Saturday, 09 January 2021 11:09

ቤተ ክርስቲያናቱ የጥምቀት ቦታዎችን ለማልማት እቅድ መንደፏን አስታወቀች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

    የጃንሜዳ ባለቤትነቷን የሚያረጋግጥ ካርታ ጠይቃለች
                               
             ቤተክርስቲያኒቱ ጃንሜዳን ጨምሮ በአዲስ አበባ የሚገኙ የጥምቀት ማክበሪያ ቦታዎችን ለማልማት እቅድ የነደፈች ሲሆን የጃንሜዳ ባለቤትነቷን የሚያረጋግጥ  ካርታ እንዲሰጣት ጠይቃለች፡፡
የኢትየጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የካርታና ይዞታ ጉዳይን የሚከታተለውና  በብፁዕ አቡነ መልከ ፀዲቅ የሚመራው ኮሚቴ ሰሞኑን  ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር ባደረገው ውይይት ላይ ቤተ ክርስቲያኒቱ በስሟ የሚገኙ 38 የጥምቀተ ባህር ቦታዎችን በተለያየ መልኩ ለማልማት እቅድ እንዳላት ማስታወቁን የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት የመረጃ ክፍል ሃላፊ ላዕከ ሰላም ግርማ ተክሉ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
አብዛኞቹ የጥምቀት ማክበሪያ ቦታዎች በመንግስትም በግል ባለ ሃብቶችም እየተቀነሱ እየተወሰዱ ያሉት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ለጥምቀት በዓል ማክበሪያ ውሎ ከዚያ በኋላ ባዶ  መክረሙን በመመልከት መሆኑን የሚጠቅሱት ላዕከ ሰላም ግርማ፤ ይህ ሁኔታ ያሳሰባት ቤተ ክርስቲያኒቱ፤ ቦታዎቹን የማልማት  እቅድ ነድፋለች ብለዋል፡፡
በተለይ ቤተ ክርስቲያኒቱ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ባገኘችባቸው 38 በአዲስ አበባ የሚገኙ የጥምቀት ማክበሪያ ቦታዎች ላይ ከእምነቱ እሴት ጋር የማይቃረኑ ፕሮጀክቶችን ለመተግበር መታቀዱን ነው ሃላፊው  የገለጹት፡፡ ሌሎች ቦታዎች የይዞታ ማረጋገጫ እንደተገኘባቸው ወደ ልማት እንዲገቡ አቅጣጫ መቀመጡም ነው የተመለከተው በቦታዎቹ ላይ ሊተገበሩ ከታቀዱት ፕሮጀክቶች መካከል ቤተ መጽሀፍት፣የመናፈሻ ውስጥ ክፍት የማንበቢያ ቦታዎች፣ከእምነት የማይቃረኑ የመዘናኛና የመናፈሻ አገልግሎት መስጫዎች፣የአረንጋዴ ቦታዎችን የማልማት እቅድ ይገኙበታል ብለዋል- ላዕከ ሰላም ግርማ ተክሉ፡፡
ቦታዎቹ ሃይማኖታዊ ክብራቸው ተጠብቆ በሰፊው የማህበራዊ አገልግሎት መስጫነት  እንዲቀየሩ እቅድ መነደፉን ይህም መንግስት ከሚከተለው የአረንጓዴ ልማት አቅጣጫ ጋር የተስማማ የአረጋውያን፣ የወጣቶችና የልዩ ልዩ ህብረተሰብ ክፍሎች የመንፈስ ማደሻ ቦታዎች እንዲሆኑ ያደርጋል፤ በዚህም በቋሚነትም በጊዜያዊነትም የስራ እድል መፍጠሪያ ይሆናሉ ተብሏል፡፡
ይህ መሆኑ ቦታዎቹ ቅርስነታቸው ተጠብቆ እንዲቆይ ያስችለዋል ያሉት ሃላፊው ከውጭ ሃገርም ተመሳሳይ የአደባባይ የሃይማኖት በአላት ማክበሪያ ስፍራዎች አጠባበቅ ልምድ መቀሰሙን ነው የገለፁት፡፡
በአሁኑ ወቅት በስፖርት ኮሚሽን ባለቤትነት ስር የሚገኘው ታሪካዊው የጥምቀት ማክበሪያ ጃንሜዳም የጥምቀት በአል በአለማቀፍ ቅርስነት ሲመዘገብ፣ በዋናነት ተጠቃሸ የማክበሪያ ቦታ እንደመሆኑ ባለቤትነቱ ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ እንዲዞር ጥያቄው ቀርቦ ምላሽ እየተጠበቀ መሆኑን ጠቁመው ምላሹ እንደተገኘም ቦታውን በተለያየ መልኩ ለማልማት ቤተ ክርስቲያኒቱ እቅድ መንደፏን  ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
ጃንሜዳ ባለቤትነቱ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቢደረግም ወትሮ ይሰጥ የነበረውን የስፖርት  ማዘውተሪያነት ከሌሎች የልማት ስራዎች ጋር አቀናጅቶ እንዲሰጥ ይደረጋልም ተብሏል፡፡   

Read 12043 times