Saturday, 06 February 2021 14:10

ስለ ማርጀት ... ስለ ማመን...

Written by  በመሣይ ደጉ
Rate this item
(4 votes)

  ያው እንደ ማንኛውም ባለ መካከለኛ ገቢ አዲስ አበቤ ከለውጡ በኋላ የሌለ ስራ  ‘ከቤት እሰራለሁ’ በሚል ሰበብ የሰፈር አውደልዳይ ሆኛለሁ...
የየዕለቱ routine በማስመሪያ እስኪመስል አስተካክሎ አልጋ በማንጠፍ ይጀምራል... ቀጥሎ በስሱ ለብ ባለ ውሀ ፈጣን shower ይወሰድና ፎጣ እንደተገለደመ ቀለል ያለ ቁርስ እንደነገሩ ይበጃጃል... ከዛ CNN እና Aljazeera እየተቀያየረ የወንደላጤ ቁርስ በሻይ ይቀመሳል... እረጅሙ ቀን ከዚህ በኋላ ነው የሚጀመረው!
አንድ ሰሞን የደጅ ውሎዬን በየቀኑ የምጀምርባት ከቤቴ አንድ block ጀርባ ያለች ትንሽዬ juice ቤት ነበረች... እዛች ትንሽዬ ቤት በደንበኛና በአስተናጋጅ ሳልጣደፍ ስልኬን ከፍቼ Facebook ላይ ያቺ የምወዳት አጭር ልጅ ምን ብላ እንደቧለተች... መቶ ምናምን አፍቃሪዎቿ ከሁለት መስመር ፖስቷ ስር ስንት paragraph አድናቆት እንደኮመቱ እያየሁ ስዝናና ግማሽ ጠዋቴ ያልቅልኝ ነበር።
አንድ ክፉ ቀን ከዚች የሰላም መደበቂያዬ ጎን ድምቅ ያለ የሴቶች ፀጉር ቤት ተከፍቶ ጠበቀኝ... የሴቶች ፀጉር ቤት መክፈታቸው መልካም... ችግሩ እነዚህ ደፋሮች እንደ ማስታወቂያ በግብዳ poster ላይ ከለጠፉት የቆነጃጂቶች ፎቶ መካከል በትልቁ የሚታየው፣ ኤክሴ ለሰርጓ ሌላ አነስተኛ ሰርግ በሚደግስ ዋጋ በተሰራችው makeup ከማርዜል ደረጃ ፊት pose አድርጋ የተነሳችው መሆኑ ነው...
ሁለተኛ ብዬ juice አቆምኩ... አቆምኩ!
እንግዲህ እንዲህ መደበቂያዬን በፎቶ ተቀምቼ እየዛዘምኩ ነው ያየኋት... የሆነ ጠበቅ ተደርጋ ብትጨበጥ ፍርጥ የምትል ነገር ነው የምትመስለው... ባለ ሱቁና ደንበኞቹ... ባለ ጀበና ቡናዋና ሰብስባ ዱካ ላይ ያስቀመጠቻቸው የኤርትራ ጎረምሶች... አጥር ጥግ ላስቲክ ወጥሮ ቀኑን ሙሉ የelectric singer እያስጮኸ ጨርቅ የሚጠግነው ልብስ ሰፊ... ብቻ በድንዛዜ ያስተዋልኳቸው ሁሉም የመንገዱ ተዋናዮች ምስጥ ብለው ያይዋታል! ሙሉ ትኩረቷ እንዳይወድቅ እየተጠነቀቀች የምታጫውተው ቆንጅዬ ጩጬ ላይ ቢሆንም፣ አካባቢዋ ሁሉ እንዳፈጠጠባት የምታውቅ ይመስላል። እየተደነቃቀፍኩ እንደምንም ያለፍኩት ይኼ የጓሮ መንገዴ scene እንደ ሱስ ነገር ሆኖብኝ፣ ትግርኛ እስክለምድ ከኤርትራዎቹ ጎረምሶች ቤት ተጎልቼ ቡና ማንቃረር ጀመርኩ... ቀስ እያልኩ ስታዘብ ቆንጆዋ ባለ ልጅ፣ ፀሀዩ ጠንከር ሲል ወደ ትንሿ juice ቤት እንደምታቀና ገባኝ... የሚወደኝን ጌታ አመሰገንኩ! ፎቶ ሊያስንቀኝ... ወደ ትንሿ የሰላም ቤቴ ሊመልሰኝ... juice መልሼ እንድጠጣ ሊፈቅድልኝ የወደደውን ደግ ጌታ፣ የልቤን እጆች ከፍ አድርጌ አመሰገንኩ...
በምስጋናዬ ማግስት ቀደም ብዬ juice ቤቷ ጥግ ላይ ቆንጆዋ ልጅ እስክትመጣ፣ የቆንጆዋን ኤክሴን ፎቶ እንዳላይ ሆኜ ተቀመጥኩ... ይቺ... ኖራ ያሳቀቀችኝ ሳይበቃ ተሞሽራም... መድሐኒአለም ይቅር ይበላትና!
ካጠናሁት ሰዓት ሳታረፍድ ቆንጆውን ጩጬ ከፊት እያንደረደረች ከች አለች... አቀማመጤን አስተካክዬ... በሙሉ ድዴ ፈገግ ብዬ ተቀበልኳት... አይታኝ ሳቅ አለች... በየሱስ ስም...
አፌን ከፍቼ ብዙ እንደቆየሁ የታወቀኝ ወፍራም juice ልሳ ልሳ የተንዘላዘለች ዝንብ ንፋስ ያደረቀው ከንፈሬ ላይ ስታርፍ ነው። ደግነቱ ልጇን አደላድላ ክብ ወንበር ላይ እስክታስቀምጥ አላየቺኝም። በቄንጥ ተቀምጣ የምትጠጣውን ካዘዘች በኋላ ድጋሚ በደንብ እያየቺኝ፣ Hi የሚመስል ሌላ ድምቅ ያለ ፈገግታ ፈገግ አለች... በአፍንጫዬ የሆነ አየር ድምፅ አውጥቶ... ዐይኔ ጥብብ ብሎ ግልፍጥ አልኩ... ምናባቴ ሆኜ ነው? እያፈርኩም ቢሆን ዐይኔን መንቀል አልቻልኩም... እሷም ደጋግማ እያየቺኝ እንደ መሽኮርመም ትላለች ነገር...
ቀስ እያለ ትከሻዬ ሰፋ እያለ መጣ... አቀማመጤን አስተካክዬ እንዴት ያለውን casual ጨዋታ እንደምጀምር መቀመር ጀመርኩ... መቼስ ይቺን የመሰለች ውበት ሁሉንም opening lines ሰምታ ጨርሳለች... አዪዪ...
ቀመሬን ሳልጨርስ ጩጬው ለቅሶና ጩኸት ቀላቅሎ ይቀውጠው ጀመር... በማንኪያ አፉ’ጋ የምታስጠጋለትን juice እየገፈተረ ይጨማለቃል... እሷ ትዕግስቷ ሳያልቅ እኔን ብስጭት አረገኝ...
የማናባቱ ቀበጥ ነው ይቺን የመሰለች እናት የሚያንገላታው? ደሞ የሆነ ጭንቄው ግብዳ ነገር ነው... ከአባቱ የወረሰው መሆን አለበት... አፍንጫው እራሱ የሆነ...
ይኼ...
ከሷ ስር ስር አይቼው ነው ቆንጆ የመሰለኝ መጀመርያም...
ከtoddler ጋር እራሴን እያፎካከርኩ ግብግብ ሲያምረኝ፣ እሷም በስጨት ማለት ጀመረች... “አይ እንግዲ...” ብላ እጁን ጧ አረገችውና “ጆሮ ቆራጩን ነው ምጠራልህ...” ብላ ኮስተር አለችበት። እሱ እናቴ ይቀውጠዋል።
ፊቷ እንደጨነቀው ቀና ብላ አየችኝ። “ህህህህህ...” የሚል የኔ ያልሆነ ድምፅ አውጥቼ፣ ድጋሚ ግልፍጥ አልኩ። የሆነ ሀሳብ እንደመጣላት አይነት ፈገግ አለችና ወደ ቀበጡ ጩጬ አጎንብሳ... “እምቢ ካልክ አባባን ጠርቼ ነው ማስቆነጥጥህ!” አለችው ወደኔ እየጠቆመች...
መድሐኒዓለምን ድርቅ አልኩ!
ከሳሁ...
ደሞ የጩጬው ዞሮ ካየኝ በኋላ ደንግጦ ረጭ ማለት...
እንዴ... እንዴ... እንዴ...
አስፈራለሁ እንዴ? አስደነግጣለሁ እንዴ? ዛሬ ሸምግዬ ተነሳሁ እንዴ?...
ይቺ... ምን ትመስላለች በልደታ...
እንደው ፈርሀ እግዜር ባይኖረኝ...
ይቺ...!
እንደውም እንደውም...
“አታምሪም!” ልበላት ይሆን?
“ከጀርባሽ ያለው poster ላይ ከሁሉም የምታምረው ልጅ ትታይሻለች?... ኤክሴ ናት አይገርምሽም?” ልበላት ይሆን?
ልጇ ደንግጦ ለቅሶውን አቁሞ...
ላስ የተባለውን ልሶ...
ሂሳብ ከፍለው...
አመስግና ተሰናብታኝ ሄዳለች፤ እሷ እናቴ...
ብስጭቴ ወደ depression ተቀይሮ፣ አንገቴን ደፍቼ የሚያፅናና መዝሙር እየዘመርኩ ወደ ቤቴ...
...አንተ ማለት ለኔ...
...ዘመን ሲከፋ ህይወት ሲከብደኝ...
...ስሜቴን አውቀህ ዝም አትልም...
...እያንዳንዱ ህመሜ ይሰማሀል...
ማመን ነው!


Read 2120 times