Saturday, 13 February 2021 12:28

ሁሉንም ሽልማቶች ጠራርጋ የወሰደችው ተመራቂ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

    “እናቴን አይዞሽ ደርሼልሻለሁ እላታለሁ”
ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ ለ12ኛ ጊዜ ባለፈው ቅዳሜ ጥር 29 ቀን 2013 ዓ.ም በዋናው ግቢ 5ሺ 310 ተማሪዎችን በመጀመሪያ በሁለተኛና በስፔሻሊቲ ዲግሪ ሲያስመርቅ፤ ሰኞ የካቲት 1 ደግሞ በዳውሮ ዞን ታርጫ ከተማ በሚገኘው ዳውሮ ታርጫ ካምፓስ  ከ360 በላይ ተማሪዎችን አስመርቋል።
በዋናው ዳውሮ ታርጫ በሚገኘው ካምፓስ ምርቃት ላይ የታደመችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ካገኘቻት አስደማሚ ተመራቂ ቅድስት ተስፋዬ ባልቻ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች። ተመራቂዋ ሁሉንም ዓይነት ሽልማቶች አራት ጊዜ ወደ መድረክ ተመላልሳ ጠራርጋ ወስዳለች።

                  እስኪ ስለ ትውልድና እድገትሽ አጫውቺን?
ትውልድና እድገቴ በወንጂ ሸዋ ነው። የተማርኩትም ያደግሁትም በስኳር ምርት ቀደምት ታሪክ ባላት ወንጂ ነው። ከወንጂ ቀጥሎ የማውቃት ሶዶ ከተማን ነው።
የወንጂ ልጆች በአብዛኛው ከአያቶቻቸው ጀምሮ በወንጂ ስኳር ፋብሪካ የሰሩ ናቸው። የአንቺ ቤተሰቦችስ?
አዎ፤ ቤተሰብን በተመለከተ እከሌ ሰርቷል አልሰራም ብሎ መነጠል ይከብዳል። ከአባቴ ጀምሮ እናቴ፣ አጎቶቼ፣ ሁሉም በስኳር ፋብሪካው ውስጥ ሰርተዋል። ከኔ ውጭ ያሉት በሙሉ በዚህ ቀደምትና ታዋቂ ስኳር ፋብሪካ ውስጥ ሰርተዋል።
እንደዚህ ውጤታማ የሆንሽበትን መሰረት ስለሚሳየኝ እስኪ ስለ አስተዳደግሽ በደንብ ንገሪኝ?
እኔ ለእናቴ የመጀመሪያ፣ ለአባቴ ደግሞ ሁለተኛ ልጅ ነኝ። በጣም ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ቤተሰቦቼ ተወልጄ ያደግሁ ነኝ። እርግጥ ነው እዚያ አካባቢ ያለው ማህበረሰብ ኑሮና ገቢ በጣም ተመሳሳይ ነው። አብዛኛው ሰው ተምሮ ሳይሆን በልምድ የሚሰራ ስለሆነ ይመስለኛል ገቢው ዝቅተኛ የሆነው። አካባቢያችን ከአዳማ 7 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ቢሆንም እንኳን ከመንገድ ጀምሮ ብዙ መሰረተ ልማት ያልተሟላለት ነው። በዚህ ጎስቋላ አካባቢ ተወልጄ እንደ ማንኛውም የአካባቢው ተወላጅ ነው ያደግሁት፡፡ የተለየ አስተዳደግ የለኝም።
የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ቆይታሽ ምን ይመስል ነበር? ያን ጊዜም ጎበዝ ተማሪ ነበርሽ? የተለየ የአጠናን ስልት አለሽ?
እርግጥ ነው በመጀመሪያ ደረጃ፣ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ት/ቤት ሳለሁ፣ በጣም የምተጋ ተማሪ ነበርኩ። ይህን ስልሽ በጣም የምጋነን ግን አልነበርኩም። ቢሆንም ከ1-3ኛ የምወጣ ነበርኩኝ። ከ5-8ኛ ክፍል ስማር የላቀ ውጤት በማምጣት ከወንድም ከሴትም እያሸነፍኩ መምጣት ጀመርኩ። 9ኛ እና 10ኛ ክፍልም ይሄ ውጤት ቀጥሎ ነበር። በመሰናዶም እንደዚሁ ውጤታማ ሆኜ ቀጥዬ፣ በዩኒቨርሲቲም ይሄው እንደምናየው ሆኗል። አጠናንን በተመለከተ የተለየ የአጠናን ስልት የለኝም። በርግጥ ተፈጥሮ የሚያግዘን ነገር ቢኖርም፣ በተፈጥሯችን ትምህርት ይገባናል ብለን ችላ ካልን ውጤታማነት የማይታሰብ ነው። በተፈጥሮ ያገኘሁትን ጸጋ ከጥረት ጋር አጣምሬ በመጠቀሜ፣ ከልጅነት እስከ ዛሬዋ ዕለት የላቀ ውጤት ማስመዝገብ ችያለሁ።
ብዙ ጊዜ ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ቤተሰቦች የሚወጡ ልጆች፣ ትምህርት ከማቋረጥ ጀምሮ በርካታ ችግሮች ይገጥሟቸዋል። አንቺ ይሄን እንዴት ተቋቁመሽ ዘለቅሽ?
እንዳልሽው ዝቅተኛ ገቢ ካለው ቤተሰብ መወለዴ እውነት ነው። ይሄ ነገር ለትምህርት እንቅፋት ቢሆንም ከስኬት ግን አልገታኝም። ይሄንን በተግባር አሳይቻለሁ። የኢኮኖሚ ዝቅተኝነት ለምን አልገታሽም ካልሽኝ፤ ሁሌም ቢሆን ያለኝን በአግባቡ ለመጠቀም፣ በራሴ አቅምና ደረጃ ልክ በመኖርና ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ያላቸው ልጆች ወይም እኩዮቼ እንደሚኖሩት ለመኖር አልያም የሌለኝን እንዳለኝ አድርጌ ባለማስመሰል ራሴንና አቅሜን አውቄ በመጓዜ ለዚህ ደርሻለሁ። ሌላውም ቢሆን ዝቅተኛ ገቢ ካለው ቤተሰብ መወለዱን ሰበብ ሳያደርግ ከጣረ፣ እንደ እኔ ውጤታማ መሆን ይችላል ባይ ነኝ።
ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ አብላጫ ውጤት ያመጡ ተማሪዎችን በመምህርነት አስቀራለሁ ብሏል። አንዷ አንቺ ነሽ መቼም?
ትክክል ነው። ዩኒቨርሲቲው በሌክቸርነት ከሚያስቀራቸው እድለኛ ሴት ተማሪዎች አንዷ ነኝ።
እስኪ በዩኒቨርሲቲ ስለነበረሽ  ቆይታ አጫውቺኝ? ከሴትነትና ወጣትነት ጋር ተያይዘው ስለሚመጡ ተግዳሮቶች ምን ትያለሽ?
እዚህ ለመድረሴና ዛሬ ላስመዘገብኩት አመርቂ ውጤት ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ምክንያቱም ሴት ተማሪዎችን በተለያየ መልኩ የሚያበረታታ ዩኒቨርሲቲ ነው። በተለይ ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰን እጅግ ላመሰገግናቸው እወዳለሁ። ለምን ካልሽኝ… ሁሌም ጥሩ ክትትልና ድጋፍ ያደርጉልናል። ሁሉም ተማሪ እንደ አባቱ ነው የሚያያቸው። የኮሌጃችን መምህራንም ቢሆኑ እጅግ የተመሰገኑና ጠንካሮች ናቸው፡፡ እነ መምህር በለጠና ሌሎቹም ቢሆኑ በተቻላቸው አቅም በተለይ ሴት ተማሪዎችን በእጅጉ ያግዙናል። እጅግ አድርጌ አመሰግናቸዋለሁ።
ያጠናሽው የትምህርት ዘርፍ ብዙ ጊዜ በወንዶች እንጂ በሴቶች የሚመረጥ አይደለም፡፡ ተመድበሽ ነው ያጠናሽው ወይስ ምርጫሽ ነበር?
እርግጥ ነው ተመድቤ የገባሁበት የትምህርት ዘርፍ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ልጅ ሆነን “ምን መሆን ትፈልጋለህ?” ሲባል ትልልቅ የሚመስሉን ዶክተርነት አውሮፕላን አብራሪነትና ሌሎች ዘርፎችን እንጂ እኔ እንዳጠናሁት “Rural Development & Agricultural Extension” ያለው አይደለም። ይሄ ግን በጣም ስህተት ነው። እኔም በተለይ በግብርናው ዘርፍ እመደባለሁ ብዬ አልጠበኩም ነበር። ነገር ግን ሆነ። ከዚያም “የምትፈልጉትን ሳይሆን ያገኛችሁትን ውደዱ” በሚለው ፍልስፍና መሰረት ነው ትምህርቴን የቀጠልኩት። ከዚያ በኋላ እጅግ ወድጄውና ተመስጬ የተማርኩት የትምህርት ዘርፍ ነው። ወደፊትም በደንብ  የማጎለብተውና በዘርፉ ተተኪዎችን የማፈራበት ዘርፍ ሆኖ ይቀጥላል።
በሁሉም ዘርፍ አሸናፊ እሆናለሁ ብለሽ ጠብቀሽ ነበር?
በቦታው ተገኝታችሁ እንዳያችሁት በአራት ዘርፎች ተሸልሜያለሁ። የመጀመሪያው ከኮሌጁ ከሁሉም ተማሪዎች ብልጫ በማምጣት፣ ቀጥሎ ከኮሌጁ ልዩ ሴት ተሸላሚ፣ ሶስተኛው ደግሞ ከግቢው ሴቶች አብላጫ በማምጣትና ከአጠቃላይ የግቢው ተማሪ የበለጠ ውጤት በማምጣት በ3.99 ሲሆን ላፕቶፕ፣ የአንገት ሃብል፣ ሜዳሊያና ዋንጫ በአራት ዙር ተሸልሜያለሁ፡፡
ይህን ውጤት ጠብቀሽ ነበር ወይ?
አዎ ጠብቄ ነበር። ነገር ግን በሁሉም አጠቃላይ ሽልማቱን እወስዳለሁ የሚል አልነበረም። ብቻ ተሳካ፤ እግዚአብሔር ይመስገን። እንደምታያቸው ቤተሰቦቼ ከፊት ለፊት ተሰብስበው በደስታ ሰክረዋል። አባቴ በህይወት የለም። እናቴ የእኛን ህይወት ለመለወጥ ዓረብ ሀገር በስራ ላይ ትገኛለች። ባለችበት ምስጋናዬ ይድረሳት፡፡ እናቴ አይዞሽ ደርሼልሻለሁ እላታለሁ። አሁን ግን ታላቅና ታናሽ ወንድሞቼ እንዲሁም አጎቴ፣ የወንድሜ ጓደኞችና ምርጥ ምርጥ ጓደኞቼ በግራና በቀኝ አሉ። እንደምታያቸው የወንድሜ ባለቤት፣ አርዓያ የሆነው መምህሬ ይኸው አብሮኝ አለ። በጣም በጣም ደስ ብሎኛል።
ለትውልድ ቀዬሽ ወንጂ ምን እያሰብሽላት ነው?
ያው ወንጂ ቀድማ አብርታ በኋላ የደበዘዘች አካባቢ ናት። ይህ እንደ ተወላጇ እጅግ የሚያሳዝነኝ ነው። ነገር ግን ወንጂን ለማገዝና ለመለወጥ ያጠናሁት  ትምህርት ይደግፈኛልና እደርስላታለሁ፣ እለውጣታለሁ፤ እግዚአብሔር ይጨመርበት ብቻ።
ቀጣይ ዕቅድሽ ምንድን ነው?
አሁን በዩኒቨርሲቲው በሌክቸርነት እቀጥላለሁ። እንደ እኔ ያሉ ተማሪዎችን የማፍራት እቅድ አለኝ። እንደማፈራም አምናለሁ። ህይወት ይቀጥላል። በትምህርት፣ በጥናትና ምርምር  እስከምችለው ድረስ እገፋበታለሁ።
በመጨረሻም ለዩኒቨርሲቲው፣ ለመምህራኖቼ፣ ለጓደኞቼ፣ ለመላው ቤተሰቤ በተለይም እኛ ቀና ብለን እንድንሄድ በአረብ ሀገር ጎንበስ ብላ ለምትሰራው እናቴ… አክብሮቴንና ፍቅሬን ልገልጽላቸው እወዳለሁ፤ አመሰግናለሁ።

Read 480 times