Monday, 08 February 2021 00:00

የመቀሌዋ የግቢያችን ቃል አቀባይ

Written by  ብሩህ ዓለምነህ
Rate this item
(9 votes)

       “ሁሉም ሰው እየተሯሯጠ ጥጉን ያዘ፡፡ የሁለት ዓመቱ ልጄም የሰማውን አስፈሪ ድምፅ መቋቋም አቅቶት ጉያዬ ውስጥ ተወሸቀ፡፡ ድምፁ የተዋጊዋ ሚግ ነበረ፤ የመጣችውም በመቀሌ አካባቢ የተተከሉትን የኢፌዲሪ መከላከያ ሮኬቶች ህወሓት እንዳይጠቀምበት ለመምታት ነበር…”
             
             በጦርነቱ ወቅት መቀሌ ነበርኩ፡፡ ከዛሬ ጀምሮ በየሳምንቱ የማስነብባችሁ ታሪክም ከጥቅምት 24 ቀን 2013 እስከ ህዳር 24 ቀን 2013 ድረስ በህወሓትና በአገር መከላከያ ኃይል መካከል በተደረገው ጦርነት ወቅት፣ ጦርነቱን በተመለከተ በመቀሌ እኔ በምኖርበት አንድ የመኖሪያ ግቢ ውስጥና በሰፈራችን ሲወራ የነበረ ወሬ ነው፡፡ ምንም እንኳ ወሬው በአንድ ግቢና ሰፈር ላይ የተወራ፣ ቢሆንም የግቢውና የአካባቢው ሰዎች ከሌላው የከተማዋ ነዋሪዎችና ተቋማት ጋር ካላቸው ሁለገብ ትስስር አንፃር፣ ወሬው የአብዛኛውን የህወሓት አባላትና ደጋፊዎቹን አስተሳሰብና ስነ ልቦና የሚያንፀባርቅ ነው፡፡
ማክሰኞ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ማታ 01፡30 ሰዓት አካባቢ ከአዲስ አበባ አንድ ስልክ ተደወለልኝ፤ ሳየው የእናቴ ነው፤ ‹‹ጦርነት እኮ ሊጀመር፤ ነው ምንድን ነው የምትጠብቀው? ቶሎ በአስቸኳይ ና እንጂ›› አለችኝ፡፡ እኔም ቋፍ ላይ ስለነበርኩ ‹‹እሺ እመጣለሁ›› ብዬ ስለ ሁኔታው ማብሰልሰል ጀመርኩ፡፡
ህወሓት ሰሞኑን መግለጫ አብዝቷል፤ መንግስት በሰሜን ዕዝ የመደባቸውን አዲስ ተሿሚ ህወሓት አልቀበልም በማለት ከመቀሌ ኤርፖርት መልሷቸዋል፤ ከዚህም አልፎ በሰሜን ዕዝ ላይ ምንም ዓይነት የአመራር ለውጥም ሆነ የመሳሪያ እንቅስቃሴ እንደማይቀበል ድርጅቱ አሳውቋል፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ሰሞኑን የትግራይ ክልል ፕ/ት ዶ/ር ደብረፅዮን፤ የትግራይ ህዝብ ለሚመጣው ነገር ሁሉ ዝግጁ እንዲሆን አሳስበዋል፡፡ እነዚህ ነገሮችን ገጣጥሜ ሳስባቸው፣ የጦርነቱ ነገር አይቀሬ እንደሆነ ተሰምቶኛል፡፡ እናም ለእናቴ ‹‹እሺ ነገ ቲኬት ቆርጬ እመጣለሁ›› ብያት ስልኩን ዘጋሁት።
ማታ ላፕቶፔ ላይ አፍጥጬ እያለሁ ወደ መቀሌ ኤርፖርት የሚያርፍ የአንድ አውሮፕላን ድምፅ ሰማሁ፡፡ ሰዓቴን ሳየው ከምሽቱ 04፡00 ሰዓት ይላል፡፡ መቀሌ ላይ ከምሽቱ 02፡00 በኋላ የአውሮፕላን ድምፅ ተሰምቶ ስለማያውቅ ግራ ገባኝ፡፡ ትንሽ ቆይቶ ከርቀት የተኩስ ድምፅ ይሰማ ጀመር፡፡ ላፕቶፔን ተውኩና በሞባይሌ ለሐሙስ በረራ የአየር ቲኬት ለመቁረጥ የቲኬት ዋጋ ማሰስ ጀመርኩ፡፡ ከሌሊቱ 07፡00 ሰዓት አካባቢ የሞባይልና ኢንተርኔት ኔትወርክ ድርግም ብሎ ጠፋ፡፡ ወደ ላፕቶፔ ተመለስኩ፡፡ እሱም ግን ብዙ አልቆየም፤ ከሌሊቱ 08፡00 ሰዓት አካባቢ መብራት ጠፋ፡፡ እኔም ላፕቶፔን ዘግቼ ወደ መኝታዬ ሄድኩ፡፡ ይሄ ሁሉ የሆነው ማክሰኞ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ሌሊት ነው፡፡
ረቡዕ ጠዋት ስነሳ ህዝቡ ተሸብሯል፤ ስልክ፣ ኢንተርኔት፣ መብራት፣ ውሃና ትራንስፖርት ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል፤ ባንክ ተዘግቷል፡፡ ባጠቃላይ ድባቡ ያስፈራል፡፡ አዛውንቶች በባትሪ የሚሰራ ሬዲዮናቸው ላይ ጆሯቸውን፣ አስጠግተው የክልሉን ሬዲዮ ያዳምጣሉ፡፡ ሬዲዮኑ ‹‹የዐቢይ መከላከያ ሰራዊት በትግራይ ህዝብ ላይ ጦርነት ከፍቷል፤ ሆኖም ግን የሰሜን ዕዝ የዐቢይ መንግስት ላይ በማመፅ ከትግራይ ልዩ ኃይል ጋር ተሰልፏል›› ይላል በተደጋጋሚ፡፡ የአከራያችን የመጀመሪያ ልጅ የሆነውን ሙሉጌታን ጠጋ ብይ፤ ‹‹ሙሌ ኧረ ምንድን ነው የሚወራው?›› አልኩት፡፡
እሱም ‹‹ይሄ ሁሉ የዐቢይ ሥራ ነው›› አለኝ፡፡
እኔም ግራ ተጋብቼ ‹‹የትኛው?›› አልኩት።
ሙሌም ‹‹ትናንት ማታ የአውሮፕላን ድምፅ ሰምተሃል?››
እኔ፡ ‹‹አዎ! 04፡00 ሰዓት አካባቢ!!››
ጎረቤቴ ‹‹እሱ አውሮፕላን ዐቢይ የላከው ነው፤ የመጣውም ወታደርና የጦር መሳሪያ ሊወስድ ነበር፡፡ የእኛዎቹ ሳተናዎቹ ግን አስቀድመው መረጃው ስለነበራቸው አውሮፕላኑን አገቱት›› አለኝ፡፡
እኔም አመንኩትና ‹‹እንዴት መንግስት እንደዚህ ዓይነት ትንኮሳ ይፈፅማል!?›› በማለት በጠ/ሚ ዐቢይ ላይ ተናደድኩ፡፡ ትናንት ዶ/ር ደብረ ፅዮን በሰጡት መግለጫ ላይ በተደጋጋሚ ‹‹እኛ ጦርነት አንፈልግም፤ ሰላም ነው የምንፈልገው፤ በራችን ሁልጊዜ ለሰላም ክፍት ነው›› ሲሉ ስለሰማሁ የሌሊቱ ትንኮሳ የተፈፀመው በመንግስት ነው በሚል ደመደምኩ፡፡
ትንሽ ቆይቶ የ16 ዓመት ጎረምሳውና የአከራያችን የልጅ ልጅ የሆነው ሔኖክ እየነጠረ ወደ ግቢ ገባ፡፡ ‹‹ሰው ሁሉ በግቢው ተሸክፎ አንተ የት ነበርክ?›› አለችው ተከራዩዋ ሜሮን፡፡ ሜሮን ትግርኛ አቀላጥፋ የምትሰማና የምትናገር ቢሆንም፣ ሀገሯ ግን ሰቆጣ ነው - አማራ ክልል፡፡ እኔም የግቢው ሰው በትግርኛ የሚያወራውን ሁሉ የማገኘው ከሜሮን ነው፡፡ ‹‹ኩሓ ነበርኩ!!›› አላት ሔኖክ፤ በድል አድራጊነት ስሜት እጁን እያወናጨፈ፡፡ ኩሓ የመቀሌ ኤርፖርት የሚገኝበት አካባቢ ነው፡፡
‹‹ኩሓ ምን አየህ?›› አለችው ሜሮን፡፡
እሱም ‹‹የአማራ ወታደር ተረፍርፎ አየሁ›› አላት፡፡
እሷም ‹‹እህ! መንገድ ተዘግቷል፤ ትራንስፖርትም ቆሟል በምን ወደዚያ ሄድክ?›› አለችው፡፡
ሔኖክም ‹‹አውቄ ነው አልሄድኩም፤ ሰዎች ሲያወሩ ሰምቼ ነው›› አላት፡፡
ሌሊት የተዘጋው የሞባይል ኔትወርክ በነጋታው ለጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ተከፈተ፤ መብራትም መጣ፡፡ ከአዲስ አበባ የሚተላለፉ ቴሌቪዥኖችን እየቀያየርኩ ስመለከት በሁሉም ጣቢያዎች ላይ ቁጣ ያዘሉ መልዕክቶች ሰማሁ፡፡ ቁጣውን የቀሰቀሰው ደግሞ ‹‹የትግራይ ልዩ ኃይልና ሚሊሺያ 21 ዓመት ሙሉ የትግራይን ህዝብ ሲጠብቅ የነበሩትን የመከላከያ ወታደሮች ሌሊት በተኙበት ገደሏቸው›› የሚለው አስደንጋጭ ዜና ነው፡፡ ግራ ተጋባሁ!! የትግራይ ሚዲያዎች ‹‹ዐቢይ ጦርነት አወጀብን›› ይላሉ፤ መንግስት የሚለው ደግሞ ሌላ ነው፡፡ ማንን እንደማምን ግራ ገባኝ!! ‹ማነው ትንኮሳውን የጀመረው?!› የሚለው ጥያቄ፣ ለደቂቃዎች በአእምሮዬ መልስ ያላገኘ ጥያቄ ሆነ፡፡
በዚህ መሐል ሚዲያዎቹን እየተከታተልኩ፣ ስለ ህወሓት ባህሪ ማሰላሰል ጀመርኩ፡፡ ህወሓት በኢህአዴግ ስም ኢትዮጵያን ለ27 ዓመታት ሲገዛ በፈፀማቸው በጎም ሆኑ መጥፎ ነገሮች የተነሳ ባህሪውን ጠንቅቄ አውቃለሁ። ከዚህም በተጨማሪ የህወሓት ባለ ሥልጣናት ‹‹ሻቢያ፣ ፌዴራልና አማራ ሊወሩን ነው›› የሚለው ድምዳሜያቸው አንድ ቀን ‹‹ሳንቀደም እንቅደም›› ወደሚል እርምጃ እንደሚያስገባቸውም አውቃለሁ። በስተመጨረሻም ‹‹ትንኮሳውን የጀመረው ህወሓት ነው›› የሚለውን የመንግስትን መረጃ አመንኩ፡፡ ይሄንንም ለጎረቤቴ ልነግረው አስብኩና ‹‹ኦ ኦ!! ጎመን በጤና›› ብዬ ተውኩት፡፡
የዚያው ዕለት ማታውኑ በትግራይ ቴሌቪዥን የቀረበው የህወሓቱ አቶ ሴኮ ቱሬ፤ ‹‹ታሪክ እንደሚያሳየን በትልልቅ ሀገሮች የመጠቃት ስጋት ያለባቸው ትንንሽ ሀገሮች ህልውናቸውንና ሉዓላዊነታቸውን ማስከበር የቻሉት አስቀድመውና ድንገት በሚሰነዝሩት ጥቃት ነው፤ እኛም ከዚህ ሐቅ ልምድ በመውሰድ መከላከያ ኃይል ላይ መብረቃዊ ሊባል የሚችል ድንገተኛ ጥቃት ፈፅመን በክልላችን ያሉትን የሰሜን ዕዝ ሁሉንም ክፍለ ጦሮች በ45 ደቂቃ ውስጥ ተቆጣጥረናቸዋል›› በማለት ተናገረ። አቶ ሴኮ ቱሬ ይሄንን ያለው ህወሓት ‹‹በፌዴራል መንግስት ጦርነት ተከፈተብኝ›› እያለ ለዓለም ማህበረሰብ አቤቱታ እያቀረበ በነበረበት ሰዓት ነው፡፡
በነጋታው ሐሙስ ጥቅምት 26 ቀን 2013 ረፋዱ ላይ መቀሌ እንዴት አደረች የሚለውን ለማየት ልጄን ይዤ ወክ እያደረኩ እያለሁ፣ በድንገት ልብን ከሁለት የሚተረትር ድምፅ ከሰማይ መጣ፡፡ ሁሉም ሰው እየተሯሯጠ ጥጉን ያዘ፡፡ የሁለት ዓመቱ ልጄም የሰማውን አስፈሪ ድምፅ መቋቋም አቅቶት ጉያዬ ውስጥ ተወሸቀ፡፡ ድምፁ የተዋጊዋ ሚግ ነበረ፤ የመጣችውም በመቀሌ አካባቢ የተተከሉትን የኢፌዲሪ መከላከያ ሮኬቶች ህወሓት እንዳይጠቀምበት ለመምታት ነበር። ሆኖም ግን፣ አስፈሪው ድምፁዋን እንጂ እሷን ማንም ሳያያት ሄዳለች፡፡ እኔም ከምን ዓይነት ቴክኖሎጂ ብትሰራ ነው ከድምፅዋ ፈጥና የተፈተለከችው ብዬ ተደነቅሁ፡፡ ወደ ልቦናዬ ከተመለስኩ በኋላ ምናልባት የጣለችው መሳሪያ ካለ ብዬ ዙሪያውን ስቃኝ ምንም ነገር የለም፡፡
ተሰብስበን ስለ ሁኔታው ስናወራ፣ ጎረቤታችን ተሾመ ‹‹ሚጓ የሻቢያ ናት›› አለን። እኔም በልቤ ‹‹ድምፁ ያለፈው ከደቡብ ወደ ሰሜን ነው፤ የሻቢያ ሚግ ደቡብ ላይ ምን ታደርጋለች?!›› ብዬ ዝም አልኩ፡፡ ልጄን ይዤ ወደ ግቢ ስገባ፣ ዓለምፀሐይ የግቢያችንን ሴቶች ሰብስባ ገለፃ ታደርጋለች፡፡ እንደ ስልክ እንጨት የተገተረ አፍንጫና የቀይ ዳማ መልክ ያላት ዓለምፀሐይ፤ እንደ እኛ ተከራይ ስትሆን መካከለኛ ቁመትና ውፍረት አላት። ዓለምፀሐይ ሁለት ወጣ ያሉ ነገሮች አሏት፤ እነሱም ግራኝ መሆኗና ወንዳወንድ የሆነ አረማመዷ ናቸው፡፡
ባሏ ሓየሎም መርማሪ ፖሊስ ነው፡፡ ሓየሎም ከፖሊስነት በተጨማሪ ዘፋኝነትም ይሞክራል፡፡ በዚህም አማራን የሚሳደብ አንዲት ክሊፕ አለችው፡፡ ይቺን ክሊፕ ዓለምፀሐይ በኩራት እንደ ሜሮን ላሉ ለምትቀርባቸው ሰዎች ታሳያቸዋለች። በባሏ የተነሳ ይሁን አይሁን አይታወቅም፣ ዓለምፀሐይ ቀንደኛ የህወሓት ደጋፊ ናት። በዚህም የተነሳ ጦርነቱን በከፍተኛ ትኩረት እየተከታተለች፣ ከህወሓት በኩል ያለውን አስተሳሰብ በየቀኑ ትዘግብልናለች። እኔም ‹‹የጦርነቱ የግቢያችን ቃል አቀባይ›› አልኳት።  
ከሚጓ ድንጋጤ መለስ ብዬ ልክ ወደ ግቢ ስገባ፣ ቃል አቀባያችን ግራ እጇን እያወናጨፈች ስለ ጦርነቱ ለግቢያችን ሴቶች ታብራራለች፤ ‹‹አታስቡ የሰሜን ዕዝ ዐቢይን ከድቶ ከእኛ ጋር ተሰልፏል፤ ይሄንን ሰራዊትና መሳሪያ ይዘን ጦርነቱን በጣም በአጭር ቀናት ውስጥ በድል እናጠናቅቀዋለን፡፡ … በነገራችን ላይ የአሁኗ አየር (ሚግ) ተመትታ ወድቃለች…›› አለች እርግጠኛ ሆና፡፡
ሴቶቹ አፋቸውን ከፍተው ያዳምጧታል። ዓለምፀሐይ ሚጓ የመመታቷን መረጃ በዚህ ፍጥነት ከየት እንዳገኘችው አይታወቅም፡፡ ሴቶቹ ግን ስለ መረጃ ምንጮቿ ሳይጠይቁ ረጅሙን የዓለምፀሐይን ገለፃ ዝም ብለው ያዳምጣሉ፤ ደግሞም ያምኗታል፡፡ እሷም ከልቧ ስለምታወራ ታሳምናለች፡፡
ከሴቶቹ ትንሽ ፈንጠር ብለው ደግሞ አከራያችን ጋሽ በርሄ፣ ጋቢያቸውን ተከናንበው፣ በርጩማ ላይ ቁጭ ብለው፣ ጆሯቸውን የጥንት ፊሊፕስ ሬዲዮናቸው ላይ ለጥፈው ያዳምጣሉ፡፡ ሬዲዮኑም ‹‹ጦርነቱ ገና ከመጀመሩ ዐቢይ የትግራይን ህዝብ በአየር ደበደበ›› ይላል፡፡ ጋሽ በርሄ በቁጭት ጭንቅላታቸውን ይነቀንቃሉ፡፡
ሬዲዮኑ ቀጠለ፣ ‹‹አድማጮቻችን አሁን ደግሞ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የትግራይ ክልል ፕ/ት ዶ/ር ደብረ ፅዮን እየሰጡ ያሉትን መግለጫ በቀጥታ እናስተላልፍለን…››። ሴቶቹ ይሄንን ሲሰሙ የዶ/ር ደብረ ፅዮንን ንግግር በቴሌቪዥን ለማዳመጥ ወደየቤታቸው ተበታተኑ፡፡
(ይቀጥላል…)


Read 9368 times