Print this page
Saturday, 02 January 2021 12:31

አብሮ መብላት አያከስርም!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

  "እናማ...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... ምን መሰላችሁ ይሄ በበዓልም በሆነ በአዘቦቱ ሰብሰብ ብሎ ማእድ መጋራት ከተውን መሰንበት ሳይሆን እኮ ከራርመናል... ገና ወረርሽኝ የሚባለው መከራ ሳይመጣ በፊት፡፡ እዚህ ደረጃ እንዴት ደረስን የሚለው ነገር የባለሙያዎች ጥናት የሚያስፈልገው ቢሆንም፣ የኑሮ መክበድ ብቻ አይደለም፡፡ ‘ቦተሊካችንም’ አለበት ለማለት ያህል ነው፡፡--"
              
              እንዴት ሰነበታችሁሳ!  
እንኳን ለብርሀነ ልደቱ የዋዜማ ሰሞን አደረሳችሁማ! የበዓሉን ሰሞን የጤናና የሰላም ያድርግልንማ! እንግዲህ እንደ ቀድሞው ቢሆን የበዓል ሰሞን በየቤቱ “ብሉልኝ፣” የሚባልበት ጊዜ ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን እየከፋ የመጣው ወረርሽኝ፤ ለእንዲህ አይነቱ  መሰባሰብ አያመችም... ለራሳችንም ለሌላውም የምናስብ ከሆነ ማለት ነው፡፡
ይቺን ስሙኝማ...አንድ ባለሱቅ ነበር። እናላችሁ... ከመሬት ተነስቶ በአካባቢው የነበሩትን የአይሁድ ቄስ አይወዳቸውም ነበር፡፡ ጥምድ አደርጎ ነበር የያዛቸው። ታዲያ አንድ ሰሞን ገቢው እየቀዘቀዘ መሄድ ይጀምራል፡፡ ከዛሬ ነገ ይሻሻላል ብሎ ሲጠብቅ እንደውም እየባሰበት ሄደ፡፡
“ይህን ሥራ የሚሠራው ያ የአይሁድ ቄስ መሆን አለበት፡፡ ፈጣሪን እንዲበቀለኝ እየለመነው ይሆናል፣” ይልና ይቅርታ ሊጠይቅ ይሄዳል፡፡
“እስከዛሬ ስላደረግሁብህ ሁሉ ይቅር በለኝ፣” ሲል ይለማመናል፡፡ 
“አንተ ይቅርታ በምትጠይቅበት ልክ እኔም ይቅር ብዬሀለሁ፣” ይላሉ ቄሱ፡፡
ግን የሰውየው ንግድ እያሽቆለቆለ መሄዱን ቀጠለ፡፡ እንደውም መጨረሻ ላይ ሁሉም ነገር ባዶ ሆነና ከስሮ አረፈው፡፡ በዚህ ነገር ግራ የተጋቡ የቄሱ ተማሪዎች፣ ወደ መምህራቸው ሄደው ለምን እንዲህ እንደሆነ ጠየቋቸው፡፡ እሳቸውም እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው...
“እኔ ይቅር ብዬው ነበር፡፡ እሱ ግን በልቡ ውስጥ እኔን መጥላቱን አላቆመም፡፡ ስለሆነም ጥላቻው ሁሉንም ነገር በከለበት፡፡ የፈጣሪ ቅጣትም እየጠነከረ ሄደ፡፡;
ጥላቻ የትም አያደርስም፡፡ ደስ የማይሉ ንግግሮች እየበዙብን ስለሄዱ ነው!
እናማ...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... ምን መሰላችሁ ይሄ በበዓልም በሆነ በአዘቦቱ ሰብሰብ ብሎ ማእድ መጋራት ከተውን መሰንበት ሳይሆን እኮ ከራርመናል... ገና ወረርሽኝ የሚባለው መከራ ሳይመጣ በፊት። እዚህ ደረጃ እንዴት ደረስን የሚለው ነገር የባለሙያዎች ጥናት የሚያስፈልገው ቢሆንም የኑሮ መክበድ ብቻ አይደለም፡፡ ‘ቦተሊካችንም’ አለበት ለማለት ያህል ነው፡፡
አንድ ወዳጃችን ሁለት ሆነን የባጡን የቆጡን እናወራ የነበረበት ስፍራ መጣ። እናላችሁ...ወዳጃችን ሰላምታ ከማቅረቡ በፊት በንዴት ግብግብ ብሎ ይንተከተካል፡፡
“ምን ሆነሀል! ሰላምታ እንኳን የለም እንዴ!”
“ሰዉ ግን ምን ነካው?”
“ምን ሆንክ?”
“ሰው ግን እንዲህ ሆዳም ይሆናል!”
“እኮ ምን ሆንክ! ወይስ ደረቋን በጠዋቱ ገጭተሀል?”
“ዛሬ ምሳ ለመብላት ከሆኑ ሰዎች ጋር ሬስቱራንት ገባን፡፡ አንድ የቅርቤ ሰው ከሌሎች ጋር ሆኖ በመመገብ ላይ ነበር፡፡ እና ሰላም ልለው  ሳሰፈስፍ ጀርባውን አያዞርብኝ መሰላችሁ!” ምን አለፋችሁ...ብስጭቱ ጣራ ነበር የነካው፡፡
“እና በቃ ጀርባውን አዞረ፣ ጀርባውን አዞረ። አንተ ምንድነው እንደዚህ የሚያናድድህ! በግድ ሰላም በሉኝ ብሎ ነገር አለ እንዴ!”
“እናንተ አልገባችሁም፡፡”
የሆነው ምን መሰላችሁ... የተባለው ሰው ከሰዎቹ ጋር ምግቡን ጥርግ አደርጎ ይጨርስና ከጓደኞቹ ጋር ወደ ውጭ እየወጡ ሳለ ምን ቢያደርግ ጥሩ ነው... ወደ ወዳጃችን ቀረብ ብሎ... “አንተ! በየት በኩል ነው የገባኸው! አጠገቤ ሆነህ እንዴት እስካሁን አላየሁህም!” (ያላየኸውማ እንድታየው ስላልፈለግህ ነዋ! ከተናግሮ አናጋሪ ይሰውራችሁማ!)
እናማ... ወዳጃችን ፈገግ ብሎ “እኔም አኮ አላየሁህም ነበር...” ምናምን ነገር ይላል፡፡ እና ከሰውየው ጀርባ ማዞር ባለፈ ያበሳጨው ምኑ መሰላችሁ... በኋላ “በየት በኩል ነው የገባኸው!” ያላት ነገር፡፡
“የሆነ ህጻን ነው እኮ ያደረገኝ፡፡”
እናላችሁ...‘ዋንስ አፖን ኤ ታይም’ ምን ነበር መሰላችሁ፣ በሆነ ሬስቱራንት ወይም የሆነ ምግብ ቤት እየተመገብን ሳለ ድንገት የምናውቀው ሰው ከመጣ እንደውም ከሰላምታ ቀድሞ “እንብላ!” ነበር የሚባለው። አይደለም የምናውቀው ሰው የማናውቀው ሰው እንኳን ቢሆን ለእኛ ያዘዝነው ምግብ ሲቀርብ ዘወር ብለን “እንብላ!” ማለት የተለመደ ነበር፡፡ (‘ነበር’ የሚባሉ ነገሮች ሲበዙ ደግም አይደል፡፡)
ደግሞላችሁ...ያኔ የሴራ ትርክት የሚሉት ነገር የለ፣ “ጠርጥር ገንፎ ውስጥ አለ ስንጥር” ምናምን ብሎ ነገር የለ...በቃ “እንብላ!” ሲባል “አመሰግናለሁ፣ አሁን ነው የበላሁት...” ምናምን ይባልና ሁሉም ወደየ ጉዳዩ፡፡ ልጄ ዘንድሮ ጨዋታውም፣ የጨዋታው ህግም ተለዋውጧል፡፡
እንግዲህ... አለ አይደል... ድንገት “እንብላ!” የሚል ሰው ተገኘ እንበል። መጀመሪያ ፈገግ እንልና “አሁን ነው በልቼ የመጣሁት...” እንላለን፡፡ ከዛማ ምን አለፋችሁ...
ራሳችን ለራሳችን ‘አፕቲቲዩድ’ ምናምን እንፈትናለን፡፡ “ግን ለምንድነው እንብላ ያለኝ! አንድ ነገር አስቦ ቢሆን ነው እንጂ!” ከዛ የቅርብ ለማመሳከሪያ የሚሆን ሰበብ አልመጣ ሲል፣ የዛሬ ስምንት ዓመት ገደማ ‘ፉቴጅ’ ብቅ ትላለች፡፡
“ያን ጊዜ እንደዛ ገንዘብ ቸግሮኝ አበድረኝ ስለው፣ የለኝም ያለኝን የረሳሁት መሰለው!” እንግዲህ ሰበብ ሰበብን ‘ይጎትት’ የለ...ልክ በዛች ደቂቃ ያለች ሰበብ ‘እጅ ከፍንጅ’  ትያዛለች፡፡ “የእሱን ሹሮ አብሬ ልዝቅለት ነው! ይሄኔ ክትፎ ቢሆን ኖሮ ቀና ብሎ አያየኝም ነበር!”
ሲብስና በጣም ሲብስ ደግሞ ምን ሊሆን ይችላል መሰላችሁ...አጅሬ ይሄኔ የሆነ ነገር ነስንሶ ሊያጎርሰኝ ፈልጎ ይሆናል!” ያልጠረጠረ እንደሚመነጠር ከተረቱ ባለፈ በተግባር የምናየው ቢሆንም፣ ጥርጣሬ አንዲህ ‘ፕሬሚር ሊግ’ ደረጃ ሲደርስ...አለ አይደል...የሚገኘውን ሁሉ ሊያሳጣ ይችላል።
በአንድ ወቅት ሁለት ሆነን ምሳ የምንቀምስባት መለስተኛ ምግብ ቤት ነበረች፡፡ እናላችሁ የባለቤትየዋ ‘አንኦፊሻል’ ምናምን የሆነ ሰው ነበር፡፡ ሁልጊዜ ምሳ ሰዓት አካባቢ ይመጣል፡፡ እናም፣ ሰላምታ መለዋወጥ ጀምረን ነበር፡፡ ታዲያላችሁ... አንድ ቀን ልክ ‘ፍርፍራችን’ ቀርቦ (እውነት እውነቷን ተናግሮ የመሸበት ማደር!) መመገብ ስንጀምር ብቅ ይላል፡፡ ወዳጄ ለወጉ ያህል “እንብላ!” ይለዋል፡፡ ምን ቢሆን ጥሩ ነው፤ ጣደፍ ብሎ ይመጣና ጉብ! ያልጠበቅነው ቢሆንም ያው ቀመስ አደርጎ ይሄዳል ብዬ ነበር፤ ቢያንስ እኔ ያሰብኩት፡፡ እሱዬው መዳፉን እንደ ግሬደር ስር ይሰቀስቅና ይንደው ገባ፡፡ ብቻ ሦስት አራቴ ሲመላለስ ‘ፍርፍሪ’ የምትመስል አስተርፎልን አረፈዋ! ብቻ ምን አለፋችሁ...በድግሳችን የበይ ተመልካች ሆነን ቀርን። ከዛ በኋላማ አይደለም “እንበላ!” ልንለው ሰላምታ እንኳን የምንሰጠው ድንገት ዓይን ለዓይን ከተጋጠምን ሆነ፡፡ ልጄ... ‘ሰልፍ ዲፌንስ’ እኮ ካራቴ ምናምን ብቻ አይደለም!
‘ሆዳም ቢፈተፍት የጠገበ ይመስለዋል፣’ የምትል አባባል አለች፡፡ እናማ... ሆነ ብለን በድንገት የደረስን ምስል ከች እያልን የምናስደነግጥም ቁጥራችን ቀላል አይደለም። በጎ ባህሪን እንደ ድክመት የምናይ ማለት ነው፡፡
“ስማ፣ እነእንትና ምሳ ውጪ ነው የሚበሉት፣ አይደል?”
“አዎ፣ ምነው... ልትጋብዛቸው አሰብክ እንዴ!”
“ሥራም አላጣሁ፡፡ ፋይቭ ስታር ሆቴል ነው የሚመገቡትሲባል ሰምቼ ገርሞኝ ነው። ሰዉ ግን ብሩን ከየት ነው የሚያመጣው!”
“ፋይቭ ስታር! ዝም በላቸው፣ ወሬኛ ሁላ! እነሱ ሁልጊዜም የሚመገቡት እንትን ምግብ ቤት ነው፡፡”
“ጎል ኦፍ ዘ ሲዝን፣” ይላችኋል ይቺን ነው፡፡ ግብ ተመታ!
ከዛማ... ሰዓት ሲደርስ እንትና ምግብ ቤት ከች ነው፡፡ “እናንተ ደግሞ እዚህ ምን አመጣችሁ!”
“አንተ ራስህ ምን አመጣህ! ይልቅ ና ተቀላቀል፡፡”
“እኔ እንኳን ጥግ ተቀምጬ ላዝ ነበር፡፡ ካላችሁ እሺ...”
የምር ግን...አለ አይደል... ‘አብሮ መብላት’ እኮ ከውድ እሴቶቻችን አንዱ ነበር። ዘመድ ወይ ወዳጅ ቤት ተሂዶ እኮ አፍጥጦ መመለስ የሚባል ነገር የለም፡፡
ከመመገቢያ እቃዎች አቅም እንኳን “እነኚህ ለቤት ውስጥ መጠቀሚያ ሳይሆን ለእንግዳ ናቸው፣; ብሎ ለይቶ የሚያስቀምጥ ነበር እኮ! የባለቤቶቹ ትልቁ ጭንቅ “እነኚህ ሰዎች መሶቡን ባዶ አደረጉት!” ምናምን ሳይሆን “እንግዶቻችን ጠግበው ይሆን!” አይነት ነገር ነበር፡፡
እናም...በንጹህ ልቦና እስከሆነ ድረስ አብሮ መብላት አያከስርም ለማለት ያህል ነው፡፡
መልካም የበዓል ዋዜማ ሰሞን፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1700 times