Print this page
Saturday, 06 February 2021 12:29

“አክስዮን ማህበሩ የሰጠው መረጃ ሃሰተኛ ነው”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    ኮራኮን ኮንስትራክሽን

           ቅዳሜ ጥር 22 ቀን 2013 ዓ.ም ለንባብ በበቃው ጋዜጣችሁ ላይ “የአዳማ ግንብ ገበያ ባለአክሲዮኖች መንግስት እንዲታደጋቸው ተማፀኑ” በሚል ርዕስ የቀረበው ዘገባ፤ በእውነተኛ መረጃና ማስረጃ ላይ ያልተመሰረተ ሲሆን የአንድ ወገን  ቅሬታ ብቻ ሚዛናዊነት በጎደለው መልኩ የተቀረበበት ነው። ከዚህ አንጻር በድርጅታችን ኮራኮን ኮንስትራክሽን ዙሪያ በዘገባው ላይ የቀረበውን ሀሰተኛ ውንጀላ መሠረት በማድረግ፣ እውነታውን በዝርዝር  እንደሚከተለው አቅርበናል።
ድርጅታችን ኮራኮን ኮንስትራክሽን፤ በአዳማ ግንብ ገበያ ግንባታ ላይ የተሳተፈውም ሆነ የግንባታውን ስራ ሲሰራ የቆየው በህግ ፊት ተቀባይነት ያለውን ውል ከአሰሪውና  ከአማካሪ ድርጅቱ ETG consultant ጋር በፈፀመው የሦስትዮሽ ውል መሰረት ነው። በዚህም መሰረት ግንባታው በሦስት ዙር (three phase) እንዲከናወን የጨረታ ሠነድ ተዘጋጅቶ ድርጅታችን ከቀረቡት የስራ ተቋራጮች መካከል አሸናፊ በመሆን  ስራው ሊሰጠን ችሏል።
 የመጀመሪያው ዙር የኮንትራት መጠኑ ቫትን ጨምሮ 60,226,998 (ስልሳ ሚሊዮን ሁለት መቶ ሃያ ስድስት ሺ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ስምንት ብር) የነበረ ሲሆን ለፕሮጀክቱ ስራ ማስኬጃ (ቅድመ ክፍያ) ሊከፈል የሚገባው የጠቅላላ ዋጋው ሰላሳ በመቶ (30%) ማለትም 20,768,099 (ሃያ ሚሊዮን ሰባት መቶ ስድሳ ስምንት ሺ ዘጠና ዘጠኝ ብር) ነበር። ይሁንና አክስዮን ማህበሩ በወቅቱ ያለኝ ገንዘብ 7,000,000 (ሰባት ሚሊዮን) ብር ብቻ ነው ቢለንም፣ እኛ የሚገባንን ክፍያ ሳናገኝ ወደ ስራ አንገባም አላልንም፤ ምክንያቱም አክስዮን  ማህበሩ ወደ ፊት የሚያመጣቸው አባላት “ከቦታችን ተባረርን ተገፋን” እያሉ የሚያለቅሱ ስለነበሩ “እንደውም ስራ ስንጀምር አባላቱ መዋጮ ያዋጣሉ፤ ያኔ ትከፍሉናላችሁ” በሚል ተስፋ በ6,000,000 (ስድስት ሚሊዮን ብር) ቅድመ ክፍያ ወደ ስራ ገብተን፣ ፌዙን ከብዙ ችግሮች ጋር ተጋፍጠን ጨርሰናል። ከችግሮቹ መካከል በተለይም ህንፃው ሊያርፍበት የታሰበው ቦታ በወቅቱ የግለሰቦች መኖሪያ በመሆኑና ነፃ ስላልነበር፣ በታሰበው ጊዜ ወደ ስራ ባለመግባታችን፣ በውለታው መሰረት ስራውን አጠናቀን ማስረከብ አልቻልንም። በተጨማሪም በጊዜ መራዘም ምክንያት ለተከሰተው የዋጋ ንረት በውሉ መሰረት ማካካሻ ክፍያ ለመጠየቅ ተገደናል።
ግንባታው የተጀመረው ህዳር 2003 ዓ.ም ሲሆን እንዲያልቅ የተሰጠው ጊዜ ሁለት ዓመት ነበር፤ ሊጠናቀቅ የቻለው ግን የካቲት 2006 ነው። አክሲዮን ማህበሩ በወቅቱ ሁለት አማራጭ ነበረው። አንድም ጨረታውን እንደ አዲስ አውጥቶ ሌላ ኮንትራክተር ማስገባት፤ ሁለትም የዋጋ ማካካሻ አድርጎ ከኛ ጋር እንዲቀጥል ማድረግ ነበር። አክሲዮን ማህበሩ ሁለተኛውን አማራጭ በመምረጥ የዋጋ ማካካሻ ዘግይቶ በመክፈሉ ለግንባታው መዘግየት የራሱ አስተዋፅኦ ነበረው። እንዲያም ሆኖ ውለታው በተፈጸመ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ስራውን ሙሉ በሙሉ (100%) አጠናቀን አስረክበናል።
ሀቁ ይህ ሆኖ ሳለ “…ተቋራጩ በ2 ዓመት ጊዜ ውስጥ ግንባታውን አጠናቆ ሊያስረክበን ቢስማማም በቃሉ ግን አልተገኘም፤ እስከ 2009 ዓ.ም ድረስ ሁሉም ሳይሳካ ቆይቶ የግንባታ ዋጋ ንሯል በሚል ተጨማሪ ማካካሻ 33 ሚ. ብር እንዲከፍሉ መገደደዳቸውን የአክሲዮን ማህበሩ አዲሱ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሽሬ ረሽድ ያስረዳሉ” በሚል ሃሰተኛ ዘገባ ቀርቧል፡፡ በአንድ በኩል በዚህ ሁኔታ የዘገየው አጠቃላይ የህንፃውን ግንባታ አስመስሎ የቀረበ ሲሆን፤ በሌላም በኩል ግንባታው እንደተባለው እስከ 2009 ዓ.ም ሳይሆን እስከ 2006 ዓ.ም ለአንድ ዓመት ነበር  የዘገየው፡፡ እሱም ቢሆን በኮንትራክተሩ ችግር ሳይሆን በአክሲዮኑ ችግር መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአክሲዮን ማህበሩ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ወዶና ፈቅዶ በስምምነት የከፈለውን የዋጋ ማካካሻ፣ተገዶ የከፈለ አስመስሎ የቀረበው ዘገባ የተሳሳተ ነው።
የሁለተኛውን ዙር ጨረታም እንደ መጀመሪያው በግልጽ ጨረታ ተወዳድረን በድጋሚ ገብተናል። ይሁንና የመጀመሪያውን ዙር ግንባታ ሙሉ በሙሉ አጠናቀን ያስረከብን ቢሆንም፣ 48ሚ ብር የሚሆን የመጨረሻ ክፍያ ለመክፈልም ሆነ ሁለተኛውን ዙር ግንባታ ለማስቀጠል የሚያስችል የገንዘብ አቅም አልነበረውም።
የሁለተኛው ዙር ኮንትራት መጠን ብር 191,233,090.08 (አንድ መቶ ዘጠና አንድ ሚሊዮን ሁለት መቶ ሰላሳ ሶስት ሺህ ዘጠና ብር) ሲሆን የተያዘለት ጊዜ አንድ ዓመት ነበር። አክሲዮን ማህበሩ ከነበረበት የፋይናንስ እጥረት አንፃር ይህን ስራ ለማስቀጠል የባንክ ብድር ማግኘት ነበረበት። የባንክ ብድሩንም ለማግኘት  የመጀመሪያውን ግንባታ ክፍያ ሙሉ በሙሉ መክፈሉን የሚያረጋግጥ የክፍያ ደረሰኝ እንዲያቀርብ ተጠየቀ። ቀደም ሲል እንደገለፅነው፤ ድርጅታችን አክስዮን ማህበሩን ለመርዳት ከነበረው ፍላጎት የተነሳ የፋይናንስ ችግሩን ለመቅረፍ ከባንክ የተጠየቁትን የክፍያ ሰነድ ማህበሩ ሳይከፈለን ከፍሎናል በማለት የብር 48,000,000 (አርባ ስምንት ሚሊዮን ብር) ክፍያ ደረሰኝ ቆርጠን በመስጠት ብድሩን እንዲያገኙ ተባብረናል። በዚህ ምክንያት የ100 ሚ ብር ብድር በማግኘቱ ቀደም ሲል ያልከፈለንን 48ሚ ብር ሊከፍለን ችሏል። ከዚህም በተጨማሪ በዚህ ዙር ለተሰሩ ስራዎች የ20 በመቶ ቅድመ ክፍያ መክፈል የነበረበት ቢሆንም፣ ስራው እየታየ እንዲከፈል በመስማማት ካገኘው ብድር ላይ 37.8 ሚ ብር ከአክስዮን አካውንት ውጪ ሆኖ የጋራ አካውንት ተከፍቶ እዚህ ውስጥ እንዲቀመጥና ስራው እየታየ እንዲከፈል በተደረሰው ስምምነት መሰረት ስራው እንዲንቀሳቀስ ተደርጓል። ይህን አሰራር የመንግስት ህግም ይፈቅዳል። በመሆኑም የሁለተኛው ዙር ግንባታ ጥር 2006 ተጀምሮ፣ ሚያዚያ 2008 ላይ ስራው 97 በመቶ (97%) ተሰርቷል።
ሀቁ ይህ ሆኖ ሳለ “… እነዚሁ አካላት ተመሳጥረው ለንብ ባንክ 40 ሱቆችን በ37 ሚ ብር ገዝተው ብሩን በማህበሩ አካውንት ቢያስገቡም፣ ያ 37 ሚ.ብር ከህግ አግባብ ውጪ ከቦርዱ ጋር ተቋራጩም ፈራሚ ሆኖ ከማህበሩ አካውንት ወጥቶ የት እንደደረሰ አይታወቅም” በሚል የቀረበው ዘገባ ሀሰት ነው።
የሶስተኛ ዙር የጨረታ ሁኔታ እንደ ሁለቱ ፌዝ በጨረታ የተወሰደ ሳይሆን የሁለተኛው ዙር ያልተጠናቀቁ ክፍያዎች እዳ ስለነበራቸው ይህን ክፍያ ለመክፈል ተጨማሪ ብድር ከባንክ ለመውሰድ ባንኩ ብድር የምሰጠው ህንፃው ወደ ስራ የሚገባ ከሆነ ነው በማለቱ ወደ ስራ ለመግባት ደሞ የሚቀረው የስራ ፐርሰንት ይታወቅ በመባሉ እና ሱቆቹን ወደ ስራ ለማስገባት የውጪው ስራ ማለቅ እና ለውጪ ስራ መገልገያ ይሆን ዘንድ የቆመው የእንጨት መወጣጫ (ፖንቴ) መፍረስ ስለነበረበት እና ስራን ለሌላ ኮንትራክተር ለመስራት የሚያመች ባለመሆኑ በነዚህ ምክንያቶች ሶስተኛው ዙር የውጪ ስራዎችንና የአንደኛ ፎቅ ፊኒሽንግ ስራዎችን አካቶ እንዲሰራ ማህበሩና አማካሪው ወስነው ድርድር ተደርጎ ለኛ ተሰጥቶናል። ይኸም ከአሰራር አንፃር ተቀባይነት ያለው ነው። የዚህ ዙር ግንባታ ሀምሌ 2007 ተጀመረ። አንድ አመት የስራ ጊዜ የተሰጠው ሲሆን ነሀሴ 2008 ተቋርጧል። ነገር ግን ስራውን 83 ፐርሰንት ሰርተናል።
ይሁንና ለሰራናቸው ስራዎች ማህበሩ መክፈል የሚጠበቅበትን የ2ኛ እና 3ኛ ዙር የግንባታ ሥራ በውላችን መሰረት በአማካሪ መሀንዲሱ የፀደቀውን ክፍያ ማህበሩ ባለመክፈል መሰረታዊ የውል ጥሰት (fundamental breach of contract) በመፈጸሙ የግንባታ ውሉ ተቋርጧል። አማካሪ መሀንዲሱ በድርጅታችን የቀረበለትን የክፍያ ጥያቄ በውሉ በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሰረት ጥያቄውን ከመረመረና በውሉ መሰረት የቀረበ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ በ28/8/2009 ዓ.ም የተፃፈና ስምምነት በሚቋረጥ ጊዜ የተረጋገጠ ክፍያ የምስክር ወረቀት (Certified Payment upon Termination) አጽድቋል። በዚሁ በጸደቀው የክፍያ ምስር ወረቀት ላይ በተረጋገጠው መሰረት ማህበሩ ብር 150,970,074.88 ብር (አንድ መቶ ሀምሳ ሚልዮን ዘጠኝ መቶ ሰባ ሺህ ሰባ አራት ብር ከሰማኒ ስምንት ሳንቲም) እንዲከፍል ድርጅታችን በማህበሩ ላይ በፌደራል ከፍተኛው ፍ/ቤት ግንቦት 22 ቀን 2009 ዓ.ም ክስ አቀረበ። ይህም በህግም በውሉም የተረጋገጠ መብታችን ነው።
ተከሳሹ ግንብ ገበያ አ/ማ በአማካሪ መሐንዲሱ የፀደቀውን የክፍያ ሰርተፍኬት አልቀበልም ብሎ በመቃወሙ ፍ/ቤቱ ድርጅታችን ለሰራው ስራ ሊከፈለው የሚገባው ክፍያ ስንት እንደሆነ፣ አስቀድሞ የተከፈለው ክፍያ ምን ያህል እንደሆነና ምን ያህል ያልተከፈለ  ቀሪ ክፍያ እንዳለ በገለልተኛ ወገን ተጣርቶ ይቅረብ የሚል ትእዛዝ በመስጠቱ፣ ለዚህም የመንግስት ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን እና ዲዛይን ሱፐርቪዥን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ይህንኑ አጣርቶ ሪፖርት እንዲያቀርብ በሰጠው ትእዛዝ መሰረት፣ ኮርፖሬሽኑ በታዘዘው መሰረት፣ የራሱን ባለሞያዎች፣ የግንብ ገበያ ንግድ አክስዮን ማህበር ከወከሏቸው ሁለት ባለሞያዎች እና ከኮራኮንም ሁለት ባለሞያዎች ቦታው ድረስ በመገኘት፣ የተሰራውን ስራ ጥራትና መጠን በመለካትና በመመልከት ልኬቱ የተወሰደ ሲሆን ላላለቁ ስራዎች  እነዚህም ጀነሬተር ፣ የውሃ ታንከርና ላልተጠናቀቀው የጣራ ስራ ባሉበት ልረከብ የሚል ጥያቄ አክስዮን ማህበሩ ለአጣሪው በማቅረቡ ያለቁት ስራዎች በልኬት ተለይተው ዋጋቸው ታውቆ፤ ያላለቁትን የማጠናቀቅያ ክፍያ ተቀንሶ የሁሉም ድርጅቶች ተወካይ ተፈራርመውበት ለፍ/ቤቱ ተልኳል።
ፍ/ቤቱም የቀረበለትን ሪፖርት መሰረት በማድረግ ተከሳሹ ግንብ ገበያ አ/ማ፡-
1ኛ፡- ለ2ኛ ዙር የግንባታ ውል ከሳሽ ሰርቶ ላጠናቀቀው ስራ ያልከፈለውን ብር 45,332,291.48 (አርባ አምስት ሚሊዮን ሶስት መቶ ሰላሳ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ዘጠና አንድ ብር ከ48/100) ከሚያዚያ 28/09 እስከ ግንቦት 30/2011 ዓ.ም ከሚታሰብ 9.5% ወለድ ጋር፣ እንዲሁም ክፍያ በመዘግየቱ ምክንያት በአማካሪ መሐንዲሱ የተሰላውን የካሳ ክፍያ ብር 5,264,247.67 /አምስት ሚሊዮን ሁለት መቶ ስልሳ አራት ሺህ ሁለት መቶ አርባ ሰባት ብር ከ67/100/፣ በድምሩ ብር 50,596,539.15 (ሃምሳ ሚሊዮን አምስት መቶ ዘጠና ስድስት ሺህ አምስት መቶ ሰላሳ ዘጠኝ ብር ከ15/100) ውሳኔ ከተሰጠበት ቀን ከግንቦት 30/2011 ዓ.ም ጀምሮ ተከፍሎ እስኪጠናቀቅ ድረስ ከሚታሰብ 9% ወለድ ጨምሮ እንዲከፍል ወስኗል።
2ኛ፡- ለ3ኛ ዙር የግንባታ ውል ከሳሽ ሰርቶ ላጠናቀቀው ስራ ያልከፈለውን ክፍያ ብር 7,228,284.83 (ሰባት ሚሊዮን ሁለት መቶ ሃያ ስምንት ሺህ ሁለት መቶ ሰማኒያ አራት ብር ከ83/100) ከሚያዚያ 28/2009 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ግንቦት 30/2011 ዓ.ም ጀምሮ ተከፍሎ እስኪጠናቀቅ ድረስ ከሚታሰብ 11% ወለድ ጋር፣ እንዲሁም ይህ ክፍያ ለዘገየበት ጊዜ በውሉ መሰረት አማካሪ መሐንዲሱ ያሰላውን የካሳ ክፍያ ብር 1,589,110.78 (አንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ሰማኒያ ዘጠኝ ሺህ አንድ መቶ አስር ብር ከ78/100)፣ በድምሩ ብር 8,817,395.61 (ስምንት ሚሊዮን ስምንት መቶ አስራ ሰባት ሺህ ሶስት መቶ ዘጠና አምስት ብር ከ61/100) ውሳኔ ከተሰጠበት ቀን ከግንቦት 30/2011 ዓ.ም ጀምሮ ተከፍሎ እስኪጠናቀቅ ድረስ ከሚታሰብ 9% ወለድ ጨምሮ እንዲከፍል ወስኗል።
3ኛ፡ የተጀምረው ያልተጠናቀቁ ስራዎችን በተመለከተ ብር 58,395,553.59 (ሃምሳ ስምንት ሚሊዮን ሶስት መቶ ዘጠና አምስት ሺህ አምስት መቶ ሃምሳ ሶስት ብር ከ59/100) ውሉ ከተቋረጠበት ከግንቦት 12/2009 ዓ.ም ጀምሮ  ተከፍሎ እስኪጠናቀቅ ድረስ ከሚታሰብ 9% ህጋዊ ወለድ ጋር ለፍርድ ባለመብት ሊከፍል ይገባል በማለት ውሳኔ ሰጥቷል።
ግንብ ገበያ አ/ማ ይህንን ውሳኔ በመቃወም ለፌደራል ጠ/ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ ቢያቀርብም፤ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤትም የከፍተኛውን ፍ/ቤት ውሳኔ አጽድቋል። ማህበሩ ግን በሁለቱ ፍ/ቤቶች ውሳኔ ቅር በመሰኘት ለፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ ያቀረበ ሲሆን፣ ያቀረበው የሰበር አቤቱታም ውድቅ ተደርጓል።
በዘገባው ላይ እንደተገለፀው፤ ማህበሩ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ከፍሎ ጠበቃ ቀጥሮ እስከ መጨረሻው የዳኝነት እርከን በመጓዝ ያቀረበው መሰረተ ቢስ ክርክር በፍርድ አደባባይ ውድቅ ሲደረግበት፣ የመገናኛ ብዙሃንን ደጅ በመጥናት፣ “ፍትህ ሲገባን የ151ሚ ብር ባለዕዳ እንድንሆን ተፈርዶብናል” የሚል አቤቱታ ማቅረብ የህግ የበላይነትን ማርከስ ነው፡፡
አክስዮን ማህበሩ ለጋዜጣው ክፍል በሰጠው ሀሰተኛ መረጃ፤ ከዚሁ ግንባታ ጋር በተያያዘ አቶ ጅብሪል ገረሱ ሀቢብ (የድርጅታችን የኮራኮን ኮንስትራክሽን ድርጅት ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ) ላይ የሙስና ክስ ተመስርቶ፣ ከሦስት ዓመት በፊት የመጣውን ለውጥ ተከትሎ፣ በፖለቲካ ውሳኔ እንደተፈቱ አድርጎ በማቅረብ አንባቢን ለማደናገር ጥረት አድርጓል። በእርግጥ ማህበሩ የኦሮሚያ ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በድርጅታችን ስራ አስኪጅ ላይ ክስ እንዲመሰረት የሰጠውን ሀሰተኛ ጥቆማ መሰረት በማድረግ በህግ ፊት ተቀባይነት የሌለው ክስ ተመስርቷል።
በኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት ምስራቅ ችሎት የነበረው ክስና የተሰጠው ውሳኔ በዘገባው ላይ ከቀረበው በእጅጉ የተለየ ነው። ይኸውም በዚህ ፍ/ቤት ከቀረበው የወንጀል ክስ ጂብሪል ገረሱን የሚመለከቱት ክሶች ከቀድሞ የቦርድ አባላት ጋር በመተባበር 1ኛ) የሁለተኛ ዙር ግንባታን በተመለከተ የአ/ማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ ሳይወስን የግንባታ ዋጋውን ቀድሞ ከተወሰነ በላይ ያላግባብ ብር 52,830,639 ለኮንትራተሩ እንዲከፈል በማድረግ፣ በግንባታ ውሉ ላይ የተገለፀው የበሮች ብዛት 188 ሆኖ ሳላ ያለ አግባብ ለ211 በሮች ክፍያ እንዲፈጸም በማድረግ ለብረት ስራ ያላግባብ ብር 13,589,965 በብልጫ እንዲከፈል በማድረግ፤ በጠቅላላ ጉባኤው የተሰጠው ውሳኔ የግንባታ ሥራው በሁለት ዙር እንዲጠናቀቅ የሚል ሆና ሳለ ያለ ጠቅላላ ጉባኤው እውቅና እንዲሁም ያለ ጨረታ 3ኛ ዙር የግንባታ ውል በብር 153,612,510 ውል በመፈራረም፣ ለ3ኛ ዙር ግንባታ የአልሙኒየም ክላዲንግ ሥራ ብር 8,521,755 ያላግባብ በአብላጫ እንዲከፈል በማድረግ ለራሳቸው የማይገባ ጥቅም ለማግኘትና አ/ማህበሩ ላይ ጉዳት ለማድረስ አስበው የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል፡-
2ኛ/ ከአንደኛው ዙር ግንባታ ብር 229,258,19 ያለ ቦርድ ውሳኔ አላግባብ እንዲከፈለው በማድረግ እንዲሁም ብር 4326,081,72 አማካሪ መሀንዲሱ ሳይጸድቅና ቦርድም ሳይወስን እንዲከፈል ብር በአ/ማህበሩ ላይ ጉዳት በማድረስ ያላግባብ የመበልጸግ ወንጀል ፈጽመዋል፡-
3ኛ/ በአንደኛው ዙር ግንበታ የዋጋ ማካካሻ ያላግባብ እንዲከፈለው በማድረግ በአ/ማህበሩ ላይ ጉዳት በማድረስ ያላግባብ የመበልጸግ ወንጀል ፈጽመዋል የሚል ነው፡፡
ይሁንና ፍ/ቤቱ ጉዳዩን በአግባብ መርምሮ በማስረጃ ካጣራ በኋላ በሰጠው ፍርድ የሙስና ወንጀል እና አላግባብ መበልጸግ ተብሎ በኮንትራክተሩ ላይ የቀረቡትና ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ክሶች ሙሉ በሙሉ መሰረተ ቢስ መሆናቸውን  በማረጋገጥ ውድቅ በማድረግ ኮንትራክተሩ ከወንጀሉ  ነጻ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ዓ/ህግ ለክሱ ዋና ማስረጃ አድርጎ ያቀረበው በኦሮሚያ የሥነ- ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን የመደበው ኦዲተር ተፈጸመ ስለተባለው ጉዳይ  አጥንቼ አገኘሁ ያለውን ጥፋትና የምርምር ኦዲት ሪፖርት ቢሆንም ፍ/ቤቱ ግን የተባለውን የኦዲት ሪፖርት ውድቅ በማድረግ ኮንትራክተሩ የፈጸመው የመሙስና ወንጀል የለም በማለት ወስኗል፡፡
ፍ/ቤቱ ኮንትራክተሩ ጥፋተኛ ነው ከዋጋ ማካካሻ ጋር ተያይዞ የቀረበውን ብቻ ነው፡፡ የዋጋ ንረት ማካካሻን በተመለከተ በመጀመሪያ ዙር ግንባታ የውል አልቀጽ GCC 47.1    መሰረት በወቅቱ የነበረው የሲሚኒቶና የብረት እጥረት ምክንያት በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ባወጣው አዋጅ መሰረት ተከፍሎናል፡፡ ይሄንንም በተመለከተ በኦሮምያ ፀረ ሙስና ቢሮ ክስ ቀርቦብን እኛም በወቅቱ የነበረውን  የሲሚንቶና የብረት እጥረት ከየፋብሪካዎቹ ጠይቀን የለንም ተባልን ማስረጃ ሲከታተለው ለነበረው ለኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምስራቅ ቋሚ ችሎት አቅርበን ፍርድ ቤቱም ከሙገር መግዛት የነበረባችሁን ከሞሰበ የገዛችሁት በደብዳቤ በጊዜው ለአሰሪዎቹም ሆነ ለአማካሪው አላሳወቃችሁም ስለዚህ የአካሄድ ችግር ነበር በማለት በአቶ ጅብሪል ላይ 6 ወር  የእስር ቅጣት ወስኖ የነበረ ቢሆንም ፍርዱ በሚሰጥበት ጊዜ ከዛ በላይ ታስረው ስለነበር ፍርድ ቤቱ ለቋቸዋል፡፡ ጥፋተኛም የተባለው አካሄድ ጋር ስህተት ተፈጽሟል በሚል እንጂ ኮንትራክተሩ ክፍያውን ለአግባብ ወስዷል ወይም ያለ አግባብ የመበልጸግ ወንጀል ፈጽመዋል ተብሎ አይደለም፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ በወቅቱ ሳይት ላይ የነበሩ የአማካሪው መሀንዲሶች የብረትና የሲሚንቶ  የጥራት ደረጃውን አስፈትሻችሁ እምጡና ስሩ መባላችንን እኛም የጥራት ማረጋገጫ አምጥተን የነበረ ቢሆንም በፍርድ ቤቱ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ውሳኔውን ባናምንበትም የህግ የበላይነትን በማክበር ተቀብለናል፡፡
ሀቁ ይህ ሆኖ ሳላ የአንባቢን ቀልብ ባልተገባ መልኩ ለመሳብ “በተለያየ ጊዜ በቦርዱ አባላት፣ በተቋጩና በአማካሪ ደርጅቱ ላይ ክስ መስርተን 9 የቦርዱ አባላትና ተቋራጩ በእስር ላይ የነበሩ ቢሆንም መንግስት የፖለቲካ እስረኞችን ሲፈታ በግርግር አብረው ወጥተዋል” በሚል የቀረበው ሀሰተኛ ዘገባ በህግ በሞራልም ተቀባይነት የሌለው አሳፋሪ ድርጊት ነው፡፡  
ፕሮጀክቱ አሁን ለደረሰበት ቀውስ ዋነኛ ምክንያት ምንድነው የሚለውን በተመለከተ አገር ያወቀውን ፀሀይ የሞቀውን እውነታ ለአንባቢ ለማጋራትና በተሳሳተ መረጃ ሀሰተኛ የሆነና ሚዛናዊ ያልሆነ ዘገባ ለማቅረብ የተሞከረው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ብዙዋቹ አንጡራ ሀብታቸውን በማፍሰስ የገነቡት አክስዮን እዚህ ደረጃ የደረሰበትን ትክክለኛ ምክንያት ለማድበስበስ ነው፡፡
የችግሩ ዋነኛ ምንጭ ግን በወቅቱ ከነበሩት የመጀመሪያ 11 የቦርድ አባላት ውስጥ ሁለት የቦርድ አባለት የሽልማት ሰጪ ኮሚቴው ያስቀመጠው የብር መጠን ያንሰናል የሌሎቻችሁ ከኛ የተሸለ ነው በማለት ያነሱት ቅሬታ ሰፍቶ ከቦርዱ ውጪ የነበሩ ስራው በመጠኛቀቅ ላይ በመሆኑ ወደ ሱቅ ክፍፍል ከመካሄዱ በፊት ቦታውን መያዝ አለብን የሚሉ የግል ጥቅም ፈላጊዎች ጋር በመሆንና በማናበብ ለህዝቡ ያሰቡ በማስመሰልና ለርክክብ የደረሰን ህንጻ ገንዘብህ ተበልቷል በማለት ነገሩን ሌላ መልክ እንዲኖረው በማድረግ የተጀመረ የሐሰት ወሬ እዚህ የደረሰ ችግር ነው፡፡
በዚህ ፕሮጀክት እዚህ ደረጃ እንዳይደርስ በኛ በኩል በቀላሉ እንዲፈታ ለማድረግ እነዚህን ሁለት የቦርድ አባላትና ሌሎቹን ለማስማማት ስንሞክር ሁለቱ የቦርድ አባላት የሚሰጡን መልስ ሌሎች ቦርዶች ለመመረጥ ስለተዘጋጁ ከስልጣናቸው ይውረዱ የሚል የሚል ነበር፡፡ ይሄንን በራሳቸው መንገድ ፈትተው አዲስ ቦርድ ተመረጠ፡፡ ሁለተኛ የተመረጡት ቦረውዶች ጋር በክፍያ እና በቀጣይ የፕሮጀክቱ እጣ ፈንታ ላይ ተወያይተን ቀሪ ክፍያዎች በ3 ዙር እንዲከፋፈልና ፕሮጀክቱም እንዲጠናቀቅ የተስማማን ቢሆንም ጉዳዩ እልባት ሳያገኝ ሲቀር ወደ ፍርድ ቤት ከመሄዳችን  በፊት ፍርድ ቤት ከሄድን በኋላም ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትእዘዝ መሰረት ሽምግልና ብንጠቀም ቦርዱና ኮንትራክተሩን በሙስና ከተከሰሱ ይጠፋሉ ግንዘቡ ይቀርልናል በሚል ሀሳብ ሽምግልናውን ሳይቀበሉ ቀርተዋል፡፡
በዚህም፣ ምክንያት ህንጻው በፍርድ ቤት ታግዶ እንዲቆይ ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ሰጥቶ ባለበት ሁኔታ በጉልበት አጥር አፍርሰው ወደ ህንጻው በመግባት ለግንባታ ስራ ያስገባነውን ግብአቶች እንዲጠፉና እንዲወድሙ በማድረጋችን በህግ የጠየቅን ሲሆን አሁንም በሂደት  ላይ ነው፡፡ ይህ ሁሉ እየሆነ ባለበት የፍትሀ-ብሔር ክሱ እየጠራ ሲመጣ አጣሪው አካል አጣርቶ ሲጨርስና ያሰቡት ነገር እንደማይሆን ሲገባቸው በወቅቱ የነበረው የቦርድ ሊቀ መንበር እና የህግ አማካሪ
(ጠበቃቸው) ገንዘብ (ጎቦ) ካልሰጣችሁን እያለ ሲያስፈራሩን ለህግ አመልክተን እጅ ከፍንጅ እንዲያዙ አድርገን ጉዳዩን አሁንም ህግ ይዞታል፡፡ ለሶስተኛ ጊዜ የተመረጡ ቦርዶች የተሸለ ነገር ከማምጣት ይልቅ የሁለተኛ ቦርዶች የጀመሩት የራስን ጥቅም የማግኛ ዘዴዎች በመጠቀም ለምሳሌ የአክሲዮን ማህበሩ ይሁንታ ሳያገኙ ሱቆቹን በአነስተኛ ኪራይ በማከራየትና ቁልፍ በመሸጥ የግል ንብረት ማፍራት ላይ በመስራት አክስዮኑን ለኪሳራ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ አሁን አለብን የሚሉት የባንክ ወለድ ዕዳና ለኮንትራክተሩ በወቅቱ  ባለመክፈላቸው የመጣ ቅጣትና ካሳ ጭቅጭቁ ከተነሳበት ጀምሮ ሲታይ ከ100,000,000 (ከአንድ መቶ ሚሊዮን) ብር በላይ ያደረሱትና ለኪሳራ የዳረጉት እነዚሁ ቦርዶች ናቸው፡፡ በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት ሀሰተኛ የሚዲያ ዘገባ መፍትሄ አይሆንም፡፡ አሁንም ለህዝቡ የሚያስብና ብቃት ያለው፤ ህዝቡን በቅንነት በታማኝነት ለማገልገል የተዘጋጀ የቦርድ አመራር ቢኖረው አክስዮኑ ካለበት ውድቀት መዳን ይቻላል ብለን እናምናለን፡፡

Read 1413 times
Administrator

Latest from Administrator