Sunday, 31 January 2021 00:00

ፖለቲከኞቻችን የገቡትን የንጋት ቃል ኪዳን ያከብሩ ይሆን?

Written by  ጤርጢዮስ ዘ-ቫቲካን
Rate this item
(0 votes)

 ሕዳር ወር 2012 ዓ.ም በአንደኛው ቀን አመሻሽ ላይ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያው አቅራቢያ ከተገነባው፣ “ስካይ ላይት” ሆቴል በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት የተላለፈ አንድ አስገራሚ መርሀ ግብር ነበር። ጉዳዩ የሀገራችንን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወስኑ ክፉና ደግ ኩነቶች ተፈትሸው፣ መልካሙ የጸደቀበት ስለኾነም የዚያ ሰሞን መነጋገሪያ ነበር፡፡ በሥፍራው የታደሙት  የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን አስተሳሰብና የፖለቲካ አቋም የሚወክሉ፣ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ብዙ ሕዝብ የሚከተላቸው ግለሰቦች ናቸው። በሰፊው መድረክ ላይ እጅ ለእጅ ተያይዘው ለሀገራቸው  አንድ የሚሹት  የጋራ ህልም እንዳለ የገለጹበት  ነው። ከነዚያ መካከል  ከፊሎቹም የከረረ የርዕዮተ ዓለምና የፖለቲካ መሥመር ቅራኔ ያላቸው ናቸው።
የመርሀ ግብሩ ድባብ እንኳን በሥፍራው የታደሙትን ዕንግዶች ቀርቶ  በቀጥታ ስርጭት በቴሌቪዥን እየተመለከትኩ ያለሁትን እኔንም በደስታ ስሜት ያጥለቀለቀ ነበር። ሠርክ በልቤ የምመኘውን ነገር በማግኘቴም በአንዳች መንፈስን ሰርስሮ የሚገባ ሀሴት መጥለቅለቄንም አስታውሳለሁ። እርስ በእርሳቸው በጥርጣሬና በጠላትነት  ይተያዩ  የነበሩ የአንድ ሀገር ልጆች፣ እንዲያ መድረኩን ሞልተውት ማየት ደግሞ በእርግጥም  ድንቅ ትዕይንት ነው። በእነርሱ መገፋፋት ሰርክ እንደ ቆቅ በሥጋት እየኖረ ላለው ሕዝብ የሚሰጠው እፎይታም በቃላት የሚገለጽ ዓይደለም።  
እንዲያ ዓይነቱን መድረክ ያመቻቸው ዘጠኝ አባላት ያሉት ፣“ዴስቲኒ ኢትዮጵያ ኢኒሼቲቭ” ወይም “የምንፈልጋት ኢትዮጵያ” የተሰኘ ሀገር በቀል ድርጅት ሲኾን፣ የቡድኑ ዋና አስተባባሪ አቶ ንጉሡ አክሊሉ ናቸው። “ዴስቲኒ ኢትዮጵያ ኢኒሼቲቭ”፤ ሀገራችን አሁን ላይ ለምትገኝበት የፖለቲካ አጣብቂኝ መፍትሔ ማፈላለግን ዓላማው ያደረገ እንደኾነም ሲናገሩ አዳምጫለሁ። ቡድኑ፣ ደቡብ አፍሪካ ረጅም ዘመን ያስቆጠረውን የፖለቲካ ቀውሷን ለመፍታት የተጠቀመችበትን፣ የሽግግርን ዘመን መጻኢ ዕድሎች የሚያመላክቱ አራት ሴናሪዮዎችን (Scenarios)  በግብዓትነት ተጠቅሟል፡፡
በዚህም መሠረት፣ ከፍ ብዬ በጠቀስኩት መስፈርት የተመረጡ 50 ኢትዮጵያውያን፣ በእኛዋም ሀገር መጻኢ ዕጣ ፈንታ ላይ ለስድስት ወራት በምሥጢር ሲመክሩ፣ ሲከራከሩ፣ሲሟገቱ ቆይተው አራት ሴናሪዮዎችን (ቢሆኖችን) ቀርጸዋል፡፡ ከቀረጹት አራቱ “ሴናሪዮዎች” መካከል ደግሞ ለሀገራችን አዋጪ ነው ብለው የተስማሙበትን አንድ “ሴናሪዮ” ብቻ መርጠዋል፡፡ የዚያን ዕለት ምሽት፣ 50ዎቹ ሰዎች ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ይፋ ያደረጉትና  እጅ ለእጅ ተያይዘው እምነታቸውን በቃለ መሃላ ያጸኑትም ይኼንኑ ነበር።
“ዴስቲኒ ኢትዮጵያ” ባመላከታቸው ሳይሳዊ ዘዴ አማካኝነት  እነዚህ 50 ሰዎች የቀረጹዋቸው አራት ሲናሪዮዎች (ቢሆኖች)፤ ኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በኋላ የምትደርስበትን የሀገረ መንግሥት አስተዳደር ባሕርያት የሚገልጹ ናቸው። ስለ ወደፊቱ በእርግጠኝነት መተንበይ ባይቻልም እንኳ ሴናሪዮዎቹ መጪውን ዘመን ያመላክታሉ ተብለው  ተወስደዋል። የሴናሪዮዎቹ ስያሜ፡- “ሰባራ ወንበር”፣ “የፉክክር ቤት”፣”አጼ በጉልበቱ” እና “ንጋት” ተብሏል፡፡ አራቱ ሴናሪዮዎች የሚወክሉትም አራት የተለያዩ መንግሥታዊ የስተዳደር ሥርዓቶችን እንደኾነም ተገልጿል።
የ”ሰባራ ወንበር” ሴናሪዮ፡- ጠንካራ መስሎ ቢታይም፣ ነገር ግን ቀላል ክብደት ያለው ነገር እንኳ መሸከም የማይችል መሆኑን ያመላክታል። አቅም ከማጣቱ የተነሳ በማኅበረሰቡ ውስጥ በየደረጃው ለሚነሱ የልማት ፍላጎቶች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የማይችል መሆኑን ይጠቁማል፡፡ የ”አጼ በጉልበቱ” ሴናሪዮ በጥብቅ ቁጥጥርና አፈና ላይ የተመሠረተ  ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝን ሲወክል፣ የሕዝብን የእድገት ፍላጎት ለመደፍጠጥ ሲል ቁጥጥር ተኮር ሥርዓትን መከተል ወሳኝ እንደሆነ ያምናል፡፡ በጊዜ ሂደት ግን መሰላቸትንና ተስፋ መቁረጥን ስለሚያስከትል አመጽ ለመቀስቀስ በር ይከፍታል፡፡
የ”ፉክክር ቤት” ሴናሪዮ ደግሞ እንደ ተረቱ “የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል” የሚለውን አበባል ፍንትው አድርጎ ያሳያል። በዚህ ጊዜ፣ የተለያዩ ቡድኖችና ክልሎች ያገኙትን አዲስ ነጻነት እነርሱ እንደፈለጉትና እንደመሰላቸው ለመጠቀም የሚሹ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ ከመንግሥት አንስቶ እስከ ቤተሰብ፣ ደረጃ በደረጃ በሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች ውስጥ የሚከሰቱ ክፍተቶችንና ክፍፍሎችን ይወክላል፡፡ አንዳንድ የክልል መንግሥታት የራሳቸውን ነጻነት ሙሉ በሙሉ ለማወጅ እስኪችሉ ድረስ ጡንቻቸውን ስላፈረጠሙም፣ እነዚህና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ቀውሶች፣ የፌደራል መንግሥቱን ሊፈረካክሱት መቃረባቸውን ይገልጻል፡፡
አራተኛውና የመጨረሻው ሴናሪዮ “ንጋት” የሚል ስያሜ  ተቸሮታል፡፡ ሴናሪዮው የኢትዮጵያ ዕድገት ቀስ በቀስ የሚመጣ ስለመሆኑ  ያመላክታል፡፡ ዛሬ ላይ በሀገራችን የንጋት ፀሐይ ሙሉ በሙሉ ወጥታ ባትታይም ነገር ግን የአዲስ ቀን ወገግታ እየመጣ እንደሆነ ፍንጭ ይሰጣል። ምክንያቱን ሲያስቀምጥም፤ በርካታ ሥር የሰደዱ ማኅበራዊ ቅራኔዎች በጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት እልባት የሚያገኙበት ምህዳር ክፍት መሆንን፤ ከቅራኔና ጥላቻ ይልቅ የይቅርታና እርቅ ዋጋ እየታወቀ መምጣትን በእማኝነት ያቀርባል።  የዴሞክራሲ ተቋማትና ኢኮኖሚው ደረጃ በደረጃ እየተገነቡ፣ በጋራ ርዕይ ላይ የተመሠረተ አንድነት እየጎለበተ መምጣቱንም እንደ ንጋት ምልክት አደርጎ ይወስዳል፡፡ 50ዎቹ ሰዎች የሚመሩትን ሕዝብ ወክለው በአንድ ድምፅ የመረጡት  ሴናሪዮም ይኸው ነው፡፡
ያን ዕለት ምሽት የመንግሥት አካላትን ጨምሮ በርካታ ዕንግዶች በተገኙበት መድረክ ላይ ቆመው፣ እጅ ለእጅ ተያይዘው፣ በጋራ የመረጡትን “ንጋት” የተባለውን ሴናሪዮ፣ በኅብረ ቃላቸው ሲያውጁ በቴሌቪዢን መስኮት  ካየኋቸው ሰዎች መካከል ለአብነት ያህል ጥቂቱን እንኳ ብጠቅስ፤ የኦነጉ ኦቦ ዳውድ ኢብሳ፣ የኢዜማው ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የአብኑ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ፣ የአረናው አቶ አብርሃ ደስታ ይገኙበታል፡፡ ከሕወኃት፣  ከአዲስ አበባ ባልደራስ ምክር ቤት፣ ከሰላም ሚኒስቴር ወ.ዘ.ተ. የተወከሉ ሰዎችም ነበሩበት። የመጡበትን ማኅበረሰብ የሚወክሉ የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ ደራሲያን፣ የሕግ ባለሙያዎች፣ ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶች፣ የንግዱ ማኅበረሰብ ተወካዮች ወዘተ በሴናሪዮ ቀረጻው ተሳትፈዋል፡፡
እነዚህ ሁሉ የአንድ የሀገር  ልጆች፣ በአንድ ዓይነት የጋራ ሕልም ተቆራኝተው ማየትም በጣም ልብ ይነካል፡፡  50ዎቹ ሰዎች ተስማምተው የመረጡት ሴናሪዮ “ንጋት” መሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ በሁሉም ፊት ላይ ያነበብኩት ለሃሳቡ የመገዛት ተመሳሳይ ስሜትና ቁርጠኝነትም፣ በምድሬና በሕዝቤ መጻኢ ዘመን ብሩህነት ላይ ተስፋ እንዲያድርብኝ አድርጓል። ይሁንና አሁን በዚያ መድረክ ላይ ቃለ መሀላ ከፈጸሙ ፖለቲከኞቻችን መካከል ምን ያህሉ ቃላቸውን ጠብቀው እየተጓዙ እንዳለ አንድዬ ብቻ ነው የሚያውቀው።
መጪው ሐገራዊ ምርጫ “የንጋት ሴናሪዮ” በሚጠይቀው ባሕርይ መሠረት እንዲከናወን፣ የሃሳብ ልዩነቶች በጨዋነት የሚስተናገዱበት፣ ቅራኔዎች በጠረጴዛ ዙሪያ ውይይቶች የሚፈቱበት፣ ከስሜታዊነት ይልቅ አመክንዮ ዋጋ የሚያገኝበት እንዲኾን ሙሉ ኃላፊነቱ በእነርሱ ጫንቃ ላይ ማረፉ ግና አሌ የሚባል ዓይደለም። እኔ ያልኩት ብቻ ይጽና የሚል ሀኬተኝነት በቅርቡ ያስከተለውን ኪሳራ ላለመድገም የተቻላቸውን ጥረት ማድረግም ይጠበቅባቸዋል።
እነርሱ ለሀገራቸው የተመኙት የንጋት ቀን፣ የሁላችንም ናፍቆት ነውና፣ ያ ብሩህ ቀን እንደናፈቀን እንዳንቀር፣ ፖለቲከኞቻችን የተቻላቸውን ሁሉ  ያደርጉ ዘንድ ይገባል። አሁን ላይ አንዳንዶቹ  ከአንድ ዓመት በፊት የገቡትን ቃል ኪዳን እየዘነጉ በመምጣታቸው፣  ሰባራ ወንበሩንና አጼ በጉልበቱን እንኳ ለጊዜው ብንተዋቸው ከንጋት ይልቅ መሬቱ ላይ እየታየ ያለው ሴናሪዮ፣ “የፉክክር ቤት” ይመስላል። ስለዚህም ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ወደ ቀልባቸው ተመልሰው የንጋትን ሴናሪዮ ጽንሰ ሀሳብ ገንዘባቸው እንዲያደርጉ ይጠበቃል።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን በሰላምና በፍቅር  ይባርክ!!

Read 2884 times