Monday, 01 February 2021 00:00

“ብርቱ ፉክክርና የተረጋጋ ሰላም

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

       የኢትዮጵያ የምርጫ እንቆቅልሽ!

    ---------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

      1. በ1997 ዓ.ም ምርጫ፣ ሃይለኛ ፉክክር ነበር። ግን በሰላም አላለቀም። በረብሻና በአፈና፣ በአመጽና በግድያ እንጂ።
      2. የ2007 ምርጫ፣ ሰላማዊ ነበር። ነገር ግን፣ ያን ያህልም ፉክክር አልታየበትም። ገዢው ፓርቲ 100% አሸንፏል።
     ----------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------          
            “ሂሳብ” የሚለው ቃል፣ ብዙ ሰዎችን አይማርክም። ምናልባት “ሂሳብ መቀበል” ብለን ካላቆነጀነው በስተቀር ማለቴ ነው። “ሂሳብ መክፈል”ብለው ማሰብ ይደብራቸዋል፡፡ የብዙ ሰዎች ፍርሃት ግን፣ ከዚህ ይለያል።ከዚህ ይብሳል፡፡
ቁጥር፣ ስሌት፣ ቀመር፣… የሂሳብ ሳይንስ ነው፤ “አለርጂክ” የሚሆንባቸው። ያሳዝናል። ብሩህ የእውቀት መንፈስን ለማላበስ የሚችል ነው የሂሳብ ሳይንስ፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው? በተውገረገረ የትምህርት ይዘትና በሰንካላ የማስተማሪያ ዘዴ፤ በመልመጃ ጥያቄዎች ንፍገትና ቀሽምነት ሳቢያ፣ተበላሸ፡፡ እናም፣ ለብዙ ህፃናት፣የሂሳብ ትምህረት መሳቀቂያ ሆኗል። ለብዙ አዋቂዎች  ደግ መጥፎ ትዝታ ነው። የሂሳብ ነገር፣ ለጊዜው ብንተወው ይሻላል?
ደግሞስ፣ስለ ምርጫና ፉክክር፣ ስለ ሰላምና ቀውስ ለመናገርስ፣ የሂሳብ ምሳሌ ምን ያደርጋል?
እንግዲውስ፤ በሌላ ምሳሌ እንጀምር። ማንኛውም ግንዛቤ፣ ማንኛውም ትክክለኛ ሃሳብ፣ቁንፅል መረጃ አይደለም፡፡ የመረጃዎች ልከኛ ውህደት ነው፡፡ ማለትም ብዙ መረጃዎች በትክክል ተቀናጅተው፣ በአንድነት፣ ግንዛቤን ይፈጥራሉ። ውህደት፣… አንድ መሆን እንደማለት አይደል?...
ማንኛውም እውቀትም፣ የበርካታ ግንዛቤዎች ጥምር ድምር ውጤት ነው። የተስተካከለ የተጣጣመ ውህደት። እንዴት?
 የእንቆቅልሽ ጨዋታ፣ ይህንን የአስተሳሰብ ባሕርይ የሚያመለክት ቀላል ምሳሌ ነው፡፡
 እንቆቅልሽ የሃሰብ መልመጃ፡፡
“እየሄድኩ አልሄድም” የሚለው ግጥም የማን ነበር? “ከውጭ ነኝ፤ ከውስጥም ነኝ፤ እኔ ማን ነኝ?” የሚለው አባባልስ?
ይሄ የሹፌሮች ግጥም ነው የሚል ይኖራል። ወደ ስራ ሲሄዱ፣ “ወጥቻለሁ” “ውጭ ነኝ” ይላሉ።  ግን፣ውስጥ ናቸው- መኪና ውስጥ፡፡ “ውጪ ነኝ፤ውስጥ ነኝ” … እውነትም የሾፌሮች አባባል ይመስላል፡፡
አዎ፣ መኪና ውስጥ ቁጭ ብለዋል፡፡  እፎይ ብለው አርፈው ተቀምጠዋል፡፡ ንቅንቅ አይሉም፡፡ ግን እየሄዱ እየተጓዙ ነው። “እየሄድኩ አልሄድም”፣ … የሾፌሮች አባባል ነው ቢባል አይገርምም። “ኳንተም” ከሚለው ቅፅል ጋር የሚወረወሩ የአላዋቂ ፈሊጦች ላይ ለመቀለድም ሊገለግል ይችላል። የኢትዮጵያ አዙሪትን የሚገልጽ አባባል ነው የሚልም ይኖራል። እውነትም፣የኢትዮጵያ ነገር፣አዙሪት ይበዛበታል፡፡ ሌላስ?
በሆነ ቦታና ጊዜ፣ የሆነ ሰው በምርምር ያገኘውና አእምሮው ውስጥ የጨበጠው እውቀት፣ …ከትንሽ ጊዜ በኋላ፣ በየአቅጣጫው ይጓዛል። የሰውየው እውቀት፣ በአእምሮው ውስጥ ተገድቦ አይቀርም። በፅሁፍና በንግግር፣ በይፋ ይወጣል።
 ከአንድ ሰው አእምሮ የወጣ ሃሳብ፣ አለምን ያዳርሳል። ግን ከአእምሮው ውስጥ ይጠፋል ማለት አይደለም። እውቀት በየአቅጣጨው ይሄዳል። መነሻ ቦታውን ጥሎ አይሄድም። “እየሄድኩ አልሄድም፤ ውጭ ነኝ ውስጥም ነኝ” …ይሉሀል እንዲህ ነው፡፡
 ምን ለማለት ፈልጌ ነው? የእንቆቅልሽ ጨዋታ፣ ቢያንስ ቢያንስ ሁለት ገፅታዎችን  እያዋሃዱ የማሰብ ልምምድ ነው ማለት ይቻላል። ምን ይሄ ብቻ?
የተፈጥሮንና የአእምሮን፣ የእውቀትንና የህይወትን መሰረታዊ ባሕርይ አጉልቶ ያሳያል፤ እንቆቅልሽ። እንዴት? የእንቆቅልሽ ጨዋታ፣ ቢያንስ ሁለት ነገሮችን እያጣመሩ የማሰብ፣ ሁለቱንም ያዋሃደ የጋራ መፍትሄ የማግኘት ጉዳይ ነው፡፡ እውቀትና ህይወትም እንደዚያው ናቸው፡፡ በቁንፅል በቁንፅል ሳይሆን፣ ቢያንስ ቢያንስ ሁለት ነገሮችን የሚያጣምሩ የሚያዋህዱ ጥበብ ናቸው፡፡
በአጭሩ እውቀትና ሕይወት ሁሉ፣ ጥምረትና ውህደት ናቸው። ይህን እውነታ ከነገጽታዎቹ አዋህደን የመገንዘብ ፍላጎት ወይም ብቃት ሲጎድለን ነው፤ ችግር የሚፈጠረው። እያንዳንዱን ነገር በቁንፅል በቁንፅሉ ብቻ እንጠልጥለን የምንዞር ከሆነ፣
ነገሩ ሁሉ፣ ፍቺ የሌለው እቆቅልሽ ይሆንብናል። ብርቱ ፉክክርና የተረጋጋ ሰላም፣… ሁለቱን ያዋሃደ ነገር ምንድነው? “የአገራችን ምርጫ” የሚል መልስ ይመጣልናል? እንዴት ሆኖ!
በአንድ በኩል ብርቱ ፉክክርና በሌላ በኩል የተረጋጋ ሰላም፣ …አብረው የተዋሃዱበት ምርጫ፣ በኢትዮጵያ ታይቶ የማይታወቅ “ፍቺ የሌለው እንቆቅልሽ” ነው።
ሁለት ሶስት ነገሮችን አቀናጅቶና አዋህዶ ማሰብ? በተግባርም አጣምሮ እውን ማድረግ?  ነገሮችን አዋህደን የማሰብ ብቃትና ፍላጎት ገና አልገነባንም። ሁሉንም ነገር በቁንጽል በቁንጽል ነው የምናስበው፡፡  የቅጽበት የቅፅበቷን ነው።
ብርቱ ፉክክር ወይስ የተረጋጋ ሰላም? በፈረቃ ብቻ!
በአንድ በኩል፣ የምርጫ ፉክክር እንዲሟሟቅ ከመመኘት ባሻገር፣ ተጋግሎ ተቀጣጥሎ አገሪቱን እስከማንደድ ካልደረሰ፣ ምርጫ የተካሄደ የማይመስለው ብዙ ሰው አለ። የምርጫ ዋና አላማ አገርን በአናቷ ማቆም ነው እንዴ?
የምረቃ በአል ወይም የሰርግ ድግስ ዋና አላማ፣ “ህፃን አዋቂውን፣ ሰማይ ምድሩ እስኪዞርበት ድረስ በስካር ማጦዝ” ቢመስለን እንደማለት ነው።
የምርጫ አላማስ፣ በፍጭትና በፉክክር አገሪቱን ቀውጢ የምናደርግበት እድል ማመቻቸት ነው? የዘወትሩ የፖለቲካ ስካር፣ በአምስት ዓመት አንዴ፣ ከጣሪያ በላይ ፈንቅሎ አገሩን ሁሉ እስኪያፈርስ ድረስ የሚጦዝበት ድግስ ነው? ምርጫ ማለት
በሌላ በኩልስ?
“ተከብሮ የሚውል በዓል” ሳይሆን፣ ለወጉ ያህል፣ “ታስቦ የሚውል ቀን” ታወቁ የለ? ለስሙ በዓል ነው፡፡ ግን ከሌላው ቀን የተለየ ነገር አይታይበትም፡፡ “ታስቦ የሚያልፍ በዓል” ነው፡፡ ምርጫም፣” ገዢው ፓርቲ፣ በምርጫ ስልጣን የያዘ ፓርቲ ነው” ለማለት ያህል ነው? ምርጫ ሁሉ፣ ለወጉ “ታስቦ የሚያልፍ ምርጫ” እንዲሆን የሚፈልጉ ይኖራሉ፡፡
በቃ ምርጫው በሰላም ይካሄዳል። “ሁሉም ነገር አማን ነው፡፡ አገሩ ሰላም ነው”። ጨርሶ ረግቷል ቢባልም ያስኬዳል፡፡
ማጣጣሌ አይደለም፡፡ አገር ከሚተረማመስና ከሚቀወጥ፣ “ድሮ በነበረበት ቦታ ላይ ረግቶ ቢቀመጥ ይሻላል”፤ ቢባል አይገርምም፡፡ ካልተተረማመሰና ረግቶ ከቆየ፣ ከጊዜ በኋላ፣ በቅጡ ነቅቶ፣ ህሊናም ገዝቶ፣ በስርዓት የመንቀሳቀስ እድል ያገኝ ይሆናል፡፡
አገር ተተረማምሶ ለይቶለት ከፈረሰ ግን፣ እንደገና ተመልሶ በቅጡ አገር የመሆን እድል ላይኖረው ይችላል፡፡ እና፣ በምርጫ ሰክረን ከመታመስ ይልቅ፣ በይስሙላ ምርጫ ደንዝዘን መርጋትን እንምረጥ?” በይስሚላ ምርጫ”፣ ቢያንስ ቢያንስ ሰላም እናገኛለን?
በእርግጥም፣ አገሬው ለተወሰነ ጊዜ ረግቶ ሊቆይ ይችላል፡፡ ግን በዚያው አይዘልቅም። ረግቶና ታፍኖ፣ ውስጥ ለውስጥ ሲብላላ፤ ብዙም ሳይቆይ፣ የስካር ቅመም ሆኖ ይፈላል፤ ይገነፍላል፡፡ የአመጽና የትርምስ ሰበብ ይሆናል፡፡ “ፉክክር አልባ የይስሙላ ምርጫ”፣ ለሰላምና ለእርጋታ ጊዜያዊ ጥቅም ይኖረዋል። እውነት ነው። ችግሩ ምንድን ነው? “ረግቶ ይዘልቃል” ብለው በከንቱ የሚመኙ ሰዎች ግን ሁሌም ይፈጠራሉ። በእርግጥ፣ ከጥቂት ዓመታት በኋላ፣ ሀሳባቸውን አይቀይሩም ማለት አይደለም። ሃሳባቸውን ለውጠው፣ “የመጣው ይምጣ” ወደ ሚል ነውጠኛ የስካር ምርጫ ያዘነብላሉ፡፡ “ያልደፈረሰ አይጠራም” ብለው ራሳቸውንና ሌሎች ሰዎችን ለማጽናናት አልያም ለመሞኘት ይሞክራሉ፡፡ በአጭሩ፣ነውጠኛ ይሆናሉ፡፡
“እኛ እናደፈርሳለን፤ በራሱ ጊዜ ይጠራል”… “ማፍረስ እንችልበታለን፤ መገንባቱ እንጃ” ..ይሄ ምን ማለት ነው?…..
ምርጫ ማለት፣ ”ማፍረሱን ለኛ፣ መገንባቱን ግን እንጃ…. የመጣው ይምጣ……” ማለት ከሆነ፣ ምኑምርጫ ሆነ! ለዚህማ፣ ምርጫ ምን ጥቅም አለው? ከንቱ ልፋት ይሆናል፡፡ የመጣው ይምጣ? ምንም አይነት ጥረት ሳያስፈልግ፣ ያለ አንዳች ወጪ፣  ያለ ምርጫ፣…. “የመጣው መጥቷል”፤ የሚመጣውስ መምጣቱ ይቀራል?
ግን፣ እንዲህ፣ በየጊዜው፣ አንዴ የብርቱ ፉክክር ነውጥ፣ ሌላ ጊዜ የይስሙላ ፈዛዛ ምርጫ በየተራ እያፈራረቅን እስከመቼ? ነገሩ ሁሉ አዙሪት የሆነብን፣…. የተነቃቃ ብርቱ የምርጫ ፉክክርን ለብቻው ነጥለን፣ በጤና ወጥቶ የመግባት የአገር ሰላምን ለብቻው ገንጥለን፣ ….አምና አንዱን ጉዳይ ብቻ፣ ዘንድሮ ሌላኛውን ጉዳይ ብቻ በቁንፅል እየነጣጠልን፣ ሰላምን ባዝን ነው። …ሁለቱንም በሚያዋህድ የአስተሳሰብ ጥበብ አማካኝነት፣ ውህድ መፍትሄ ማበጀት ስላልፈለግን ወይም ስላቃተን ነው፡፡
በዚህም ሳቢያ፣ የምርጫ ጉዳይ፣ ይቺ የሌለው እንቆቅልሽ እንዲሆንብን አድርገነዋል፡፡ ወይም ከአቅማችን በላይ ከብዶብናል፡፡ በሂሳብ ትምህርት፣ ገና ”ተጣማሪ ቀመር” (“ሳይመልቲንየሥ ኢኮዥን”) ላይ ያልደረሰ መሀይም መስለናል። ወይም የተማረውን ሁሉ  በማግስቱ አራግፎ የሚረሳ አላዋቂ ሆነናል፡፡ ሁለት ቀመሮችን በአንድነት አዋህዶ የማስላትና መፍትሄውን የማግኘት የሂሳብ እውቀት ነው፤ ነገሩ፡፡ ማወቅና ማሰብ ማለትስ፣ ከዚህ ውጪ ምን  ሊሆን ይችላል?
ጥራትን ብቻ ወይም ዋጋውን ብቻ ሳይሆን፣ ሁለቱንም አጣመረን ሳናስብ፣ አንዲት ነገር እንገዛለን? አንዲት ብር እናወጣለን? አይነቱንና አገልግሎቱን፣ መጠኑንና ዋጋውን አዛምደን አዋህደን ማስላት፣ የእለት ተእለት ውሏችን አይደለምን? ታዲያ፣ ምርጫንና አገልግሎቱን፣ ፉክክርንና ሰላምን አጣምረን ማሰላሰል፣ ሁሉንም ነገር ያዋሀደ መፍትሄ ማበጀት ያቃተን ወይም ያልፈለግነውን ለምንድን ነው?


Read 8805 times