Sunday, 31 January 2021 00:00

"የአገሪቱ የቱሪዝም ፖሊሲ የሚያላውስ አይደለም"

Written by 
Rate this item
(0 votes)

· የቱሪዝሙን እንቅስቃሴ ለማዘመን የሚደረገው እንቅስቃሴ የተናበበ አይደለም
                · የዘንድሮ የጎንደር ጥምቀት ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ተስፋ የፈነጠቀ ነው


            በቱሪዝም ማኔጅመንትና በማርኬቲንግ ማኔጅመንት ዘርፎች ሁለት ዲግሪዎችን  የተቀበሉት አቶ ደሳለኝ ይልማ፤ በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ዘርፍ ውስጥ ከ10 ዓመታት በላይ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በጎንደር ከተማ እምብርት ላይ በሚገኘው AG ሆቴል በሥራ አስኪያጅነት እያገለገሉ የሚያገኙት አቶ ደሳለኝ፤የአገራችን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ  ያለበት ሁኔታ እንደሚያንገበግባቸው ይናገራሉ፡፡ ለምን ? ቱሪስቶች ወደ እኛ አገር የሚጎርፉት  አያት ቅድመ አያቶቻችን በሰሩልንና ተፈጥሮ በለገሰችን ስጦታ እንጂ እኛ ምንም የጨመርነው ነገር ኖሮ  አይደለም የሚሉት ባለሙያው፤ነባሮቹን ቅርሶቻችንን እንኳን በቅጡ መንከባከብና መጠበቅ አልቻልንም ሲሉ ክፉኛ ይወቅሳሉ፡፡ የቱሪዝም ፖሊሲውንም እግር ከወርች የሚያስር ነው ሲሉ ይተቹታል፡፡ ችግር መንቀስ ብቻ ሳይሆን መፍትሄም ያቀርባሉ፡፡ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ተስፋ የሚያስቆርጥ እንዳልሆነም ያምናሉ፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ሰሞኑን ለስራ ወደ ጎንደር በተጓዘችበት ወቅት፣ በኮቪድ-19 ክፉኛ ስለተጎዳው የቱሪዝም ኢንዱስትሪው፣ ለጥምቀት በአገር ውስጥ ቱሪስቶች ስለተነቃቃችው ጎንደር፣ ስለ ወደፊቱ የቱሪዝም ዕጣ ፈንታና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ  አቶ ደሳለኝ ይልማን አነጋግራቸዋለች፡፡ እነሆ፡-

               እርስዎ በትምህርት ዝግጅትዎም ሆነ በስራ ልምድዎ በቱሪዝም ዘርፉ ለረጅም ጊዜ የቆዩ እንደመሆንዎ፣ የአገሪቱ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ያለበትን ሁኔታ እንዴት ይገመግሙታል?
የአገራችን ቱሪዝም ብዙ ይባልለታል። በዘርፉ የተሰማሩ ሙያተኞች በጥናት አገኘነው ያሉትን ብዙ ነገር ይላሉ። ነገር ግን አዲስ ነገር አይደለም። ለአገሪቱ ወሳኝ ኢንዱስትሪ መሆኑን ለማወቅ ብዙ ጥናትና ምርምር አያስፈልገውም። ይሁን እንጂ የሚባልለትን ያህል ኢንዱስትሪው እንዲያድግ፣ የሚፈለገውን ያህል ገቢ ለአገሪቱ እንዲያመጣ ስራ ተሰርቷል ወይ ስንል፣ አሁንም ጉዳዩ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይገባል።
እስቲ ምንድን ነው የጎደለው? ዘርዝረው ሊነግሩን ይችላሉ…?
በቀላሉ ምሳሌ ላቅርብልሽ። ያሉንን ወርቅ ወርቅ የሆኑ ቅርሶችን መመልከት እንችላለን። የጥንት አባቶቻችን አእምሯቸውን ጨምቀው የሰጡንን ቅርሶች መጠበቅ እንኳን አልቻልንም። መንከባከብና መጠገን ላይ እንኳን ዳተኛ ነን። ቅርሶቻችንን ተጠቅመን ቱሪዝሙን ለማሳደግ፣ የሚመጣው ቱሪስት እዚህ ቆይቶ ገንዘቡን እዚሁ ጨርሶ እንዲሄድ ለማድረግ በዘርፉ በቂ አገልግሎት እየሰጠንም አይደለም።
ቀድሞ ከነበሩት ውጪ አዳዲስ የቱሪዝም ፕሮዳክቶችን ከመስራትና ከማስተዋወቅም አንፃር እዚህ ግባ የሚባል ነገር አልሰራንም። አንድ ቱሪስት ሲመጣ የተለመዱ ቦታዎች ይጎበኛል፡፡ አንዳንድ ቦታ የስጦታ እቃዎች ይሸጣሉ፡፡ በቃ። በዚህ መሃል ቱር ኦፕሬተሮች፣ የጉብኝት ሳይቶችና ቱር ጋይዶች የተወሰነ ነገር ያገኛሉ። ቱሪስቱ ቶሎ ይመለሳል። ሁላችንም የየድርሻችንን ብንሰራ ኖሮ ግን ከዚህም በላይ የምናገኝበት ዕድል ሰፊ ነበር። እንዴት ካልሽኝ አዳዲስ ፕሮዳክቶችንና የጉብኝት ሳይቶችን በመፍጠር ቱሪስቱ እነዛን ለማዳረስ ሲል ይቆያል፣ አገልግሎቶችን በማዘመን ይበልጥ ሳቢና ማራኪ በማድረግ፣ ቱሪስቱ ለበለጠ ቆይታ እንዲነሳሳ በማድረግ፣ ይበልጥ ተጠቃሚ መሆን እንችል ነበር። ግን አልሰራንም፡፡
ግን እኮ የቱሪስቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል --ከኮቪድ-19 በፊት ማለቴ ነው--
እውነት ነው፤ ቱሪስቱ ገፍቶ ወደ እኛ ይመጣል። ቁጥሩም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነበር፡፡ ይሄ የሆነው ግን አያት ቅድመ አያቶቻችን በሰሩት ነባር ሰው ሰራሽ ቅርሶችና ተፈጥሮ በቸረችን ስጦታዎች እንጂ እኛ በዘመናችን የሰራነው አዲስ ነገር ኖሮ አይደለም። ታዲያ እነዚህን ብዙ ቱሪስት ስበው የሚያመጡልንን ቅርሶች እንኳን በአግባቡ እየጠበቅናቸውና እየጠገንናቸው አይደለም። የቱሪዝሙን እንቅስቃሴ ለማዘመን የሚደረገው እንቅስቃሴና ትብብር እንኳን  የተናበበ አይደለም። አይደለም ዓለም ከደረሰበት፣  በአፍሪካ ደረጃ እንኳን ተወዳዳሪ ለመሆን ገና ብዙ ይቀረናል። እነ ኬንያን፣ ታንዛኒያን፣ ግብፅን ብናይ …እንኳ እኛ በጣም ወደ ኋላ የቀረን ነን።
በዘርፉ በቂ የሆነ ሙያተኛ አለ ወይ ስንል ሌላ ጥያቄ ነው። ዩኒቨርሲቲዎች  በርካታ ሰው ያስመርቃሉ። የሰው ሀይል ብክነት ነው ለኔ። ምክንያቱም የቱሪዝም ፕሮዳክቱ ዳይቨርሲፋይድ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ ከሚመረቁት ጥቂቶቹ  ቱር ጋይድ ይሆናሉ ወይ በተወሰኑ ቦታዎች ላይ ይሰራሉ፤ ይሄው ነው። በሌላ በኩል፤ ሁሉም ነገር አዲስ አበባ ላይ ነው ያለው፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉ የቱሪዝም ባለሙያዎችም እየተጠቀሙ አይደለም። በክልል ደረጃ እንኳን ቱር ኦፕሬተር ለመክፈት የሚያስችል አሰራር አልተዘረጋም። ይህን ስትመለከችው ቱሪዝሙን አሳድገነዋል፤ ቱሪዝሙን በለባለሙያ እንዲመራ አድርገነዋል ለማለት ይቸግራል። በተለይ ደግሞ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታትም ሆነ ከዚያ ወዲህ ባለው ጊዜ፣ ሙያተኞች ቦታቸው ላይ እንዲቀመጡ ከማድረግ አንፃር ብዙ የሚቀሩ ነገሮች አሉ። ሙያተኞች ወደ ላይ ወጣ እንዲሉና ቦታቸውን እንዲያገኙ የማድረግ ጅምር ግን በትንሹ ታይቷል፤ ግን በጣም ይቀረዋል። በአጠቃላይ ከበጀት አመዳደብ ጀምሮ ለቱሪዝሙ የተሰጠውን ትኩረት አናሳነት በግልፅ መመልከት ይቻላል።
ከላይ ለጠቀሷቸውና በግልፅ ለሚታወቁት የኢንዱስትሪው ችግሮች  ሃላፊነቱን የሚወስደው ማን ነው ይላሉ? የግሉ ዘርፍ ወይስ መንግስት? ወይስ--?
ወደ ፖለቲካው  ለመግባት ሳይሆን የኢትዮጵያን ፖለቲካ እንዲህ የተዛባና የተቃወሰ እንዲሆን ያደረገው ማነው? ስንል ከህገ-መንግስት ቀረፃው ጀምሮ እንደምንለው ሁሉ፣ፖሊሲም ትልቅ ቦታ አለው። የቱሪዝም ፖሊሲው በራሱ የሚያሰራና የሚያላውስ አይደለም። የሚወራውና በተግባር ያለው ነገር ፍፁም አይገናኙም። ስለዚህ ሃላፊነቱን መውሰድ አለበት ብዬ የማምነው መንግስት ነው።  መንግስት በዚህ በኩል አልሰራም። መንግስት ለሚዲያ ፍጆታ የሚሆን ነገር ከማውራት ውጪ መሬት የወረደ፣ የሚዳሰስና የሚጨበጥ ስራ አልሰራም። ይሄ ማለት ባለ ድርሻ አካላት በየደረጃው ኃላፊነት የለባቸውም ወይም ኃላፊነት አይወስዱም ማለት አይደለም። ቢሆንም ባለድርሻ አካላትን የሚመራው፣ መንገዱን የሚያመቻችለት፣ ፖሊሲ የሚቀርጽለት ደንብና መመሪያ የሚያወጣለት መንግስት ነው። ስለዚህ የችግሩን 80 እና 90 በመቶ ሃላፊነት የሚወስደው መንግስት ነው።
ስለዚህ ጎንደርም ካላት ታሪክ፣ በዩኔስኮ ካስመዘገበችው ቅርስ፣ ከጥንታዊነቷ ወዘተ አንፃር መጠቀም የነበረባትን ያህል ያልተጠቀመችው --- ከላይ ከገለፁት ተግዳሮት ጋር ይገናኛል?
አዎ በደንብ ይገናኛል። ጎንደርም የኢትዮጵያ አንድ አካል ናትና… ያው ቱሪዝሙ እንዳልኩሽ፤ ቀደም ብሎ በተሰራ ስራና በተፈጥሮ ፀጋ ሃይል ነው ያለው። ጎንደርም ያለውም ይሄው እውነታ ነው። ቱሪዝሙ አንዴ ተስፋ አስቆራጭ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ልባችንን የሚያሞቅ ሆኖ ነው የቀጠለው። በተለይ ባለፈው ዓመት ሁላችንም እንደምናውቀው፤ በባህረ ጥምቀቱ የተከሰተው አደጋ አስደንጋጭና ተስፋ አስቆራጭ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ኮሮና ቫይረስ ተከትሎ፣ የቱሪዝም እንቅስቃሴውን ዜሮ ወደሚባል ደረጃ አወረደው፡፡ እነዚህን ክስተቶች ተከትሎ፣ በዘንድሮው ጥምቀት ቱሪስት ይመጣል አይመጣም የሚለው ነገር ለሁላችንም ጭንቀት ነበር። አከራካሪም አነጋጋሪም ሆኖ ቆይቶ ነበር። የሆነውና ያየነው ነገር ከላይ የገለፅኳቸውን ስጋቶች፣ ጭንቀቶችና ክርክሮች እንደ ጉም ያተነነ ሆኖ ነው ያለፈው። እንደውም ለቱሪዝሙ አዲስ ተስፋ ነው የፈነጠቀው።
ምን አይነት ተስፋ?
እስከ ዛሬ የነበረውን በውጭ ቱሪስት ላይ የመመካትን ነገር አስወግዶ፣ የአገር ውስጥ ጎብኚ ላይ እንድናተኩርና አይናችንን እንድንጥል የሚያደርግ አዲስ ተስፋ ነው የፈነጠቀው፡፡ ጥምቀትን ለማክበር የመጣው ቱሪስት በሙሉ ኢትዮጵያዊ ነው። ከውጪም የመጣው ዲያስፖራ የአገር ልጅ ነው። ከመላው ኢትዮጵያ ጥምቀትን ለማክበር ጎንደር የከተመው ወንድም ህዝብ ነው። ከዚህ በላይ ተስፋ ከየት ይገኛል። ይሄ በጣም የሚያስደስት ነው። ከሚጠበቀው በላይ ነው ሰው የመጣው። ስለዚህ ለጎንደር ቱሪዝም እጅግ ተስፋ ሰጪ ነው። ይህን ተምሳሌት በማድረግ፣ መንግስት ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ፣ የአገር ውስጥ ቱሪዝሙ ላይ ለመስራት ፍኖት የፈነጠቀ ጉዳይ በመሆኑ ልናስብበት ይገባል።
እንዲያውም በዚህ አጋጣሚ፣ ከጥምቀቱ ጎን ለጎን፣ በአገር ውስጥ ቱሪዝም ዙሪያ የፓናል ውይይት ማዘጋጀት ይቻል ነበር። ሌሎች የምክክር መድረኮችንም ማዘጋጀት ይቻል ነበር። ይሄ እድል አምልጦናል ግን አሁንም ከታሰበበት መደረግ የሚችል ነው። የሆነ ሆኖ የዘንድሮ የጥምቀት በዓል፣ በብዙ መልኩ ተስፋ ፈንጣቂ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
ኮቪድ- 19 ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ከተጎዱ ዘርፎች  አንዱ ቱሪዝም ነው። በተለይ ሆቴሎች በእጅጉ ተጎጂዎች ነበሩ። ይህንን ችግር እንዴት ተቋቋማችሁት? የሆቴል ማህበሩ ምን ሲሰራ ቆየ?
እውነት ነው፡፡ በጎንደርም በክልሉም ሆነ በአጠቃላይ እንደ አገር ዘርፉ ክፉኛ ተጎድቷል። በተለይ ሆቴሎች ከፍተኛ ጉዳት ነው የደረሰባቸው። ሰራተኛ ለመቀነስ የተገደዱ፣ ሙሉ ለሙሉ ሆቴሎቻቸውን የዘጉም ሁሉ ነበሩ።  እንደ AG ሆቴል ከጠየቅሽኝ፣ ለሰራተኞች እረፍት እንሰጥ ነበር። ደሞዛቸውን ሳንከለክል እያረፉ በየተራ ወደ ስራ እንዲገቡ እናደርግ ነበር። ከዛ ውጪ ሰራተኛ አልቀነስንም፣ አላሰናበትንም። ያንን ስናደርግ ቆይተን ከመስከረም በኋላ በተወሰነ መልኩ እንቅስቃሴ ሲጀመር፣ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ መልሰናቸዋል። ይሄ ሲባል ግን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ምንም ትርፍ ሳይኖረን ነው ስንሰራ የቆየነው። እንደ ሆቴል ማህበር ደግሞ ንግግርና ውይይት እናደርግ ነበር። ማህበረሰባችንን ብትመለከቺው፤ በተፈጥሮው ባህል፣ እምነት፣ ተስፋ ያለው ማህበረሰብ ነው። በዚህ ምክንያት ሰው በተፈጥሮው ምንም አይነት ችግር ቢመጣ ያልፋል ብሎ በትዕግስት የመጠበቅን ነገር የተላበሰ ነው። እንደ ሆቴል ማህበርም እንደ ቱሪዝም ባለሙያም፣ ከዚህ በፊት የነበሩና የተከሰቱ ችግሮችን በማስታወስ የታለፈበትን ልምድ እያነሳን፣ በፅናት ማለፍ አለብን በሚል እንነጋገር ነበር። ለምሳሌ በ1990 እና በ1991 በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜ እንዲሁ የቱሪዝሙና የሆቴል ኢንዱስትሪው የተዳከመበት ጊዜ ነበር። የአሁኑን ግን ለየት የሚያደርገው “ዝምተኛ ገዳይ” (Silent killer) መሆኑ ነው። ሳይታሰብ መጥቶ ሳይታሰብ እየገደለ ያለ መሆኑ ነው ልዩ የሚያደርገው። እና ይሄ ደግሞ ዓለም አቀፍ ችግር በመሆኑ ዓለም ራሱ መፍትሄ ያመጣለታል በሚል ተስፋ ነበር የቆየነው። ወይ ሙሉ ለሙሉ መድሃኒት አለበለዚያ ክትባት ይገኝለትና እንፈወሳለን፤ ካልሆነም ሰው ይላመደውና የበሽታው የመግደል አቅም እያነሰ ይሄዳል፤ ወደ ቀድሞው ሁኔታችንም እንመለሳለን እያልን፣ እርስ በእርስ እየተጽናናን ነው የቆየነው።
በመንግስት በኩልስ የተደረገ ድጋፍ አለ?
እውነት ለመናገር  መንግስት ለሆቴሎች የመደበው ወደ 3 ነጥብ ምናምን ቢሊዮን ብር ብድር ነበር። እሱ ተሸራርፎም ቢሆን ንግድ ባንክ ላይ ያለው መስፈርት ጠበቅ ያለም ስለነበር፣ ትንሽ ትንሽ ብር በብድርና በእፎይታ የማግኘት ዕድል ገጥሞናል። ቱር ኦፕሬተርና ባህል አካባቢ ይሰሩ የነበሩትን፣ የሰው እንቅስቃሴም ሆነ መሰባሰብ ስለማይፈቀድ ቱር ጋይዶችም ቱሪስት ስለሌለ፣ ከእጅ ወደ አፍ የነበረው ኑሮአቸው በእጅጉ በሚያሳዝን ሁኔታ ነው የተጎዳው፡፡ ለምን ብድር አያገኙም ሲባል ኮላተራል (መያዣ) ስለሌላቸው ያንን ማድረግ አይቻልም ተባለ፡፡ ይሄው ከአንድ ዓመት  በላይ ያለ ምንም ድጋፍ፣ ማንም ዞር ብሎ ሳያያቸው ወድቀው ነው ያሉት። ይሄ በእጅጉ የማዝንበትና ልቤን የሚያደማው ነገር ነው፡፡ ይሄ መቼ ያልፋል? ቱሪስት መቼ ይመጣል? እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም፤ ግን ተስፋ እናድርጋለን። በተለይ የአገር ውስጡን ቱሪስት ማነቃቃት ከተቻለ፣ ሁኔታዎችን በመጠኑ ማሻሻል ይቻላል፡፡ ለምሳሌ የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ስብሰባ እዚህ  ጎንደር ተዘጋጅቶ፣ ከተለያየ አካባቢ ወደ ሁለት ሺህ ሰው መጥቶ ነበር። ይሄ ከተማውን ለማነቃቃት የተደረገ ነው። በመጠኑ አነቃቅቶንም  ነበር። የጥምቀት በዓል ከዛም የጎንደር ዩኒቨርስቲ ከ7 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በጥምቀት ማግስት ማስመረቁ፣ ለከተማው ድንቅ ነገር ነበር። ይሄ ሳይበርድ የተለያዩ ኢንቨስትመንቶች በማዘጋጀት ከተማው እየተነቃቃ እንዲቆይ ቢደረግ፣ የውጪ ቱሪስት እስኪመጣ ድረስ እፎይታን ይሰጣል የሚል እምነት አለኝ፡፡
የአገር ውስጥ ቱሪዝሙን ከማነቃቃት አንጻር በጥምቀት በዓል ላይ እንደ እንቅፋት የተነሳ ነገር አለ፡፡ የሆቴሎች የአልጋ ኪራይ ዋጋ ያለ ቅጥ ማሻቀብ ነው፡፡ ይሄንን እንደ ቱሪዝም ባለሙያና እንደ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ እንዴት ያዩታል? ቱሪስቱን የሚያሸሽ አይሆንም?
እውነት ነው፤ የጎንደር ህዝብ ባለማተብ ነው፡፡ ጥያቄው ወሳኝ ነው፡፡ ጎንደር ካላት ክብር፣ከሚጠበቅባት ነገርና የህዝቡ ስነ- ልቦና አንጻር እንዲህ አይነት ክፍተቶች ገጽታዋን ያበላሻሉ፤ ክብሯንም ዝቅ ያደርጋሉ በሚል ተቆርቋሪነት ጭምር ጥያቄውን ያነሳሽው ይመስለኛል፡፡ ጉዳዩም የሚካድ አይደለም፡፡ ጭማሪ ተደርጓል? አዎ! ጭማሪዎቹ ከተጠበቀው በላይ ናቸው? አዎ ናቸው!! ለምሳሌ እኛ ጭማሪ እናደርጋለን ብለን እንደ ማኔጅመንት ስንወያይ፣ በጣም ትንሽ ጭማሪ ለማድረግ ነው የተስማማነው፤ ምክንያቱም የሚመጣው ሀበሻ ነው፤ የውጭ ቱሪስት የለም፡፡ በፊት ቱሪስት እያለ ዓለም አቀፍ ሁነቶች ሲካሄዱ ጭማሪዎች ይደረጋሉ። በዓለም ላይ የታወቀና ያለ ነገር ነው፡፡ ሆኖም ዘንድሮ የመጣው በሙሉ ሀበሻ ነው፡፡ የሚመጡት ወገኖቻችን ናቸው፡፡ ብንጨምር እንኳን ትንሽ በማይጋነን ሁኔታ መሆን አለበት ብለን እንደ ማኔጅመንት መክረናል፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሀላፊዎችም ጭማሪ አንዳታደርጉ ይላሉ፡፡ በቀደሙት ዓመታት ቱሪስቶች በነበሩበት ጊዜ አትጨምሩ የሚባለው ነገር ትክክል አይደለም፡፡ ነገር ግን እንዴት ነው የሚጨመረው? በስንት ፐርሰንት ነው? በሚለው ላይ ነው መነጋገር ያለብን። አሁን ግን ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን ሲመጡ በተለይ ትንንሽና ደረጃቸውን ያልጠበቁ በ150 እና በ200 ብር ይከራዩ የነበሩ ፔኒሲዮኖችና የሆቴል አልጋዎች ወደ 1500 እና 2000ብር  ሲገቡ፣ የሚያሳፍርም  የሚያስደነግጥም ነው፡፡ ቅድም እንዳልሽው፤ ለከተማው ክብርና ለህዝቡ ስነ ልቦና የማይመጥን ነው፤ ያሳዝናል፡፡ አሁን እኛ ደረጃውን የጠበቀ ሆቴል ይዘን በአዘቦት ቀን 800 እና 600 ብር እናከራይ የነበረውን 1ሺህ 300 እና 1500 ብር ብናከራይ ምክንያታዊ ጭማሪ ነው ይባላል፡፡ አልጋችን  ደረጃውን የጠበቀ ነው፤ አገልግሎታችንም ቀልጣፋ ነው፤ አልጋ ለያዙ ቁርስ በነፃ እናቀርባለን፤ ብዙ ነገሮች አሉ። ተራ ቤቶች በአግባቡ መጸዳጃ ቤት እንኳን የሌላቸው ግን ይህን ሲያደርጉ ሲታይ ይሄ በጣም አስደንጋደጭ ነው፡፡ በበኩሌ እንደ AG ሆቴል ሀላፊነታችንን በአግባቡ ስለተወጣን በጣም ነው ደስ የሚለኝ፤ እንግዶቻችን ሳይማረሩ፣ ጥሩ አልጋ ላይ ተኝተው አገልግሎት ሳይጓደልባቸው፣ በመሄዳቸው የምሬን ነው የምልሽ ኩራት ይሰማኛል፡፡ ሌሎችም አሉ፤ ትላልቅና ዘመናዊ አልጋ፣ ደረጃውን የጠበቀ ሆቴል ይዘው “ቱሪስት ይምጣ እንጂ ምንም ጭማሪ አናደርግም” ብለው በቀደመ መደበኛ ዋጋቸው፣ እንግዳ ተቀብለው አስተናግደው የሸኙ፡፡ እነሱም ክብርና ሽልማት ይገባቸዋል፡፡ ጎንደር ዘላቂ የሆነ የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲኖራት ለማድረግ፣ መንግስት በህገ-ወጦች ላይ እርምጃ መውሰድ አለበት ብዬ አምናለሁ። በከተማው ህግና መመሪያ፣ ለበዓሉ ከተሰጠው አፅንኦትና ከነበረው ገፅታ አንጻር ተነስቶ መንግስት ቢያንስ ግሳፄ ማድረግ አለበት። ይሄ መደገም የለበትም። በሌላ በኩል እንግዶች ተቀብለው አግባብ ያለው ጭማሪ አድርገውም ሆነ ጭማ ሳያደርጉ አስተናግደው የሸኙትን በመሸለምና በማወደስ፣ አጥፊዎቹን የስነ- ልቦና ጫና ውስጥ መክተት ይቻላል። የግድ ቅጣት ብቻ አይደለም  የሚያስተምረው፡፡
በመጨረሻም፤ሙያተኞች በመንግስት ሀላፊነት ላይ ብቻ ሳይሆን በየቦታው አሉ፤ ገንቢ ሀሳብ ማዋጣት ይችላሉ፤በሚል መጥታችሁ ስላነጋራችሁኝ ፣አንቺንና ዝግጅት ክፍሉን በእጅጉ አመሰግናለሁ፡፡


Read 2118 times