Saturday, 23 January 2021 11:54

ከአለማችን ድሃ አገራት የኮሮና ክትባት ያገኙት 25 ሰዎች ብቻ ናቸው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን ለሁሉም የአለም አገራት በፍትሃዊነት ለማዳረስ ተይዞ የነበረው ዕቀድ በሃብታም አገራት የክትባት ሽሚያ ሳቢያ እየተሰናከለ እንደሚገኝና፣ እስከ ሳምንቱ መጀመሪያ ድረስ 49 የሚሆኑ ሃብታም የአለማችን አገራት ከ39 ሚሊዮን በላይ ክትባቶች ለዜጎቻቸው ሲሰጡ፣ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ድሃ አገራት ክትባቱን ያገኙ ሰዎች ግን 25 ብቻ መሆናቸውን የአለም የጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡
ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው የአለማችን ድሃ አገራት መካከል ለዜጎቿ የኮሮና ቫይረስ ክትባትን መስጠት የጀመረችው ብቸኛዋ አገር ጊኒ መሆኗን ድርጅቱ እንዳስታወቀ የዘገበው ዘ ጋርዲያን፣ በጊኒ ባለፈው ሳምንት መሰጠት የጀመረውን ሩስያ ሰራሽ ክትባት ያገኙት የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ጨምሮ 25 ሰዎች ብቻ መሆናቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ ባለፈው ሰኞ በተደረገው የቦርድ ስብሰባ ላይ ባሰሙት ንግግር እንዳሉት፣ በርካታ የአለማችን ሃብታም አገራት የኮሮና ቫይረስ ክትባትን ለዓለም ሕዝብ በፍትሐዊ መንገድ ለማከፋፈልና ድሃ አገራት ክትባቱን በወቅቱ ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ ለማመቻቸት ታስቦ የተመሰረተውን ኮቫክስ የተባለ አለም አቀፍ ትብብር አሰራር በመጣስ ክትባቶችን በሽሚያ በገፍ እየገዙ በማከማቸት ድሃ አገራትን ለከፍተኛ ችግር እያጋለጡ ይገኛሉ፡፡
ኢፍትሃዊው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት አለማችንን እጅግ ለከፋ የሞራል ውድቀት እያንደረደራት ይገኛል ያሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ፣ ፍትሃዊነት የጎደለው የክትባት ክፍፍል ወረርሽኙን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚደረጉ ጥረቶችን ከንቱ የሚያስቀርና ኮሮና እያሳደረ የሚገኘውን ሰብአዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የሚያባብስ በመሆኑ አገራት ለፍትሃዊ ክፍፍል ትኩረት እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡
ከ25 በመቶ በላይ እስራኤላውያን ክትባቱን ማግኘታቸውን ያስታወሰው ዘ ጋርዲያን፣ በእንግሊዝ ከ6 በመቶ በአሜሪካ ደግሞ 4 በመቶ የሚሆነው ህዝብ የመጀመሪያውን ዙር ክትባት ማግኘቱንም አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ የኮሮና ቫይረስ ዜና ደግሞ፣ በመላው አለም በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ከሰሞኑ ከ95.5 ሚሊዮን ማለፉና ለሞት የተዳረጉትም ከ2.4 ሚሊዮን በላይ መድረሱ የተነገረ ሲሆን፣ በአሜሪካ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ለሞት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥርም ባለፈው ማክሰኞ ከ400 ሺህ ማለፉን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
በአፍሪካ በአንጻሩ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር በሳምንቱ መጀመሪያ ከ3.3 ሚሊዮን ማለፉን የዘገበው ሮይተርስ፣ ለሞት የተዳረጉት ሰዎች ቁጥርም ከ79 ሺህ ማለፉን ባወጣው ዘገባ አስነብቧል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ በደቡብ አፍሪካ በፍጥነት እየተዛመተ የሚገኘው አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ በቦትስዋና፣ ዛምቢያ እና ጋምቢያ መገኘቱ የተነገረ ሲሆን፣ በኬንያ የደቡብ ምስራቅ ግዛት ውስጥ ደግሞ ሌላ አዲስ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ መገኘቱን አንድ የአገሪቱ የህክምና ምርምር ተቋም ባወጣው ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው የጥናት ሪፖርት ማመልከቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ኦል አፍሪካን ኒውስ በበኩሉ፤ የዚምባቡዌው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲቡሲሶ ሞዮ በሳምንቱ መጀመሪያ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ከዚህ አለም በሞት መለየታቸውን ዘግቧል፡፡

Read 3513 times