Saturday, 30 January 2021 10:59

“ላቭ ቱ ኔሽን" ያዘጋጀው የቡና ኤግዚቢሽን

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

   ቡና አምራቾች፣ ነጋዴዎች፣ ላኪዎች፣ ዓለማቀፍ ቀማሾች ተሳትፈዋል

           ከሰኞ እስከ ትላንት ድረስ ለ5 ቀናት የዘለቀ የቡና ኤግዚቢሽን በኢሊሌ ሆቴል ሲካሄድ ሰንብቷል፡፡ በቡና አምራቾች ዘንድ የተወደሰውን ይህን ኤግዚቢሽን ያዘጋጀው “ላቭ ቱ ኔሽን" የተሰኘ አገር በቀል ሰናይ ድርጅት ሲሆን ዓላማውም የኢትዮጵያን ቡና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅና ተወዳዳሪ ለማድረግ እንዲሁም የገበያ ትስስር ለመፍጠር ነው ተብሏል፡፡ በኤግዚቢሽኑ  ላይ  የቡና አምራቾች፣ ነጋዴዎች፣ ላኪዎች፣ ዓለማቀፍ ቀማሾች ተሳትፈዋል። በኢሊሌ ኤግዚቢሽን ላይ የተገኘችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ በቡናው ዘርፍ የተሰማሩ ጥቂት የቡና  አምራቾችን አነጋግራለች፡፡

            “ዘር የምንመርጠው እንኳን ከተፈጥሮ የጫካ ቡና ነው”
                      (አቶ አብርሃም ይታገሱ፤ የጉጂ ሃይላንድ ኮፊ ፕላንቴሽን ማርኬቲንግና ዶክሜንቴሽን ክፍል ኃላፊ)


           የእኛ ቡና ችግኝ ከማፍላት ጀምሮ በራሳችን እርሻ ላይ አምርተን፣ ፈልፍለን፣ ወደ ውጪ እስከ መላክ ነው የምንሰራው። በቀጣይ ሁለትና ሶስት ወራት ውስጥ ደግሞ ቆልተንና ፈጭተን ወደ መሸጥ እንገባለን። ለኤግዚቢሽን ያቀረብነውን የእኛን ቡና ብትመለከቺ፤ ከማሳችን ላይ አምርተን፣ አጥበን፣ ቀሽረን ነው የምንሸጠው። ያልታጠበም ለሚፈልግ እንደዚሁ እናቀርባለን። አራት አይነት ደረጃ ያላቸው ቡናዎችን ይዘን ነው በኤግዚቢሽኑ ላይ የቀረብነው።
ጉጂ ሃይላንድ ኮፊ ፕላንቴሽን ስፔሻሊቲ ኤክስፖርት አለን። ስፔሻሊቲ ኤክስፖርት ምን ማለት ነው ካልሽኝ፣ በራሳችን ማሳ ላይ ተመርተው ራሳችን ለቅመን፣ በራሳችን ማሽን ፈልፍለንና አጥበን፣ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ኤክስፖርት የምናደርጋቸው የቡና ዓይነቶች ናቸው፡፡
በጉጂ፣ ሲዳማ፣ ይርጋጨፌና ሊሙ በሚገኙ ሰፋፊ እርሻዎቻችን ላይ ነው የምናመርታቸው። እኛን ለየት የሚያደርገን ከዘር መረጣ ጀምሮ የምናደርገው ጥንቃቄ ሲሆን፣ ዘር የምንመርጠው ከትክክለኛውና ከተፈጥሮው የጫካ ቡና  ነው። ችግኝ ካፈላንም በኋላ ለቡና አብቃይ ገበሬዎች ሁሉ እንሰጣለን። ይህንን ሁሉ ጥንቃቄ አድርገን ነው ቡናዎቻችንን አምርተን  ለውጪ ለገበያ የምናቀርበው።
የቡና ኤግዚቢሽኑ ጥቅሙ ከፍተኛ ነው። በኤግዚቢሽኑ ላይ ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው የቡና ቀማሾች መጥተዋል። እነዚህ ከሌላው ዓለም የመጡ ባለሙያዎች፣ የቡናችንን ደረጃና ጥራት ሲመለከቱ ተጨማሪ ዓለም አቀፍ ገዢዎችን እንድናገኝ ድልድይ ይሆናሉ። በእርግጥ እኛ ከበቂ በላይ ዓለም አቀፍ ደንበኞች አሉን። ነገር ግን ተጨማሪም ደንበኛ ብናገኝ አንጠላም። ስለዚህ በመሳተፋችን ደስተኞች ነን። ከዚህም በኋላ የትኛውም ኤግዚቢሽንና ባዛር ቢዘጋጅ የመሳተፍ አላማ አለን። ይጠቅመናል እንጂ አይጎዳንም። ከሌሎች ቡና አምራችና ላኪ ተፎካካሪዎቻችን ጋር መገናኘት መወያየት፣ በዘርፉ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ መነጋገር እንድንችል መሰል መድረኮች ይጠቅማሉ።
ስለዚህ እንዲህ አይነት መድረኮች መቀጠል አለባቸው፡፡ አዘጋጁን “ላቭ ቱ ኔሽን" እናመሰግናለን።
የአገራችን ቡና ችግር ብዬ የማስበው ኤክስፖርት ማድረግ ላይ መዘግየት፣ ፕሮሞሽን አለመስራት፣ መንግስት ከቡናው የሚያገኘው የውጭ ምንዛሬ ከፍተኛ እንደመሆኑ  ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ የተለያዩ ቢሮክራሲዎችን አለመቅረፍ  ናቸው፡፡ አሁን እንደ ጉጂ ሃይላንድ ኮፊ ፕላንቴሽን ለስታንዳርድ የሚሰሩ ድርጅቶች እየተፈጠሩ ነው።
የእኛ ኦዲተር አስመጥቶ የማስገምገም ድፍረት ያለው ግንባር ቀደም የቡና ተቋም ነው ብለን ደረታችንን ነፍተን የምንናገርለት ነው። ስለዚህ ተግዳሮቶችንም በግል እየተቋቋምን እዚህ ደርሰናል፡፡
ከስታርባክስ ባለሙያዎች መጥተው ኦዲት ተደርገን፣ በጣም የሚገርም ውጤት አግኝተናል። ደረጃችንን ይዘን እንቀጥላለን።

_____________________


               “ኤግዚቢሽኑ የዓለም ቡና ገዢዎችን ቀልብ ለመሳብ ይረዳል”
                    አቶ ልዑል ቀለም፤ የልዑል ቀለም ቡና ልማት ድርጅት ባለቤት

           ወደ ኤግዚቢሽኑ የመጣነው “ላቭ ቱ ኔሽን"  ባደረገልን ግብዣ ነው። በእንደነዚህ አይነት አገር አቀፍም ሆነ ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽኖች መሳተፍ ለቡናችንም ሆነ ለአገር የሚያስገኘውን ፋይዳ በመገንዘብ ነው የተሳተፍነው፡፡ አንዱና ዋነኛው ነገር የገበያ ትስስር ይበልጥ ማጠናከር ነው፡፡ ከኛ ውጪ ያሉ ሌሎች አልሚዎች ምን አይነት ደረጃ ላይ እንዳሉ ለመገንዘብ ትልቅ ዕድል የሚፈጥርልን በመሆኑ ግብዣውን ተቀብለን እዚህ ተገኝተናል፡፡
ልዑል ቀለም ቡና ልማት ድርጅት፤ አልሚ ድርጅት ነው። ቡናን የሚያለማው ከችግኝ ጀምሮ ነው። ችግኛችን ከሚያፈሉ በመቀበል ለቦታው ተስማሚ የሆኑትን መርጠን እናለማለን፡፡ ከዚያ ከጀንፈል ቡና ጀምሮ ጥራት ያለውን ቡናችንን ኤክስፖርት እናደርጋለን ማለት ነው። የቡና እርሻችን በሸካ ዞን ማሻ ወረዳ ኬቦ በሚባል ቀበሌ ይገኛል። 428 ሄክታር ቦታ አለን፡፡ የለማው ደግሞ 320 ሄክታር ነው። በዚህ ዓመት 50 ሄክታር መሬት ላይ አዳዲስ የቡና ችግኞችን ተክለን፣ በቀጣይ 3 ዓመት ምርት እስኪሰጠን እየተንከባከብንና እየጠበቅን እንገኛለን። በዛሬው ዕለት ከውጭም ከአገር ውስጥም ለመጡ ቡና ቀማሽ ኤክስፐርቶች አስቀምሰን፣ እንደ ሌሎቹ አቻ ድርጅቶች፣ ውጤት እየጠበቅን እንገኛለን፤ ጥሩ ውጤት እንደምናገኝም እምነታችን ነው።
በዚህ አጋጣሚ የቡና ኤግዚቢሽኑን ያዘጋጀውን አገር በቀል በጎ አድራጎት ድርጅት ማመስገን እፈልጋለሁ። ምክንያቱም ለአገር ኢኮኖሚ ዋልታ የሆነውን ቡናችንን በዓለም ገበያ የበለጠ ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ መድረኩ ጠቃሚ ነው፡፡ ከውጭ የቡና ኤክስፐርቶችን በማምጣት፣ እኛም ሀገር ውስጥ አምራቾችና ላኪዎች የምናገናኝበትን መድረክ ማመቻቸቱ ትልቅ ነገር ነው። አንዱም የኢትዮጵያ ቡና ችግር በከፍተኛ ሁኔታ በዓለም ገበያ ላይ ትውውቅ አለመደረጉ ነው። እንደዚህ አይነት ኤግዚቢሽኖች ግን የዓለምን የቡና ገዢ ድርጅቶች ቀልብ ወደ ኢትዮጵያ ለመሳብ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራሉና ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው እንላለን።


___________________


                     “ቡናችንን በዓለም ገበያ በፕሪሚየም ዋጋ ነው የምንሸጠው”
                            (አቶ ቃልኪዳን ጎሹ፤ የኃይሌ ቡና ፋርም አግሮኖሚስት)


             ኃይሌ ቡና፤ ከኃይሌ- ዓለም ኢንተርናሽናል ቢዝነሶች አንዱ ነው። ቡናችን በደቡብ ክልል ማሻ ዞን ላይ  የሚመረት ሲሆን  ማሻ ቡና ይሰኛል። በ1500 ሄክታር መሬት  ላይ ነው የምናመርተው።
እስካሁን 850 ሄክታሩ ሙሉ በሙሉ ለምቶ ኤክስፖርት ማድረግ ከጀመርን አራት ዓመት ሆኖናል። ቡናችን በጥራቱ የተመሰከረለትና ሰርቲፋይድ የሆነ ኦርጋኒክ ቡና በመሆኑ፣ በዓለም ገበያ በፕሪሚየም ዋጋ ነው የምንሸጠው። ዛሬም እዚህ ቦታ ላይ በ “ላቭ ቱ ኔሽን"  ተጋብዘን የመጣነው ከፈረንሳይ አገር የመጡ ትልልቅ የቡና ቀማሽ ኤክስፐርቶች፣ ቡናችንን አይተው፣ አሽትተውና ቀምሰው ውጤት እንዲሰጡንና ዓለም አቀፍ ተቀባይነታችንን ለማሳደግ ነው።
ከዚህ ቀደምም በሀያት ሬጀንሲ ሆቴል ተጋብዘን ተወዳድረን ነበር፡፡ ስድስት ቀማሾችም ነበሩ። በስድስቱም አንደኛ ወጥተናል። በዚህኛውም አንደኛ እንደምንሆን ጥርጥር የለንም። ሀይሌ አንደኝነትን በቢዝነሱም አስተምሮናል። እኛ ቡናውን የምናዘጋጀው በታጠበና ባልታጠበ መልኩ ነው፡፡ ሁለቱንም አይነት አስቀምሰናል፤ ኤክስፖርትም አድርገናል። የተሻለ ስፔሻሊቲ ነው ያለን። ትክክለኛ ቴክኒኩን ጠብቆ ነው የሚዘጋጀው፡፡ በቡናው ላይ ከፍተኛ ባለሙያዎች ናቸው የሚሰሩት። እስካሁን በጥራትም በጣዕምም ተወዳጅ ሆኖ ነው የቀጠለው። ቡናችንን ወደ አሜሪካ ፣ ጀርመን፣ ጃፓንና ሌሎችም አገራት እንልካለን። ከዓመት ዓመት ኤክስፖርታችን እየሰፋ ነው የሄደው። ይሄ ኤግዚቢሽንም ሌላ ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥራል ብለን እናምናለን።
የእኛ አገር የቡና ዘርፍ ተግዳሮቶች፤ ከእርሻው ጀምሮ የሰው ሃይል እጥረት፣ የመሰረተ ልማት አለመሟላት በዋነኝነት ይጠቀሳሉ፡፡
በሌላ በኩል፤ መንግስት የገበያ ማስተዋወቁ ስራ ላይ ምንም የሰራው ነገር የለም። እኛው በራሳችን አቅም ፕሮሞሽን እየሰራን ነው ገበያችንን ለማስፋት እየታገልን ያለነው።
መንግስት መሬት ከመስጠት ባለፈ በትኩረት የሚደግፈው ነገር የለም። እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ቡና ኦርጋኒክ ነው፤ ጣዕሙ ልዩ ነው፡፡ በዓለም ገበያ ላይ ሲቀርብና ከወጪው ጋር ሲነፃፀር፣ በጣም ወደ ኋላ የቀረ ነው። ስለዚህ መንግስት የማስተዋወቅ ስራ መስራትና ቡናችን የዓለምን ገበያ ሰብሮ እንዲገባ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡


___________________


             “ቡና ብዙ ትኩረት ያገኘ ዘርፍ አይደለም”
                   (አቶ ንጉሴ ክፍሌ፤ ከአዳኬና ትሬዲንግ)


            የቡና ንግድ ላይ በመሰማራት የ25 ዓመት ልምድ ቢኖረንም፣ በኤክስፖርት ደረጃ የተሰማራነው በቅርቡ ነው። በምዕራብና በምስራቅ ጉጂ ወደ 50 ሄክታር የቡና እርሻ አለን፤ 50 ሄክታሩም ሙሉ በሙሉ ባይሸፈንም።  “ላቭ ቱ ኔሽን"  የተሰኘው ድርጅት ጅምር የሚደነቅ ነው። ኢትዮጵያ ቡና አብቃይ ባለ-ታሪክ ሆና ለምን በቡና ገበያ ላይ ወደ ኋላ ቀረን በሚል ተቆርቋሪነት ነው ኤግዚቢሽኑን ያዘጋጀው።  
እንደኛ ኤክስፖርት በማድረግ  ጅምር ላይ ላለ ድርጅት ደግሞ ዓይን ገላጭ ይሆናል። በሌላ በኩል፤ ዓለም አቀፍ ቡና ገዢ ድርጅቶችን ከእኛ ጋር የማገናኘት፣ ልምድ የማለዋወጥና የቡና ገቢያችንን የማሳደግ እድሉም ከፍተኛ ስለሆነ ቀጣይነት ቢኖረው መልካም  ነው እላለሁ።
የኢትዮጵያ ቡና  ለምን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና የሚፈልገውን ውጤት ማምጣት አቃተው የሚለው ጉዳይ አነጋጋሪ ነው። ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች ያለበት ነው። የቡና ዘርፉ አንዱ ችግር በመንግስት ትኩረት ተሰጥቶት፣ መንገዱ የተመቻቸለት አይደለም። ከፖሊሲ ችግር ጋርም ይገናኛል። ቡና ትልቅ የሀገር ሀብት ሆኖ ትንሽ የሚባል ትኩረት እንኳን አልተሰጠውም ባይ ነኝ፡፡
በሌላ በኩል፤ እኛ ይሄንን የመሰለ ቡና በዚህ መልኩ መላክ አልነበረብንም። ቆልተን ፈጭተን፣ እሴት ጨምረን ብንልክ የተሻለ ዋጋ እናገኝበታለን። ስለዚህ መንግስት ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት አለበት። ኤግዚቢሽኑም መቀጠል ይገባዋል፡፡ በገዢና ሻጭ መሃል ያለውን ደላላ በማስወጣት፣ ቡና በትክክለኛ ዋጋ ትክክለኛ ቦታውን እንዲያገኝ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እንደዚያ ሲሆን አገርም አምራች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡


Read 1230 times