Saturday, 13 February 2021 12:30

የልጅ ሚካኤል “አትገባም አሉኝ” አዲስ አልበም ለአድማጭ ሊቀርብ ነው

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(3 votes)

 በዓለም ላይ  እጅግ ተወዳጅ ከሆኑትና በሀገራችንም ከልጅ እስከ አዋቂ ተቀባይነት እያገኙ ከመጡት የሙዚቃ ስልቶች አንዱ በሆነው የሂፕ ሆፕ ስልት ተቀባይነትን ያገኘው ድምጻዊ ሚካኤል ታዬ (ልጅ ሚካኤል) ሁለተኛ ሥራ የሆነው “አትገባም አሉኝ” አዲስ አልበም ማክሰኞ ለአድማጭ ይቀርባል።
የአልበሙ ፕሮሞተር “አሜዚንግ ፕሮሞሽንና  ኤቨንት” በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እዳስታወቀው ይህ አልበም 15 ዘፈኖችን የያዘ ሲሆን ግጥምና ዜማው በኢዮኤል ብርሃኑና በራሱ በልጅ ሚካኤል (ፋፍ) እንደተሰራም ታውቋል።
ድምጻዊው በግጥሞቹ አገርን፣ ባህልን፣ አንድነትንና ፍቅርን ለማንፀባረቅ እንደሞከረ የተገለጸ ሲሆን አቀናባሪው በቅርቡ “ሸግዬ ሸጊቱ” በተሰኘው ሙዚቃው ተወዳጅነትን ያተረፈውና በስቱዲዮ ስራ ከ10 ዓመት በላይ የሰራው ዮናስ ነጋሽ ሲሆን ሂፕ ሆፕ በማቀናበር የመጀመሪያው የሆነውን የልጅ ሚካኤልን አልበም  ሁሉንም  በማቀናበር አሻራውን አሳርፏል ተብሏል።
ድምፃዊ ሚካኤል ታዬ (ልጅ ሚካኤል) በሀገራችን እየተወደደ የመጣውን የሂፕ ሆፕ የሙዚቃ ስልት በ2008 ዓ.ም ባወጣው የመጀመሪያ አልበሙ ይበልጥ እንዲወደድ በማድረግና በግጥሞቹ ባህሉን፣ ወጉንና የሀገሩን እሴቶች በመግለጽ የዝናና እውቅናን ማማ መቆናጠጡ አይዘነጋም። ልጅ ሚካኤል የመጀመሪያ አልበሙን ማውጣቱንና ተቀባይት ማግኘቱን ተከትሎ በአውሮፓ፣ በአሜሪካና በሌሎች ዓለማት ኮንሰርቶችን በመስራት የኢትዮጵያን ሂፕ ሆፕና ኢትዮጵያን በስፋት ማስተዋወቅ የቻለ ሲሆን ከተለያዩ ዓለማት የሙያ አቻዎቹ ጋር በጋራ የመስራት አድልም ገጥሞታል።
ልጅ ሚካኤል የመጀመሪያ አልበሙን ከሰራ ከአምስት ዓመታት  በኋላ ሁለተኛ ስራውን በተለየ ጥራትና ከፍታ ይዞ መምጣቱን በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የገለጸ ሲሆን የፊታችን ማክሰኞ ለአድማጭ ይቀርባል ተብሏል።


Read 13657 times