Print this page
Saturday, 06 February 2021 13:52

ለብልፅግና ብቻ የሚፈቀድ ሰልፍ … ያስቀናል?!

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(5 votes)

    በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ- “ለድጋፍ ወጥቶ ማውገዝ”!
                            ሰሞኑን በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞችና አካባቢዎች ለጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ድጋፍ ለመስጠት የተደረጉት ሰልፎች  አጃኢብ ያሰኛሉ። (ግራ የሚያጋቡም አልጠፉም!) በተለይ በአንዳንድ ከተሞች የወጣው ህዝብ ህልቆ መሳፍርት የለውም። (ማን ነበር “ዐቢይ በኦሮሚያ ድጋፍ የለውም” ያለው?!) የሰሞኑን ምን እንብለው? “በብልፅግና ፓርቲ ወይም በካድሬዎች ቅስቀሳ የተደራጀና የተጠራ ሰልፍ ነው” በሚል  ለማጣጣል የሚሞክሩ አይጠፉም (አይጠፉም ሳይሆን ሞልተዋል!) ግን ውሃ አያነሳም፡፡ (እውነቱን በመሸሽ የትም አይደረስም!) በነገራችን ላይ የትኛውም ሰልፍ እኮ ቀስቃሽ፣ አስተባባሪ፣ አደራጅ፣ ካድሬ ወዘተ… ይኖረዋል (የትራምፕን የድጋፍ ሰልፍ ጨምሮ!) የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰልፍም ቢሆን፣ በጥሪና በቅስቀሳ ነው የሚካሄደው። ያለዚያማ ህዝብ ዝም ብሎ አደባባይ አይወጣም። ዋናው ነገር ምን መሰላችሁ? ህዝቡ እንደ ደርግ ዘመን ተገድዶ አሊያም በቅጣት አለመውጣቱ ነው። ወይም እንደ ኢህአዴግ ዘመን በአበል ወይም በቲ-ሸርት እየተደለለ ከወጣ ነው ችግሩ።
እርግጠኛ ነኝ በዚህ ዘመን በድለላና ተገዶ ሰልፍ የሚወጣ የለም። (ካለም ሞኝ ነው!) በነገራችን ላይ በትኩረት የማየት ዕድል የገጠመኝ የቢሾፍቱ የድጋፍ ሰልፍ ተመችቶኛል። ለምን መሰላችሁ? የሰልፉ አካሄድና ስርዓት፣ የሚስተጋቡ አነቃቂ መፈክሮች፣ (ስራ ወዳድነት ሲወደስም ሰምቻለሁ) ሰልፈኛውን የሚያነቃቁት ወጣቶች ንቃት፣ በአየሩ ላይ የሚውለበለበው የኢትዮጵያ ባንዲራና የኦሮምያ ክልል ሰንደቅ ህብር፣ የድጋፍ ሰልፉ በሁለት (አማርኛና ኦሮምኛ) ቋንቋዎች መመራቱ (እየተፈራረቀ)፣ አንዴ የኦሮምኛ ዘፈን፣ ሌላ ጊዜ “ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ” የሚል ተወዳጅ የአማርኛ ዜማ በስሜት መቀንቀኑ፣ ጠ/ሚኒስትሩንና ብልፅግናን ከማድነቅና ከማወደስ ውጭ ለፍረጃና ውግዘት የታጨ ፓርቲ፣ ግለሰብ፣ ተቋም አለመኖሩ… ተመስገን ያሰኛል ተመችቶኛል።  ይሄ ለእኔ… ጨዋነትም ስልጣኔም ነው።
በአንዳንድ አካባቢዎች ግን ከድጋፍ ይልቅ ፍረጃና እርግማን ጎልቶ ታይቷል (ድጋፍና ውዳሴ አልቆባቸው ይሆን?።) አዳዲስ ጠላት ፈጥረው… ወይም ተፈጥሮላቸው ሲያወግዙ የሰማናቸው ሰልፎች አሉ፡፡ ምናልባት አንዳንዶቹን ጭራሽ ላያውቋቸው ይችላሉ፡፡
 በሰልፉ ማግስት ታዲያ ውዝግብ ተፈጥሮ ነበር፡፡ “ፓርቲያችን ያለአግባብ ተወንጅሏል” ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች አቤቱታ አሰምተዋል።  የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን፣) ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ያለአግባብ ላይ ተወንጅለዋል ተብሏል፡፡
በሰልፉ ላይ ሶስቱን ፓርቲዎች በአመፃ ተግባር በመሳተፉ ከምርጫ ቦርድ ከተሰረዘው ጁንታ በሚል ከሚጠራው የህውሃት ፓርቲ ጋር አንድ በማድረግ፣ የኢትዮጵያ  ጠላት ናቸው ብሎ በመፈረጅና ህገ-ወጥ በማለት፣ የምርጫ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና ስነ-ምግባር ህግ ላይ ያሉ ድንጋጌዎችን ጥሰዋል”ሲል ቦርዱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ በርግጥ የኦሮሞ ብልፅግና ፓርቲ ራሱን ተጠያቂ ላለማድረግ ብዙ ተጣጥሯል-የህዝቡ ስሜት ነው በሚል። መረጃዎች ግን ከተጠያቂነት እንደማያመልጥ ነው የሚጠቁሙት።
ይሄ ዓይነቱ አካሄድ በምርጫ ውድድር ላይ ፓርቲዎች በእኩልነት የመወዳድር መብታቸውን ችግር ላይ የሚጥል መሆኑ እንዳሳሰበው የገለፀው ቦርድ፤ የገዢው ፓርቲ አመራሮችና በተለያየ የአስተዳደር እርከን ያሉ የመንግስት ሃላፊዎች በተመሳሳይ ተግባራት ከመሳተፍ እንዲቆጠቡ አሳስቧል። በቀጣይ በተመሳሳይ ተግባር ላይ ሲሳተፉ ከተገኙም እጩ አስከ መሰረዝ የሚያደርስ አስተዳደራዊ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል አስጠንቅቋል-ቦርዱ፡፡  ህግና ሥርዓት ሲኖር ምቾት ይሰጣል፡፡ ለአቤቱታ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ ተቋም ማግኝትም መታደል ነው። ገዢውንም ተቃዋሚውንም በእኩል ዓይን የሚያይና የሚመዝን (በመርህ ብቻ!) ነፃና ገለልተኛ የመንግሰት ተቋም የመገንባት ሂደት መጀመሩን ማየት ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ያውም ምርጫ ቦርድን የመሰለ ወሳኝ የዴሞክራሲ ተቋም! (ባለፉት 30 ዓመታት እኮ አልተቻለም ነበር!)
ከዚህ አንፃር በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ እንደ አዲስ ተዋቅሮ፣ ነፍስ የዘራውን  ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አለማድነቅ ንፉግነት ነው። ሴትየዋን አመራሯንም ማወደስ ይገባል፡፡ ልብ በሉ! ገና ካሁኑ የቦርዱን ገለልተኝነት ለመጠራጠር የሚዳዳቸው ፖለቲከኞችንና ፓርቲዎች  አሰፍስዋል። (ዓመል ነዋ!)
በነገራችን ላይ በቦርዱ ማስጠንቀቂያ የሚያኮርፉና ጥርሳቸውን የሚነክሱ የብልጽግና ፓርቲ ሃላፊዎችና የመንግስት አመራሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ እገምታለሁ-እንዴት ተነካን? በሚል፡፡ ዕድሜ ዘመናቸውን ሲያስጠነቅቁና ሲያስፈራሩ ነዋ የኖሩት። (እነሱንማ ማን ቀና ብሎ ያያቸዋል?!) እንኳንስ ማስጠንቀቅ!
አሁን ግን ጊዜው ተለውጧል። ዘመን ተቀይሯል። ወደፊትም ብዙ እየተለወጠ መሄዱ አይቀርም። በእርግጥም ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እየተጓዝን ከሆነ ማለቴ ነው። በእግራችን በተጨባጭ እየተጓዝንም ባይሆን እንኳን ቢያንስ በልባችን ከተጓዝንም አንድ ነገር ነው። (አንድ ቀን እንደርሳለን) ኪሳራ የሚሆነው በልባችንም በእግራችንም እየተጓዝን ካልሆነ ነው።
እግረ መንገዳችንን አንድ ትዝብት ቢጤ ጣል እናድርግ፡፡ ለብልፅግና ፓርቲ ብቻ የሚፈቀድ ሰልፍ ምን የሚሉት ነው? በምን መስፈርት ነው? ለመረጃና ደጋፊዎች ያህል ነው!
በነገራችን ላይ እንዲያ ያለው ከልካይ መ/ቤት ወይም ቱባ ባለስልጣን ለራሱ ለብልጽግናም  አይጠቅመውም። የምርጫ ምህዳሩ ይበልጥ እየጠበበ ነው የመጣው የሚል የተቃዋሚዎች ስሞታና ነቀፋ በቀር ሌላ ምንም አያተርፍም። (ከክልከላና አ-ፍታዊ አሰራር ትርፍ ተገኝቶ አያውቅም!)  ተቃዋሚዎች ሰልፍ የማይፈቀድላቸው ምናልባት በፀጥታ ስጋት … ሃላፊነቱን ሙሉ በሙሉ ፓርቲዎቹ ላይ መጣል አንድ ነገር ነው፡፡ በተረፈ በክልከላና እገዳ  ይታያችሁ…  ብልፅግናና ደጋፊዎቹ በየአደባባዩ ወጥተው  እንደልባቸው ሲደግፉ… ሲቃወሙ ሲያወግዙ… ሲረግሙ ሲያወድስም እንደሆነ ነው የሰነበቱት፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲ ግን የአንድ ቀንም ሰልፍ አልተፈቀደለትም።
መንግስት ነገሩ ብዙም የማያሳስበው “ምህዳሩ ቢሰፋም ባይሰፋም ተቃዋሚዎች እንደሆነ እርግማን እንጂ ምርቃት አያውቁም” በሚል ተስፋ ቆርጦ ከሆነም ሆነ ጥሩ ምልክት አይደለም፡፡ መቼም ቢሆን አያመሰግኑም፡፡
ስለ ምህዳር ከተነሳ አይቀር፣ ሳልረሳው አንድ ምክር (ሁነኛ ምክር) ጣል ማድረግ እፈልጋለሁ። ሁላችንንም የሚጠቅም ነው! አገርን በምርጫው ወቅት ከቀውስና ከጥፋትም በከፊል ሊያድን ይችላል። በቅጡ ከተተገበረ። ምን መሰላችሁ? ህግ ነው! ምርጫውን በሰላምና ያለ ውዝግብ ለማጠናቀቅ ሊያግዝ የሚችል ጥብቅ ህግ ነው።!
አንደኛ፡- ብሄረሰቦች ላይ ያነጣጠሩ የድሮው ኢህአዴግ ፍረጃዎች፣ ትምክህተኛ፣ ጠባብ፣ ነፍጠኛ ወዘተ የመሳሰሉትን በምርጫ ቅስቀሳውም ሆነ እስኪጠናቀቅ ድረስ ጥቅም ላይ እንዳይውል ማገድ በእነዚህ ተንኳሽና ቆስቋሽ ፍረጃዎች የሚቀጣጠለውን ውዝግብና  አሳምረን እናውቀዋለን።
ሁለተኛ፡- ያለፉ ዘመናት ንጉሶችና ነግስታት ፈፅሞ ለምርጫ ቅስቀሳ መታገድ መከላከል አለባቸው። በየ5 ዓመቱ ምርጫ የሚወዳደሩ የሚመስሉት ከዛሬ 100 ዓመት በፊት የአገሪቱ ንጉስ የነበሩት ምኒልክ ለዚህ ተጠቃሽ ምሳሌ ናቸው። ወላ ቴዎድሮስ፣ ወላ ምንሊክ ፣ወላ ኃይለሥላሴ፣ ወላ ጣይቱ፣ወላ ኢያሱ፣ወላ ዘውዲቱ፣ ወዘተ… በአጠቃላይ በታሪክ ብቻ የሚታወቁ ያለፈ የነገስታት ዘመንና ታሪክ ለምርጫ ቅስቀሳ ፈጽሞ አይውልም በ2013 የምርጫ ፕሮፓዛሌ መሰረት ምርጫውን ያለውዝግብ ለማጠናቀቅ ሌላ አማራጭ ያለ አይመስለኝም፡፡  በአጭሩ ምርጫውን በተረትና በተፈበረከ ታሪክ እንደተለመደው መሸወድ አይቻልም እያልኩ ነው-በዘንድሮ የምርጫ ፕሮፓዛል በሌላ በኩል ምርጫው በምኞትና በፍላጎት ብቻ ነፃና ዲሚክራሲያዊ እንደማይሆን መገንዘብ ያስፈልጋል። የ97 ምርጫ ተሞክሮአችንም ይሄንኑ ያረጋግጥልናል፡፡ የቀድሞ ጠ/ሚኒስተር መለስ ዜናዊ  (መሬት ይቅለላቸውና!) ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም “ነፃ፣ ፍትሀዊና፣ እንከን የለሽ ምርጫ” እንደሚያደርጉ በልበ ሙሉነት ቃል ከገቡና ከፎከሩ በኋላ የተፈጠረውን አደገኛ ቀውስ አይተነዋል፡፡ መመኘትና መፎከር የፈለግነውን ውጤት አያመጣም፡፡ ለዚያ ነው አንዳንድ ጠበቅ ያሉና ጠንካራ ህጎች መውጣት አለበት የምንለው፡፡ የምንመኘውን ተጨባጭ ለማድረግ  በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ቅስቀሳ ላይ መውቀስም መተቸትም… ማሳጣትም ማቃለልም የሚቻለው ለስልጣን የሚፎካከሩ ፓርቲዎችን ብቻ ነው፡፡ አንድም ገዢውን ፓርቲ  አሊያም ሌሎች በምርጫው የሚወዳደሩ ፓርቲዎችን (አንዱ ሌላውን ሊሆን ይችላል!) በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ወደ ኋላከ20 ዓመት በላይ  ተጉዞ ታሪክ መፈብረክ ወይም መተርተር አይፈቀድም። የሚፈቀደውና የሚበረታታው ወደፊት…እስከ 20 ዓመትም ይሁን 50 ዓመት የሚያሻግር….. ነገን የሚያሳዩ ራዕይና ተስፋ የተሞላ ተጨባጭ ቅስቀሳ ማድረግ ብቻ ነው፡፡ (ለብዙዎች ፓርቲዎች መከራ እንደሚሆንባቸው ይጠበቃል!)


Read 2125 times