Saturday, 02 January 2021 11:40

ስለ ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   ልዑል አልጋ ወራሽ በግቢያቸው ውስጥ ላቆሙት የመፃህፍት ማተሚያ ቤት ዲሬክተር ያደረጉት አቶ ገብረ ክርስቶስ ተክለ ሀይማኖት ስራውን ለማስፋፋት እጅግ ይተጋ ነበር፡፡
በዚህም ዘመን ማተሚያ ቤቱ አንድ ሳምንት ጋዜጣ እያተመ ቢያወጣ፣ ለኢትዮጵያ ጠቃሚ መሆኑን በመግለፅ፣ ለልኡል አልጋ ወራሽ ሀሳብ አቅርቦ እያስታወሰ ቆይቶ ነበርና ስለፈቀዱለት ስራውን ለመጀመር ይሰናዳ ጀመር፡፡ በዚሁም ጊዜ ለጋዜጣው ፅህፈት የአማርኛ ችሎታ ያለው አንድ ሰው ይታዘዝልኝ ብሎ ልዑል አልጋ ወራሽን ስለ ለመነ፣ እኔን የእልፍኝ አሽከሩ ልጅ በልሁ ደገፉ ፈልጎ አስጠርቶ፣ የጋዜጣ ስራ ፀሀፊ እንድትሆን ከልዑልነታቸው ታዘሀል ብሎ አስታወቀኝ። ቀጥሎም ወደ አቶ ገብረ ክርስቶስ ወስዶ አጋጠመኝና ስራውን ተረክቤ እሰራ ጀመር። የጋዜጣው ዋጋ በኢትዮጵያ ውስጥ በዓመት አምስት ብር ሲሆን ለውጭ አገር ግን በዓመት ሰባት ብር ሆኖ ተወሰነ፡፡
ከዚህ በኋላ የጋዜጣው ስም ምን ተብሎ እንደሚሰየምና በምን ቀን መውጣት እንደሚገባው፣ የስራውንም አጀማመር በማጥናት ሀሳብ በማቅረብ ሶስት ሳምንት ያህል አለፈ፡፡ በመጨረሻም ልዑል አልጋወራሽ ጋዜጣውን “ብርሃንና ሰላም” ብለው ሰየሙትና የመጀመሪያው ጋዜጣ ታህሳስ 23 ቀን 1917 ዓ.ም ሀሙስ በ4 ገጾች ታትሞ ወጣ፡፡ ከዚያም ቀጥሎ በየሣምንቱ ሀሙስ ሀሙስ የሚታተም ሆነ፡፡
በመጀመሪያው ቁጥር ጋዜጣ ዳሬክተሩ አቶ ገብረ ክርስቶስ፣ ስለ ብርሀንና ስለ ሰላምታ ሐተታ በመስጠት የጻፈ ሲሆን እኔም ዋና ጸሀፊውም በበኩሌ ወደ ጅሩ ሄጄ ሳለ ስለአየሁት አዝመራ ሀተታ በመስጠት ጽፌ አቀረብሁ፡፡ አርእስቱ “ስለ ዘንድሮ አዝመራ ከሀገር ውስጥ የመጣልን ወሬ” የሚል ሆኖ “ጅሩ በሚባል አገር ነጭ ስንዴና ጥቁር ስንዴ፣ ባቄላና ተልባ ሽንብራና ጓያ ይበቅልበታል” እያለ የሚቀጥል ነበር፡፡
በዚያ ጊዜ ጋዜጣውን ለህዝብ ለማስታወቅና ለማስለመድ ብዙ ድካም ነበር፡፡ የዳሬክተሩም ትጋት በተለይ የሚደነቅ ነበር፡፡
የራስ ስዩም ባለቤት ወይዘሮ ተዋበች ሚካኤል (የንጉስ ሚካኤል ልጅ) ጥር 12 ቀን አዲስ አበባ ላይ ስለሞቱ ሬሳቸው ወደ ደብረ ሊባኖስ ተወስዶ በአያታቸው በወይዘሮ ባፈና መቃብር ቤት ተቀበረ፡፡ ሐዘንተኞቹም ከተመለሱ በኋላ ጃንሜዳ ላይ ድንኳን ተተክሎ ጥር 16 ቀን ውሎ ሆነና የለቅሶው ስነ ስርዓት ከፍ ባለ ሁናቴ ተፈፀመ፡፡
የሥርአቱ ዝርዝር ጥር 21 ቀን ታትሞ ወጥቶ ነበርና ጋዜጣው ለመኳንንትና ለሀዘነተኞቹ በነፃ ታድሎ ብዙዎች ስለ አነበቡት የጋዜጣው ዝና በሁሉም ዘንድ የታወቀ ሆነ፡፡ ከዚህ በኋላ የጋዜጣው አንባቢና የማህበረተኞቹ ቁጥር እያደገ ይሄድ ጀመር፡፡
(ትዝታዬ፤ መርስዔ ኃዘን ወልደ ቂርቆስ)  

Read 12078 times