Saturday, 06 February 2021 12:33

በአሜሪካ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ በጎ አድራጊ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

   • ለጋዜጠኛ ካሳሁን አሰፋ ባለቤት 305 ሺ ብር አስረክቤአለሁ
           • በልጅነቴ ለማውቀው ለልብ ህሙማን ማዕከል ከ1 ሚ. ብር በላይ ለግሻለሁ

              ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ጉለሌ ሩፋኤል ቤተክርስቲያን አካባቢ ነው። ኑሮውን አሜሪካ ኮሎራዶ ግዛት ካደረገ 16 ዓመታትን አስቆጥሯል። ገና የ11 ዓመት ልጅ እያለ በሚማርበት ት/ቤት ለልብ ህሙማን ህ”ፃናት ብር በማዋጣት የበጎ ስራ እንደ ጀመረና ከዛን ጊዜ ጀምሮ ከበጎ አድራጎት ስራዎች እንዳልራቀ ይናገራል። የዛሬው እንግዳችን  አቶ ሚኪያስ አለሙ አበበ  በቅፅል ስሙ ሚኪ ኤቢ።
ሰሞኑን ለበጎ አድራጎት ስራ ከአሜሪካ ወደ አገር  ቤት በመጣ ወቅትም ከልጅነቱ ጀምሮ ለሚያውቀው አንድ ተቋምና አንድ ግለሰብ ድጋፍ (ልገሳ) አድርጓል። የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ  አቶ ሚኪያስ አለሙ ባረፈበት ሳሬም ኢንተርናሽናል ሆቴል ጎራ ብላ አነጋግራዋለች።


            እስኪ ስለ አስተዳደግህ ትንሽ አጫውተኝ አስተዳደግ አሁን ለምንገኝበት ስብዕና መሰረት ስለሆነ ነው?
አስተዳዳሪ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ልጅ ቤተክርስቲያን በመሄድ የተለያዩ በጎ ነገሮችን በመስራትና ወላጅን በመታዘዝ ነው።
እደሰማሁት ባለፉት 16 ዓመታት ኑሮህን ያደረከው በአሜሪካ ነው እንዴት አሜሪካ ሄድክ ህይወት በአሜሪካስ ምን ይመስላል?
ወደ አሜሪካ የሄድኩት እዛ ቤተሰብ  ስለነበረኝ በተፈጠረልኝ አጋጣሚ ነው። እዛ እንግዲህ ስራ ላይ ነው የምገኘው። የራሴ ስራ አለኝ በጥሩ ሁኔታ ነው የምኖረው።
በሌላው ዓለም ስለ በጎ አድራጎት ያለውን አመለካከት ከአገራችን ጋር ስታነጻጽረው ምን ይመስላል?
ኢትዮጵያ ውስጥ የበጎ አድራጎት ላይ ያለው አመለካከት ትንሽ የሚቀረው ነገር እንዳለ በተለያዩ አጋጣሚዎች አስተውያለሁ። ሁሉ ነገር ገብቶን ብንሰራበት የውጪ ድጋፍ ሳያስፈልገን፣ ችግራችንን በራሳችን መቅረፍ እንችል ነበር ብዬ አምናለሁ።  በአሜሪካ  የበጎ አድራጎት ስራ ትልቅ ክብር ያለው ነው። በአሜሪካ ትልቅ ሥራና ምግባር ከሚባሉት ውስጥ በጎ አድራጎት ቅድሚያ የሚሰጠው ነው። ስለዚህ በዛ አገር በጎ ስራ መስራት በክብር ቦታ የሚያስቀምጥ ነው። ይሄ አመለካከት እዚህ አገሬ ላይም በደንብ ቢዳብር በጣም ደስ ይለኛል። ይህ አመለካከት እንዲዳብርም የበኩሌን ለማድረግ እሞክራለሁ።
እስኪ በምትኖርበት አሜሪካ የምታደርገውን የበጎ አድራጎት ስራ በሚመለከት ጥቂት አብራራልኝ?
በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኮሙኒቲ አካባቢዎች ላይ ችግሮች ሲከሰቱ፣ ለምሳሌ ሰው ሲታመም ወይም ሲሞት ማህበረሰቡን በማስተባበር የበኩሌን አደርጋለሁ። አንድ ሰው ታሞ ወይም ህይወቱ አልፎ ወደ አገር ቤት ሲመጣ ብዙ አስቸጋሪ ነገሮች ይከሰታሉ።
አንድ ሰው ሲሞትና አስክሬኑ ወደ ሀገር ቤት ሲመጣ የሚከፈለው የገንዘብ መጠን ታምሞ ሲመጣ ከሚከፈለው ይበልጣል። አንድ ሰው ህይወቱ አልፎ አስክሬኑ ሲመጣ ከ110 ሺህ 500 ዶላር በላይ ለአውሮፕላን ይከፈላል። ይሄ እንግዲህ ለአውሮፕላኑ ብቻ ነው። ከዚያ ውጪ ላሉት ሂደቶች ደግሞ ሲታሰብ ወጪው ከፍተኛ ይሆናል። ይህንን ወጪ ዘመዱ የሞተበት ሰው ብቻውን ለመክፈል ይከብደዋል። ለምን ካልሽኝ አብዛኛው ውጪ ያለው ዲያስፖራ እዚህ ያለውን ቤተሰብ ስለሚረዳና ስለሚደጉም እዚያ ብዙ ገንዘብ የማጠራቀም እድሉ አያጋጥመውም።
ስለዚህ እንዲህ አይነት ችግር ድንገት ሲጋጥመው ብቻውን መቋቋም ስለሚያቅተው፣ የሌላውን ወገኑን ድጋፍ ይሻል። እኔ በምኖርበት ኮሎራዶ ማህበረሰቡን በማሰባሰብ፣ ያ ችግር የሚፈታበትን መንገድ እፈጥራለሁ።
ይሄንን የበጎ አድራጎት ስራ በተቀናና ከፍ ባለ መልኩ ለመከወን ወደ ተቋምነት እንዳሳዳግከው ሰምቻለሁ። ስለ አዲሱ የበጎ አድራጎት ድርጅትህ ብታብራራልኝ?
እውነት ነው። “በጎ ራዕይ” የተሰኘ የበጎ አድራጎት ድርጅት መስርቼ፣ በአሜሪካ ህጋዊ ፈቃድ አግኝቷል። የተቋቋመው በ2019 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ነው። በ2019 እውቅናውን ያገኘበት ነው እንጂ “በጎ ራዕይ” ከተቋቋመ ቆይቷል። አሁን ህጋዊ ሰውነት ለው ተቋም ሆኖ በተጠናከረ መልኩ ስራውን ቀጥሏል።
ሰሞኑን ለአንድ ቤተሰብና ለአንድ የህክምና ተቋም በድርጅትህ በኩል ያሰባሰብከውን ገንዘብ ለመለገስ ነው የመጣኸው። እስኪ በዚህ ላይ እናውራ?
በመጀመሪያ ይህንን ያደረገው ሃያሉ እግዚአብሔር ነውና እሱ ነው መመስገንና ውለታውን መውሰድ ያለበት። ምክንያቱም እግዚአብሔር ያተጨመረበት ነገር በእኔ ተነሳሽነት ብቻ ሊሳካ አይችልም ነበር ብዬ አምናለሁ። ልብን ለበጎ ነገር የሚከፍት እግዚአብሔርን ማመስገን እፈልጋለሁ።
በተረፈ ግን ልገሳውን ያስረከብኩበት ባለፈው ዓመት ለእምቦጭ ነቀላ ባህር ዳር ተጉዞ በገጠመው ድንገተኛ ህመም ህይወቱ ላለፈው ጋዜጠኛ ካሳሁን አሰፋ ቤተሰብ ነው። ስለዚህ ጋዜጠኛ ስሰማ ልጅና ቤተሰብ ያለው፣ ሀላፊነቱ በእሱ ላይ የወደቀ፣ መሆኑን አወቅኩኝ። በዚያ ላይ ሚስቱና ልጆቹ በቤት ኪራይ እንደሚኖሩ ሳውቅ በጣም ከባድ ነው አልኩኝ። ብዙ ጊዜ የቤቱ  አውራ የሆነ ሰው ሲሞት፣ ጋብቻ ሲፈርስ የልጆች ዕጣ ፋንታ በተለይ ያሳስባል። ልጆች ወደ ጎዳ ያመራሉም ጭምር። ይሄ ነገር ደግሞ መከሰት የለበትም የሚለው ነገር ወደ ጭንቅላቴ መጣ። ስለዚህ የጋዜጠኛ ካሳሁንን ጓደኞች ጋዜጠኛ ምስክር ጌታውንና በፍቃዱ አባይ ነው ያነጋገርኳቸው። እነሱ በመጀመሪያ የጠየቁኝ ነገር ምንድን ነው… ምን ያህል ኮሚሽን ነው የምትወስደው የሚል ነው።
የምን ኮሚሽን ነው?
እንግዲህ “Go Fund Me” ሲከፈት ኮሚሽን የሚጠይቁ አካላት አሉ መሰለኝ። እነሱንም ከዚህ በፊት ኮሚሽን የጠየቃቸው ሰው አለ መሰለኝ። እኔንም ምን ያህል ኮሚሽን ነው የምትጠይቀው አሉኝ። እኔም ምንም የምጠይቀውም የምወስደውም ኮሚሽን የለም አልኳቸው። የምንሰራው ለበጎ ስራ እስከሆነ ድረስ መመስገንም በእግዚአብሔር መባረክም ካለ…ሁሉንም ሰጥቶ እንጂ ግማሹን አስቀርቶ አይደለም። ስለዚህ እኔ ምንም አይነት ኮሚሽን አልፈልግም ብዬ ምላሽ ሰጠሁኝ። ከዚያ በአካባቢዬ ያሉትን እየሄድኩ ካርዳቸውን እያስገቡ እንዲለግሱ ሊንኩን በስልካቸው እየላኩኝ፤  በተለያየ አካባቢ ያሉትን ደግሞ በግሌና በ”በጎ ራዕይ” የፌስ ቡክ ገፅ በማስተዋወቅ 305 ሺህ 969 ብር ከ37 ሳንቲም ስብስቤ ለጋዜጠኛ ካሳሁን አሰፋ ባለበት ወ/ሮ ራሄል ቀለመወርቅ አስረክቤያለሁ። አየሽ ይሄ ገንዘብ ለዚህ ቤተሰብ ቀላል አይደለም።
ሁለተኛው የለገስከው ተቋም የኢትዮጵያ ልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል ነው አይደል?
ትክክል ነው። ከዚህ ተቋም ጋር የምተዋወቀው ገና የ11 ዓመት ህፃን እያለሁ ዶ/ር በላይ አበጋዝ ባቋቋሙት ጊዜ ነው። ያኔ በት/ቤት ፎርሞች እየወሰድን ለቤተሰብ እየሰጠን፣ ቤተሰብ የሚሰጠንን ብር ለማዕከሉ እንለግስ ነበር። ትልቅ ሆኜ አድጌ ብደግፈው የምለው ማዕከል ነበር። ያው ገንዘቡን ማሰባሰብ ቀላል አይደለም ትግል ይጠይቃል። ነገር ግን አንቺ አንድ ዓላማ ከያዝሽ  ያ ዓላማ ግቡን እስኪመታ ስትታገይ፣ በርቺ የሚልሽ እንዳለ ሁሉ የሚተችሽም በርካታ ነው። ሁለቱንም እየተቀበልሽ፣ አላማሽን ሳትሰለቺ ከጣርሽ ሁሉን ፈጣሪ ያሳካል።
እኔም በዚህ መንገድ ሁሉን በፅናት ችዬ እግዚአብሔር አሳክቶት፣ ከ29 ሺህ ዶላር (ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ) ለልብ ህሙማን ማዕከል መለገስ ችለናል። ነገ አገር የሚረከቡ ህፃናት ከባድ የልብ ህመም ውስጥ ሆነው ማየት ይረብሻል። እስካሁን ጥቁር አንበሳ ግቢ ውስጥ የሚገኘው ይሄው ማዕከል፤ እንደዚሁ እርዳታዎችን እያሰባሰበ እስካሁን ከ5 ሺህ በላይ ህፃናትን በነፃ አክሟል። ከ7 ሺህ በላይ ደግሞ ገና ወረፋ እየጠበቁ የሚገኙ ህፃናት አሉ። የእኛም ልገሳ የተወሰነ አስተዋፅኦ ያደርጋልና ደስተኞች ነን።
እንዳልኩሽ የ11 ዓመት ልጅ እያለሁ ነው ተቋሙን መለገስ የጀመርኩት። ት/ቤት እያለን የተለማመድነው ማለት ነው። ያ በውስጥሽ ሲያድግ እንዲህ ከፍ ብሎ እንዲመጣ መሰረት ይሆናል። ቅድምም አስተዳደጌን የጠየቅሽኝ ለዚህ መሆኑን ገልፀሽልኝ ነበር። የልቤን መሻትና ፍላጎቴን አይቶ እግዚአብሔር የአቅሜን ያህል በጎ እንዳደርግ ስለረዳኝና ልቤን ለዚህ ስለከፈተልኝ አሁንም አመሰግነዋለሁ። ያኔም ልጅ እያሁ ሰዎችን ስለመርዳት ሳስብ ተስፋው ነበረኝ። አንቺ መልካም ስታስቢ፣መልካም ለማድረግ ስትጠሪ እግዚአብሔር አቅም ይሆንሻል። በእኔም ህይወት እያየሁ ያለሁት ይሄንኑ ነው፡፡ አሜሪካ ከሄድኩ በኋላም አላረፍኩም። በሜሪ ጆይም፣ በመስራት በጎ አድራጎት ድርጅትም በሌሎቹም የምችለውን ሳደርግ ነበር፡፡ እነዚህን በጎ አድራጎት ድርጅቶች ስንደግፋቸው አሳዳጊ በማጣቴ ለውጪ ጉዲፈቻ ስንሰጣቸው ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውን፣ ማንነታቸውን ረስተው የሚያድጉ ዜጎቻችንን ቁጥር እንቀንሳለን፡፡ በአገራቸው፣ ከባህላቸው፣ ከወገኖቻቸው ከማንነታቸው ጋር እየተደገፉ ያድጋሉ። አገራቸውን ያገለግላሉ። ይሄ እሳቤ በደንብ መስፋትና መተግበር አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡
ይህንን የውጪ ጉዲፈቻ (ማደጎ) ለመቀነስ ብሎም ለማስቀረት ምን ዓይነት ሥራዎች ናቸው መስራት ያለባቸው?
እንደኔ እንደኔ፤ ሁላችንም ብንተባበር… ችግራችንን በራሳችን ለመፍታት የምናንስ ህዝቦች አይደለንም፡፡ እንደ ሙዳይ፣ ጌርጌሲዮን፣ መሰረት በጎ አድራጎትና ሌሎችም ቅንነትና በጎነት ስላላቸው ብቻ በትንሽ አቅም ብዙ መልካም ስራ የሚሰሩ ድርጅቶች በአገር ውስጥ ባለሃብቶችም ሆነ በዲያስፖራው በደንብ ሊደገፉ ይገባል የሚል ጠንካራ እምነት አለኝ፡፡ እነዚህ በጎ አድራጎት ድርጅቶች በዚህ መልኩ ተቋቁመው፣ በጎ የሚሰሩት ወገንተኝነት፣ ተቆርቋሪነትና ሃላፊነት ተሰምቷቸው እንጂ ግዜ ተርፏቸው አይደለም፡፡ እነሱ ይህንን ሀላፊነት ሲሸከሙና  ወገባቸው ሲጎብኝ እኔም  መደገፍ አለብኝ፡፡ ድጋፍ ማለት ብር መስጠት ብቻም አይደለም፡፡ ጉልበት፣ ሙያ፣ ጊዜ መስጠት በራሱ ድጋፍ ነው። ሀኪም በሙያው ሄዶ ያክም፣ የስነ ልቦና ባለሙያው፣ አስተማሪው፣ ሁሉም ያለውን ማዋጣት ይችላል፡፡ ይህንን ለማድረግ የሚያስፈልገው ቅንነትና መልካም ልብ ብቻ ነው፡፡ እንዲህ ስንተባበር አገራችን ላይ ለውጥ ማምጣት እንችላለን፡፡ ዲያስፖራው ለምሳሌ ለሁለት ወርም ይምጣ ለአንድ ወር ወይም ለ10 ቀን ይምጣ ቤተሰብ አይጠይቅ ወይም አይዝናና አይባልም። ነገር ግን ቢቻለው ከመጣባቸው ወራትና ቀናት ቢያንስ አንዷን ቀን ለበጎ አድራጎት ማዋል የሞራል ግዴታ ነው፡፡ የዜግነት ግዴታም ጭምር ነው፡፡ ሁሉንም መጎብኘት አይቻልም። ያደርጋሉ። ነገር ግን አንዱንና የመረጠውን በጎ አድራጎት ጎብኝቶ አይዟቹ አለንላችሁ ብሎ ለምን አንድ ዶላር አትሆንም፣ ሰጥቶ ቢመለስና ሁሉም ይህንን እንደ ባህል ቢይዘው … እርግጠኛ ነኝ ለውጥ እናያለን፡፡
በሌላ በኩል፤ አገራችን ውስጥ ብዙ ባለሃብቶች ለዚህ ተግባር ትኩረት ቢሰጡ፣ ችግራችን ውጪ አይወጣም ነበር፡፡ በእርግጥ እኔ እስከ ማውቀው፣ የkk ኩባንያ ባለቤት አቶ ከተማ ከበደ፣ወርቁ አይተነውና አትሌት ሀይሌ ገ/ስላሴ ልገሳ ያደርጋሉ። ነገር ግን እነሱ ብቻ አይደሉም። በሀገሪቱ ያሉት ባለሃብቶች ገንዘብ መሰብሰብ ላይ ብቻ የምናተኩርና ማህበራዊ ሀላፊነታችንን የማንወጣ ከሆነ፤ የሰበሰብነውን ሳንበላው መሰብሰብ( ጠብቆ ይነበባል) ይመጣል። በገንዘብ እንድትሰበስቢ የፈቀደልሽ አምላክ ለሌላው ካላከፈልሽ፣ ሳትበይው ሊሰበስብሽ ስልጣን አለው፡፡ አንቺ ገንዘብ ስትሰበስቢ፣ እንደ ኤጀንት ነሽ ማለት እንጂ ለብቻሽ እንድትበይ አይደለምና ማካፈል አለብሽ፡፡
አሁን ላይ አንድ ህፃን 2 ሚ.ብር መታከሚያ አጥቶ እየሞተ አንዳንድ ሀብታሞች በአንድ ቀን ምሽት በመሸታ ቤትና በአስረሽ ምችው ያንን ያህል ብር አጥፍተው ያድራሉ፡፡ ይሄ እንደ ሃገር ያማል። ቅድም ሰው በገንዘቡ የፈለገውን አያድርግ አይዝናና ማለቴ አይደለም፡፡ በሁሉም ነገር ውስጥ በጎ አድራጎትና ልገሳን ቦታ ያግኝ ነው የምለው፡፡ ያኔ ለውጥ ይመጣል ብዬ አምናለሁ እና ልናስብበት ይገባል፡፡
ድርጅትህ “በጎ ራዕይ”ም ሆነ ዲያስፖራው  ችግር የደረሰበትን ሰው ለማገዝ መስፈርታችሁ ምንድን ነው?
የመስፈት ጉዳይ አይደለም፡፡ ሰው እርዳታ ሲጠይቅ ለምሳሌ የህክምና እርዳታ ሲጠይቅ የህክምና ማስረጃው ትክክል ነው ወይ የሚለው መረጋገጥ አለበት፡፡ “Go fund me” ሲከፈት የዚያ ሰው የህክምና ማስረጃ  ትክክለኛ ስለመሆኑ ማረጋገጥ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ እኛ ውጪ ሆነን እዚህ ያሉ ተወካዮቻችን እንልክና ስለ ህክምናው ማስረጃ ትክክለኛነት እናረጋግጣለን፡፡ ይሄን የምልሽ ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ በርካታ “ጎ ፈንድ ሚ” እየተከፈተና ገንዘብ እየተሰበሰበ፣ መጨረሻ ላይ ገንዘቡ የት እንደሚገባ ሳይታወቅ የሚቀርበትን በርካታ አጋጣሚ እያየን ነው፡፡ “ጎ ፈንድ ሚ” ተከፍቶ የሚሰበሰበው ገንዘብ ለትክክለኛ ዓላማ ለትክክለኛው ተረጂ መዋል አለበት እንጂ የግለሰብ መጠቀሚያ መሆን የለበትም፡፡ ስለዚህ የደረሰን የእርዳታ ጥሪ ትክከለኛነት ተጠናክሮ ትክክለኛነቱ ተብጠርጥሮ ነው ጥሪውን የምንቀበለው፡፡ ዲያስፖራው ሆነ እዚህ አገር ያለው መለገስ ያለበት፣ እርዳታ ፈላጊው ትክክለኛ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ ነው። እንደ መስፈርት ከተቆጠረ መስፈርታችን ይሄ ነው፡፡
ከመጣህ ምን ያህል ጊዜ ሆነህ? ከጋዜጠኛ ካሳሁን ባለቤትና ከልብ ህሙማን ህጻናት መርጃ ማዕከል በተጨማሪስ የትኞቹን የበጎ አድራጎት ማዕከላት ጎበኘህ?
እኔ ከመምጣቴ በፊት በተወካዮቻችን አርቲስት ማስተዋል ወንደሰን በያያ ዘልደታ አማካኝነት ለጌርጌሴኖን የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል 500 ለሚሆኑ ሰዎች የምሳ ግብዣ አድርገናል፡፡ እኛ እዛ ሆነን እዚህ ባሉ ተወካዮች በኩል ድጋፉን እናድርግና ክትትል እናደርጋለን፡፡ የሆነ ሆኖ ሁሉንም ማዳረስ ባይቻልም አንዳንድ መጠየቅ ያለባቸውን ሄጄ አይቻለሁ፡፡ በዚያ ላይ የወደፊት ድጋፋችን ትክክለኛ እንዲሆን እስካሁን ከተቋቋሙት ማን ነው በቂ ድጋፍ ያለው? ማንስ ነው ያለ በቂ ድጋፍ በድካም ብዙ ስራ እየሰራ ያለው የሚለውን በመለየት ላይ ነን፡፡
ይህንን ካላየን በኋላ ድጋፍ የሌላቸው ላይ ትኩረታችንን አድርገን ለመስራት ነው እቅዳችን አሁን የሙዳይ በጎ አድራጎትን ብንመለከት የተረጂ ህጻናት እናቶች እዛው ግቢ ውስጥ የእጅ ስራ ውጤቶችን እየሰሩ እየሸጡ፣ በጣም በከፍተኛ ትግል  ነው እየሰሩ ያሉት አንዳንዶቹ ደግሞ በቂ ስፖንሰር እያላቸው አሁንም ወደ ልመናው ያዘነብላሉና እነሱን ለይቶ አቅም የሌላቸውን መደገፍ ላይ እናተኩራለን።  ሌላ ጊዮርጊስ አካባቢ “የብርሀን ልጆች”  የተባለ እየተቋቋመ ያለ ድርጅትም አለ፡፡ እነዚህንም እንደግፋለን፡፡
“በጎ ራዕይ” አወቃቀሩ ምን ይመስላል?
በቦርድ የሚተዳደር በአሜሪካ መንግስት እውቅና ያገኘ ነው። ስራውን ይበልጥ ቀልጣፋና የተደራጀ ለማድረግ፣ እዚያም ፈቃድ ለማውጣት በእንቅስቃሴ ላይ ነን። እሱን ሂደት እየሰራን ነው እርግጥ ነው በአሜሪካው ፈቃድ እዚህም መስራት እንደምንችል ተነግሮናል። ሆኖም የበለጠ ቀልጣፋ ተቀባይነት ያለው እንዲሆን ነው እዚህም ፈቃድ ለማውጣት የፈለግነው። ይሄም ይሳካል ብዬ አምናለሁ፡፡
በአጠቃላይ ግን የካሳሁንን ቤተሰብ ለመደገፍ ስንነሳ፣ መረጃ በመስጠት በሀሳብ ሲያግዙኝ ለነበሩት ለጋዤጠኞቹ ምስክር ጌታነው፣ በፍቃዱ አባይ፣ ትዝብት አሰፋ፣ሚካኤል አለማየሁ፣ ያያ ዘልደታ፣ አርቲስት ማስተዋል ወንደሰንንና ሳሬም ኢንተርናሽናል ሆቴልን ከልብ አመሰግናለሁ።


Read 3047 times