Print this page
Wednesday, 17 February 2021 00:00

ፈጣን ልጆች፤ ቀርፋፋ ወላጆች

Written by  ኢ.ካ
Rate this item
(1 Vote)

   ዛሬ ጽሑፌን አንድ የሥራ ባልደረባዬ ባወጋኝ ገጠመኝ ነው የምጀምረው። ባልደረባዬ ቤት ውስጥ አንድ ትንሽዬ ልጅ አለ- የ4 ዓመት። የእህቱ ልጅ ነው። ይሄ ህፃን አንድ ልማድ አለው። ጠዋት ከቤተሰቡ ሁሉ ቀድሞ ይነቃና በባዶ እግሩ ከአንዱ መኝታ ክፍል ወደ ሌላኛው እየሮጠ፣ የተኛውን ሁሉ ይቀሰቅሳል ወይም እንቅልፍ ይነሳል። ባልደረባዬ (የህፃኑ አጎት ማለት ነው) ይህን አልወደደለትም። እናም ሁለተኛ እንደዚህ እንዳያደርግ ያስጠነቅቀዋል። ለጥቂት ቀናት ህፃኑ በማስጠንቀቂያው መሰረት ሁሉም እስኪነቃ አልጋው ላይ ማርፈድ ጀመረ። ከጥቂት ሳምንት በኋላ ግን አንድ ማለዳ ላይ ፣ አንደኛው መኝታ ክፍል ውስጥ እንደ ቀድሞው በባዶ እግሩ ሲንጎዳጎድ አጎቱ ደረሰበት።
“ለምን ከእንቅልፍህ ተነሳህ?” አለና ጠየቀው አጎቱ።
ይሄ የ4 ዓመት ልጅ ከመቅጽበት “ልስምህ!” አለውና አፉን ወደ አጎቱ አሞጠሞጠ። የሥራ ባልደረባዬ፣በህፃኑ ምላሽ ተገርሞ ተሳመለትና፣ ተመልሶ ወደ አልጋው እንዲወጣ ነገረው። አያችሁልኝ… የዚህን ጨቅላ ህፃን ብልሃት ፣ ከመቅጽበት በፈጠረው ብልሃቱ ከቁጣ ዳነ።
ይሄን ገጠመኝ ያስቀደምኩት የዘመኑን ልጆች ፈጣንነት ለማሳየት ያህል ነው። በርግጥ ይሄ መጣጥፍ ትኩረቱን ያደረገው በአንዳንድ ወላጆች ዙሪያ ነው። እናም  ምክር ያስፈልጋቸዋል ባልኳቸው ወላጆች ዙሪያ ሰሞኑን የገጠመኝን አወጋችኋለሁ። ወደዚያ ከመግባቴ በፊት ግን  የአንድ ሌላ ትንሽ ልጅን ታሪክ  ልመርቅላችሁ። መቼም የልጆች ነገር ይጥማል ብዬ ነው።
የ5 ዓመት ህፃን ልጅ ነው። መኝታ ክፍሉ ውስጥ ቋንጣ ተሰቅሏል። ልጁ ቋንጣው ቢያምረውም እናቱን መጠየቅ አልደፈረም። በሆዱ ግን አንድ ነገር አስቧል። አንድ ማታ ታዲያ እራት ተበልቶ ሁሉም ይተኛል። የእናትና የልጅ መኝታ ክፍል አንድ ቢሆንም፣ አልጋቸው የተለያየ ነው። እናት ልጇን ስማ መብራቱን አጠፋችና ተኙ። ብዙም ሳይቆዩ ግን ኮሽታ ተሰማ። እናት ምን መጣ ትልና መብራቱን ታበራለች። ያየችውን ግን ማመን አቃታት፡፡ አልጋው ላይ ቆሟል- ህፃኑ። ልጁ ደግሞ  የቋንጣው ገመድ ላይ ነው። እናት በድንጋጤ፣ “አንተ ምን እየሰራህ ነው?” ህፃኑም እየተኮላተፈ … እየቆጠርኩኝ”አላት. ቋንጣውን መሆኑ ነው። እናት ሳቀች እንጂ አልተቆጣችውም።
“አይገርምም የህፃኑ ብልሃት! በእኔ የልጅነት ዘመን ጥፋት ፈጽመን  ለቤተሰቦቻችን ስለምንሰጠው ሰበብ እንዴት እንደምንጨነቅ ትዝ ይለኛል። ለዚያውም እንዲህ ወላጅን የሚያሸንፍ ምክንያት ከቶውንም አይመጣልንም። የዛሬ ልጆች ግን እንዲህ ፈጣን ሆነዋል። በስለው የሚወለዱ እስኪመስለን ድረስ። ህፃናቱ ቶሎ መብሰላቸው ቶሎ መንቃታቸው፣ ቶሎ መምጠቃቸው እሰየው ነው። ግን ደግሞ መሪ ያስፈልጋቸዋል። በበጎ ስነ-ምግባር የሚመራቸው። ደጉንና ክፉው እንዲለዩ የሚያስተምራቸው። ከፍጥነታቸው እኩል የሚራመድ። ይሄን በቃዳሚነት የሚያደርጉላቸው ደግሞ ወላጆቻቸው ናቸው። አንዳንድ ጊዜ ግን ከልጆቻቸው ያነሰ የሚታያስቡ ጨቅላ ወላጆች (Immature parents) ያጋጥሙንና ተስፋ እንቆርጣለን።
ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ መነሻ የሆኑኝን ክስተቶች ልንገራችሁ። በቅርቡ አንድ ግሮሰሪ ውስጥ ምሳ እየበላን ነበር። ከጓደኞቼ ጋር። ፊት ለፊታችን ባልና ሚስት ከህፃን ልጃቸው ጋር ይታዩናል። ባል ቢራ ይጠጣል። ሚስት ለስላሳ ይዛለች። አባትየው ከቢራው ጠርሙስ  ወደ ልጁ ብርጭቆ ሲቀዳ አይተን ሁላችንም በድንጋጤ አፈጠጥን። ልጅ አንስቶ ተጎነጨነውና ፊቱን አኮማተረ። በቢራው ምሬት። ማንም ግን “ተወው፣ ይቅርብህ” አላለውም። እናት ይባስ ብላ ከለስላሳዋ ጨመረችለት መጎምዘዙ እንዲቀንስለት። ይህን ጊዜ ህፃን ተደላድሎ የቢራና የለስላሳ ብርሙሱን መጠጣት ጀመረ።
አስቡት… ይህ ልጅ ቢበዛ ሰባት ዓመት  ቢሆነው ነው። ወላጆቹ ግን ገና በሰባት ዓመቱ ከቢራ ጋር በግድ እያለማመዱት ነው። ከሁሉም የገረመኝ ደግሞ ከሁለት አንዳቸው እንኳን ይሄን ጉዳይ መቃወም አለመቻላቸው ነው። “ባልና ሚስት ከአንድ ወንዝ ይቀዳሉ” ማለት እንዲህ ይሆን እንዴ?
እኔና ጓደኞቼ ከግሮሰሪው ከወጣን በኋላም ስለ ጉዳዩ ማውራቱን ቀጠልን፡፡ አንደኛው ጓደኛችን እነዚህን ወላጆች “ወላጅጆች መሆን የማይገባቸው” በማለት  ሲወቅሳቸው፣ ሌላው ጓደኛችን ግን ወቀሳው በቂ አይደለም በማለት “አሁን እነዚህ ወላጆች መታሰር የለባቸውም?” ሲል ጠየቀን።
እውነት አለው። በሰለጠኑት አገራት እኮ ከ18 ዓመት በታች የሆነ ወጣት መጠጥ ቤት እንዲገባ አይፈቅድለትም። እኛ አገር እሱ ቢቀር እንኳ ህፃናትን መጠጥ ቤት ይዘው የሚገቡ ወላጆችን የሚጠይቅ ህግ ሊኖር በተገባ ነበር።
ባልና ሚስቱ የፈፀሙት ድርጊት ምክንያት ሆኖን የተለያዩ ገጠመኞችን ማውጋት ቀጥለናል። ሌላኛው ጓደኛችን ስለሚያውቀው አንድ  የሰፈሩ ልጅ ማውራት ጀመረ። ልጁ ጠጅ አድናቂ ነው። በየምሽቱ ጠጥቶ ሳይሆን ተነክሮበት ነው ወደ ቤቱ የሚገባው። ጠጅ መጠጣት እንዴት እንደ ጀመረ ጓደኞችን ጠይቆት የሰጠው ምላሽ ከአጀንዳዬ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ይሄን ልጅ አባቱ በህፃንነቱ ጠጅ ቤት ይዘውት ይሄዱ ነበር። እሳቸው ከሚጎነጩት ጠጅም በጣታቸው እየነከሩ ምላሱ ላይ ጠብ ጠብ እያደረጉለት ነው ያደገው  -እንደ ጡጦ። ልጁ ከጠጅ ጋር  ያለው  ትውውቅ ይህንን ይመስላል። ዛሬ ታዲያ ልጁ የለየለት  የጠጅ ደንበኛ  ሆኗል። ታዲያ እንዲህ ያለውን ወላጅ በህግ መጠየቅ ምን ነውር አለው? መቼም “በገዛ ልጄ ምን አገባህ?” በሚል ተልካሻ ምክንያት ሊከራከር አይችልም- ምክንያቱም ዜጋም እያበላሸ ነውና።
ካዛንቺስ አካባቢ ደግሞ ያየሁትን እነሆ። አንድ ጸጉራቸውን ሽበት የወረሰው ሽማግሌ፣ ከትንሽዬ ልጅ ጋር ቆመዋል። በግምት 5 ዓመት ይሆናታል- ህጻኗ። “ታዲያ ቢቆሙ ምን አለበት” እንዳትሉኝ። ሽማግሌው የቆሙት እኮ ታክሲ ለመሳፈር አይደለም። መንገድ እየተሻገሩም እንዳይመስላችሁ። ሱቅ መስኮት ላይም አልነበሩም። ሽማግሌው ከልጅቱ ጋር የቆሙት ጫት ቤት በር ላይ ነበር፤ ጫት ለመግዛት- ከትንሿ የ5 ዓመት ልጃቸው ወይም የልጅ ልጃቸው ጋር። አሁን እኚህ ወላጅ ጤነኛ ናቸው? አላየንም እንጂ እኚህ ሰውዬ ማታ ደግሞ ይቺኑ እንቦቀቅላ ይዘው ለጨብሲ ከመውጣት የሚመለሱ አይመስለኝም። እንዲህ ያሉት ወላጆች ህግ እስኪወጣ ቢያንስ ምክር ያስፈልጋቸዋል እላለሁ፤ ከተቻለም ማስጠንቀቂያ!!
ሌላ ምሳሌ ደግሞ ላክል። አንድ የቅርብ ወዳጄ የነገረችኝ ነው። አንዲት እናት፤ የ6 ዓመት ህፃን ልጇን በአንድ ሩቅ የኮሚኒቲ ት/ቤት ውስጥ ታስተምረው ነበር። ለአንድ  ዓመት ከተማረ በኋላ ግን አስወጥታ ሌላ ት/ቤት አስገባችው። ምክንያቱን ጠየቅኋት።
“ልጄን እንዳይበላሹ ብዬ ነው” አለችኝ።
    “እንዴት ማለት?”    
“በየቀኑ የኪስ ገንዘብ ካልሰጠሽኝ ት/ቤት አልሄድም እያለ አስቸገረኝ።”
“የምን የኪስ ገንዘብ?”
“በቃ የኪስ ገንዘብ ነዋ!”
የ6 ዓመት ልጅ ምን ዓይነት የኪስ ገንዘብ እንደሚፈልግ በማሰላሰል ተጠምጄ፡
“ለመሆኑ ምን ያህል ስጪኝ ይላል?”  አልኳት።”
“100 ወይም 200 ብር”
“ምን? ለመሆኑ በዚህ ብር ህፃናቱ ምን ያደርጉበታል?”
ምን አውቃለሁ በሚል ጭንቅላቷን ነቀነቀች። ይህቺ ወዳጄ እንደ ነገረችኝ፣ እዚህ ት/ቤት ህፃናቱ ይዘው የማይመጡት ነገር የለም። ዲጂታል፤ ካሜራ፣ ቪዲዮ ካሜራ፣ አዳዲስ የሆሊውድ ዲቪዲ ፊልሞች ወዘተ… አንዳንዴም ዶላሮች ይዘው ይመጣሉ። ከዚያ እርስ በርስ ፉክክር ይገባሉ። ለዚህ ነው ወዳጄ የልጇን ት/ቤት  የቀየረችው።
አንድ የስነ-ልቦና ባለሙያ እንደ ነገሩኝ፣ ለልጆቻቸው ያልተገባ ገንዘብ የሚሰጡ ወላጆች በተለያዩ ምክንያቶች ለልጆቻቸው ፍቅር መለገስ ያልቻሉ ናቸው። እንዲህ ያሉ ወላጆች ያጎደሉትን ፍቅር በውድ ቁሳቁሶችና በብዙ ገንዘብ ለማካካሰ ይሞክራሉ የሚሉት ባለሙያው፤ ይሄ ግን ፍቅርን አይተካም ባይ ናቸው። አንድ ያነበብኩት መጽሐፍ (“The last lecture” የሚል) አንዳንድ ነጠላ ወላጆችም (Single parents) ለልጆቻቸው የተለያዩ ቁሳቁሶችና ገፀ-በረከቶች በማጉረፍ ህጻናቱ  ያጡትን የወላጅ ፍቅር ለመተካት ይሞክራሉ የሚል ነገር አንብቤአለሁ። ይሄ ግን ህፃናቱ  እንደ እሴት በሚያስቡት ነገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል -ይላል መጽሐፉ።
እኔ መቼም ለህጻናት ልጆቻቸው ይሄን ያህል ብር እየሰጡ ወደ ት/ቤት የሚሸኙ ወላጆች ትክክል አይመስሉኝም። ሃላፊነት የሚሰማቸው ናቸው ለማለትም አያስደፈፍርም። የገንዘብ አያያዝን ለማስለመድ ነው የሚል ወላጅ አይጠፋም። ይሄ ግን ተቀባይነት የለውም። የህፃናቱ ዕድል ለዚያ አልደረሰማ። የገንዘብ አያያዝ ለማስተማር ከሆነም እየተመጠነ ተሰጥቷቸው አጠቃቀሙን እንዲጨምሩ ማድረግ ይሻላል። እና ስላላቸው ብቻ ለልጆቻቸው መቶና ሁለት መቶ ብር “የኪስ” እየሰጡ ት/ቤት የሚልኩ ወላጆችም  ለልጆቻቸው ከሚያጠጡ፣ ልጆቻቸው ፊት  ሲጋራ ከሚያጨሱ፣ ከልጆቻቸው ጋር ጫት ቤት  ከሚሄዱ ወላጆች ፈጽሞ የሚለዩ አይመስለኝም። እነሱም ምክር ያስፈልጋቸዋል። በጽሑፉ መጀመሪያ ላይ  በሁለት ሁነቶች ለማሳየት እንደሞከርኩት፤ ህጻናቱ ከዕድሜያቸው ልቀዋል። በሃሳባቸው ፈጥነዋል። ግን ወላጆችስ? ከህፃናት ልጆች ጋር ቁጭ ብለው ለህፃናት የማይመጥን  ፊልም የሚመለከቱ ወላጆች አልገጠሟችሁም? ልጆቻቸው  ፊት የቤት ሰራተኛን ሙልጭ አድርገው የሚሳደቡስ? ህጻናትን አስቀምጠው ሚስቶቻቸውን የሚደበድቡ አባወራዎችስ? እንዲህ ያሉት ወላጆች ተቀድመዋል። ፈጣን ልጆች፤ ቀርፋፋ ወላጆች ያልኩትም ለዚህ ነው። እኔ በአካል በየቤቱ  ወላጆቻቸውን ቁጭ አድርገው  የሚመክሩ ህጻናቶች  ይኖራሉ የሚል ግምት አለኝ እድል ከተሰጣቸው። ለምን መሰላችሁ? ማናችንም ከምናስበው በላይ ህፃናቱ መጥቀዋል። ምናልባት የዚህን ምክንያት የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች ጥናት አድርገው ሊናገሩ ይችላሉ። አሁን ጥያቄው ሁለቱ እንዴት ይጣጣሙ የሚለው ነው። ከዕድሜያቸው የላቀ የሚያስቡ ህፃናትና ምክር የሚያስፈልጋቸው ወላጆች … እንዴት ይኑሩ? ማን መሪ ማን ተመሪ ሊሆን ነው!
በርግጥ አብዛኛው ቤተሰብ ልጆቹን በስነ-ስርዓት ቀርጾ እንደሚያሳድግ ከሚታየው ጨዋ ኢትዮጵያዊ ባህርይ መረዳት ይቻላል። ምናልባትም ወደፊት  የእንደዚህ አይነቶቹን ወላጆች ምሳሌ የሚሆኑ ማሳያዎችን ይዤ እመለስ ይሆናል፡፡ እስከዛው ግን ወላጆችን በጊዜ መምከር ህፃናቱን ይታደጋል እላለሁ። የነገ ሰው ይበለን!!


Read 8694 times