Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 11 August 2012 12:39

ከ“የት ነው?” እስከ “የኢህአዴግ ቀይ እስክሪብቶ”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“የሚገባበት አይታወቅምና በደንብ ይገንቡ”

ጊዜው ቆየት ብሏል፡፡ ደራሲ ሲሳይ ንጉሱ በአንድ መድረክ ተጋብዞ ልምዱን ሲያካፍል “በሕይወቴ ትልቁን ትምህርት የተማርኩት በማረሚያ ቤት አንድ ዓመት በቆየሁበት ጊዜ ነው፡፡ ከመታሰሬ በፊት የዩኒቨርስቲ ምሩቅ የነበርኩ ቢሆንም ከትምህርት ያላገኘሁትን ዕውቀት በእስርቤትአግኝቻለሁ”
ማለቱን አስታውሳለሁ፡፡ ዐፈሩ ይቅለለውና ጋዜጠኛ አብርሃም ረታ ዓለሙም “እስር ቤት ገብቶ የወጣ ሰው ስለ ዓለምና ሕይወት ያለው አመለካከት ከሌሎች ይለያል፡፡ መታሰርን ማንም የማይመርጠውና የማይደገፍ ነገር ቢሆንም ከአስተማሪነቱ አንፃር ሁሉም ታስሮ ቢያየው አይጠላም” ብሎ ነበር፡፡ ስለ እስር፣ አሳሪዎችና እስር ቤት ከጥንት ጀምሮ እየተነገሩና እየተፃፉ የመጡ ብዙ ታሪኮች አሉ፡፡ በአገራችንም ነገሥታት ተወላጅ ቤተሰቦቻቸው በስልጣን እንዳይጋፏቸው በተመረጠ ቦታ ሰብስበው ያስቀምጧቸው (ያሰሯቸው) እንደነበር፤ ይህም ሂደት ለብዙ ዘመናት ባህል ሆኖ መቆየቱን በተለያዩ የታሪክ መፃሕፍት ተመዝግቧል፡፡ ነገሥታት ቤተሰቦቻቸውን ብቻ ሳይሆን በስልጣናቸው የሚመጣባቸውን ወይም ከሕግ ውጪ ነው ያሉትን ተራ ዜጋም ቢሆን በማረሚያ ቤት እንዲቆይ ማድረግ አንዱ ተግባራቸው ነው፡፡
ለምሳሌ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በእስር ከቆዩ ኢትዮጵያዊያን አንዱ ለ27 ዓመታት መንገላታታቸውን “የ20ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ በጥላሁን ብርሃነሥላሴ ቤተ ተዘጋጅቶ በ1998 ዓ.ም በታተመው መጽሐፍ ውስጥ ተጠቅሷል፡፡ የነፃነት ታጋዩን የኔልሰን ማንዴላን ያህል ዓመታት በእስር ስለቆዩት እኚህ ኢትዮጵያ ወይም ተመሳሳይ የእስር ቤት ቆይታ ስላሳለፉ ሰዎች በጽሑፍ የቀረበ ብዙ መረጃ አልነበረም፡፡ አሁን ለውጥ እየታየ ነው፡፡ ታስረው የተፈቱ ወይም በእስር ላይ ያሉ ታዋቂ ኢትዮጵያዊያን ከሚጠበቅባቸው ነገሮች አንዱ ለሕትመት የሚቀርብ መጽሐፍ ማሰናዳት ሆኗል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ባለፉት ዓመታት ጥቂት የማይባሉ መፃሕፍት ታትመው ለአንባቢያን ቀርበዋል፡፡ በአገራችን እስር ቤትና እስረኝነትን መነሻ አድርጐ በመታተም፤ የ11 ዓመታት የሶማሊያ እስር ቤቶች ቆይታዋን “የት ነው?” በሚል ርዕስ በ1981 ዓ.ም መጽሐፍ ያሳተመችው ሰዓሊናገጣሚከበደች
ተክለአብ ከጀማሪዎቹ ተጠቃሽ ሳትሆን አትቀርም፡፡ በ1993 ዓ.ም በዶ/ር ፀሐይ ጀምበሩ ተዘጋጅቶ “ደመላሽ” በሚል ርዕስ፤በደርግዘመነመንግሥት ብዙ ግፍ፣ ስቃይና በደል ስለተሰራበት የደብረ ማርቆስ እስር ቤት ታሪክ፤ በአጫጭር ልቦለዶች ቀርቧል፡፡ በ1995 ዓ.ም በጀማል አክበር ታትሞ
የቀረበው “ካገር ፍቅር አዲስ አበባ” ረጅም ልቦለድ ታሪክም በአገራችን እስር ቤትና እስረኝነት ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው፡፡ እስር ቤትንና እስረኝነትን በግጥምና በልቦለድ ማቅረብ ተጀምሮ አሁን ግለ ታሪክ መጽሐፍ ለማዘጋጀት ትልቅ መነሻ ርዕሰ ጉዳይ እየሆነ ነው፡፡ ከዚህም አልፎ ታሳሪው ሀሳቡን በጋዜጣና መጽሔቶች ያቀረበባቸው ጽሑፎች ተሰብስበው በመጽሐፍ እስከ ማቅረብ ተደርሷል፡፡ የዛሬ ሳምንት በራስ አምባ ሆቴል የተመረቀው የጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ “የኢህአዴግ ቀይ እስክሪብቶ” መጽሐፍ ለዚህ በምሳሌነት ይቀርባል፡፡ በመጽሐፍ ምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተጋብዘው ንግግር ያደረጉ ሰዎች ከእስር ቤትና እስረኝነት ጋር በተያያዘ ያነሷቸው ሀሳቦች በሳልና አስተማሪ ነበሩ፡፡ “እስር ቤት መግባት መማር ለፈለገ ሰው ትልቅ ትምህርት ቤት ነው” በማለት አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፤ እስር ቤት በነበሩበት ጊዜ ያጋጠማቸውን አሳዛኝ ታሪክ ለታዳሚው አጋርተዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ ወደነበሩበት ክፍል እንዲገቡ የተደረጉት ሁለቱ እስረኞች አንዱ ዳኛ ሌላኛው አቃቤ ህግ ሆነው በፍርድ ቤት ይሰሩ የነበሩ ናቸው፡፡ ይህንን የሚያውቀው ታራሚ ለሁለቱ የሕግ ባለሙያ እስረኞች ምንም ርህራሄ ስላልነበረው ለአእምሮ ህመም በተዳረጉ ጊዜ ነበር ፕሮፌሰሩ ወዳሉበት ክፍል ተቀይረው የመጡት፡፡ “ያኔ ያየሁት ነገር ለእኔ ትልቅ ትምህርት ሆኖኛል” ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፤ መታሰር ይበልጥ ለማወቅ፣ ለመማር ይጠቅማል ብለዋል፡፡ በመቀጠል ንግግር ያቀረቡት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ “ካልታሰሩ ይልቅ የታሰሩ ሰዎች የተሻለ ነፃነት አላቸው… ከእስር ቤት ውጭ የሆነ ሰው በሹመቱ፣ በቢሮው፣ በሥራው፣ በቤቱ …ተደብቆ ነው የሚኖረው፡፡ ታሳሪዎች የተሻለ ነፃነት አላቸው” በማለት ገጣሚ ሰለሞን ሞገስ “እውነትን ስቀሏት” በሚለው መጽሐፉ “ስንቅ የሚያቀብሉኝ እስረኞች ናቸው” በሚል ርዕስ የቋጠረውን ግጥም እንደማሳያ አቅርበዋል፡፡ እስረኛ ነኝ እኔ መብቱ የጐደለ፣
ነፃ እርግብ ለመሆን ከቶም ያልታደለ፡፡
በአጥር - በጠመንጃ - በዘብ ተጠብቄ፣
በአንዲት ጠባብ ክፍል ምኞቴን አምቄ፣
ታስሬ እኖራለሁ፣
በመጽሐፍ ቅጠል ዓለምን እያየሁ፡፡
የለም ነፃ ሰው ነኝ እስረኛ አይደለሁም
ጭንቅና ሰቀቀን ከእኔ ጋራ የሉም፡፡
“እታሰር ይሆን ወይ?” ብዬ መች ልፈራ?
ታስሬያለሁና ከራሴ እውነት ጋራ፡፡
የሚዳቋ ስጋት፣ ጭንቅ የሞላባቸው፣
የታሰሩትማ በደጅ ያሉ ናቸው፡፡
እኔ ነፃ ሰው ነኝ!
ያሻኝን ሰርቼ፣
የልቤን አውርቼ፣
ይኸው እዚህ አለሁ ነፃነት አግኝቼ፡፡
የታሰሩትማ በውጭ ያሉ ናቸው
የልብን ለማውራት
የልብን ለመስራት ወኔ የከዳቸው፣
የሚደናበሩ በገዛ ጥላቸው፣
እኔ ነፃ ሰው ነኝ! የታሰሩትማ ያልታሰሩት ናቸው፡፡
“የቤት ስሟ ሉሉ ነው፡፡ ከሦስቱ ልጆቼ የመጀመሪያው ናት፡፡ እሷን ስንወልድ የእኔና የባለቤቴን ትዳር ሙሉና ደስተኛ አድርጋው ነበር፡፡ አሁን መጽሐፏን አሳትማ አያት አድርጋናለች፡፡ እኔ ርዕዮትን የምወክላት በሻማ ነው፡፡ ሻማ እየቀለጠ ያበራል፡፡ ርዕዮትም ከመታሰሯ በፊትጀምሮላመነችበት ነገር እየኖረች እየቀለጠች አብርታለች” ያሉት አባቷ አቶ ዓለሙ ለመጽሐፉ መታተም የጣሩትን ሁሉ አመስግነዋል፡፡ የርዕዮት አባት በመሆናቸውም ኩራት እንደሚሰማቸው ገልፀዋል፡፡ “እንኳን በሠላም ተገናኘን” በማለት የመጨረሻውን ንግግር ያደረጉት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በበኩላቸው፤ የጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙን መታሰር የሰሙ ዕለት 1997 ዓ.ም እና የወቅቱን ግርግር እንዳስታወሳቸው አመልክተው ኢህአዴግ አካፋን አካፋ ማለት ስላስተማረኝ አመሰግነዋለሁ፤ ርዕዮት ዓለሙም ግልፁን ነገር በግልጽ ተናግራለች በማለት አድናቆታቸውን ገልፀዋል፡፡ እስር ቤትና እስረኝነትን ማዕከል አድርገው የታተሙት መፃሕፍት በሁለት ክፍል ሊመደቡ የሚችሉ ናቸው፡፡ ከከበደች ተክለአብ እስከ ርዕዮት ዓለሙ በሚል ክፍል ተመድበው ሊቀርቡ የሚችሉት ጥራዞች፤ ያለፈን ታሪክ መዝግበው ማኖራቸው አንደኛው ሲሆን ሁለተኛው (ከ1997 ዓ.ም ወዲህ የታተሙት) የፖለቲካ ትግሉ አካል ሆነው ቀርበዋል፡፡ በየትም አገር ቢሆን እስር ቤት የሌለው መንግስት ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፡፡ በአገራችንም በእስረኛ ጥበቃና በእስር ቤት አያያዝ ላይ ለውጥ ለማምጣት እስር ቤትን በሚያውቁ ሰዎች እየተዘጋጁ በመታተም ላይ ያሉት መፃሕፍት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ አለ፡፡ ከ”የት ነው?” እስከ “የኢህአዴግ ቀይ እስክሪብቶ” የታተሙት መፃሕፍት ቢጠኑ፣ ቢመረመሩ “የሚገባበት አይታወቅምና በደንብ ይገንቡ” እየተባለ የሚቀለድበትን እስር ቤት የመልካም ትምህርት መቅሰሚያ ማዕከል
ማድረግ ይቻላል፡፡

 

 

Read 2518 times Last modified on Saturday, 11 August 2012 12:51