Thursday, 14 January 2021 12:19

ደቡብ ኮርያ ልጅ የሚወልዱ ዜጎቿን በሽልማት ልታንበሻብሽ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የደቡብ ኮርያ የህዝብ ቁጥር በተጠናቀቀው የፈረንጆች አመት 2020 በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ መቀነስ ማሳየቱና ብሔራዊው የውልደት መጠን ከሞት መጠን በእጅጉ ማነሱ ያሳሰበው የአገሪቱ መንግስት፣ ብዛት ያላቸው ልጆችን ለሚወልዱ የአገሪቱ ዜጎች የገንዘብ ሽልማት እንደሚሰጥ ማስታወቁን አናዶሉ ኤጀንሲ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ መንግስት ዜጎች ከመጪው የፈረንጆች አመት 2022 ጀምሮ በሚወልዱት አንድ ልጅ በየወሩ 275 ዶላር ያህል የማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት እንደሚሰጣቸው ማስታወቁን የጠቆመው ዘገባው፣ ለነፍሰጡር እናቶችም የቅድመ ወሊድ ወጪያቸውን ለመሸፈን የሚውል የ1 ሺህ 827 ዶላር ገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግና በየወሩ የሚሰጠው የገንዘብ ድጋፍ  ከ2025 ጀምሮ ወደ 457 ዶላር እንደሚያድግ ቃል መግባቱንም አክሎ ገልጧል፡፡
መንግስት ወሊድን ለማበረታታት አስቦ ባረቀቀው በአዲስ ፕሮግራሙ፣ ወላጆች ልጃቸው አንድ አመት እስኪሞላው ድረስ ለሶስት ወራት የሚቆይ የስራ ዕረፍት ሲወስዱ እያንዳንዳቸው በየወሩ እስከ 2 ሺህ 741 ዶላር የሚደርስ ደመወዝ እንዲከፈላቸው የሚያደርግ መሆኑም ተነግሯል፡፡
በአገሪቱ ባለፈው አመት የተወለዱት ህጻናት 275 ሺህ 800 መሆናቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ይህ ቁጥር ከ2019 ጋር ሲነጻጸር በ10 በመቶ ያህል የሚያንስ ሲሆን በ2020 ከዚህ አለም በሞት የተለዩት ዜጎች ቁጥር ግን 307 ሺህ 764 እንደነበርና ይህም የአገሪቱን መንግስት በቀጣይ አገር ተረካቢ ትውልድ ይጠፋል የሚል ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደጣለው አመልክቷል፡፡
የአገሪቱ መንግስት ከዚህ ቀደም ተግባራዊ ባደረገው የማበረታቻ ፕሮግራም አንድ ህጻን ዕድሜው 7 አመት እስኪሞላው ድረስ በየወሩ 91 ዶላር የማበረታቻ አበል ለቤተሰቡ ሲሰጥ መቆየቱንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
በሌላ ወሊድ ተኮር ዜና ደግሞ፣ በአዲሱ የፈረንጆች አመት 2021 የመጀመሪያዋ ዕለት በመላው አለም 372 ሺህ ህጻናት መወለዳቸውንና በዕለቱ 60 ሺህ ያህል ህጻናት የተወለዱባት ህንድ ከአለማችን አገራት ብዙ ህጻናት የተወለዱባት ቀዳሚዋ አገር መሆኗን ተመድ አስታውቋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ ከሰሞኑ ባወጣው መረጃ እንዳለው፣ በአዲሱ የፈረንጆች አመት በመላው አለም 140 ሚሊዮን ያህል ህጻናት ይወለዳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Read 1927 times