Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 11 August 2012 11:04

የፖለቲካ ሥልጣን በብቃት - እንደ ለንደን ኦሎምፒክ!

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ደራሲያን ማህበር በጥራት ወይም በአባልነት?

የእኛ ዩሴይን ቦልት መቶ  ብር ነው”

የለንደን ኦሎፒክ ተዓምር አሳየን እኮ! ግን አይገርምም! ከሃሳብ የሚፈጥኑ አትሌቶችን እኮ ነው እንደ ጉድ በቲቪ መስኮታችን የኮመኮምነው፡፡ የታደለማ … ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ኮሚቴ ጋር ተለጥፎ ላፍ ይላል፡፡ ለነገሩ 44ሚ. ብር ተዋጥቶ የለም … ምን ችግር አለ! ገንዘቡ እንደሆነ የእኛ ነው - የህዝብ! የእኛማ ስለሆነ እኮ ነው ከአትሌቶቹ ቁጥር የበለጠ የኮሚቴ አባላት ለንደን መሄዳቸዉን በወሬ ወሬ የሰማነው (ግፍ ነው!) በእርግጠኝነት የሰማነውም ነገር አለ፡፡ ምን መሰላችሁ? በረዥም ርቀት በተተኪ ስም የተያዙ አትሌቶች እንኳን ለንደን ቦሌ ኤርፖርት ባለመድረሳቸው፣ በሩጫ የተጐዱ አትሌቶች በማደንዘዣ ሃይል እንዲሮጡ ሲደረጉ ሰነበቱ የሚል መረጃ ተሰምቷል፡፡ እኔማ አላምንም ብዬ ከለንደን ሲመጡ ቦሌ ኤርፖርት ቆሜ ልጠብቃቸው ወስኛለሁ፡፡ ማን በሥራ፤ ማን ያለ ሥራ እንደሄደ ለማረጋገጥ፡፡ ከዛስ? … ከዛማ እንደተወራው ከሆነ እታዘባዋለሁ! (የአትሌቲክስ ኮሚቴውን)

ለነገሩ አንዳንድ የአትሌቲክስ ምንጮች እንደነገሩኝ ከሆነ፣ አገራችን ከአትሌቶች ይልቅ በርካታ ቁጥር ያላቸው የኮሚቴ አባላት ወደ ለንደን ኦሎምፒክ ያጓጓዘች አገር ተብላ በድንቃድንቅ ታሪኮች መዝገብ (Guiness Books of Records) ላይ የመስፈር ዕድል የምታገኝበት ሁነኛ ጊዜ አሁን ነው ስለተባለ ትዝብቱንም ልተወው እችላለሁ፡፡ ለምን ብትሉ … ከአገር ወዳድነት (ብሄራዊ ስሜት) ጋር የሚያያይዘው አንዳች ነገር እንዳለ ስለተሰማኝ ነው፡፡

ይኸውላችሁ ሳላውቀው ወደ ሌላ ርዕስ ጉዳይ ዘው አልኩላችሁ - አገር ወዳድነት ወይም ብሄራዊ ስሜት ወደሚለው፡፡ የዚሁ ጋዜጣ አንጋፋ ፀሃፊና ሃያሲ እንዲሁም ደራሲ የሆነው ዓለማየሁ ገላጋይ ሰሞኑን ለንባብ ባበቃው “የፍልስፍና አፅናፍ” መፅሃፍ ላይ ስለ አገር ወዳድነት ከአሜሪካዊው ፈላስፋ ከዶ/ር አድለር መፅሃፍ ውስጥ ተርጉሞ ያቀረበልንን አብረን እንይለት (ሁልጊዜ ፖለቲካ በፈገግታ የለማ!)

“ለዚህ ዘመን ጆሮ እንደ አገር ወዳድነት ያለ ተደጋግሞ የሚሰማ ሌላ ቃል አለ ማለት ይቸግራል፡፡ አንድ ሰው አፍሪካና እስያ ውስጥ ስለተነሳ “የአገር ወዳድነት” ማዕበል እንዲሁም የአብዮትና የአብዮት ቅልበሳ መንስኤ ሆኖ በአንድ ጊዜ ሊሰማ ይችላል፡፡ የቻይና አገር ወዳዶች ንቅናቄ፣ የእንግሊዝ  አገር ወዳዶች ንቅናቄ፣ የአረብ አገሮች የአገር ወዳዶች ንቅናቄ፣ የሰርቢያ አገር ወዳዶች ንቅናቄ፣ የፈረንሳይ አገር ወዳዶች ንቅናቄ …” እያለ ይተነትናል … መፅሃፉ፡፡ አያችሁ ወደ ለንደን ኦሎምፒክስ በርከት ብሎ ተጉዟል የተባለው ኮሚቴ… የኢትዮጵያ አገር ወዳዶች ንቅናቄን ቢመሰርት አንድ ቁም ነገር ነው - ከአጉል ሃሜትም ይድናል እኮ! አያችሁ … “ተጠባባቂ አትሌቶች መሄድ ሲገባቸው እናንተ ወደ ለንደን ለምን ሄዳችሁ?” ሲባሉ … “በአገር ፍቅር ስሜት ሰክረን” የሚል መልስ ከሰጡ አጥጋቢ ይመስለኛል፡፡ ቀስ ብለው የአገር ወዳዶች ንቅናቄውን ያቋቁሙታል (ዕድሜ ይስጣቸው እንጂ!)

እኔ የምለው የጃማይካውን ፈጣራ ሯጭ ዩሴይን ቦልትን አወቃችሁት አይደል! ባታውቁትም አይገርመኝም - መች ይታያል! ነፋስ እኮ ነው ሲከንፍ! እናላችሁ ከሱ ጋር ተያይዞ ሰሞኑን የሰማሁት ቀልድ ምን ይላል መሰላችሁ? “የእኛ ዩሴይን ቦልት መቶ ብር ነው፤ በአስር ደቂቃ ውስጥ ተዘርዝሮ የሚያልቅ!” (ያውም ለበረከተለት!)

በነገራችሁ ላይ የዓለማየሁ ገላጋይ የፍልስፍና መፅሃፍ እንዴ ተመቸኝ መሰላችሁ… “የፖለቲካ መሪዎች ፍልስፍና” በሚል ርዕስ ከሰፈረው እንዲህ የሚል ይገኝበታል፡፡ (ግን … መሪና ፍልስፍና ምን አገናኛቸው?)

“…ግሪካዊው ታላቁ ፈላስፋ ፕሌቶ ሪፐብሊክ ላይ ያሰፈረው የመሪነት መስፈርት እዚህ ላይ ተጠቃሽ ነው፡፡ በፕሌቶ አቋም አንድ መሪ ስነ ምግባራዊ ዕውቀት፣ ንድፈ ሃሳባዊና ተግባራዊ ጥበብ የተላበሰ መሆን አለበት ይላል፡፡ በአጭሩ መሪ ፈላስፋ ሊሆን ግድ ነው ሲል አፅንኦት ይሰጣል”

አያችሁልኝ “ቀበጡን ፕሌቶ”… ዕውቀት … ጥበብ… ፈላስፋ? ለማን ነው ይሄ ሁሉ … ለመሪ? (እንዴት ቢደላው ነው ባካችሁ!) በእናት አፍሪካ አንዱም ሳይኖራቸው 40 ዓመት የገዙ እንዳሉ ስለማያውቅ ነው! (ያውም በአምባገነንነት!) ስለዚህ መሪ ፈላስፋ ሊሆን ግድ ነው የሚለው ተጨባጭ እውነታውን ከግምት ውስጥ ያላስገባ እንደሆነ ይታወቅልኝ፡፡ መፅሃፉ ስለመሪዎች ጠንካራ ጐኖች ሲተነትን ይቆይና የመልካም መሪዎች ዋነኛ እንቅፋት ምን እንደሆነ ሲያብራራ “የህዝቡን ችግር እንዲፈቱ በየቢሮው የተመደቡ ሹመኞች ገታራና ለጋሚ ሆነው መገኘት ነው፡፡ ከፕሌቶና አርስቶትል አንስቶ ብዙ ፈላስፎች ይሄንን የመልካም መሪዎች እንቅፋት እያነሱ ብዙ ብለዋል፡፡ አንዳንድ ሰዎች በሚሰጡት አስተያየት በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ የተከሰቱ ችግሮች በሙሉ የደረሱት ጠንካራና ተገቢ መሪዎች በነበሩበት ጊዜ ነው…” ይላል፡፡ እኛስ ጋ ቢሆን? አሁን ትንሽ ጠፉብን እንጂ መሪስ ነበረን - ለአፍሪካ የሚበቃ! የእኛም አገር ችግር እኮ እንደ አሜሪካ ነው፡፡ የመሪዎች ሳይሆን የገታራና ለጋሚ ሹመኞች ችግር! (ተሳሳትኩ እንዴ?) እኔ የምለው… ቢፒአርን ተካ የተባለው የዜጐች ቻርተር ምን ደረሰ? (መቼም አልተለወጠም!)

ሰሞኑን ከጥበብ ወዳጆች ጋር ሆነን የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበርን እንደ ጉድ ስናማው ነበር፡፡ (ተራ ሃሜት እኮ አይደለም - 1st Class ነው) የሃሜቱ መነሻ ምን መሰላችሁ? “ማህበሩ ከየማተምያ ቤቱ በሚያገኘው ሪቮልቪንግ ፈንድ የሚያሳትማቸው መፃህፍት እዛው በዛው ለመጠቃቀም እንጂ ለአገሪቱ የሥነ ፅሁፍ ዕድገት ምንም የረባ ፋይዳ የለውም” የሚል ነው (የጥበብ ወዳጆች አቋም) ይሄኔ አስተዋይ አንባቢ ምን ይላል መሰላችሁ? ፋይዳ እንደሌለው የደመደማችሁት በስሜታዊነት ነው ወይስ በምክንያታዊነት? (ጐሽ!) “እስካሁን ያሳተማቸው መፃህፍት ብዙም ትኩረት አልሳቡም፤ በዚያ ላይ ሥራው ለኖቤል የሚመጥን ቢሆን እንኳን የሥራው ባለቤት (ደራሲው) የማህበሩ አባል ካልሆነ፣ እንኳን ሊያሳትምለት ዞር ብሎም አያየው” (ይሄም የጥበብ ወዳጆች አቋም ነው) አሁንም ሌላ አስተዋይ አንባቢ፤ ታዲያ ምን ችግር አለው - አባልነትን እንደ መስፈርት ቢያቀርበው ሊል ይችላል፡፡ ችግርማ የለውም! ግን ከኢህአዴግ በምን ተለየ? ኢህአዴግም እኮ አባላት ላልሆኑት የሥራ … የትምህር ወዘተ ዕድል አይሰጥም … በሚል ሲታማ ነው የከረመው (እሱ እንኳን አያዋጣም ብሎ ተወው መሰለኝ) ከጊዜ ጋር አብሮ መዘመን እንዲህ ነው! እናም የተከበረውን የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ከተቸነው አይቀር … የሥነ ፅሁፍ ሥራዎችን ለህትመት ብርሃን ለማብቃት ሲመራርጥ ቅድሚያ ለሥራው ጥራትና ደረጃ ቢሰጥ የተቋቋመለትን ዓላማና ግብ ያሳካል ብለን እናምናለን - የጥበብ ወዳጆች! ልብ አድርጉ! ሃሳብ ለመስጠት ያህል እንጂ ለኢትዮጵያ ሥነ ፅሁፍ ከእናንተ ከማህበሩ አመራሮች የበለጠ እናውቃለን ብለን አይደለም (ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው!)

በነገራችሁ ላይ … የማህበሩ አመራሮች ዲሞክራትነት ላይ ጥያቄና ጥርጣሬ ስላለን እግረመንገዳችንን ጠቀስ አድርገን ብናልፈው አይከፋም፡፡ እንግዲህ የፓርቲ መሪዎች የሥልጣን ዘመን ስንት ነው እያልን እንደምንጠይቀው ሁሉ የማህበሩ አመራሮች ስልጣን ዕድሜው ስንት ነው? … ብንልስ … እናስቀይም ይሆን? ወይም Expiry date የለውም? ልብ በሉ! የእኛ ዓላማ ግልፅነትንና ተጠያቂነትን ማስፈን ብቻ ነው … እና መልካም አስተዳደርን! ምናልባት ምን አገባችሁ … የሚል የቁጣ በትር ከተሰነዘረብን “ኧረ ምንም አያገባን …የጥበብ ፍቅር ሆኖብን እንጂ …” ብለን ወደ ሌላ አጀንዳ ሸርተት እንላለን፡፡

ሰሞኑን የለንደንን ኦሎምፒክ የስኬት፣ የብቃት፣ የትጋት፣ የጥረት፣ የልፋት፣ ወዘተ ውጤት ደማቅ ቀለማት በቲቪ ስኮመኩም … አትሌቶቻችን በድልና በአሸናፊነት ሲያኮሩን፤ ወርቁንና ነሐሱን ሲያሳፍሱን እጅግ ኮራሁ፡፡ እጅግ ተነሸጥኩ፡፡ በስሜት ተጥለቀለቅሁ፡፡ በዚህ መሃል ነው አንድ ሃሳብ ብልጭ ያለልኝ፡፡ እያንዳንዱ የፖለቲካ መሪ ችሎታውና ብቃቱ እንደ አትሌቶቹ በአደባባይ ተፈትሾና ተፈትኖ ሥልጣንም ሆነ ሹመት ቢሰጠው እንዴት አሪፍ ነበር … የሚል! አቦ ድምፅ ተጭበረበረ የለ! የሥልጣን ሽኩቻ የለ! ሁሉም በብቃት ብቻ - እንደ ለንደኑ ኦሎምፒክስ! በነገራችን ላይ በለንደኑ ኦሎምፒክስ በጥረታቸውና በብቃታቸው ላኮሩን አትሌቶቻችን በሙሉ እንኳን ደስ ያላችሁ … ብያለሁ!! ለኢትዮጵያ ህዝብም!

 

 

Read 3865 times Last modified on Saturday, 11 August 2012 11:14