Saturday, 06 February 2021 14:34

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በሚያልፍ ጊዜ የማያልፍ ስራ -- ከትውልድ ወቀሳ ነጻ ያወጣል
                       ሙሼ ሰሙ

            ጦርነት የሚጠላውና የሚፈራው የሚያስከፍለው ዋጋ፣ ኪሳራና መዘዙ ገደብና ልክ የሌለው፤ በተለይ ደግሞ ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት ቁማር አስይዞ የሚካሄድ የእሳት ላይ ጨዋታ በመሆኑ ነው፡፡ ለዚህም ነው፣ ጦርነት አንዴ ከፈነዳ የቀጥተኛም ሆነ የጎንዮሽ (Collateral) ጉዳቱንና የተዋናዮቹን ጣልቃ ገብነት መቀነስ እንጂ ማስቀረት የማይቻለው። ጦርነት ይቆየን የተባለውም ለዚሁ ነበር።
በእርግጥ ጦርነትን ስለሸሹትና ስለፈሩት አይቀርም። ይህም ሆኖ ግን ጦርነት የሚፈራና የሚሸሽ ጉዳይ እንጂ እሰይ መጣልኝ ተብሎ አታሞ የሚደለቅለት ተግባር አይደለም። እሳት የሚተፋ መሳርያ ተደግኖ፣ መግደልና መሞት ከተጀመረ በኋላ ጦርነት ምቹና ሚዛናዊ (Fair) እንዲሆን መጠበቅ ቅንጦት ነው። ጦርነት ምቹና ሚዛናዊ (Fair) የሚሆነው፣ አቅምን ሁሉ አሟጦ በመጠቀም በድርድርና በጠረጴዛ ዙርያ ጦርነት እንዳይጀመር “ሰጥቶ የመቀበልን” ተግባር መርህ ማድረግ ሲቻል ብቻ ነው፡፡
ዜጎች አላፊዎች ነን፣ ሀገር ግን ዝንተ ዓለማዊ ነው። የጦርነትን፣ ሂደትና ውጤቱን ከማጦዝ፣ ከማጋነንና በጥላቻ ተሞልቶ እርስ በርስ ጭቃ ከመለጣጠፍ ይልቅ ፕሮፓጋንዳውን በቅጡና በልኩ ይዞ፣ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር መረባረብ፤ ስለ ነገና ከነገ ወዲያ ትውልድ ማሰብ ነው የሚበጀው። ይህ ደግሞ ለመንግስት ብቻ የሚተው ተግባር አይደለም።
የጦርነት ፍሬው ወደ ግራም ሞት ነው፤ ወደ ቀኝም ውድመት ነው። ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶችና ሹመኞች የጦርነቱን ሂደትና ውጤቱን ለፖለቲካ ፍጆታ፣ ለምርጫ ቅስቀሳ፣ ለማሻሻጫና ለዳግም እልቂት መቀስቀሻነት መጠቀማቸውን አቁመውና አደብ ገዝተው፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ሊገነቡና ሊያጎለብቱ ይገባል። በሚያልፍ ጊዜ የማያልፍ ስራ መስራት፣ ከትውልድ ወቀሳ ነጻ ያወጣል።
“ሀዘንሽ ቅጥ አጣ፣ ከቤትሽም አልወጣ
የገደለው ባልሽ፣ የሞተው ወንድምሽ” እንዲሉ።

Read 2912 times