድሞ የክልሉ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል ጋር በተገናኙበት አጋጣሚም ጦርነት ለትግራይ ህዝብ ጠቃሚ አይደለም ብዬ ነግሬዋለሁ። ነገር ግን ባልታሰበ ሁኔታ ጦርነቱን አፈነዳ ብለዋል። እንዴት እንደዚህ አይነት ድርጊት እንደፈጸሙ ለማወቅ ጊዜ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። ህውሃት አንዱ አላማው በኤርትራ የመንግስት ለውጥ ማካሄድ እንደነበርም ጠቁመዋል ኢሳያስ አፈወርቂ።
መንግስታቸው በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እጁ ረዝሟል ለሚለው ሃሜትም ፕሬዚዳንቱ ሲመልሱ እኛ በኢትዮጵያ ክልሎች  ጣልቃ ገብተን ማበጣበጥ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ነው የሚያመዝንብን። እዚያ  ያለው እሳት ጊዜ ሊፈጅ ይችላል እንጂ ለኛም መትረፉ አይቀርም፤ ስለዚህ በቀጠናው ሰላም እንዲፈጠር ብቻ ነው የምንሰራው ብለዋል።
ከጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ ጋ መልካም ግንኙነት እንዳላቸው የተናገሩት የኤርትራው መሪ፤ ዶ/ር ዐቢይ ለሁለቱ ሀገሮች በጣም ተስፋ ሰጪ ሃሳቦች ይዞ የተነሳ ነው፤ ይህንን መልካም ሃሳብ በችኮላ ሳይሆን በተረጋጋ ሁኔታ ነው ፍጻሜውን የምናየው ብለዋል።
በድንበር ጉዳይም ቢሆን የሚያስቸኩለን ነገር የለም፤ ከድንበር በላይ የቀጠናው መረጋጋትና ሰላም ነው የሚያስፈልገን ያሉት ፕሬዝዳንት ኢሣያስ፤ በዚህ ሪገድ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በጣም  የተረጋጋና ብስለት የተሞላው ፍላጎት ነው እያሳየን ያለው ብለዋል። ከሁለት ዓመት በፊት ትግራይን ከኤርትራ በሚያገናኘው የኦምሃጅር ድንበር መክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ከትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል ጋር እንደተገናኙ ጠቁመው፤ ለምን ለአላስፈላጊ ጦርነት ዝግጅት እንደሚያደርጉ እንደጠየቋቸው ተናግረዋል።
በወቅቱም ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር እንጂ ከክልል ትግራይ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት ማድረግ እንደማትችል ማስገንዘባቸውንና ህውሃቶች ለአካባቢው ሰላም ቅድሚያ ሰጥተው እንዲሠሩ ማሳሰባቸውን አስታውቀዋል ፕሬዝዳንቱ።
ነገር ግን ህውሃት የተከፈተው ድንበር ተመልሶ እንዲዘጋና በሁለቱ ሃገራት መካከል የተጀመረው መልካም ግንኙነት እንዳይሰምር እንቅፋት ለመሆን ሲሰራ መቆየቱን በመጠቆም ወቅሰዋል።
መንግስታቸው በአንፃሩ፣ ከኢትዮጵያ ጋር የተደረገው የሰላምና የወዳጅነት ስምምነት ለአካባቢው ጠቃሚ መሆኑን በመገንዘብ፣ ለኤርትራ የተወሰነው ድንበር ተግባራዊ እንዲሆን ከመግፋት ይልቅ ቀዳሚ ያደረገው የሰላም ሂደቱና ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲጠናከር  ማድረግ እንደነበረም ኢሳያስ ተናግረዋል።
አንድነቷ የተጠበቀች ኢትዮጵያን ማየት እንደሚሹ የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ  በደርግ ውድቀት ማግስት ክልሎች በብሄር መደራጀታቸውንና አንቀጽ 39 የመገንጠል መብትን መደንገጉን በተመለከተ ከወቅቱ የሃገሪቱ መሪ መለስ ዜናዊ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን አካሄዱ ጠቃሚ አለመሆኑን እንደገለፁላቸው በቃለ ምልልሳቸው ላይ አውስተዋል።
“አሁን በኢትዮጵያ ላለው ብሄር ተኮር ግጭትም ዋነኛው ምንጭ ህውሃት ነው” ያሉት ፕሬዚዳንቱ አሁን በስራ ላይ ያለው ህገ-መንግስት  በተለያዩ ክልሎች ውስጥ የተጠመዱና ጊዜ እየጠበቁ የሚፈነዱ ቦንቦች የሚያጠምድ በመሆኑ አገሪቱን ወደ ግጭትና መበታተን የሚወስድ ነው ብለዋል-። ሊቢያ፣ የመን፣ ሶርያና ኢራቅ ያጋጠማቸውንና አሁን ያሉበትን ሁኔታ በምሳሌነት በመጥቀስ።
ፕሬዚዳንቱ በዚህ ዘለግ ያለ  ቃለ-ምልልሳቸው፤ በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል ስላለው የድንበር ውዝግብ ፣ ስለ ህዳሴው ግድብና ሁኔታም የሁሉንም ሃገራት ጥቅም ባማከለ መልኩ መፍትሄ  መፈለግ እንደሚገባና የቀጠናውን ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ ቀዳሚው ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።


Read 10144 times