Monday, 25 January 2021 00:00

የብሔር ፖለቲካ ሰለባ የኾኑቱ ራስ ተፈሪያውያን አሳዘኑኝ!

Written by  ጤርጢዮስ ዘ-ቫቲካን
Rate this item
(2 votes)

   https://youtu.be/KcReNBEYpgw?t=251

 የተጨቋኝነት ብሶት የወለደው የራስ ተፈሪያዊነት ሃይማኖታዊ ንቅናቄና ዕንግዳ የአኗኗር ዘይቤ የተጠነሰሰው በ1930ዎቹ አካባቢ  በጃማይካ ሲኾን የእምነቱ ተከታዮች “ጌታዬና አምላኬ” ብለው የሚያመልኩት ደግሞ ደርግ ንጉሣዊውን ሥርዓት በመቃወም ከዙፋናቸው ያወረዳቸውን፣ በሽምግልናቸው ለእሥር የዳረጋቸውን፣ ከሞቱ በኋላ አስከሬናቸው የት እንደተቀበረ ሳይታወቅ ቆይቶ ወታደራዊው አገዛዝ  ከወደቀ በኋላ አጽማቸው ከተቀበረበት ወጥቶ ዳግመኛ ግብዓተ መሬት የተፈጸመላቸውን ኢትዮጵያዊውን ንጉሥ፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን  ነው።
የራስ ተፈሪ እምነት ተከታዮች አምላካቸውን “ራስታፋራይ” ብለው ሲጠሩ፣ ይህም ሰውዬው ወደ ንግሥና ከመምጣታቸው አስቀድሞ ከሚጠሩበት “ራስ ተፈሪ መኮንን” ከሚለው ስያሜ ጋር የተያያዘ  ነው። ዛሬ ላይ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ራስ ተፈሪያውያን በዓለም ዙሪያ እንዳሉ ሲገመት የተስፋይቱ ምድር ወይም ጽዮን  ብለው የሚጠሯት  ሀገራቸው  ደግሞ ኢትዮጵያ ናት። ስሟ ከአርባ ጊዜ በላይ በመጽሐፍ ቅዱስ መጠቀሱንና የንጉሧን ከይሁዳ ነገድ ጋር መቆራኘትም ለቅድስት ሀገርነቷ ማረጋገጫ አድርገው ያቀርባሉ።
 ይህ ነቢይ  በትውልዱ ጃማይካዊ ሲኾን ስሙም ማርከስ ጋርቬይ (ከ1887-1940) ይሰኛል። ጋርቬይ አፍሪካ በቅኝ ገዢዎች መተዳደሯን አጥብቆ የሚቃወም ብርቱ የጥቁሮች መብት  ተሟጋች እንደነበር ይነገርለታል። በ1920ዎቹ ገደማ “ዩኒቨርሳል ኔግሮ ኢምፕሩቭመንት” (UNIM) የተሰኘ ተቋምም መሥርቶ ነበር። በጥቁሮች የነጻነት ትግል በተፋፋመበት በዚያ ወቅት የተናገረው አንድ ትንቢት ከኃይለ ሥላሴ ዘውድ መጫን ጋር ተገጣጥሞ፣ የራስ ተፈሪያውያን እምነት ለመፈጠሩ ምክንያት የኾነውም እሱ ነው።
“አውሮፓ ለአውሮፓውያን እንደኾነች፣ አፍሪካም ለአፍሪካውያን [ለጥቁሮች] መኾን አለባት” ይል የነበረው ጋርቬይ፤ ከዚህም አለፍ ብሎ፦”ቃሉ እንደሚለው፤ በአምሳሉ ተፈጥረናልና ለእኛ ለጥቁሮች ነጻነት የሚጨነቅ አምላክ ጥቁር  እንጂ ሌላ ሊኾን አይችልም” እስከ ማለት ዘልቋል። እሱ የዘራው እንዲህ አይነቱ ኑፋቄ ፍሬ በማፍራቱም የመጽሐፍ ቅዱሱን ቃል ከተጻፈበት መንፈስና ዐውድ ውጪ የሚተረጉሙ በርካታ ተከታዮችን አብቅሏል።
“የአፍሪካ መዳን መቼ እንደሚሆን ማንም የሚያውቅ የለም፤ ነገር ግን መምጣቱ አይቀርም” በማለት የጥቁር ሕዝቦችን መጻኢ ተስፋ ይሰብክ የነበረው ማርከስ ጋርቬይ፤ የኃይለ ሥላሴን የፖለቲካ አቋም የማይደግፍ በመኾኑ ለአጼው  አምላክነት ቃል በቃል እውቅና የሰጠበት አጋጣሚ ባይኖርም፤ “ወደ አህጉረ አፍሪካ ተመልከቱ፤ አንድ ጥቁር ይነግሣል፣ ነጻነትም ይኾናል” የሚለውን የጋርቬይ ትንቢት የሰሙ በርካታ ጃማይካውያን ግና ያ ነጻ አውጪ ንጉሥ፣ አጼ ኃይለ ሥላሴ መኾናቸውን ለመቀበል አላንገራገሩም። ወደ ኢትዮጵያ መትመም የጀመሩትም ሰውዬው በ1923 ዓ.ም “ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ” ተሰኝተው  የንግሥና ዘውድ የመጫናቸውን ዜና ከተሰማ በኋላ ነው።
በወቅቱ “ፈጣሪያችን በሥጋ ተገልጧል፣ ጠባቂያችን ነግሷል” በማለት “ወደ ተስፋይቱ ምድር” መጉረፍ ለጀመሩት ጃማይካውያን፤ ንጉሡ ሻሸመኔ ውስጥ መሬት ሰጥተዋቸው መኖር ከጀመሩም ዓመታት ተቆጥረዋል። “ጃ ማለት ፈጣሪ” እንዲል ቴዲ አፍሮ፣ ሰውዬው ሞተው ከተቀበሩ በኋላም  ያለ ግብራቸው የአምላክነት ግብር ተቸሯቸው፤ “ጃ” (Jah) በሚለው መለኮታዊ ስያሜ እየተጠሩ እስከዛሬም በመመለክ ላይ ይገኛሉ።
ንጉሡም በሕይወት ሳሉ በአንድ ወገን “እኛ አምላክ አይደለንም” ይሉ እንደነበር አንዳንድ መጻሕፍት ላይ ሠፍሮ ቢገኝም፤ በሌላ በኩል ደግሞ የእምነቱን ሀሰተኝነት በመቃወም ጠንከር ያለ ግሳጼ ባለመስጠታቸው ከቅርባቸው ሰዎች ሳይቀር ወቀሳ ይቀርብባቸው እንደነበር የሚናገሩ ሰዎችም አጋጥመውኛል። ለምሳሌ በአንድ ወቅት ዶ/ር ሄኖክ ገ/ሕይወት የተባሉ ሰው ሲናገሩ እንደሰማሁት፤ አጼ ኃይለሥላሴ “በራስ ተፈሪያኑ” ዘንድ እንደ  አምላክ መቆጠራቸው  ለከነከናቸው የቅርቦቻቸው ሰዎች፣ “ለምን ተወደድክ ነው እንዴ የምትሉኝ?” የሚል ምላሽ እንደሰጡ፤ ከሚኒስትሮቻቸውም አንዳንዶቹ  በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ግልጽ አቋም እንዲነግሯቸው በጠየቋቸው ጊዜም “በሀገራቸው በድንጋይና በዛፍ የሚያመልኩ ሰዎች እኛን ቢያመልኩን ችግሩ ምንድነው?” የሚል አጸፋ  ስለመስጠታቸው  አውስተዋል።
የራስታዎች ጸጉራቸውን ማስረዘም፣ “ጋንጃ” የተሰኘ እጸ ፋርስ ማጨስና ጭንቅላት የሚወዘወዝበት “ቢንጊ” የተሰኘ የዳንስ ስልታቸው ከሃይማኖታዊ ማንነታቸው ጋር የተሰናሰለ ነው። በሬጌ ሙዚቃ ስልተ - ምት የሚያሳዩትን ጭንቅላት ውዝወዛ አንዳንድ ወገኖች “ሞት ለነጮች” የሚል ትርጉም እንዳለው ይገልጻሉ። ሠርክ ከአፋቸው የማትጠፋውና ውድቀቷን አብዝተው የሚመኙላት “ባቢሎንም “ ብትኾን በተምሳሌትነት የምትወክለው፤ የክፋት ሁሉ መከማቻ እንደኾነ ለሚያምኑት የምዕራቡ ዓለም ነው።
ወደ ዛሬው  ዋናው ጉዳዬ ስገባ፣  በሻሸመኔ  መኖር ከጀመሩ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠሩቱ የራስ ተፈሪ እምነት ተከታዮች፣ እምነታቸው እኔ ከምከተለው ወንጌላዊ  ክርስትና  ጋር  ሰማይ ከምድር እንደሚርቅ እንዲሁ የተራራቀ ቢኾንም የእምነቱ ተከታዮች አሁን ላይ  እየደረሰባቸው ባለው ጥቃት ግን በፍጹም ደስተኛ ዓይደለሁም። የሰዎቹ እምነት ክርስትና መሠረቱን ከጣለበት ሁለት ሺህ ዓመታት በኋላ በአዲስ የአረዳድ ቅርጽ ብቅ ያለ መጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሽ ዕንግዳ ሃይማኖት በመኾኑ በኑፋቄነት ፈርጄ ባወግዘውም፤  “ኢትዮጵያ ሀገሬ ናት” የሚሉቱ የእምነቱ ተከታዮች፣ የብሔር ፖለቲካ  ሰለባ ኾነው፣ ዘረኛ በኾኑ ሰዎች ሲገፉ ሳይ ግን እጅግ  ነው ያሳዘኑኝ።  ለቅሷቸውም  አንጀቴን አላውሶታል።
ራስታዎች ንጉሡ ዘውድ የጫኑበትን ዓመት፣ ወርና ቀን በልዩ ሁኔታ በማክበርም የሚታወቁ ናቸው። ያ ዕለት ለእነርሱ አምላካቸው በሥጋ የተገለጠበት ቀን መኾኑንም ልብ ይሏል። ከጥቂት ሳምንት በፊት  ይኼንኑ ኩነት  መነሻ በማድረግ  በኢቢኤስ (EBS) ቴሌቪዥን በተሰናዳ  አንድ መርሀ ግብር ላይ ቃለ ምልልስ  ያደረጉ  ሁለት የሃይማኖቱ ካህናት  ስለ እምነታቸው መነሻና ሃይማኖታዊ ቀኖና በዝርዝር  ከማስረዳታቸውም ባሻገር በቀዬአቸው ሻሽመኔ  እየደረሰባቸው ስላለው መገፋትም የሆዳቸውን ብሶት ሲናገሩ ተደምጠዋል።
“ኢትዮጵያ ሀገራችን ናት፣ እኛም ኢትዮጵያውያን ነን” የሚሉቱ እነዚህ ወገኖች፤ “ቅድስት” ብለው የሚጠሯትን ሀገር እጅግ አድርገው ከመውደዳቸው የተነሳ ቤታቸውን፣ ልብሳቸውን፣ መለዮአቸውን... ወ.ዘ.ተ በኢትዮጵያ ባንዲራ የማስጌጥ የቆየ ልማድ አላቸው። አሁን ላይ ግን ይኸው  ምክንያት ኾኖ አካባቢያቸው ባሉ [ዘረኛ] ሰዎች እየተገፉ ይገኛሉ። ከሁለቱ አንደኛው ስለሁኔታው ሲገልጽም፤ “አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ቀለም ያለው ልብስና ኮፍያ በማድረጋችን መገፋት እየደረሰብን ነው” በማለት ጥልቅ በሆነ የሀዘን ስሜት ነው ስለ ሁኔታው የገለጸው፡፡  
መነሻቸው ሃይማኖታዊም ቢኾን “ኢትዮጵያ ለእኛ  ትልቅ ቁም ነገራችን ናት።  ወራሪ  ጠላት ቢመጣባት  የምንሞትላት" ያሉቱ  እነዚህ  ሁለት የራስ ተፈሪያኒዝም ሃይማኖት ካህናት እነርሱ  እንደሚሉት፤ “የአምላክን” ጥሪ ተቀብለው፣ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት ብዙ ገንዘብ ሊያስገኝላቸው የሚችል ሥራና ሙያ  የነበራቸው፤ በትውልድ ሀገራቸው ጥሩ ኑሮ  መኖር የሚችሉ  ሰዎች ናቸው። ይሁንና ለጠሪያቸው ምላሽ ለመስጠት ሁሉንም እርግፍ አድርገው ጥለው ኢትዮጵያ ከገቡ፣ አንደኛው ሃያ ስድስት፣ ሌላኛው አሥራ ስድስት ዓመት ኾኗቸዋል።
ግና ምን ያደርጋል “ቅድስቲቷ ሀገራችን” ብለው በሚጠሯትና መጠጊያቸው ባደረጓት ምድር በሰላም እንዳይኖሩ ትልቅ ተግዳሮት ገጥሟቸዋል። ለዓመታት ከኖሩበት ቀዬ ሊያፈናቅላቸው ጊዜ ያጀገነው ጠላት ዙሪያቸውን ይዞራቸው ከጀመረ ሰነባብቷል። በዚህም ምክንያት እንደ ቆቅ በሥጋት የመኖር አደጋ በፊታቸው ተደቅኗል።
“ሀገራችንን በግብርና ልናግዝ እንፈልጋለን፣ መሬታችንን ግን እየተነጠቅን ነው" የሚል አቤቱታም በማሰማት ላይ ናቸው።
ይህ ጥቃት ደግሞ ዛሬ ላይ በሀገራችን የተለያዩ ክልሎች በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ፣ ማንነትን መሠረት አድርጎ እየተሰነዘረ ካለው ጥቃት የተለየ ዓይደለምና እነዚህም “ዜጎቻችን” በቀያቸው በነጻነት መኖር እንዲችሉ ተሟጋች ያስፈልጋቸዋል። ያሻቸውን እምነት ቢከተሉም በሰውነታቸው የሚደርስባቸውን  ጥቃት  የሚያስቆምላቸው ወገን ያሻቸዋል። መንግሥትም እንደ መንግሥትነቱ ተገቢውን ጥበቃ  ሊያደርግላቸው  ይገባል።  
በቃለ ምልልሱ  ማሳረጊያ ላይ  በዕድሜ አንጋፋ የኾነው ካህን፤ “መንግሥት የኢትዮጵያ ነዋሪነታችንን የሚያረጋግጥ መታወቂያ ስለሰጠን ትልቅ ምሥጋና እናቀርባለን፤ እኛ ፖለቲካ አናውቅም፣ በዘር መከፋፈልን አንደግፍም። እኛ የሰው ልጆች ሁሉ በሰላምና በፍቅር እንዲኖሩ ነው የምንፈልገው” ሲል መናገሩም በቀጣይ ዋጋ  እንደሚያስከፍላቸው እሙን ነው። ሁለተኛው ካህን ደግሞ  ጉሮሮው ላይ ሳግ እየተናነቀውና እንባው ከዓይኖቹ እየፈሰሰ ከአንደበቱ ያወጣው ቃል “ለሻሸመኔ ሕዝብ ይቅርታ አድርጌያለሁ” የሚል ነበር። ለኔ ግና ከይቅርታ አድራጊነቱ በላይ ጎልቶ የታየኝ የልቡ ስብራቱ ስለነበር፣ ከውስጥ ፈንቅሎ በሚወጣ እንባ ለቅሶውን ተጋርቻለሁ።
ዛሬ ላይ በአንዳንዶች ዘንድ የብሔርን ፍቅር ለመግለጽ ኢትዮጵያን መጥላት፣ ባንዲራዋን መጸየፍ እንደ መሥፈርት እየተወሰደ በመኾኑ በእርግጥም ባንዲራዋ ጌጣቸው ለኾነላቸው ራስታዎች ጊዜውና ሁኔታው እየከበደ መምጣቱ የሚያከራክር ዓይደለም። ከኢቢኤሱ ቃለ ምልልስ መረዳት የቻልኩትም ይህንኑ  ነውና ለእነዚህ ግፉአን ወገኖች ድምጽ ልንሆንላቸው ይገባል።

Read 10665 times Last modified on Thursday, 11 February 2021 19:46