Sunday, 14 February 2021 00:00

“የሕግጋቱ ድምጽ ይወቅሰኛል”

Written by  ጤርጢዮስ ዘ - ቫቲካን
Rate this item
(0 votes)

   https://youtu.be/kTTahgC6OO8?t=27

"-በፖለቲካውም ኾነ በሃይማኖቱ ጎራ ያሉ ሰዎች የየሠፈራቸውን የሕግጋት ድምጽ በሕሊናቸው የሚሰሙ ቢኾን ኖሮም፣ ዛሬ ላይ ማንም እየተነሳ በግብታዊነት የሚፈነጭባት ሀገር አትኖረንም ነበር ብዬ አስባለሁ።--"
           
          ይኼ ዓለም በሕግ እንጂ በዘፈቀደ የሚመራ አለመኾኑ እሙን ነው። የሰው ልጅም ከመነሻው አሳቢነትን ከሕገ ልቦና ጋር የተቸረው ፍጥረት በመኾኑ የሚተዳደረው በሕግ ነው። ከሥነ መለኮት አንጻር የሕግ ምንጩ መለኮታዊ በመኾኑም በሰዎች ሁሉ ዘንድ  የሞራል ቅቡልነት አለው። ሐዋርያው ጳውሎስ፤ “ሰው ባለበት ዘመን ሁሉ ህግ እንዲገዛው አታውቁምን?” ሲል ሕግ መለኮታዊ መነሻ እንዳለው ይጠቁማል። የሰው ልጅ የምድራዊውና  የሰማያዊው ዓለማት አማካኝ ፍጥረት በመኾኑም አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ መጓዙ ከእውነት መጉደልን ያመላክት እንደኾነ እንጂ ረብ የለውም።  
እጓለ ገብረ ዮሐንስ የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ በተሰኘው መጽሐፋቸው፦ “ሰው በሁለት ዓለማት መካከል የሚገኝ አማካኝ ፍጥረት ነው። በአካሉ የጉልሁ ዓለም ተካፋይ ነው። በመንፈሱ የረቂቁ የዘላቂው ዓለም ተሳታፊ ነው። በሥነ ፍጥረት ላይ የሚጸናው የግዴታ ሕግ በእሱም ላይ ይጸናል። በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ የሚጸናው የነጻነት ሕግ በሱም ላይ ይጸናል። ስለ ሁለቱም ዓለማት አግባብ አለው። ስለዚህ የምርመራውን አቅጣጫ ወደ ሁለቱም ይመራል።” ይላሉ። የፍልስፍና መምህሩ ኢያሱ ባሬንቶ ደግሞ “ሰው የመሆን ጉዞ” በተሰኘው መጣጥፋቸው ለዚህ የእጓለ አስተያየት በሰጡት ማፍታቻ ይህንን ብለዋል፦
“የፍልስፍና ምርመራ ሁለቱንም ዓለማት [ምድራዊውንና ሰማያዊውን] ባንድ ላይ አስተባብሮ በመያዘ ስለ መላው ዓለምና ስለ ሰው ልጆች ይበጃል ያለውን በሕግ ምክንያት የተመሰረተ አስተያየት ያቀርባል።  ሁለቱን ዓለማት በአግባቡ ተረድቶ የዜግነት ግዴታውን የሚወጣበትንና መብቱን የሚያስከብርበትን ሕግጋት ነድፏል ማለት እንችላለን። ሰው የምድራዊና የሰማያዊ ዓለማት ዜጋ ከሆነ ሁለቱን ዓለማት በአግባቡ ተረድቶ የዜግነት ግዴታውን የሚወጣበትንና መብቱን የሚያስከብርበትን ሕግጋት ነድፏል ማለት እንችላለን።” በማለት አብራርተዋል።
በቅርቡ ለንባብ የበቃው የዳዊት በዛብህ “የሕግ ፍልስፍና” የተሰኘው መጽሐፍም፣ የምዕራቡን ዓለም ንጽረተ ዓለም መነሻው አድርጎ  ስለ ሥነ ሕግ  እና የሞራል ፍልስፍና ያለውን ሁለቱንም ዓይነት እይታዎች አቅርቧል። “ሕግ ማለት የሰው ልጆች ለአንድ የተለየ ዓላማ ብለው የሚፈጥሩት ሥርዓት እንጂ በተፈጥሮ የተገኘ ወይም ከፈጣሪ የተሰጠ ዓይደለም” የሚሉትንም ኾነ ሕግ ዘላለማዊና የማይለወጥ ባሕርይ እንዳለው የሚያምኑትን ፈላስፎች  ሃሳብና መሟገቻ ነጥቦች መሳ ለመሳ አቅርቧል።
በመጽሐፉ ውስጥ በአማኝነትም ኾነ ባላማኝነት ጎራ ተሰልፈው ስለ ሞራልና ሕግ ግንኙነት የተነተኑ ፈላስፎችም፤ ነገሮችን በጥልቀት የሚገነዘቡ አሳቢያን የሥነ መለኮት ሰዎችም እንደየ ዕይታቸው ተስተናግደውበታል። ሕግ ከሞራልና ከፍትሕ ጋር ያለው ተዛምዶም በስፋት ተዳስሷል። በአንድ ወገን ኢ - አማኒያኑ የሞራል ህግ እንደ ማንኛውም ባህል ሁሉ በዝግመተ ለውጥ እየተቀየረና እየተሻሻለ የሚሔድ ማኅበራዊ ስምምነት  (Social Contract ) እንደኾነ ማሰባቸውን ሲገለጽ፣ በሌላም በኩል ከዚህ በተቃራኒ የቆመው  ምልከታ  ቀርቧል።
ሕግ ከማኅበረሰባዊ ሞራል እና ልማድ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያለው ብቻ ሳይኾን ውጤታማ ሊኾን  እንደሚገባውም በመጽሐፉ ውስጥ ተገልጿል። ጠንካራ የሕግ የበላይነት እንዲኖር ጥሩ ሕግጋት እንደሚያስፈልጉም ጥቆማ ይሰጣል። የመንግሥት ሥልጣን  የተገደበና  ተጠያቂነት ያለው እንዲኾን የሚያደርገው ህግ መኾኑ ሲጠቀስ፣ የብዙሀን አምባገነንነት የነጻነት ፀር  እንደኾነ የሚናገሩ  ምንባባትም  አሉ። በእርግጥም ደግሞ የሕግ ህልውና  ባልተረጋገጠበት ሁኔታ የሰውን ዓለም ማሰብ ከባድ ነው። ሕግ በሌለበት ሀገር በሰላም ወጥቶ መግባት፣ ዘርቶ ማጨድ፣ ወልዶ ማሳደግ  አይቻልም።
የሰው ልጅ በምድር ላይ ተዘልሎ መቀመጥ ይችል ዘንድ ሕግ ዋና ነገር ነው። ያጠፋ የሚከሰሰውና የሚቀጣው፤ የተበደለ የሚካሰው በሕግ አማካኝነት ነው። ሕግና ፍትህ ከሰው ልጅ ነጻነት ጋር በእጅጉ የተቆራኙ በመኾናቸውም ስለ ሕግ ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነው።  ይልቁንም አሁን ላይ ሕገ ወጥነት ለሚያምሳት፤ ጊዜና ወቅት እየጠበቁ ከየሠፈሩ በሚነሱ የጎበዝ አለቆች እየተናጠች ላለች ሀገራችን  ዘላቂ ሰላም መስፈን፣ ስለ ሕግ አስፈላጊት ብቻ ሳይኾን ስለ ዋጋው  ማወቅ ግድ ይለናል።
የሕግ ባለሙያው ዳዊት በዛብህ፣ “የሕግ ፍልስፍና” የተሰኘ መጽሐፍ ደግሞ በዚህ ረገድ ያለብንን የእውቀት ክፍተት የሚሸፍን ኾኖ አግኝቼዋለሁ። ስለ ሕግ ባላቸው ጥልቅ ግንዛቤ  በመጽሐፉ ውስጥ ዋቢ ከተደረጉ በርካታ ፈላስፎችና አሳቢያን መካከል ለሕግ የበላይነት ትልቅ ትምህርት ከመስጠቱ አንጻር የሶቅራጥስን  የሕይወት ፍጻሜ  የሚመለከተውን ክፍል በተሞክሮ የተፈተነ ስለሆነ በምሳሌነት ልጠቅሰው ወድጃለሁ፡፡  
ታሪኩ ባጭሩ እንዲህ ነው። “ሶቅራጥስ ከ470-399 ዓመተ ዓለም የኖረው የግሪክ ፈላስፋ ሲኾን ሰውዬው በዘመኑ የነበረውን ያኗኗር ዘይቤ ክፉኛ በመተቸት ይታወቃል። ራሱን “የአቴናን ጃጃታምነት ለማንቃት ከመለኮት ዘንድ የተላክሁ ተናዳፊ ተርብ ነኝ” ይልም ነበር።  ይሁንና እንዲህ ዓይነቱ ነገር ያልተመቻቸው የሀገሬው ሰዎች በተቃውሞ ይነሱበታል። “የወጣቱን አእምሮ አበላሽተሀል፣ አማልክቱን ተሳድበሀል” የሚሉ ክሶች አቅርበውበትም የሞት ፍርድ ይበየንበታል። ይሁንና በፍርዱ ኢ-ፍትሐዊነት ያልተስማሙ ደቀመዛሙርቱ ሶቅራጥስን ከእሥር ቤት ሊያስመልጡት በመሻት  የዘየዱትን መላ በቅርብ ባልንጀራው በኩል ያስታውቁታል።  የሶቅራጥስ ምላሽም እምቢታ ይኾናል። የተፈረደበት ሞት ኢ-ፍትሐዊ መኾኑን ቢያውቅም ከእሥር ቤት ማምለጡ ግና የባሰ ሕገ ወጥነትና  ኢ-ፍትሐዊ መኾኑን በማስረዳት አሻፈረኝ ይላል።  
ሶቅራጥስ በአቴና አደባባይ ከአምሥት መቶ የሚልቁ አባላት ባሉት ሸንጎ ፊት ቀርቦ የቀረበበትን ክስ እንዲከላከል እድል ተሰጥቶት እንደነበር የሚተርከው “የሕግ ፍልስፍና” መጽሐፍ፤ ዝርዘሩን በሚከተለው መልኩ አስቀምጦታል፦ “በዚህም ወቅት [ሶቅራጥስ] ራሱንና ፍልስፍናውን በሚገባ የተከላከለ ቢኾንም ኢ-ፍትሐዊ በኾነ መንገድ የሞት ፍርድ ተጣለበት። ሶቅራጥስ በእሥር ቤት ኾኖ የሞት ፍርዱ የሚፈጸምበትን ቀን እየተጠባበቀ ሳለ ፍልስፍናውን በሚያስተምርበት ወቅት የሚያውቁት ባለሀብቶች ወደ ሌላ ከተማ ሊያስመልጡት ሴራ ጠነሰሱ። ይህንንም  እቅድ ክሪቶ የተባለ የሶቅራጥስ ወዳጅ ለሶቅራጥስ  በመንገር አሳምኖት ከወህኒ ቤት እንዲያስመልጠው በማሰብ ልከውት ነበር።”
“በመኾኑም አንድ ቀን ክሪቶ ራሱ ሶቅራጥስ ወዳለበት የወህኒ ክፍል ከጥበቃው ጋር ተመሳጥሮ በመግባት ይህንኑ ሃሳብ ይነግረዋል። ሶቅራጥስና ክሪቶ በዚያች አነስተኛ ክፍል ውስጥ የሚያደርጉትን ውይይት አፍላጦን ‘ክሪቶ’ በሚለው አስደናቂ ድርሳን ውስጥ በዝርዝር አስፍሮታል። ክሪቶ ያቀረበለትን ሃሳብ ሶቅራጥስ ሙሉ ለሙሉ ያልተቀበለው በመኾኑ ክሪቶ ሶቅራጥስን እስከ መለመን ደረጃ ደርሶ ነበር። ሶቅራጥስ ሚስትና ልጆች ስላሉት ለእነሱ እንኳ ብሎ ሕይወቱን እንዲያተርፍ፣ ኢ-ፍትሐዊ በኾነ መንገድ የከሰሱት ሰዎችም በእኩይ ተግባራቸው ተደስተው እንዳይኖሩና የአቴንስ ሕዝብ ልብም እንዳይሰበር በማባበል ይጠይቀዋል።”
“ሶቅራጥስ የተላለፈበት የሞት ፍርድ ኢ- ፍትሀዊ መኾኑን ቢያውቅም ከእሥር ቤት ማምለጡ ግን የባሰ ሕገ ወጥነት እና ኢ-ፍትሐዊ መኾኑን ለክሪቶ ለማስረዳት ይሞክራል። በአቴንስ ከተማ በኖረበት ሰባ አመታት  የአቴንስ ሕግጋት እንቅፋት ኾነውበት እንደማያውቁ፣ እንዲያውም ራሱን በፈቃዱ አስገዝቶ የኖረ እንደነበር ያወሳል። ሕግጋቱ የተለያዩ ቢኾኑም በአንድ ሥርዓትና ሰብዕና የታቀፉ እንደመኾናቸው ድምጻቸውን ጥርት ባለ መንገድ እንደሚሰማና ከድቷቸው ቢሸሽ እንደሚወቅሱት ጭምር ይናገራል። በአቴንስ ከተማ ይህን ሁሉ ዓመታት ሲኖር በማወቅም ኾነ ባለማወቅ ከሕግጋቱ ጋር ውል እንደፈጸመና እስከ ዛሬ ድረስ መብቱን እየጠበቁ እንዳኖሩት፣ አሁን ግን በጥቂት ሰዎች ሴራ አማካኝነት ከሕግጋቱ ጋር የፈጸመውን ውል ሊያፈርስ እንደማይገባ እየደጋገመ ለክሪቶ ይነግረዋል። (ገጽ 11-13)
“የሕግ ፍልስፍና” መጽሐፍ ደራሲ ዳዊት በዛብህ፣ “የሕግጋቱ ድምጽ ይወቅሰኛል” የሚለውን ይህን የሶቅራጥስ አባባል የተለያዩ ፈላስፎች አስፋፍተውት በመንግሥትና በሕዝብ፣ በመንግሥትና በግለሰብ መሀል የሚደረግ ውል መኾኑን ለማስረዳት እንደተጠቀሙበትም ገልጿል። እኔ ደግሞ ይህ አባባል ለማኅበራዊውና ፖለቲካዊው ሠፈራችን ብቻ ሳይኾን ለሃይማኖቱም መንደራችን ትልቅ መልዕክት እንዳለው ይሰማኛል። በፖለቲካውም ኾነ በሃይማኖቱ ጎራ ያሉ ሰዎች የየሠፈራቸውን የሕግጋት ድምጽ በሕሊናቸው የሚሰሙ ቢኾን ኖሮም፣ ዛሬ ላይ ማንም እየተነሳ በግብታዊነት የሚፈነጭባት ሀገር አትኖረንም ነበር ብዬ አስባለሁ።
የዛሬን አያድርገውና ኃይለማርያም ይርጋ፤ “የሕግ የበላይነት” በተሰኘ  መጣጥፉ ስለ ቀደመው ዘመን ልምዳችን ሲገልጽ ፦ “የኛ ሰው ፀብ የለሽ በዳቦ የሆነ አምባጓሮ ሲገጥመው፣ ንብረቱ ሲደፈር፣ ቃል አባይ በሆነ ሰው ሲከዳ፣ በመንግሥት አካላት ሆነ በግለሰብ መብትና ጥቅሙ ያለ አግባብ ሲገፈፍ ፍትህ በ’ጄ’ ብሎ መብቱን በሃይል ከማስከበር ይልቅ ‘በህግ አምላክ’ ብሎ እማኝ ቆጥሮ ጉዳዩን ወደ ባህላዊ ፍርድ ሰጪ ወይም ህግ አስከባሪ አካል ወይም መደበኛ ፍርድ ቤት ይዞ በመሄድ መብቱን የማስከበር አኩሪ ባህል አለው” ይለናል።  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግዘፍ ነስቶ የሚስተዋለውና አሁንም ድረስ ብቅ ጥልቅ እያለ ሰላማችንን የሚያውከን ግና የግለሰቦችና የቡድኖች  ፍላጎት እንጂ የሕግ የበላይነት ዓይደለም።
እነሆ “የሕግ ፍልስፍና” የተሰኘውን ወቅታዊ መጽሐፍ የሚያነብብ ሰው ሕግን በተመለከተ ጥሬ አተገባበሩን ብቻ ሳይኾን ከነገሩ ጀርባ ያለውን ጥልቅ ፍልስፍናዊ ዕይታና ነባራዊ እውነታ ለመመልከት፣ የነገሩን ውል በቅጡ ለመረዳት ዕድል ያገኛል። የደራሲው የቃላት አጠቃቀምና የሀሳብ ፍሰት የተዋጣለት በመኾኑም ለንባብ ይመቻል። በየመሀሉ የሚገኙ ጸናን የፍልስፍና ሃሳቦችም ውስጥን ሰቅዘው በመያዝ ያመራምራሉ። የመጽሐፉ ደራሲ ዳዊት በዛብህ፣ ከባድ የሚመስለውን ፍልስፍናዊ ርዕሰ ጉዳይ አቅልሎ፣ ውስብስቡን ዕሳቤ በቋንቋችን አፍታቶ ስላቀረበልንም ትልቅ ምሥጋና ይገባዋል።


Read 4999 times Last modified on Thursday, 25 February 2021 19:58